ልጅነቷን በተወለደችበት ስፍራ አልገፋችም። እናቷን በህጻንነቷ ማጣቷ ተነግሯታል። ነፍስ እያወቀች፣ ዕድሜ ስትጨምር የአንድ እግሯን ችግር አወቀች። አንድ እግሯ እንደሌሎች አይደለም። እንዳሻት አይሆንላትም፣ በወጉ አይራመድም። ልጅ ብትሆንም የእግሯን ከሁሉም መለየት አውቃለች። ዝም አላለችም። በኮለተፈው አንደበቷ ምክንያቱን ጠየቀች። ለምን? እንዴት? አለች። ቤተሰቦቿ የእግሯን ጉዳት ሰበብ ነቅሰው እውነቱን ነገሯት።
አጋጣሚው
ህጻን ነበረች። በወጉ ማትናገር፣ ፈጥና የማትሮጥ ጨቅላ። ገና በጠዋቱ ሞት በእናቷ ጨክኗል። ጡት አስጥሎ ከእሷ ነጥቆታል። ልጅ የእናት ፍቅሯን፣ ጠረን ሽታዋን አታውቅም። የዛኔ ስለእሷ ግድ የሚላቸው አባትና ወንድሞቿ ነበሩ። ስታለቅስ አባብለው ዕንቅልፍ ሲጥላት ከጠፍር አልጋው ያስተኝዋታል።
እናት ለምን ትሙት
አንድ ቀን ትንሽዋ ልጅ ዕንቅልፍ ይዟት ሄደ። አዝላ ‹‹እሹሹ›› የምትል፣ ሲርባት ጡት የምታጎርስ፣ ተኝታ ስትነቃ አቅፋ የምትስም እናት የለችም። የተኛችው ከተለመደው የጠፍር አልጋ ነበር። ተኝታ ትወራጫለች፣ ትፈራገጣለች። ቤተሰቦቿ እሷን ትተው ከጉዳያቸው ውለዋል። የህጻኗ አንድ እግር ከጠፍር አልጋው ቀዳዳ ገብቶ ተቀርቅሯል። ልብ ያላት፣ያስተዋላት የለም።
ቆይታ ከዕንቅልፏ ነቃች። ቤተሰቦቿ እንደወትሮው ታቅፈው ካልጋው ላይ አነሷት። እግሯ እንደነበረው አልቆየም። እንዳሻት መንቀሳስ፣ መላወስ አቃታት። እግሯ ከጠፍሩ አልጋ ተቀርቅሮ መቆየቱ ለጉዳት ዳርጓታል። በሁኔታው የደነገጡ ዕለቱን ብዙ ሞከሩ። የጨቅላዋ ለስላሳ አካል አልተገራም። እግሯ ደንዝዞ መታዘዝ ፣ መላወስ አቁሟል።
ስፍራው ገጠር የሚባል ነው። በወቅቱ ቤተሰቦቿ ከህክምና አላደረሷትም። በአካባቢው ከሚገኝ ጸበል አመላልሰው አስጠመቋት። ለውጥ አልተገኘም። ከወዳጅ ዘመድ ተማክረው ከአዋቂ ቤት ወሰዷት። ከድካም በቀር መፍትሄ አልነበረም ። የትንሽዋ ልጅ ትንሽዬ እግር ከነህመሙ ዘለቀ።
የአድና አለባቸው ውልደት ዳንሻ ከተባለ ስፍራ ነው። በዕድሜ ከፍ ማለት ስትጀምር ጉዳቷ ለይቶ ታወቀ። የቀኝ እግሯ ከግራው እኩል አይራመድም። ከተለመደው አቋም ለይቶ ወደላይ ተሸማቋል፣ እሷን በእኩል ሆኖ አይከተላትም። ሁሌም የአድና ወንድሞች ከትምህርት ውለው ይመለሳሉ። እሷ ወደፊቷ አይታወቅም እንደነሱ ለዚህ ዕድል አትበቃ ይሆናል። ትንሽዋ አድና ከልጅነቷ ጥቂት ጊዚያትን ቆንጥራ በዳንሻ አሳለፈች።
ከቀናት በአንዱ
አንድ ቀን የአድና አባት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ። ብቻቸውን አይደሉም። ትንሽዋ አድና ከጎናቸው አለች። የመንገዳቸው ምክንያት እሷን ለእህታቸው ሰጥቶ ለመመለስ ነው። አዲስ አበባ ከዳንሻ ይለያል። ከተማው ከገጠሩ ይበልጣል፣ የነዋሪው፣ ሕይወትና ኑሮው ካሉበት ዓለም አይመስለልም።
