መረጋጋት ተወዳጅ ፀባይ ነው። አስተውላችሁ ከሆነ በተለምዶ ሴቶች በጣም የተረጋጋ ወንድ ይወዳሉ። ወንዶች ደግሞ ስክን ያለች፣ ቁጥብ የሆነችና የተረጋጋች ሴት ይወዳሉ ሲባል እንሰማለን። በጣም የምናደንቃቸውና ምናከብራቸው ሰዎች ራሱ የተረጋጉ ናቸው። ግርማ ሞገሳቸው፣ አነጋገራቸው፣ ሁኔታቸው እርጋታ የተሞላበት ነው።
በተቃራኒው ደግሞ እኛ ሰዎች በባህሪያችን የሚንቀለቀሉ፣ የሚቸኩሉ፣ የሚፈጥኑ ሰዎች አንወድም። የሆነ ሰው ፈጠን ፈጠን ሲል የሚያጭበረብረን ነው የሚመስለን። ሌባ ነው የሚመስለን፣ ኸረ እኔ ቀልቤ አልወደደውም እንላለን። የምንወዳቸው ሰዎች ቢሆኑ እንኳን ፍጥን ፍጥን ካሉ ለቁም ነገር አናስበባቸውም። በቃ! ከመጀመሪያውም ቀልባችን አይወዳቸውም።
የተረጋጉ ሰዎች ግን ቀልብ ይገዛሉ። ስሜት ይገዛሉ። አንዳንድ ሰው በጣም ከመቸኮሉ የተነሳ ሻይ ሲያማስል እንኳን ደወል የሚደውል ነው የሚመስለው። አንዳንድ ሰው ደግሞ ሲናገር በጣም ከመቸኮሉና ስሜታዊ ከመሆኑ የተነሳ እጁ ሲወራጭ አይናችሁን ሊያጠፋው ነው የሚደርሰው። አንዳንድ ሰው ብዙ ከተናገረ በኋላ ነው የሚያስበው። ውይ! እንዲህ ባልናገር ኖሮ እኮ ብሎ ይቆጨዋል። መልሶ የሚያስበው ከተናገረ በኋላ ነው። ስለዚህ በሰዎች ዘንድ ለመወደድ ሳይሆን ለራስ ሲባል መቀየር ያስፈልጋል ማለት ነው። ካልተረጋጋህ፣ የምትቸኩል ከሆነ፣ ፍጥን ፍጥን የምትል ከሆነ የምትወስናቸው ውሳኔዎች ብዙ ግዜ ስሜትህን ይጎዱታል።
የስሜት ብስለት /Imotinal intelegenet/ መረጋጋት ይጠይቃል። አየህ በፍቅር ሕይወትህ ካልተረጋጋህ፣ ስሜታዊ ከሆንክ፣ ቶሎ የምትናደድ አይነት ሰው ከሆንክ ራስህን ትጎዳለህ። በስራህ፣ በትምርትህ ስኬታማ ልትሆን የምትችለው በጣም ተረጋግተህ የምታስብና ምትወስን ከሆነ ነው። መረጋጋት ብልህ ያደርግሃል። ስለዚህ ለመተግበር የሚመቹ፣ በጣም ቀለል ያሉና አጠር ያሉ ጥሩ መረጋጋትን ለማምጣት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ግን አሉ።
1ኛ. የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠር
ብዙ ግዜ መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ስንሄድ ወይም ፓርኮች ውስጥ ስንገባ ስሜታችን መታደስ ይጀምራል። መንፈሳችን ይረጋጋል። ለምን ይመስላችኋል? ቦታው፣ ሁኔታው ራሱ መንፈስን ስለሚያረጋጋ ነው። መቼም ቤተ ክርስቲያን ወይም መስኪድ ሄደህ የሚያማርር ሰው አታይም፤ የሚያመሰግን እንጂ። ቦታው፣ ስሜቱና ሁኔታው ራሱ አንተን ያድስሃል። ብሶት የምትሰማ ከሆነ፣ ምድራዊ ሃሳብና ችግር ብቻ የምታደምጥ ከሆነ መንፈስህ ሊረጋጋ አይችልም።
