ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ሂደት ውስጥ ኑሮን ቀለል ማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ያስፈልጋሉ። ለእዚህ ደግሞ ጊዜ ወስደን የምናገኛቸውን ወይም የምናዘጋጃቸውን ማናቸውንም ነገሮች በቀላሉ ማግኘት እንፈልጋለን። ዘመናዊ አኗኗር አዳዲስ የአሰራር መንገዶችን ከማምጣቱ በተጨማሪ፣ ቀደም ሲል ማህበረሰቡ እንደ ነውር የሚቆጥራቸውን በርካታ አሰራሮች ወደ ስራ አስገብቷቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ ዘመናዊነት ባመጣው ውጤት ነውር ይባሉ የነበሩ አሰራሮች ነውርነታቸው አክትሞ አዋጭ መሆን ችለዋል፡፡
ማህበረሰቡ ነውር አድርጎ ካቆያቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ሽሮ፣ በርበሬ፣ እንጀራ ወዘተ… ከገበያ ገዝቶ መጠቀም አንዱ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት እንጀራን ጨምሮ የባልትና ውጤቶችን በማጀት ማዘጋጀት እንጂ ከገበያ መግዛት እንደነውር ሲታይ መኖሩ ይታወሳል፡፡ በተለይም ሴቶች እንጀራና ሽሮ በርበሬ የሚገዙ ከሆነ ደግሞ ከነውርም በላይ ነውር ሆኖ ይታይ ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ ከተቀየረ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንጀራም ይሁን ሌሎች ማንኛቸውም የበሰሉና የተዘጋጁ ምግቦችን ከገበያ ገዝቶ መጠቀም፣ እነዚህን ምግቦች በቤት ውስጥ ለማዘጋጀት የሚውሰደውን ጊዜና ድካም ይቀንሳል፤ ምግቦቹን ለማዘጋጀት በቂ ቦታ እና ቁሳቁስ ለማይኖራቸው ደግሞ ገዝቶ መጠቀሙ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ምግቦቹን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው እውቀትና ክህሎት ለሌላቸውና እጥረቱ ላለባቸው ደግሞ ሌላው የተዘጋጁ ምግቦች ፋይዳ ነው፡፡
የዛሬው የስኬት ገጻችንም የባልትና ውጤት ምርቶችን ወደ ገበያ ይዞ በመውጣት ፈር ቀዳጅ የሆነ አንድ ቤተሰብን ሊያስተዋውቃችሁ ይወዳል፡፡ ይህ ቤተሰብ ሽሮ በርበሬ መግዛት ነውር በሆነበት ወቅት የባልትና ውጤቶችን ወደ ገበያ ይዞ በመውጣት ቀዳሚው ነው፡፡ ይህ ቤተሰብ የባልትና ውጤቶችን በቤት ውስጥ አዘጋጅቶ ገበያውን ለማግኘት በብዙ ችግር ውስጥ አልፏል፡፡ ሊገዛ የመጣውም ቢሆን ምርቱ እንዳይታይ በጥቁር ፌስታል፣ በጋዜጣና በሌላ መሸፈኛ እንዲጠቀለልለት ይወተውት እንደነበርም የባልትና ውጤት አዘጋጆቹ ያስታውሳሉ፡፡
ዛሬ ግን ያ ሁሉ አልፎ ድካማቸው ፍሬያማ መሆን ችሏል፡፡ የትኛውም ሰው የባልትና ውጤቶችን ያለሀፍረት በኩራት የሚገዛበት ወቅት ላይ ተደርሷል። ትናንት በቤት ውስጥ ለሁለት የተጀመረው የባልትና ውጤት የማዘጋጀት ሥራ ዛሬ ሙሉ ቤተሰቡን ማሳተፍ ተችሏል፡፡ በወቅቱ በአካባቢያቸው መስፋት ያልቻለው ገበያም ዛሬ ላይ ከአገር ውስጥ አልፎ በተለያዩ ውጭ አገራት በተለይም በአውሮፓ በስፋት ተደራሽ በመሆን ለሀገር ኢኮኖሚም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ለዚህ ነው የዕለቱ የስኬት ገጻችን በተለያዩ መጠሪያዎች ከምናውቃቸው ቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤት አምራች ላኪዎች መካከል አንዱ የሆነውን “ፋሲካ ቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤት አምራች ድርጅትን” የስኬት ጉዞ ሊያስቃኛችሁ የወደደው፡፡
ድርጅቱ ጅማሮውን ያደረገው በ1980 ዓ.ም እንደሆነ የፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኤልሳ ሃብቴ ትናገራለች። እሷ እንዳለችው፤ በወቅቱ ኢትዮጵያን ሴቶች የባልትና ውጤት ምርቶችን በባህላዊ መንገድ በቤት ውስጥ እንደሚያዘጋጁ ሁሉ ወላጅ እናቷ ወይዘሮ ወለተኪዳን ገብረመድህን ከወላጅ አባቷ አቶ ሃብቴ ገብረማርያም ጋር ሥራውን በቤት ውስጥ ጀመሩት። ጥንዶቹ በባህላዊ መንገድ የጀመሩትን የባልትና ሥራ በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው ተረክበው ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማስቀጠል ችለዋል፡፡