በተለይ ለአድና የዳንሻ ሕይወት ይከብዳል። አባት ልጃቸውን ለአክስቷ ሲሰጡ የወላጅ ልባቸው ባብቷል። አሁን ለእሷ ማንነት የሚሻለው አዲስ አበባ ሆኗል። ይህን ያመኑት ሰው እጇን በእጃቸው ይዘው ከአዲሱ ቤት አደርሷት። ከአክስቷ፣ ከእህታቸው ጎጆ።
የእናት ምትክ
አክስት ትንሽዋን አድና በሙሉ ዓይን ቃኟት። በስስት ተቀብለው፣ በፍቅር አቅፈው ‹‹ልጄ›› ሲሉ ሳሟት። አባት ባስተዋሉት እውነት ደስ አላቸው። በአክስቷ ውስጥ የልጃቸውን የነገ ተስፋ አሻግረው እያዩ ፈጣሪን አመሰገኑ። ለቀናት በእንግድነት ዘልቀውም ወደ አገራቸው ገቡ። አድና አክስቷን እንደ እናት ተቀበለች። ጠዋት ማታ የምታየው ፈገግታ ተስፋዋን አለመለመ። ድካም ህመሟ ቀለላት። ቤቱን ቤተሰቡን ወደደች። ሕይወትን በአዲስ መልክ ልትኖረው ፈቅዳ ከራሷ ተስማማች።
አዲስ ሕይወት
አሁን አድና የአዲስ አበባ ልጅ ነች። ከዚህ በኋላ ገጠር ይሉት ሕይወት የላትም። በዚህ ስፍራ ሁሉም መልካም እንደሆነ አውቃለች። ልበ ቀናዋ አክስት ከአንድ ልጃቸው አይለይዋትም። የሙት አደራን ተቀብለው ትርጉም ያለው ሕይወት ሊሰጧት ተዘጋጅተዋል።
አክስቷ እንደ እኩዮቿ ከመሆን አላገዷትም። ዕድሜዋ ሲደርስ ትምህርት ቤት አስገቧት። አገር ቤት ሳለች ሳትወድ በግድ ልታጣ የነበረውን ዕውቀት ማግኘቷ ተስፋዋን አበራው። ሳትሰለች ከሌሎች እኩል ለትምህርቷ ታገለች። የትምህርት ቤት ውሎዋ ፈታኝና አጓጊ ሆኖ ቀጠለ። በልጅነቷ ሀ ብላ በጀመረችው ትምህርት መሰረት ጣለች። ከቤት ስትደርስ የእናቷ ምትክ አክስቷ በፈገግታ ይቀበሏታል። በውሎዋ የሸመተችውን እውቀት በጥናት እንድትደግፍ ጊዜ አይነፍጓትም።
አድና ከአንደኛ ክፍል ትምህርቷ አንስቶ የአክስቷ ድጋፍ አልራቃትም። ከቤት ያለችው ትልቋ ልጅ እህትነቷን ተቀብላለች። ሁሌም ስለእሷ ብቻ የሚባል አድሎ የለም። በእነሱ ቤት ሕይወት አንድ አይነት ነው። ልጅነት የእኩል ነው። በአንድ በልተው፣ በእኩል ሰርተው፣ ኑሮን በእኩል ይጋራሉ። አድና አካል ጉዳተኛ ስለሆነች፣ የምታጣው፣ የማትሰራው አይኖርም። ሌሎችም ቢሆኑ እንዲሁ። ከቤት ሰራተኛ እኩል የመስራት፣ ቢያሻት ደግሞ የመተው መብት ከእሷው ነው።
ትምህርት በፈተና
አድና ትምህርት ቤት ገብታ መማር ይዛለች። ከቤት አስከ ትምህርት ቤቷ ለመድረስ በእግሯ እየተጓዛች ነው። ከቀኑ ይልቅ የማታውን ትምህርት መርጣለች። ይህ መሆኑ ጥሩ ዓላማ ላላት ታዳጊ አልከበደም። እሷ ካለችበት የትምህርት ቀዬ ሰፊ የዕወቀት ገበታ እንዳለ ታውቃለች። ሁሌም በመንገዷ ድካም አትሸነፍም። ደስ እያላት ተምራ በፈገግታ ትገባለች።
አድና በዕድሜ ከፍታዋ የትምህርት ደረጃዋም አደገ። ይህ አጋጣሚ ግን ለምትወደው ትምህርት ፈተና መጋረጡ አልቀረም። ትምህርት ቤቱ ለእሷ መሰል ጉዳተኞች ታሳቢ አልሆነም። ለመማር፣ ዕውቀት ለመገብየት ከፍ ያለን ደረጃ መውጣትና መውረዱ የግድ ይላል። እኩዮቿ ሁሌም ይህን ማድረግ ከብዷቸው አያውቅም። ለእነሱ ደረጃ ማለት የሩጫ፣ የመፈንጫ ገጠመኝ ነው።