እስኪ አስበው በስልክህ ምንድን ነው? የምታየው በየቀኑ። ምንድን ነው የምትሰማው? ወየውላችሁ!፣ አበቃላችሁ! አለቀላችሁ! የዚች ሀገር መጨረሻ የሚሉ ሃሳቦችን እየሰማህ እንዴት ትረጋጋለህ። አየህ የምትሰማው ነገር፣ ሁኔታዎች ራሱ፣ የምታያቸው ነገሮች መቀየር አለባቸው።
2ኛ. ጠዋትን ማሳመር
ጠዋትህ በጣም የተረጋጋ ከሆነ፣ በጥሩ ስሜት ከጀመርከው ሙሉ ቀንህ ያማረ ይሆናል። ይህ ሲደጋገም ሕይወትህ የተረጋጋ ይሆናል። ‹‹first impression is last impression›› ይባላል። በቃ ጠዋት አጀማመርህ ማማር አለበት። ብዙ ሰው አርፍዶ ይነሳል። ከዛ ተጣድፎ ወደ ሥራ ይሄዳል። አያመሰግን፣ አይፀልይ፣ ሻወር አይወስድ.. ዝምብሎ ይቀላቀላል። ስራ ቦታ ይገባል፤ ቀኑን ሙሉ ሲያማርር፣ ፀሃዩን ሲወቅስ፣ መስሪያ ቤቱን ሲያማርር፣ ደሞዙን አስቦ ሲያዝን ይውላል።
ትንሽ የሚያደነዝዘውና ሁሉን ሚያስረሳው ስልኩ ነው። ስልኩን አውጥቶ ማህበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም ይውልና የስራ መውጫ ሰዓት ሲደርስ ይወጣል። እግረ መንገዴን እስኪ ፉት ልበል ብሎ የሆነች ነገር ቀመስ ቀመስ አድርጎ ወደቤቱ ይገባል። ራቱን እየበላ ቲቪ ያያል። ከዛ ይተኛል። በማግስቱ እንደዛው አርፍዶ ይነሳና የትናንቱን ይደግመዋል። ይሄ ሕይወቱ ነው። ስለነገ አያስብ፣ አይረጋጋ፣ ሕይወቱን አይቀይር፣ ትዳሬን፣ ገቢዬን፣ ሕይወቴን እንዴት ላሳምር አይለም።
ለምን? ጠዋቱ አያምርማ፤ አጀማመሩ አያምርም። ለዛ ነው አጨራረሱ የማያምረው። የሆነ ቀን እኮ ቢረጋጋ፣ የሆነ ቀን ስክን ቢል ሕይወቱን የሚቀይር ሀሳብ ሊያስብ ይችላል። ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚቀይር ሀሳብ የሚያስቡት ከተረጋጉ ነው። የራስህን፣ የቤተሰቦችህን ሕይወት መቀየር ከፈለክ ቀንህን ማረጋጋት አለብህ። ቀንህ የሚረጋጋው ጠዋትህ ካማረ ብቻ ነው። ጠዋት በግዜ ተነሳ። ፀሎትህን ለምታምነው ፈጣሪ አድርስ። አምስግን፤ ስፖርት ስራ፤ ሻወር ውሰድ። ከዛ በኋላ ወደ ስራ እንኳን ስትሄድ ፈገግ እያልክ ነው። ምንም ነገር አታማርርም። የተረጋጋ ሕይወት ይኖርሃል።
3ኛ. በጥልቅ መተንፈስ