ሥራውን ከቤተሰብ ተረክቦ ዘመናዊ በሆነ መንገድ በማስቀጠል ሂደት ኤልሳ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኗ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ቤተሰቦቿን በማገዝ ሙያውን ቀስማለች፡፡ ለዚህም ነው ቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤት የሆኑ ምርቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማዘጋጀት ብዙም ያልከበዳት። ለሥራው ቅርብ እንደመሆኗ ትምህርቷን ከ12ኛ ክፍል ገታ አድርጋ ቤተሰቦቿ የጀመሩትን የባልትና ሥራ የተቀላቀለችው ኤልሳ፤ አሁን ላይ ወንድሞቿን ጨምራ ሥራውን ማስፋት ችላለች፡፡ ገበያውም ቢሆን ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ መድረስ ችሏል፡፡
በወቅቱ በቤት ውስጥ የተዘጋጀው ሽሮና በርበሬ ወፍጮ ቤት ወስዶ በማስፈጨት፤ በነጭ ላስቲክ በሻማ እንባ ታሽጎ ለገበያ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሰችው ኤልሳ፤ ያን ጊዜ ታዲያ ሽሮ፣ በርበሬና ሌሎች ምርቶችን መግዛት እንደ ነውር ይቆጠር እንደነበር ትናገራለች። በወቅቱ ሥራውን የጀመሩት ወላጆቿ ቴክኖሎጂውና ዕውቀቱ ባይኖራቸውም ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ኤክስፖርትን ታሳቢ አድርገው ወደ ሥራው እንደገቡ ነው ያስረዳችው፡፡
የወላጆቻቸውን ውጥን ለማሳካት ያለሙት ልጆች ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና የሚለውን ድርጅት በማቋቋም ኤክስፖርቱን በቀላሉ ተቀላቅለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እና የባልትና ውጤት የሆኑ ምርቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ አዘጋጅቶ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ የፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና ምርቶች 70 በመቶ ያህሉ ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ ሲሆን 30 በመቶ ያህሉ ብቻ ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል፡፡
እናትና አባት ሁለት ሆነው በልጆች አጋዥነት የጀመሩት ሥራ ተስፋፍቶ በአሁኑ ወቅት 60 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት፤ እንዲሁም ከ100 እስከ 150 ለሚደርሱ ሠራተኞች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡
ከዛሬ 35 ዓመት በፊት ወደ ባልትና ሥራ በመግባት ለዘርፉ ፈር ቀዳጅ መሆን የቻለው ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና አሁን ኤክስፖርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ ሳሪስ አካባቢ በቤት ውስጥ የተጀመረው የባልትና ሥራ ወደ ፋብሪካ አድጓል፤ በተጨማሪም ቃሊቲና ጀሞ ላይ ተጨማሪ ማምረቻዎች ተከፍተዋል። በእነዚህ ሶስት ማምረቻዎችም ዘመናዊ የሆኑ ማሽኖች ሲኖሩ፤ ማሽኖቹ መቁላት፣ መከካት፣ መፍጨት፣ ማሸግና ሌሎች ተግባራትንም ማከናወን የሚችሉ ናቸው። መሸጫ ቦታን በተመለከተም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉት የመሸጫ ሱቆች ምርቶቹን ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ፡፡
ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና ድርቆሽን ጨምሮ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቡላና ሌሎች ኢትዮጵያዊ የሆኑ ማናቸውንም የባልትና ውጤት ምርቶችን ያዘጋጃል። ‹‹በባልትናው ዘርፍ በአገሪቱ ፈር ቀዳጆች ነን›› የምትለው ኤልሳ፤ ሥራውን ከልብ ወዳውና አምናበት እንደምትሠራው ትናገራለች፡፡
በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ከዛ በኋላ ግን በግለሰብ ደረጃ በዘመነ ደርግ የባልትና ውጤቶችን ማምረት የጀመሩት ወላጆቿ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ በወቅቱ ሥራው ነውር እንደነበርና በብርቱ ትግል ዛሬ ላይ መድረሱን አጫውታናለች፡፡
ትናንት እንደነውር ይታይ የነበረው የባልትና ውጤቶችን መግዛት ዛሬ ላይ በማህበረሰቡ የተለመደና የዘመናዊነት መገለጫ ሆኗል፡፡ ጊዜያቸውን አትርፈው ድካም መቀነስ እንደቻሉ የሚናገሩ በርካታ ደንበኞች አሉን ስትል ኤልሳ ትገልጻለች፡፡ በቅመማ ቅመም ምርቶች በኩል አብዛኞቹ ደንበኞች በውጭ አገር ያሉ እንደመሆናቸው በዘርፉ በስፋት አልተሠራም ትላለች፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ልክ እንደ ቡና ሁሉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ቢቻል ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ መሆኑን ታነሳለች፡፡
“በቁጥር 20 የሚደርሱ የቅመማ ቅመም አይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ” የምትለው ኤልሳ፤ እነዚህን ቅመማ ቅመም በጥራትና በብዛት ማምረት ቢቻል የሚያስገቡት ገቢ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ ከእያንዳንዱ ቅመማ ቅመም የሚገኝ ገቢም ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው የጎላ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ደግሞ በውጭው ዓለም እጅግ ተፈላጊ ነው የምትለው ኤልሳ፣ ይህን ዕድል መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቅመማ ቅመም አይነቶች በሙሉ በውጭው ዓለም ስለመኖራቸው በማንሳት፣ የቅመሞቹ ቃና ከኢትዮጵያ ቅመም በእጅጉ እንደሚለይ ነው የምትናገረው፡፡ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመሞች ቃናና ጣዕም እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡
በውጭው ዓለም ተመራጭና ተወዳጅ በሆነው የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመምና ባልትና ላይ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት የምትለው ኤልሳ፤ ምርቱን አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን ጨምሮ አገርም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል በማመላከት ዘርፉ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት አስገንዛባለች። በተለይም በጥራት በኩል ተወዳዳሪ ለመሆን እንደ በርበሬና ዝንጅብል በመሳሰሉ ምርቶች ላይ የሚፈጠሩ ፈንገሶችን በማስወገድ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ከተቻለ የቅመማ ቅመም ዘርፍ ከቡና ያልተናነሰ ገቢ ማምጣት እንደሚችል ጠቁማለች፡፡
ኤልሳ እንደምትለው፤ የፋሲካ ቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤቶች በአውሮፓ ሰፊ ገበያ አላቸው። የኢትዮጵያ በርበሬም በውጭው ዓለም እጅግ ይፈለጋል። ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን በበርበሬ ላይ አፍላቶክሲን የተባለ ፈንገስ ተከስቷል መባሉን ተከትሎ ችግሩ ለገበያው እንቅፋት እንደሆነም ጠቁማለች፡፡ በዚህ ምክንያትም በውጭው ዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆነው የኢትዮጵያ በርበሬ በአሁኑ ወቅት ገበያው መቀዛቀዙንና ይህም በእጅጉ እንደሚያስቆጫት ትናገራለች፡፡ ይሁንና በርበሬን ተክቶ ሽሮና የተለያዩ የባልትና ውጤቶች እንዲሁም በቁጥር 20 የሚደርሱ ቅመማ ቅመሞችን ጭምር ኤክስፖርት በማድረግ አገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች ነው ያመላከተችው፡፡
ፋብሪካቸው በጥሬው ወደ ገበያ የሚያወጣው ምንም አይነት ምርት እንደሌለም አስረድታለች። ማንኛውም ቅመማ ቅመም እሴት ተጨምሮበት ለምግብነት ተዘጋጅቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ነው የገለጸችው፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም የተለያዩ አስተዋጽኦዎች ያሉት ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና መነሻ በሆነው ሳሪስ አካባቢ ለሚገኙ ወጣት የእግር ኳስ ቡድን ድጋፍ ያደርጋል። ወጣቶቹም የተደረገላቸውን ድጋፉ ተጠቅመው አልባሌ ቦታ ላይ ከመዋል ይልቅ በኳስ ጨዋታ ጊዜያቸውን እያሳለፉ እንደሆነ አስረድታለች። ክብር ለአረጋውያን ለተባለ ድርጅትም እንዲሁ በየወሩ ሽሮና በርበሬን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ አስቤዛ ይቀርብላቸዋል፡፡ ይህም ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ በጎ ተግባር ሲሆን፤ በተጨማሪም በተለያዩ አጋጣሚዎች በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ አገራዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪዎችም አቅም በፈቀደ መጠን ፈጣን ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ማሽኖችን እንደሚጠቀም የተናገረችው ኤልሳ፤ ለአብነትም ሽሮን ቆልቶ፣ ከክቶ፣ አበጥሮና ፈጭቶ የሚያሽግ ማሽን በመጠቀም በቀላሉ ምርቱ እንደሚመረት ገልጻለች። ሌሎችም መታመስ የሚፈልጉ ቅመሞችንም እንዲሁ ማመስ የሚችሉ ማሽኖች ስለመኖራቸው አጫውታናለች፡፡
በባህላዊ መንገድ የተጀመረው ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና በዘመናዊ መንገድ ጥራቱን አስጠብቆ በማስቀጠል ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ መቆየት በመቻሉ በተለያየ ጊዜ ሽልማቶችም ተበርክተውለታል፡፡ በቅርቡም ለረጅም ጊዜ ገበያ ውስጥ በመቆየቱ፣ በጥራቱና በማኔጅመንቱ ከአቢሲኒያ አዋርድ ሽልማት የተበረከተለት መሆኑን ጠቅሳ፣ ሽልማቶቹም የወርቅ፣ የዋንጫና የዲፕሎማ መሆናቸውን ነው ኤልሳ የጠቀሰችው፡፡
ድርጅቱ ሰፊ የማምረቻ ቦታ ማግኘት ባለመቻሉ በተለያየ ቦታ እያመረተ መሆኑን ጠቅሳም፤ ተጨማሪ ሰፊ የማምረቻ ቦታ ከመንግሥት እንዲሰጣው ጥያቄ ማቅረቡን ትናገራለች፤ ጥያቄው ምላሽ ሲያገኝም ትልቅ ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለውም የጠቆመችው፡፡ ፋብሪካው ሲገነባም ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ጠቁማ፣ ዘርፉን ለትውልድ በማስተላለፍ ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትናን የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስረድታለች። ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያን ቅመማ ቅመምና የባልትና ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በማስተዋወቅ አገሪቷ ከዘርፉ የሚገባትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንድታረጋግጥ ፋሲካ ቅመማ ቅመምና ባልትና ተግቶ እንደሚሠራ አጫውታናለች፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015