በፍጥነት ማሰብ!

አስተውላችሁ ከሆነ ሀገራት ከባድ ሩጫ ላይ ናቸው። የኢንተርኔት ፍጥነትን ለማሳደግ ‹‹ፎር ጂ›› እና ‹‹ፋይፍ ጂ›› ይላሉ፡፡ ለምን ይመስላችኋል? የኢንተርኔት ፍጥነት በጨመረ ቁጥር መረጃዎችን በፍጥነት ለመቀያየር ስለሚያስችላቸው ነው፡፡ መረጃዎች በፍጥነት በተቀያየሩ ቁጥር ደግሞ ሥራቸውን በፍጥነት በማከናወን ያለሙት የእድገት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡

እኛም ማደግ፣ መለወጥና ሕይወታችንን እስከ መጨረሻው መቀየር የምንፈልግ ከሆነ አዕምሯችን የሚያስብበት ፍጥነት መቀየር አለበት፡፡ አዕምሯችን እንደ ተንቀሳቃሽ ስልክ ነው፡፡ መተግበሪያው ደግሞ ሃሳብ ነው። ሃሳባችን በፍጥነት ከተንቀሳቀሰ ሕይወታችንን መቀየር እንችላለን፡፡ የምንፈልገውን ነገር በአንዴ እንለምዳለን። ሥራችንን በፍጥነት እናከናውናለን፡፡ የተሻለ ቦታ ላይ እንገኛለን፡፡ ውጤታማም እንሆናለን፡፡

በፍጥነት ስናስብ በርካታ ነገሮችን በቀላሉ ማሳካት እንችላለን፡፡ በቶሎ ሥራችንንና ትምህርታችንን እናጠናቅቃለን፡፡ የምንፈልገውን ነገርም በፍጥነት እንለምዳለን፡፡ ምናልባት ቋንቋ ይሆናል መልመድ የፈለግነው፡፡ ወይ ደግሞ በትምህርታችን ይሆናል መጎበዝ የፈለግነው፡፡ አልያም ሥራችንን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ ፈልገን ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አዕምሯችን ከፈጠነ ሁሉ ነገር ቀላል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በፍጥነት የማሰብ ችሎታን እንዴት ማዳበር እንችላለን?

1ኛ. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

ተክዘን፣ ድክም ያለ አቀማመጥ ተቀምጠን በፍፁም በፍጥነት ልናስብ አንችልም፡፡ ቢያንስ መንቀሳቀስና መራመድ አለብን፡፡ ልክ ሲንቀሳቀስ ስሜታችን ይቀየራል። በደንብ ማሰብ እንጀምራለን፡፡ ‹‹emotions are created from motions›› ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ጥሩ ስሜት የሚሰማን ስንቀሳቀስ ነው እንደ ማለት ነው፡፡ በተንቀሳቀስን ቁጥር ጥሩ እናስባለን፡፡ ስለዚህ አዕምሯችን በሙሉ አቅሙ እንዲያስብ የሚያደርገው አንዱና ዋነኛው ነገር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ነውና የግድ ከባድ ሳይሆን ቀላል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለብን፡፡

ለምሳሌ ትንፋሻችንን ለማስተካከል የሚረዱ ኤሮቢክ እንቅስቃሴዎችን መሥራት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ረዘም ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ ይቻላል፡፡ በመጠኑ ፈጠን ብሎ መሮጥም ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ዋናው ዓላማው ትንፋሽ እንዲወጣ፣ እንዲገባና በሰውነታቸውን ጥሩ የአየር እንቅስቃሴ እንዲኖር ነው የሚፈለገው፡፡ ይህም አዕምሯችን ነፃ ሆኖ እንዲያስብ ያስችለዋል፡፡ ይህን በሳምንት ውስጥ ለሶስት ወይም ለአራት ቀን ካደረግነው በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡

ታዲያ መቼ ልሥራ ካሉ በጠዋት ይሁን፡፡ ለምን መሰለዎ? በጠዋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሰሩ አብዛኛውን የአዕምሮ ማሰብ ሥራ የሚከውኑት ‹‹ኒውሮ ትራንስሚተር›› የተሰኙት ክፍሎች ሥራቸውን በፍጥነት ስለሚሰሩ ነው፡፡ ከስፖርቱ በኋላ ቢያነቡ፣ ሥራ ቢሠሩና አዲስ ነገር ቢሞክሩ አዕምሮዎ በፍጥነት ያስባል፡፡ ‹‹እኔ ማታ ከሥራ በኋላ ነው ስፖርት የምሠራው›› ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ማታ ስፖርት ከሰሩ በኋላ ይደክምዎታል፡፡ አዕምሮዎም በዚህ ሰዓት አዲስ ነገር ሊያስብ አይችልም፡፡ ስለዚህ ስፖርት በጠዋት ቢሰሩ ይመከራል።

2ኛ. ነገሮችን እንደመዝናኛ መቁጠር

ይህ ማለት የሚማሩትን ትምህርትና የሚሠሩትና ሥራ እንደ መዝናኛ መቁጠር እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን አዕምሮዎ በተቀላጠፈ ሁኔታ ያስባል፡፡ ልብ ብለው እንደሆነ ሲዝናኑ ቶሎ አይሰለቹም፡፡ ቶሎ አይደክሙም፡፡ መቆምም አይፈልጉም፡፡ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ የተዝናኑበትን ወቅት አይረሱትም፡፡ ስለዚህ ሥራውንም፤ ትምህርቱንም እንደ መዝናኛ መቁጠር ነው። የግድ መሥራት ያለብን ነገር ካለ ለራሳችን ጥሩ ጥሩውን ነገር መንገር ነው፡፡ ‹‹እኔ እኮ በጣም የምወደውን ሥራ እየሠራሁ ነው፣ እኔ እኮ በጣም ነው ደስ የሚለኝ ሥራዬን ስሠራ፣ በጥሩ ስሜት ውስጥ ነው ያለሁት፣ ሥራዬን እንደ መዝናኛ እኮ ነው የማየው›› ማለት አለብን፡፡

እነዚህን ንግግሮች በደጋገምናቸው ቁጥር አዕምሯችን እውነት ይመስለዋል፡፡ መቼም ታውቃላችሁ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› ሲባል፡፡ አያችሁ! ስለዚህ በሥራችን እንደምንዝናና ለአዕምሯችን ደጋግመን በነገርነው ቁጥር የሆነ ሰዓት ላይ ሥራውን እያቀላጠፍነው ነው፡፡ በፍጥነት እየጨረስን ነው፡፡ ለምን? አዕምሯን የሚያውቀው ያ ነገር እንደሚያዝናንን ነው፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ያስባል ማለት ነው፡፡

3ኛ. መደጋገም

ዓለምን ጉድ ካስባሉ የአዕምሯዊ ጥናቶች መካከል ዶናልድ ሄብ የተሰኘው የሳይንስ ሊቅ የሠራው ጥናት አስደማሚ ነው፡፡ የሄቢያን ቲዎሪ እንዲህ ይላል- ‹‹አንድን ሥራ በመጀመሪያው ቀን ልክ ስናደርገው በአዕምሯችን ውስጥ ያለች አንዲት ትንሽዬ ህዋስ ነቃ ትላለች፡፡ ከዛ አጠገቧ ያለውን ሌላ ደቃቅ ህዋስ ትነካዋለች፤ ታግለዋለች። እሱ ደግሞ ሌላውን ያጋግላል፡፡ እንዲህ እያሉ አንዱ ሌላውን ህዋስ እያጋጋለ መላው ህዋስ ይጋጋላል፡፡ በዚህም ሁሉም ህዋሳት ስሜት ውስጥ ገብተው organic transformation ይፈጥራሉ፡፡ ወይም በሌላ አነጋገር የሁኔታ ለውጥ ይፈጠርና ከዚህ በኋላ ሥራውን ደጋግመን ስንሰራ ህዋሳቱ ቶሎ ቶሎ መነቃቃት ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ሥራውን እንሠራዋለን››

ለምሳሌ ስልክ የመጀመሪያችን ከሆነ የኪቦርድ ፊደላትን ፈልጎ ለመንካት ጊዜ ይፈጅብናል፡፡ ነገር ግን አዕምሯችን እነዚህ ሴሎች ካለማመደ በኋላ አንዱን ነክቶ ሌላውን መንካት ቀላል ይሆንለታል፡፡ ከዛም ሁሉንም ፊደላት በፍጥነት መንካት እንችላለን፡፡ ለምን? አዕምሯችን ይህን ተግባር ለምዶታል፡፡ ስለዚህ በምንም ነገር በፍጥነት ማሰብ ከፈለግን፣ ምንም ዓይነት ምድራዊ የሆነ ክህሎት መቻል ከፈለግን በቃ አዕምሯችንን ማለማመድ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ መደጋገም ነው፡፡

ዓለምን ያስደመሙ ሰዎች የተሳካላቸው በመደጋገማቸው ነው፡፡ የዓለማችን እግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ወዶ መሰላችሁ እንደው በየቀኑ ኳስ ሳልነካ አልውልም የሚለው፡፡ እነ ቢልጌት የኮምፒዩተር ፕሮግራም ሳልሰራ ውዬ አላድርም ነበር የሚሉት። ሌሎቹም እንደዛው ክህሎታቸውን ይደጋግሙታል። እርስዎም ሕይወትዎን ሊቀይር የሚችልና በጣም የሚፈልጉት ነገር ካለ ይደጋግሙት፡፡ ስኬታማ ያደርግዎታል፡፡

4ኛ. የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል

የምንበላው፣ የምንጠጣው፣ የምናየውና የምንሰማው ነገር ሊያፈጥነውም ሊያዘገየውም ይችላል፡፡ ለምሳሌ በጣም ጠግቦ የሚበላ ሰው ማሰብ ይከብደዋል። ይደክመዋል፡፡ ማረፍ፤ መተኛት ነው የሚፈልገው። ውሃ በደንብ የማይጠጣ ሰው አዕምሮው ቶሎ ማሰብ አይችልም፡፡ ይደክመዋል፡፡ መጠጥ የሚያበዛ ሰውማ የሚያውቀውንም ሁሉ ሊረሳ ይችላል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ውሃ በደንብ መጠጣት፣ የተመጣጠን ምግብ መመገብ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል የምናያቸው ነገሮች ተደጋጋሚና አሰልቺ መሆን የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰው ከጦርነት ፊልም ውጭ ምንም አያይም፡፡ ስለዚህ አዕምሮው በፍጥነት ለማሰብ ይቸገራል፡፡ እንደውም የሚያስበው በጉልበቱ ሊሆን ይችላል። አዕምሮዬ እንዴት በፍጥነት ሰርቶ ገንዘብ ላግኝ አይልም፡፡ ለምን? የሚያየው የድብድብ ፊልም ነዋ! ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ወጣ ያለና አዲስ ነገር መሞከር አለብን፡፡ ‹‹እኛም እኮ ይህን ስለምናውቅ ነው የፍቅር ፊልም የምናየው›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ የፍቅር ፊልምም ደጋግሞ የሚያይ ሰው ከዛ ውጪ የማያይ ከሆነ ስሜቱ ስስ ነው የሚሆነው፡፡ በቃ ነገሮችን የሚተረጉመው ከስሜት አንፃር ብቻ ነው፡፡ ቶሎ ይጎዳል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ውስጥ አዲስ ነገር መሞከር አለብን፡፡ የምናየውና የምንሰማው መቀየር አለበት፡፡ አድማሳችንን ባሰፋነው ቁጥር አዕምሯችን በፍጥነት ያስባል፡፡ ብዙ ነገር ማሰብ ይችላል፡፡

5ኛ.መጠነኛ ቅዝቃዜ ላይ መሆን

በጣም ሙቀት ውስጥ ከሆንን ድካም ነው የሚሰማን፡፡ እንቅልፍ እንቅልፍ ነው የሚለን፡፡ መተኛት ነው የሚታየን፡፡ ውጫዊ ድካም ደግሞ ውስጣዊውን ይገለዋል፡፡ እንዴት ነው እርስዎ ደክሞዎት የሚገርም ሃሳብ ሊያስቡ የሚችሉት? ስለዚህ ቀዝቀዝ ያለ ሻወር መውሰድና መጠነኛ የሰውነት ሙቀት ላይ መሆን አለብዎ። በፍጥነት እንዲያስቡ መቀዝቀዝ አለብዎ፡፡

6ኛ.ውጫዊና ውስጣዊ ማነቃቂያ ማስቀመጥ

የሰው ልጆች ሆነን አንድ ነገር ለመሥራት፣ ለማሰብና በደንብ ለመማር የሆነ ሽልማት እንፈልጋለን፡፡ ውጫዊ ሽልማቶች አንዳንዴ ይኖራሉ፡፡ ሽልማቱ ገንዘብ፣ በትምህርት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አልያም የሰዎች አድናቆት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ከራሳችን ሳይሆን ከሰዎች የምናገኘው ሽልማት ነው፡፡ አያችሁ! አንዳንዴ ስንሰራ ሰዎች ዞር ብለው ላያዩንም ይችላሉ፡፡ እኛ ግን ምርጥ ነገር እየሰራን ነው፡፡

ለአዕምሯችን ሽልማት ካስቀመጥንለት በፍጥነት ያስባል፡፡ ስለዚህ ከሰው ሳንጠብቅ ራሳችንን መሸለም አለብን፡፡ ‹‹ይህን ሥራ ከሠራሁት በደንብ አድርጌ እዝናናለሁ፡፡ እደሰታለሁ፡፡ የምወደውን ምግብ እበላለሁ። ከምወደው ሰው ጋር አወራለሁ፡፡ ከመውደው ሰው ጋር እዝናናለሁ፡፡ የእግር ጉዞ አደርጋለሁ፡፡ አዕምሮዬን የሚያስደስተኝን ነገር አደርጋለሁ›› ስንል ያንን ሥራ ለመሥራት ሲል አዕምሯችን በፍጥነት ያስባል፡፡ ሥራው ይሰራል፡፡ ትምህርቱም ቶሎ ይገባናል፡፡ ለምን? ሽልማት አስቀምጠናላ! እንጓጓለን፡፡

ለአዕምሯን ውጫዊ ማነቃቂያ ብቻ በቂ አይደለም። ውስጣዊም ያስፈልጋል፡፡ ውስጣዊ ስንል አንድን ነገር ስንሰራ በውስጣችን የሚሰማን ስሜት መጋል አለበት ማለት ነው፡፡ ‹‹ይሄን ሥራ እኮ በደንብ ከጨረስኩት፣ በደንብ አድርጌ አስቤ ትምህርቴን ካጠናሁት፣ ቋንቋውን በደንብ ከቻልኩት ምን ዓይነት በራስ መተማመን ነው የሚሰማኝ›› ስንል ውስጣችን ለራሱ ሲል፣ በራስ መተማመኑን ለማሳደግ ሲልና ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ለማድረግ ሲል ቶሎ ይገባናል፡፡ ቶሎ እናነባለን፡፡ በፍጥነት ማሰብ እንችላለን፡፡ ሥራው ይቀላጠፍልናል፡፡

7ኛ. መፃፍ

ችግር ገጥሞዎት መፍትሔ ፈልገው ይሆናል። ስልክዎን ያጥፉ፡፡ በጥሩ አቀማመጥ ወንበር ላይ ይቀመጡ፡፡ ከዛ ወረቀትና እስክርቢቶ ያውጡ፡፡ የገጠመዎን ችግርና ምን መፍታት እንደሚፈልጉ ይፃፉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሁለት ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡ የመጀመሪያው ችግሩ ቀለል ይልዎታል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ልክ መፃፍ ሲጀምሩ አዕምሮዎ መፍጠር ይጀምራል፡፡ ‹‹ችግሩን እንዲህ ቢፈቱትስ›› እያለ አዕምሮዎ ያስባል፡፡

ከምንጽፈው ፍጥነት በላይ አዕምሯችን ያስባል፡፡ ከዛ መፃፍ ነው እንግዲህ የመጣልንን መፍትሔ፡፡ ብዙ ሰዎች ‹‹ወረቀት ላይ በፃፍኩ ቁጥር ችግሬን እየፈታሁት ነው፤ ደስተኛ እየሆንኩ ነው›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ ችግሮቻችንን ወረቀት ላይ መፃፍ አስገራሚ መፍትሔ ነውና እርስዎም ይለማመዱት፡፡

8ኛ. ትክክለኛውን ጥያቄ መጠየቅ

አንድን ነገር በግልፅና ቅልብጭ ባለ መልኩ ከጠየቅን አዕምሯችን በአንድ አቅጣጫ ያስባል፡፡ መፍትሔ ለማግኘት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ‹‹እንዴት ሕይወቴን ልቀይር?›› ብሎ ጥያቄ ቢያስቀምጥ ግልፅ አይደለም፡፡ በጣም ውስብስብ ነው። ሕይወቱን የሚቀይረው በገንዘብ ነው፣ በሥራ ነው፣ በትምህርት ነው ወይስ በፍቅር ግንኙነት ነው? ‹‹አይ እኔ በገንዘብ ነው ሕይወቴን መቀየር የምፈልገው›› ካለ ሁለተኛ ማንሳት ያለበት ጥያቄ በገንዘብ እንዴት ሕይወቴን ልቀይር? ሊሆን ይችላል፡፡

ይህም ቢሆን ግልፅ ጥያቄ አይደለም፡፡ በገንዘብ እንዴት ሕይወቴን ልቀይር ሲል ገንዘብ እኮ በተለያየ መንገድ ይገኛል፡፡ በቢዝነስ ነው ሕይወቱን የሚቀይረው፣ በብድር ነው ገንዘቡን የሚያሳድገው ወይስ በደሞዝ ነው ገንዘቡን ከፍ የሚያደርገው? ማሳደግ የምፈልገው ደሞዜን ነው ብሎ ወርሃዊ ገቢዬን እንዴት ላሳደግ? ብሎ ሶስተኛ ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ይሄ ይሻላል፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም ጥያቄው ግልፅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወርሃዊ ደሞዙ ሃምሳ ብር ከሆነ ሃምሳ አንድ ብር ወር ላይ ቢመጣ አድጓል፡፡ ግን አንድ ብር ሕይወቱን አይቀይረውም፡፡

ጥያቄው ግልፅና ነጠላ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ማለት ያለበት ‹‹ወርሃዊ ገቢዬን እንዴት ሁለት እጥፍ ማሳደግ እችላለሁ›› ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። አሁን አዕምሮው በሁለት እጥፍ ደሞዙን ለማሳደግ የማይፈነቅለው ድንጋይ፤ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። ‹‹ለምን ኦንላይን አትሰራም?›› ይላል፡፡ ከፈለገ ደግሞ ‹‹ለምን ሁለት ሶስት ሥራ አትሠራም?›› ሊልህ ይችላል። እርስዎም ትክክለኛውን ጥያቄ ከጠየቁ አዕምሮዎ ለመመለስ በጣም ፈጣን ነውና ትክክለኛውን ጥያቄ ይጠይቁ፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You