የአሜሪካ የባህር ሃይል መርከበኛ ነው። ከባድ ጦርነት ላይ ነው። መርከቡን እየዘወረ በጣም ብዙ ፍንዳታዎች አሉ። እርሱ ግን ሃሳቡ ሁሉ ሌላ ነገር ላይ ነበር። በቃ ተኩሱና ረብሻው ላይ ነበር። የሆነ ሰዓት ወደታች ሲያይ ከታች እግሩ ተሰብሯል። ደም በደም ሆኗል። አላወቀም ነበር። በጣም ደነገጠ። በድንጋጤ ራሱን ሊስት ደረሰ። ከዛ ግን አንድ ነገር አስታወሰ ውትድርና ሲሰለጥኑ እንደዚህ አይነት ከባድ ችግር ሲገጥም ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተነገራቸውን አስታወሰ።
ምን አደረገ፤ አየር በጣም በጥልቀት ወደ ውስጥ አስገባና ወደ ውጪ አወጣ። ሁለት ሶስቴ ተነፈሰ። ከዛ ተረጋጋ። ከዛ የደማውን እግር ተወና መርከቡን አስተካክሎ ማድረግ ያለበትን አደረገ። ለጓደኞቹ ሽፋን ሰጠ። እየተተኮሰባቸው ነበር አዳናቸው። ሕመሙን ሁሉ ውጦ ያውም በባህር ጦርነት ትልቅ ጀብዱ ፈፀመ። ዓለም ከማይረሳቸውና ከሚጠቀሱ የባህር ኃይል የጀግንነት ታሪኮች ውስጥ አንዱ ነው።
ይህ ሰው ይህንን ታላቅ ጀግንነት የፈፀመው አንድ ቀላል ነገር አድርጎ ነው። በጥልቀት ተንፍሶ እርሱን ደጋግሞት ነው። አየህ አንተም ከባድ ችግር ውስጥ ትገባለህ። የሚያስጨንቁ፣ የሚያናድዱ፣ ከመረጋጋት የሚያወጡ፣ ስሜትን የሚረብሹ፣ እንድትቸኩል የሚያደርጉ ወቅቶች ይመጣሉ። በቃ! በጥልቀት አየር ወደ ውስጥ አስገባና አስወጣ። በአንድ ግዜ የአይምሮ ስርዓትህ መስከን ይጀምራል። ልትቸኩል የነበረው፣ ከባድ ውሳኔ ልትወስን የነበርከው ሰው ትረጋጋና በጣም ብልህ ሆነህ ማሰብ ትጀምራለህ። በጥልቀት መተንፈስ በጣም ወሳኝ ነው።
4ኛ. ከባዱን ስራ ማስቀደም
ብዙ ግዜ በጣም የሚጨንቅህ፣ እንድትቸኩል፣ እንዳትረጋጋ የሚያደርግህ በጣም ከባድ ስራ ካለብህና ካልሰራኸው ነው። አይምሮህ ራሱ አያርፍም። ስትዝናና እንኳን ውይ! ያንን ነገር ሳልሰራው፤ ሳልጨርሰው ይላል። ስሜትህ ይረበሻል። መንፈስህ መስከን አይችልም። መረጋጋት አትችልም። ያንን ስራ መስራት አለብህ። ስለዚህ ሁልግዜ በጣም ከባድ የሚባለውን ስራ አስቀድመህ ስራ። እንደውም ብሪያንት ሬሲ የተባለ ትልቅ አነቃቂ ንግግር ተናጋሪና የቢዝነስ አማካሪ ‹‹eat that frog›› በሚለው መፅሃፉ በጣም ወሳኝ የተባለውን ከባዱን ስራ አይምሮህ ትኩስ እያለ ከጥዋቱ አስራ አንድ ሰዓት እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ባለው ሰርተህ ጨርስ ይላል። ከዛ በኋላ ያለው ግዜ ላንተ የነፃነትህና የደስታህ ግዜ ነው። መንፈስህም ጥሩ ነው፤ ትረጋጋለህ ይላል። ስለዚህ በተቻለህ አቅም ከባዱን ስራ አስቀድመህ ጨርስ።
5ኛ. የተረጋጉ ነገሮችን ማዘውተር
አንተ ማለት ደጋግመህ የምታየው፣ ደጋግመህ የምትሰማው፣ ደጋግመህ ምታደርገው ነህ። ስለዚህ በየቀኑ የምታደርጋቸው ነገሮች መቀየር አለባቸው። ጌም እንኳን ስትጫወት እንድታስብ፣ እንድትረጋጋ የሚያደርጉህን ጌሞችን ተጫወት። ያለበለዚያ ጦርነት፣ ጥድፊያና ችኮላ ያለበት ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ መረጋጋትን ያሳጡሃል። ነገር ግን ማሰብ የሚጠይቁ የሚያረጋጉ ጌሞች ስትጫወት የማሰብ ችሎታህ ራሱ ይጨምራል። ለምሳሌ ፐዝሎች፣ ሶዱኩ እና ቼዝ የምትጫወት ከሆነ እርጋታህን ነው የሚጠይቁት። ስለዚህ ታስባለህ።
ፊልሞች እንኳን ስታይ ያንተን እርጋታ የሚጠይቁ እንጂ ጥድፊያ ያለባቸውና ምንም የማይጠቅሙህን ነገሮች አትይ። የምትሰማቸው ዘፈኖች፣ የምታየቸው ነገሮች ሁሉ እርጋታህን የሚጠይቁ፣ ብትችል መንፈሳዊ መዝሙሮችን፣ ከሃይማኖት ጋር የሚገናኙ ክላሲካሎችን አድምጥ። ለምን? አንተን ያድሱሃል፤ መንፈስህ ይታደሳል፤ ትረጋጋለህ። አትርሳ በአይምሮህ የዘራኸውን በሕይወትህ ታጭደዋለህ። መረጋጋትን መዝራት አለብህ። አዘውትረህ የተረጋጉ ነገሮችን ማድመጥ፣ ማየትና ማድረግ አለብህ።
6ኛ.ችግሮችን የምታይበትን መንገድ ቀይር
ምን መሰለህ በራስህ መንገድ ብቻ ሄደህ የማትፈታቸው ችግሮች አሉ። ለምሳሌ አረንጓዴ መነፅር ካደረክ የምታያቸው ነገሮች ሁሉ አረንጓዴ መስለው ነው የሚታዩህ። አየህ በራስህ መንገድ ብቻ ስታስበው ሰዎችን መረዳት አንዳንዴ ከባድ ነው። ስለዚህ በነሱ ጫማ ውስጥ ሆነህ ማሰብ አለብህ። እሱ ግን ምን እየተሰማው ይሆን? ምን እያሰበ ይሆን? ምን አስቦ ነው እንዲህ ያለኝ? ብለህ በርሱ ጫማ ውስጥ ሆነህ ስታስብ ትረጋጋለህ። ቶሎ ስሜታዊ አትሆንም። ቶሎ አትወስንም። አሃ! ለካ እንዲህ የተናገረኝ እንዲህ ስላሰበ ነው፣ እንዲህ ስለሆነ ነው ትላለህ። ችግሮች እንኳን ሲገጥሙህ ፈጣሪ እኮ ይህን ችግር የላከው እንድማርበት ነው፣ የሆነ ነገር እንድቀይር ነው ትላለህ እንጂ ቸኩለህ የማይሆን ውሳኔ አትወስንም። ችግሮችን የምታይበትን መንገድ ቀይር። በሰው ጫማ ውስጥ ሆነህ በተለያየ መንገድ ለማሰብ ሞክር።
7ኛ. ከስልክህ ጫና ነፃ ውጣ
ስልክህን እንደምትፈልገው ብቻ አድርገህ ካልተጠቀምክበት እሱ ይጠቀምብሃል። ባሪያው ያደርግሃል። አንዳንድ ሰው እስኪ ጠይቁ ካለስልክ አንድ ቀን ብታድር ምን ትሆናለህ? ብትሉት ኸረ! የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እኔ እንደዚህ እንዲሆን አልፈልግም፤ ከስልኬ መለየት አልፈልግም ይላችኋል። አያችሁ ብዙ ግዜ ስልካችን ካልጠራ መልዕክት ካልገባ ዛሬ ከነጋ ማንም አልደወለም ብለን ሊከፋን ሁሉ ይችላል። ከስልካችን ጋር በጣም ተጣብቀናል። ስልካችን ካልጮኸና የሆነ አዲስ ነገር ከሌለ በጣም መጥፎ ስሜት ይሰማናል። አያችሁ ውስጣችን ከውጫዊ ነገር ጋር ጥገኛ ሆኗል። ለዛ ነው የማንረጋጋው። ችኩል የምንለው። ፍጥን የምንለው ውጫዊ ነገሮች ሕይወታችንን ስለሚገለባብጡት ነው። ዓለም ሲገለባበጥ ውስጥህ ይገላበጣል።
ታዲያ ምን ይሻላል? የሚሻለው ስልክህን አንተ ብትቆጣጠረው ነው። በተቻለህ አቅም ከጠዋቱ አስራ አንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ባለው በጣም ምርታማ በሆንክበት ግዜ ትኩስ በሆንክበት፣ ብልህ በሆንክበት ወሳኝ ሰዓት ስልክህን አትጠቀም። በጣም ወሳኝ ስልክ ካልሆነ በስተቀር አታንሳ። አትደውል። በቃ! ከአምስት ሰዓት በኋላ ማስተናገድ ያሉብህን ነገሮች አስተናግድ። አየህ እንድትረጋጋ የምትፈልግ ከሆነ በሕይወትህ በዙሪያህ ያሉትን ውጪያዊ ነገሮች መቆጣጠር አለብህ። ውጪያዊ ነገሮችን ከተቆጣጠርክ ነው ውስጥህ ጀግና የሚሆነው። የሚሰክነው።
8ኛ. አመስግን
ስታመሰግን፣ የተደረገልህን ስታስብ ስሜትህ ይረጋጋል። የዚህ ዓለም ችግር በቀላሉ አንተን አይረብሽህም። ስክን ትላለህ። ጉድለትህን ልቁጠረው ካልክማ በጣም ብዙ እኮ ነው። በዚህ ዓለም ምን የማይጎድለን ነገር አለ። ግን የተሰጠህን ማሰብ አለብህ። በጣም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች አይተህ ከሆነ በጣም የተረጋጉ ናቸው። ለምን ይመስላችኋል? አመስጋኝ ናቸው። ውስጣቸው የሚታያቸው ፈጣሪ ያደረገላቸው ምህረት ነው እንጂ ያጎደለባቸው ነገር አይደለም። መረጋጋት ከፈለክ አመስጋኝ መሆን አለብህ።
9ኛ. የሚያረጋጉህን ነገሮች ለይተህ እውቃቸው
ሁሉም ሰው በተመሳሳይ መልኩ አይረጋጋም። አንዳንድ ሰው የሚረጋጋው ከሰዎች ጋር ሲቀላቀል ነው። በቃ ሲጫወት ምን ሲል መንፈሱ ስክን ይላል። ሌላው ደግሞ ብቻውን ሲሆን ነው የሚረጋጋው። መቀላቀል አይፈልግም። ፓርክ ሄዶ ወይ መኝታ ቤት ገብቶ ነው መረጋጋት የሚፈልገው። ላንተ የሚሰራልህን መድሃኒት ተጠቀም። አንተ ነህ የምታውቀው። አየህ አንዳንዴ ስሜት የሚሰጡህንና የሚያረጋጉህን ነገሮች አንተ ራስህ ማወቅ ይኖርብሃል። ስራዎቹን ስትሰራ፣ ግንኙነቱን ስታስኬደው ሰዎች በሚፈልጉት መንገድ ብቻ አትሂድ። እንደዛ ከሆነ ስሜትህ ይረበሻል። መረጋጋት ከፈለክ አንተ በሚያስደስትህና ትክክል ነው ብለህ በምታስበው መንገድ አስኪደው። በራስህ መንገድ ሕይወትን ቅረፃት። ያኔ ትረጋጋለህ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም