አዲስ አበባ፡- በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የ25ቱ ትምህርት ቤቶች ጥገና ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መከናወኑን የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አብዱሐሰን ያዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸው 25 ትምህርት ቤቶች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ ተከናውናል።
ከክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅት እና ከማኅበረሰቡ በተገኘ 126 ሚሊዮን 967 ሺህ ብር ድጋፍ የተጠገኑት ትምህርት ቤቶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ሲሉ አስረድተዋል። አቶ አብዱሐሰን እንዳስታወቁት፤ ጥገና ከተደረገላቸው 25 ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱ በጦርነቱ የተነሳ ሙሉ በሙሉ የወደሙ፣ 22ቱ ደግሞ መካከለኛ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው አስፈላጊው ጥገና የተደረገላቸው ናቸው።
በአጠቃላይ በጦርነቱ የተነሳ በክልሉ የሚገኙ 400 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወቁት ኃላፊው፤302ቱ በከፊል የወደሙ ሲሆኑ፤ 98ቱ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ናቸው። ለትምህርት ተቋማቱ መልሶ ግንባታ ሥራ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ሙሉ በሙሉ የወደሙ አምስት ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ አቶ አብዱሐሰን ገለጻ፣ ውድመት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የተሟላ ጥገና እስከሚደረግላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ ለማድረግ ጊዜያዊ የመማሪያ ክፍሎችን በማዘጋጀት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይቋረጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በዛፍ ስር እና በሼድ ውስጥ እንዲማሩ እየተደረገ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የመልሶ ግንባታ ሥራውን በፍጥነት ለማከናወን ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት አለ ያሉት ኃላፊው፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ ሥራው ተጨማሪ ድጋፍ በማቅረብ የተጀመሩ ሥራዎችን ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ከመገንባት በተጨማሪም ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የማቅረብ እና የምገባ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ኃላፊው አስረድተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም