በውስጡ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ፤ የመለማመጃና የመወዳዳሪያ የመዋኛ ገንዳዎችን፣ ጅምላዚሞችን፣ የስፖርተኞች መኖሪያ ህንጻዎችን፣የግራውንድ ቴኒስ ሜዳንና የአስተዳደር ህንጻዎችን አካቶ መያዙን ተመልክተናል፡፡እንዲሁም ከ2000 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽ፣ ቤተ መጻህፍት፣ የመማሪያ ክፍሎችን፣ ካፍቴሪያና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በውስጡ ይዟል፡፡ ይህ ዘመናዊ የድሬዳዋ ሁለገብ የወጣቶች የስፖርት አካዳሚ በአሁኑ ጊዜ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
307 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቀሪ ስራዎቹን ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በመጪው ዓመት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚናገሩት በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የፋሲሊቲ ቡድን መሪና የግንባታው ክትትል ባለሙያ አቶ ምህረቱ ዘላለም፤ ማዕከሉ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያና በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚሰለጥኑበት አካዳሚ መሆኑን ነግረውናል፡፡
የአካዳሚው ግንባታው የተጀመረው ግንቦት ወር በ2011 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ግንባታ አፈጻጸም 97 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት፡፡ አዲሱ አካዳሚ በከተማዋ የተቀዛቀዘውንና የቀነሰውን የስፖርት እንቅስቃሴ ይመልሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል የሚሉት አቶ ምህረቱ፤ በዚህ አካዳሚ ሁሉም ስፖርተኞች እንደየፍላጎታቸው ስልጠናቸውን በመከታተል ለተለያዩ የስፖርት ክለቦች የሚሆኑ ብቁ ስፖርተኞች የሚፈሩበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በተለይ ከተገነቡት ሁለት የመዋኛው ገንዳዎች አንዱ መለማመጃ ሲሆን ሁለተኛው ዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟላና በአገራችን ደረጃ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ አገር በውሃ ዋና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ስፖርተኞችን ለመፍራት የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ።
120 ሰልጣኖች የሚሰለጡንበት የተሟላ የአካዳሚ አገልግሎት የሚሰጡ የስፖርትና የመዝናኛ መሰረተ ልማቶች ያሉት አካዳሚ ነው፡፡ አካዳሚው በግንባታው ወቅትም ለበርካታ የከተማው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በቀጣይም ብቁ፣ ስነ ምግባር የተላበሱና ጤናማ ስፖርተኞችን ያፈራል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
አካዳሚው በውስጡ አንፊ ቲያትር የተገነባለት ሲሆን ለወጣቶችና ለህጻናት ለስፖርታዊ እንቅስቃሴና መዝናኛ ቦታ ሆኖ የሚያገለግል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን አቶ ምህረቱ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የ10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያስተናገደው የድሬዳዋ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ 448 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተካሄደ ይገኛል፡፡በ1968 ዓ.ም ለአገልግሎት የበቃውና ከአዲስ አበባ ስታዲየም ቀጥሎ ዓለም አቀፍ ወድድሮችን ሲያስተናግድ የቆየው ይህን ታሪካዊ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማሻሻያ ግንባታዎችን እየተካሄዱለት መሆኑን አቶ ምህረቱ ይናገራሉ፡፡
የማሻሻያ ግንባታው ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች ማሟላት ያሉባቸውን መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ነው፡ ፡ ስታዲየሙ 25ሺህ ሰዎችን የሚይዝ ሲሆን በፊፋ ደረጃ መሰረት ልብስ መቀየሪያና መልበሻ ክፍሎች፣ የማሳጅ፣ የሚዲያና መሰል አስፈላጊ ክፍሎችን ያሟላ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆኑ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅና በመጪው ዓመትም ዓለም፣ አህጉርና አገር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደሚችል ነው ያብራሩልን፡፡
በከተማዋ የሙቀቱ መጠንና የውሃው ጨዋማነት ከፍተኛ በመሆኑ በስታዲየሙ የመጫዋቻ ሳሩ ችግር ይፈጥር እንደነበር አቶ ምህረቱ አስታውሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የከተማ አስተዳደሩ የፊፋን ደረጃ ያሟላ አርቲፊሻል ሳር እንዲገዛና እንዲነጠፍ ውሳኔ አሳልፎል፡፡ ይህ አርቲፊሻል ሳር ለ10 ዓመታት የሚያገለግልና የፊፋን መስፈርት ያሟላ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜ የማንጠፍ ስራው ተከናውኖ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ድሬዳዋ ለማምጣት ዝግጁ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የማሻሻያ ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የድሬዳዋ ታሪካዊ ስታዲየም ሲጠናቀቅም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የፊፋን ስታዳርድ የሚያሟላ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባለመኖሩ ምክንያት ውጭ አገር በመሄድ የሚጫወተውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እዚህ አገሩ ላይ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ የሚያስችልም ነው፡፡
በመጪው ዓመት አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በድሬዳዋ ስታዲየም ለማስተናገድ ነው እየሰራን ያለነው የሚሉት አቶ ምህረቱ፤ ካፍ በሰጠን አስተያየት መሰረት ግንባታው የተካሄደ የሚገኘው፡፡ የካፍ ተወካዮችም ይህን የማሻሻያ ግንባታ ተመልክተው ዓለም አቀፍ ፍቃድ ይሰጡናል ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት፡፡
ከተማዋ ዘመናዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ታሪካዊውን የድሬዳዋ ከተማ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እያካሄደች መሆኑን የሚገልጹት፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፤ ይህም የከተማ አስታደድሩን ስፖርታዊ ውድድሮች በማሳደግ ከተማዋን ብሎም ሀገርን የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡
እየተገነቡ ያሉ መዝናኛዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወጣቶችን ከደባል ሱስ በማላቀቅ አምራች ትውልድ መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቶቹ ትውልድን በመቅረጽና ብቁ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለህፃናትና ወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ብቁ ዜጋ ለመፍራት ዓላማ ያላቸው መሆኑን አመልክተው፤ የወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎችን መፍትሔ ለመስጠት የስፖርት ልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉን ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ ወጣት በእነዚህ የስፖርትና የመዝናኛ ቦታዎችን በመጠቀም ለአገሩና ለከተማዋ የሚያስጠራ ስፖርተኛ መሆን እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015