የሕይወታችን ስኬት በየቀኑ በውስጣችን በሚመላለሱ ሃሳቦችና በምንፈፅማቸው ድርጊቶች ይወሰናል። አሸናፊዎች ሁሌም የመሻሻልና የእድገት አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ባሉበት መርገጣቸውን በፀጋ ተቀብለው ከሚኖሩ ወይም ለመሻሻል የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማድረግ ድፍረት አጥተው ከተቀመጡ ሰዎች በእጅጉ ይለያል፡፡ ህልማችንን እናሳካለን ወይስ ሁሌም የሌሎችን ስኬት በስስት እያየን አልያ ደግሞ የአርባ ቀን እድላችንን እንኖራለን የሚለውን ከሚወስኑት መካከል አንደኛው አስተሳሰባችን ነው፡፡ ከዚህ በታች የሚቀርቡት ሰባት ነጥቦችም አሸናፊዎች ጠንካራ አስተሳሰብና አመለካከት የሚያዳብሩባቸው መንገዶች ናቸው፡፡
1ኛ. አሸናፊዎች ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ስኬቶች ይማራሉ
አንዳንድ ጊዜ የተሳካላቸው ሰዎች ስናይ ያገኙትን ስኬት ለማግኘት ያለፉበትን መንገድ በደምብ ተረድተን ከዛ የምንማረውን ከመለየት ይልቅ ወይ ስኬቱን እናንኳስሳለን አልያ ደግሞ ስኬቱን ያገኙት በዘመድ፣ በጉቦ፣ በስርቆት፣ በአጋጣሚ… ወዘተ ነው ብለን እናጣጥላለን፡፡ ሰርቆም ሆነ አጭበርብሮ የሚሳካለት ጥቂት ባይጠፋም የዛኑ ያህል በጠንካራ ስራ የሚያድግ አለና እነሱን ለይቶ የተሻለውን እውቀት መቅሰም ተመራጭ ነው፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ እነዚህን ስኬታማ ሰዎች እንደተለዩ ሰዎች በመውሰድ ያን ስኬት ለእኛ እንደማይሆን አድርገን እንደመድማለን፡፡ ነገር ግን ይህ ልክ አይደለም። ልብ በሉ የሆነ ነገር ልታደርጉ አስባችሁ ‹‹አይ! የሄማ አይሆንም›› ስትሉ ገና ሳትጀምሩ ተሸንፋችኋል፡፡ አሸናፊዎች ሊሳሳቱ ወይም ያሰቡት ላይሳክ እንደሚችል አስቀድመው ያውቃሉ፡፡ ሳይወድቁ በፊት ግን ‹‹ተሸንፌያለሁ ወይም ያሰብኩት አልሆነም›› ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም፡፡ ያሰቡት ሳይሳካ ቢቀር እንኳን ከስህተታቸው ተምረው ለተሻለ ሕይወት የጀመሩትን ጉዞ ይቀጥላሉ፡፡
2ኛ. አሸናፊዎች ከራሳቸውም ይሁን ከሌሎች ሰዎችና በተለያዩ ሁኔታዎች በሚመጡ መሰናክሎች ምክንያት የጀመሩትን ጉዞ አያቋርጡም
ችግር ወይም መሰናክል አያጋጥምም ማለት አይቻልም፡፡ ነገ ግን አሸናፊዎች ለህልማቸው ታማኝ ስለሆኑ የሚያጋጥሟቸውን መሰናክል እንደሰበብ አይጠቀሙባቸውም፡፡ የሚገጥማቸውን ችግር አግዝፎ በማየትም እጃቸውን በተስፋ መቁረጥ አይሰጡም። ይልቁንም ለችግሮቹ መፍትሄ በመፈለግ የጀመሩትን ለውጥ ቀን ተቀን ይተገብራሉ፡፡ አስተውሉ ስኬት በአንድ ጀምበር የሚሆን ተዓምር አይደለም፡፡ በእያንዳንዷ ቀን የምናደርጋቸው ትንንሽ ስራዎች ስብስብ ውጤት እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ልናደርግ የምንፈልገውን ለውጥ ከወሰንን በኋላ ያዝ ለቀቅ ማድረግ የለም፡፡ በየቀኑ ለራሳችን ስንታመን የምናደርገው ለውጥ መልካም ልማድ ሆኖ በብዙ ትግል ልንተገብረው እንችላለን፡፡
3ኛ. አሸናፊዎች ነገሮች ባላሰቧቸው አቅጣጫ ሲሄዱ ‹‹ወይ እድሌ! ወይም የአርባ ቀን እድሌ! ነው›› አይሉም፡፡
ያን ካደረግን ከጅምሩ ከጨዋታ ውጭ ሆነናል። ማን የአርባ ቀን እድሉን መቀየር ይቻለዋል እያሉ ማማረር ተገቢ አይደለም፡፡ ማንጄሎ የተሰኘው ታዋቂው አሜሪካዊ ፀሐፊ በልጅነታቸው አያታቸው የሰጧቸው አንድ ምክር ነበር፡፡ ‹‹ሰማሽ ልጄ አንዳንድ ሰዎች በትልቁም በትንሹም ያማርራሉ፡፡ ስለሙቀቱ፣ ስለብርዱ …ወዘተ፤ የምናማርርባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ልጄ በእያንዳንዱ ቀን ከዓለማችን አንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ በሰላም ወደ አልጋቸው ሄደው ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ የሚቀሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ሀብታምና ደሃ፣ ነጭና ጥቁር፣ ረጅምና አጭር ብቻ እነዚህ ሰዎች አልፈዋል፡፡ ለአምስት ደቂቃ ያህል እንኳን ተመልሰው ይሄ የምናማርርበትን አየር ማየትና እንደገና መሳብ ቢችሉ ምን ያህል በተደሰቱ፡፡ ስለዚህ ልጄ አንቺም ብትሆኚ በረባ ባልረባው ከማማረር ራስሽን ጠብቂ፡፡ የማትወጂው ነገር ካጋጠመሽ ለመቀየር ሞክሪ፡፡ ያልወደድሽውን ነገር መቀየር ካልቻልሽ ደግሞ ነገሩን የምታይበትን እይታ መቀየር እንጂ አታማሪ›› ሲሉ መክረዋታል፡፡
ስለዚህ ሕይወታችንን በማንፈልገው አቅጣጫ እየሄደ ከሆነ ጊዚያችንን በማማረር ሳይሆን መፍትሄ በመፈለግ ልናሳልፍ ይገባል፡፡ ሰዎች ስለሚጠሉት ነገር ሲያማርሩ ከሚውሉ ይልቅ የሚወዱት ነገር ላይ በትጋት ቢሰሩ ዓለም እንዴት የተሻለች ትሆን ነበር፡፡
4ኛ. አሸናፊዎች የሚደሰቱት በሌሎች ሰዎች ውድቀት ወይም መከራ አይደለም
ሌሎች ሰዎች ሲያሸንፉ ወይም ሲሳካላቸው ማየት ደስ ይላቸዋል፡፡ ስለሆነም የሚናገሩት ነገር ሰዎችን የሚያበረታታ እንጂ ሰዎችን የሚጎዳ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳይሆን ይጠነቀቃሉ፡፡ ምክንያቱም ቃል ይገድላልም፤ ያንፃልምና፡፡ ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ እንደሚባለው ለዚህ እውነት አስረጂ ታሪክ እንካችሁ፡፡
በአንድ ወቅት ብዙ እንቁራሪቶች በአንድ ላይ ሆነው በጫካ ውስጥ እየሄዱ እያለ ሁለት እንቁራሪቶች ጥልቅ ከሆነ ጉድጓድ ውስጥ ወደቁ፡፡ ከገደል ያልወደቁት እንቁራሪቶች ከጉድጓዱ አፋፍ ዙሪያ ተሰባስበው የጉድጓዱን ጥልቀት ተመለከቱና ሁለቱን እንቁራሪቶች ‹‹አዬ ጉድ ምን አይነት ጉድ አገኛችሁ እናቴ! ይሄ ጉድጓድ ጥልቅ ነው መውጣት አትችሉም›› አሏቸው ሁለቱ እንቁራሪቶች ግን ከጉድጓዱ ዘለው ለመውጣት ጥረታቸውን ሳያቋርጡ ቀጠሉ፡፡ ከጉድጓድ ውጭ ያሉ እንቁራሪቶችም ‹‹ይሄ ነገር ተስፋ የለውም ነው የምንላችሁ፤ ዝም ብላችሁ ነው የምትደክሙት›› ማለታቸውን አላቋረጡም፡፡
ከብዙ ቆይታ በኋላ ታዲያ አንደኛው እንቁራሪት ውጭ ያሉ እንቁራሪቶች የሚሉትን ተቀብሎ ዘሎ ለመውጣት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት አቆመ፡፡ ተስፋውን ሲያጣም ነው መሰል ብዙም ሳይቆይ ሞተ። ሌላኛው እንቁራሪት ግን ምንም ያህል ቢደክመው መዝለሉን አላቋረጠም። ውጭ ያሉት እንቁራሪቶችም ‹‹ኧረ አሟሟትህን እንኳን አሳምር፤ እንደው ዝም ብለህ አትድከም፤ አጉል መንፈራገጥ ለመላላጥ ነው ሲሉ አልሰማህም›› እያሉ መጮሃቸውን ቀጠሉ፡፡ ያ እንቁራሪት በመጨረሻ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ ከጉድጓድ መውጣት ቻለ፡፡
ውጭ ያሉት እንቁራሪቶችም ዙሪያውን ከበው ‹‹አልሰማኸንም እንዴ? እኛ እኮ ያለመታከት ተው ይቅርብህ ብለንህ ነበር›› ቢሉት እንቁራሪቱ ግን ምን እያሉት እንደሆነ እንኳን ሊገባው አልቻለም፡፡ ለካስ መስማት አይችልም ነበር፡፡ ያን ሁል ጊዜ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ አትችልም፤ ይቅርብህ እያሉ ሲጯጯሁ ‹‹በርታ! ትንሽ ነው የቀረህ!›› እያሉት መስሎት ነበር ዝላዩን ያላቋረጠው፡፡
ስለዚህ ለጓደኞቻችን፣ እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና ልጆቻችን የምንሰጣቸው ምክሮችና የምንናገራቸው ነገሮች ለሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም ስለሚኖረው ቃላቶቻችንን መምረጥ ተገቢ ነው፡፡
5ኛ. አሸናፊዎች ከሚያሳንፉና ተስፋ ከሚያስቆርጡ ሀሳቦች ራሳቸውን ይጠብቃሉ
በእያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ውስጥ በአማካይ ወደ ስልሳ አራት ሺ ሃሳቦች በየቀኑ ይመላለሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሀሳቦች ያለኛ ቀጥተኛ ፍቃድ ነው በአእምሯችን ሲመላለሱ የሚውሉት። አስተውላችሁ ከሆነ የሆነ ነገር እየሰራችሁ ወይም ዝም ብላችሁ በተቀመጣችሁበት በሀሳብ ሩቅ ሄዳችሁ ብንን ስትሉ ወይ ስላለፈ ጊዜ አልያም ገና ስለሚመጣው ጊዜ ስታውጠነጥኑ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ፡፡ ከየት ተነስታችሁ እንዴት እዛ እንደደረሳችሁ ግር እስኪላችሁ ድረስ፡፡ የእንደዚህ አይነት ሀሳብ ችግሩ ብዙን ጊዜ ወይ ድሮ ስለሰራነው ስህተት፣ ስላመለጠን እድል፣ ስላላገኘነው እድገት… ወዘተ አልያ ደግሞ መጪውን ጊዜ በፍራቻና በስጋት ማየታችን ነው፡፡
አሸናፊዎች ሀሳባቸውን ይመረምራሉ፡፡ በውስጣቸው ለሕይወታቸው መሻሻል የማያግዙ ሃሳቦች ብልጭ ሲሉ በፍጥነት ይቀጯቸዋል፡፡ አትችልም አልችልም፣ ከባድ ነው አይሆንም፣ አንተማ እንዴት ሆኖ፣ አንቺማ በየት ብለሽ አይነት ጨለምተኛና ጎታች ሃሳቦችን ቦታ አይሰጧቸውም፡፡ ይልቁንም ‹‹እችላለሁ፤ እደርሳለሁ ፈጣሪ የሚያስፈልገኝን እምቅ አቅም ሰጥቶኛል ያን ደግሞ አውጥቶ መጠቀም የኔ ኃላፊነት ነው ለዛም ጠንክሬ እስራለሁ፤ ህልሜንም አሳካለሁ›› ብለው ጉልበት የሚሰጡ ሃሳቦችን ያዘወትራሉ፡፡
6ኛ. አሸናፊዎች መድረስ የሚፈልጉበትን ቦታ በግልፅ ያውቁታል
አሸናፊዎች ህልማቸውን ሲያልሙም በትልቁ ነው፡፡ ይሆናል ብላችሁ ከምታስቡት በላይ አልሙ፡፡ አለበለዚያ ሁሌ ልንደርስበት የምንችልበትን ቦታ አሳንሰን ስለምንነሳ ጥረታችንም ያን ያህል ትንሽ ይሆናል፡፡ ትንሽ ችግር መንገዳችን ላይ ሲያጋጥመን ስንነሳ ከሰነቅነው ትንሽ ህልም ያነሰ ቦታ የመድረስ እድላችን ይሰፋል። ያን ካደረጋችሁ በኋላ በሕይወታችሁ የምታዩትን ለውጥ በቀጣይነት ገምግሙ፡፡ የምትከታተሉት ያሰባችሁበት ቦታ የመድረስ ያለመድረሳችሁን ብቻ ሳይሆን ከእለት እለት በሕይወታችሁ የምታዩትን ለውጥ መሆን አለበት፡፡
ለምሳሌ አንድ መቶ ኪሎ ግራም የሚመዝን ሰው ቢኖርና ወደ ሰባ ኪሎ ግራም መቀነስ ቢፈልግ ከአምስት ወር ጥረት በኋላ ራሱን ሲለካ ሰማንያ አምስት ኪሎ ግራም ቢመዝን ሰባ አለመድረሱ ደስታውን ሙሉ ባያደርገውም እያሳየ ላለው ለውጥ ተገቢውን እውቅና ካልሰጠ ተስፋ ቆርጦ ከጀመረው መልካም መንገድ ሊያፈገፍግ ይችላል። ሰማንያ አምስት ኪሎ ግራም ላይ ለመድረስ በራሱ ብዙ ለውጦችን አድርጎ ወይም አድርጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአብነትም በየቀኑ ስፖርት መስራት፣ ጤናማ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ አስፈላጊውን ያህል እንቅልፍ በየቀኑ መተኛት …. ወዘተ፡፡ እነዚህ ለውጦች በራሳቸው እንደ ትልቅ ድል ተቆጥረው ለቀጣዩ ጥረት የበለጠ መነቃቃት እርሾ መሆን ይችላሉ፡፡
ለዚህ ነው መድረስን ብቻ ሳይሆን መቅረብን መከታተል ያስፈልጋል የሚባለው፡፡ ትልቅ ህልም ከሰነቅን በኋላ ያንን ህልም ማሳካት የምንችልበት እቅድ ያስፈልጋል፡፡ ያ እቅድ ሊኖሩት ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡ መቼ ምን አድርገን መቼ ውጤቱን ለውጡን ለማየት እናስባለን፤ አለበለዚያ እንዲሁ በድፍኑ ሀብታም መሆን እፈልጋለሁ፣ በስራ ቦታዬ እድገት ማግኘት እፈልጋለሁ፣ ስራ ማግኘት እፈልጋለሁ፣ ሚስት ማግባት እፈልጋለሁ….ወዘተ ቢባል አይሰራም፡፡ አስፈላጊውን ሥራ የምንሰራበትና ቆም ብለን ራሳችንን የምንገመግምበት ግልፅ ቀን፣ ሳምንት፣ ወር ወይም ዓመት ያስፈልገናል፡፡
7ኛ. አሸናፊዎች ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጠንካራ ማህበራዊ የስራ፣ የቢዝነስ ወዘተ ግንኙነትን ይመሰርታሉ
ለብቻ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ከሰዎች ጋር የምንመሰርታቸው ግንኙነቶች መረጃ ለመለዋወጥ በሃሳብ ለመረዳዳት፣ በስራ ለመተጋገዘ ወዘተ ወሳኝ ናቸው፡፡ ሕይወታችሁ እንዲሄድ በምትፈልጉት መንገድ ላይ ያሉ ወይም ተመሳሳይ ህልም ካላቸው ሰዎች ጋር መሆን ጉዟችሁን የተቃና ሊያደርገው ይችላል፡፡ ታዲያ በእንደዚህ አይነት ግንኙነት ውስጥ ከሰው የምንጠብቅ ብቻ ሳንሆን ይነስም ይብዛ የአቅማችንን የምናበረክትም ብንሆን መልካም ነው፡፡
በዚች ዓለም መውደቅም መነሳትም ያለ ነው፡፡ አንዱ ሲሳካለት ሌላኛው ይወድቃል፡፡ የወደቀው ሲነሳ የተሳካለት መልሶ ይወድቃል፡፡ ዋናው ቁምነገሩ ግን ከውድቀት ተምሮ ዳግም ላለመውደቅ መጣር ነው። ስኬትና አሸናፊነት ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ ባለመሆኑ ሁሌም ቢሆን የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ለመቋቋምና እንደ አመጣጣቸው ለመመለስ ራስን ማዘጋጅት እንዲሁም ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
እናም ሰው ሆይ ህልምን ለማሳካትና አሸናፊ ለመሆን ከፈለክ እነዚህን ሰባት ነጥቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ይሞክር!! ነገር ግን እነዚህ ነጥቦች አንዳንዴ ላይሰሩም የሚችልበት እድል ስለሚኖር ከራስ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ተግባራዊ ማድረጉ አይከፋም፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015