ባልንጀሮቿ ከደረጃው ቆመው የስሩን ያያሉ፣ ከስሩም ሆነው የላዩን ይቃኛሉ። ሲላቸው ፈጥነው፣ አልያም ተራምደው፣ ይወጡታል። አንዳንዴ ብረቱን ተደግፈው ይዝናኑበታል። ለአድና ይህ ሁሉ እውነት ከዓይኗ አልፎ አያውቅም። ለእሷ እንደመሰሎቿ በደረጃው መፍጠንና መሮጥ ቀልድ ይሆናል። ደረጃውን በወጉ አልፋው ለመውጣት የየዕለት ችግሯ ነው።
በየቀኑ ረጃጅም ደረጃዎችን በጭንቅ ማለፍ የማትወጣው ፈተና ሆኗል። ይህ ደረጃ በምትማርበት አራተኛ ፎቅ በየቀኑ በመሰናክል ደግፎ ያደርሳታል። ተመልሳ ስትወርድም የሚቀርላት የለም። ለእሷ ማር ለመቁረጥ ከንብ እንደሚታገል ሰው መሆኑ ግድ ይላታል። በየቀኑ በድጋፍ ክራንች ተደግፋ ሽቅብ መውጣት፣ ቁልቁል መውረድ መንገዷን የፍራቻና የስጋት አድርጎታል።
አድና ትምህርቷን በእጅጉ ወዳለች። በተለየ ፍቅር የምትደክምለት ዕውቀት አንድ ቀን እንደሚበጃት አልጠፋትም። አንዳንዴ ደረጃውን ወጥቶ ለመመለስ በእጅጉ ይደክማታል። እንዲህ ሲሆን የሚመለከታቸውን ‹‹እርዱኝ፣ተረዱኝ›› ስትል ትጠይቃለች። ምናልባት ከአራተኛ ወደ አንደኛ ፎቅ ቢቀይሩኝ ብላ።
ለአድና የሁሉም አተያይ አንድ አይደለም። አንዳንዱ እንደሆነች ሆና መማር ግዴታዋ መሆኑን ይነግሯታል። ሌላው በግዴለሽነት ሰምቶ ይተዋታል። ይህ ሁሉ እውነት የአድናን ልብ አልሰበረም። ጨለማውን ታግላ መንገዱን አቋርጣ የምትመጣለት የትምህርት ፍቅር በምክንያት መሆኑን ጠቆማት እንጂ።
አድና ትምህርቷን ከፈተናዎች እየታገለች ያዘችው። እንዳሰበችው አልሆነላትም። ድካሟ አየለ፣ ውጥረቷ በረታ። እንዲያም ሆኖ የምትወደውን ትምህርት አልተወችም። ያላትን መረጃ ይዛ የርቀት ትምህርት ቀጠለች።
እንደገና
ትምህርትና አድና መልሰው በሌላ መንገድ ተገናኙ። ከጨለማ ለመውጣት በጨለማ የጀመረችውን ዕውቀት እጁን ይዛ ተጓዘች። ፈጽሞ አልከሰረችም። የዓመቱ ውጤት መልካም ሆኖ ለቀጣዩ ክፍል አዘጋጃት። ሀሳቧ አምና ወደነበረችበት ትምህርት ቤት አቀና። ዘንድሮን ተመልሳ ዕድሉን ልትጠቀም ፈለገች። ያሰበችው አልቀረም። ተመልሳ የሚመለከታቸውን አዋየች። መልካም ሰው ገጠማት። የማታ ትምህርቷን ባመቻት ክፍል መማር እንደምትችል ተነገራት።
አድና የምትወደውን ትምህርት እስከ ስምንተኛ ክፍል ገፋችበት። ከዚህ በኋላ ጉዞዋን የመቀጠል ዕድል አልገጠማትም። ትምህርቷን ትታ በሌላ አማራጭ ተጓዘች። አክስቷ አዲስ ዕቅዷን አጸደቁ። ሀሳቧን አክብረው በይሁንታ ደገፏት። እሷም በውሳኔዋ ገፋች። ራሷን ለአዲስ ሕይወት አዘጋጅታ ማንነቷን አበረታች።
ዛሬ አድና ጥሩ ወጣት ሆናለች። ዕድሜዋ ክፉ ደጉን ያሳያታል። አሁን ጣፋጭ፣ መራራውን አውቃለች። የሚጠቅማትን ከሚጎዳት ለይታለች። ይህ ዕድሜ ከትምህርት ይልቅ ራስን መቻል እንደሚበጅ እየነገራት ነው ። ውስጧን ማዳመጥ የጀመረችው አድና ያገኘችውን ስራ ማለፍ አልፈለገችም። አጋጣሚውን ተጠቅማ ውላ መግባቱን አምናለች።
የእንጀራ ነገር
አድና ዛሬ ባለስራ ወጣት ነች። እንደእሷ አካል ጉዳት ካለባቸው ወገኖች ጋር ተደራጅታ የቆዳ ውጤቶችን እያመረተች ነው። አሁን ‹‹ክፍል ቀይሩኝ፣ እርዱኝ፣ ተረዱኝ›› የሚባል ተማጽኖ የለም። ያም ሆኖ ለስራ የምትመላለስበት መንገድ ምቹ አልሆነም። ታክሲ ለመሳፈር፣ ከአውቶቡስ ለመውጣት በየዕለቱ ትፈተናለች። እሷ ውጣውረድ ብርቋ አይደለም። ያለፈችበት የትምህርት ዓለም ትምህርት ሆኗት አልፏል።
ደሞዝተኛዋ አድና በሰዓቱ ስራ ለመድረሰ ማልዳ ትወጣለች። አንዳንዴ በለስ አይቀናትም። ፈጥና መውጣቷ ብቻውን መፍትሄ አይሆናትም። እንደማንም ታክሲ ለመሳፈር መንገዱ ቀና አይደለም። አንዳንዴ አንዳንድ የታክሲ ረዳቶች ወንበር ይዛ እንዳትጓዝ ከበር ይመልሷታል። ለምን ማለት አትችልም። አስቀድመው ‹‹ለአንቺ አይመችም›› ይሉትን ምላሽ ተክነዋል።
አድና ታክሲ ለመጠበቅ ሁሌም ክራንች ተደግፋ መቆም ግድ ይላታል። ያዘኑ፣ ስለእሷ የተጨነቁ ቅድሚያውን ይሰጧታል። የቸኮሉና ግድ የሌላቸው ደግሞ ሲላቸው፣ ቀድመው ሲመቻቸው ገፍተዋት ያልፋሉ። አድና በትራንስፖርት ግልጋሎት ለሽገር አውቶቡሶች ክብርና ምስጋና አላት። እነሱ ቅድሚያውን ሰጥተው፣ አመቺነትን ፈጥረው ያስተናግዷታል።
አንድ ቀን አድና ያላሰበችው ሆነ። በዕለቱ ወደቤት ለመግባት ትራንስፖርት እየጠበቀች ነበር። አጋጣሚ የሸገር አውቶቡስ ከፊቷ ደርሶ ቆመ። የአድና የሰለቸ ፊት በእፎይታ ፈካ። ወዲያው ሁለቱን ክራንቾች አንስታ በጥበቃ የዛሉ እግሮቿን አላወሰች። ወደ አውቶቡሱ መጠጋቷን ያየው ሾፌር እንደተለመደው የመግቢያ በሩን ዝቅ አድርጎ ወደውስጥ እንድትገባ ረዳት።
አድና በእርጋታ ወደበሩ ተጠግታ ወደ ውስጥ ማለፍ ያዘች። ወዲያው ለእሷ በተከፈተው በር መቅደም የፈለገች አንዲት ሴት ከኋላዋ ደርሳ ገፍትራ ጣለቻት። የሚደግፋት አጋዥ ክራንች ከእጇ ተፈናጥሮ ወደቀ። ሁኔታው አስደንጋጭና ድንገቴ ነበር።
«እችላለሁ…»
አድና በስራና በቤተሰብ ሕይወቷ ደስተኛ ነች። ለእሷ ባይሆኑም በእጆቿ የሚመረቱ ጫማዎችን ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ስታደርስ ትረካለች። ይህ ደስታ ደግሞ በሌሎች ተጋብቶ ብታየው ፍላጎቷ ነው። አንዳንዴ ግን ነገሮች ሁሉ በተቃራኒ ይሆናሉ። የእጇን ጥበብ የሚያዩ፣ በሁኔታው የሚገረሙ አንዳንዶች ከአድናቆት ይልቅ አለመቻሏን ሊነግሯት ይፈጥናሉ። ጫማዎቹን በእጃቸው ይዘው እሷ እንዳልሰራችው ደፍረው ይሞግቷታል። አድና ግን በንግግራቸው ታፍራለች እንጂ ፈጽሞ አታዝንም። ሁሌም ከከንቱ ሀሳባቸው ጀርባ ‹‹እችላለሁ›› የሚለውን እውነት በተግባር ታሳያቸዋለች።
አድና ከደጓ አክስቷ መዳፍ ማረፏ የቀን ውሎዋን እንድትረሳ የአካል ጉዳቷን እንዳታስብ ሰበብ ሆኗል። ቤት የሚቆያት ደማቅ ፈግታ የሚያቅፏት መልካም እጆች ሕይወቷ ቀላል እንዲሆን፣ ነገን በተስፋ እንዳታደር አድርጓል። ይህ እውነት ብዙዎች ዘንድ የማይኖር ሀቅ ነው።
እንዲህም ይኖራል
አድና ስለ አክስቷ ቅንነት ስታስብ የነገው ሕይወቷ ጭምር መልካም ሆኖ ይታያታል። አክስቷ ከእናት በላይ ማንነቷን ገንብተዋል። አይምሮዋን አንፀዋል። ከአንድ ልጃቸው እኩል የልጅነት ማዕረግ ሰጥተው ‹‹ልጄ›› ሲሉ እናት ሆናዋል። አድና ስለዚህች ሴት ያላት ክብር ቃላት ገልጾት፣ ንግግር ተሸክሞት አያውቅም።
እሷን መሰል አካል ጉዳተኞች በማንነታቸው ያለባቸውን ጫና አሳምራ ታውቃለች። ቤት ተከራይተው፣ ሩቅ መንገድ አልፈው፣ በቤተሰብ ተጽዕኖ አንገት ደፍተው የሚኖሩትን ታውቃለች ። እሷ ግን ለአንድም ቀን ይህ አይነቱ ስሜት ውስጧ ዘልቆ አላደረም።
አድና ሁሌም ከ‹‹እችላለሁ›› ጀርባ ‹‹አያቅተኝም›› ይሉት ስሜት አብሯት አለ። ይህ ጥንካሬ በውስጧ እንዲኖር ያደረጉ ቤተሰቦቿ ነገ የተሻለ እንዲሆን ከጎኗ ናቸው። አድና ማለት በቤት ውስጥ ከሁሉም እኩል ነች። ስራ የምትታዘዘው፣ እንግዳ የምትቀበለው፣ እንደ አቅሟ እየተባለች አይደለም። ሌሎች የሚሰሩትን ሁሉ ታደርጋለች ። የምታደርገው ከሌሎች አያንስም። እንደ ሴት ልጅ ሙያውን፣ ቤት አያያዙን፣ የማወቅ ግዴታና ውዴታው ተጥሎባታል። ይህ መሆኑ ደስታዋን ጨም ሯል። ተስፋዋን አብርቷል።
ስለነገ
አድና ዛሬ ላይ ቆማ ስለነገ ብዙ ታልማለች። አሁን ባለችበት ሙያ በተሻለ መንገድ ብታድግ፣ ብትለወጥ ምኞቷ ነው። ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች ‹‹አይችሉም›› ከሚለው ስሜት ተላቆ ጥንካሬቸውን እንዲያደንቅ የሚያስችል እውነት ቢፈጠር ትሻለች። ለዚህ ደግሞ እሷን መሰል ወገኖች ከልመና ይልቅ በስራ አምነው፣ በዓይምሯቸው ጥበብ እንዲኖሩ፣ ሰርተው እንዲለወጡ ትመክራለች።
ከምንም በላይ ግን አድና ነገን በትዳር ዓለም ጎጆ ቀልሳ፣ ልጆች ወልዳ ብትኖር ምኞቷ ነው። ለዚህ ሀሳቧ ከፍላጎትና ምኞት በላይ የሁልጊዜው የ‹‹እችላለሁ›› ጥንካሬዋ ከእሷ ጋር ነው። አድና በመልካም እጆች ውስጥ አድጋ፣ በፍቅር ዓለም የምትኖር፣ ነገን በበጎ የምታልም ጠንካራ ወጣት ነች። ይህ ለአብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች የማይቸር ዕድል በተቃራኒው የእሷን ሕይወት አቅንቶ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ያስብል ዘንድ ግድ ብሏል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015