በሕይወታችን ውስጥ ቆራጥነት እንዳለ ሆኖ ለውጥ እንዳንጀምር የያዘንን የሆነ ነገር መቀየር፣ ማስተካከል እንዳለብን ውስጣችን ያውቃል። አዕምሯችን ተከፍቶ ቢታይ በየደቂቃው ሃሳባችን እንደሰከረ ዝንጀሮ ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላው በፍጥነት እየዘለለ ነው። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ፍሬድ ለስኪ ‹‹አዕምሯችን በየቀኑ 60 ሺ ሃሳቦችን ያስባል›› ይለናል። አስገራሚው ነገር ሃሳባችን ተደጋጋሚ ነው። ወይ ስለትናንትና ትካዜ ነው፣ ቁጭት ነው ወይ ደግሞ ስለነገ ምኞት ነው። ለውጥ የሚጀምረው ግን በመወሰን ነው።
የሆነ ጊዜ ቆራጥ ሆነህ የወሰንካቸው ውሳኔዎች የሰጡህ ደስታ አለ። የአዕምሮ ሰላም አለ። ለውጥ አለ። ለካ እንደዚህ ጠንካራ ነኝ ያልክባቸው ቆራጥ የሆንክባቸው ወቅቶች አሉ። ሰዎች ራሱ መጥተው በጆሮህ አንተ እኮ ጀግና ነህ! ኮራሁብህ! ያሉህ በዛ ወቅት ነው። በጣም ጀግና ነሽ! አድንቄሻለሁ! ያሉሽ ቆራጥ በሆንሽባቸው ጊዚያቶች ነው። አሁንስ መቼ ነው ቆራጥ የምትሆኚው? አንተስ መቼ ነው ሱሱን የምታቆመው? ያቋረጥከውን ትምህርት የምትጀምረው መቼ ነው? ያሰብከውን ቢዝነስ የምትጀምረው መቼ ነው?
ለውጥ እፈልጋለሁ፣ በትምህርቴ፣ በሥራዬ፣ በፍቅር ግንኙነቴ፣ በትዳሬ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቴ የተሻለ ነገር ይገባኛል ካልክ መጀመሪያ መወሰን ከዛ ወደ ተግባር መግባት አለብህ። ግን እንዴት አድርጌ ልወስን? እንዴት አድርጌ ሕይወቴን ልቀይር? ካልክ በጣም ቀላል፣ ለመተግበር የሚመቹ፣ ቆራጥ የሚያደርጉ የለውጥ ሃሳቦችን እንካ…
1ኛ. አዲስ ነገር መጀመርን መፍራት አቁም!
ብዙ ሰዎች ይህን ማቆም አልችልም፤ ብዙ ዋጋ ከፍዬበታለሁ በሚል አስተሳሰብ ተይዘዋል። ነገር ግን እንደ አዲስ መጀመር እችላለሁ ቢሉ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ አብዮት ያስነሳሉ። ያለኝን ነገር ሁሉ እዚህ ነገር ላይ ጨርሻለሁ። ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ። ወደኋላ መመለስ የማይታሰብ ነው ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን በተሳሳተ መንገድ ከሄድን ማቆም ነው ያለብን። አንዳንድ ተማሪዎች ህክምና፣ ወይም ሕግ አልያም ደግሞ ሲቪል ምህንድስና ይማራሉ። ሁለተኛና ሶስተኛ ዓመት ላይ ሲደርሱ ግን ተመርቀው በዛ ሞያ እንደማይሰሩበት ያውቃሉ። በቃ አይፈልጉትም ግን ይህን ሁሉ ተምሬማ ሁለትና ሶስት ዓመት ሲቀረኝ ሌላ የምፈልገውን ከዜሮ አልጀምርም ይላሉ።
የማይፈልጉትን የሚማሩ፣ የሚሰሩ ብዙ ሰዎች ናቸው። ለምን ሥራውን አቁመህ ሌላ ነገር አትሰራም? ብትሏቸው ‹‹ትቀልዳለህ እንዴ እዚህ መሥሪያ ቤት ስንት ዓመት እንደሰራሁ ታውቃለህ? ይሏችኋል። ረጅም ጊዜ ስለተጓዝክ፣ ብዙ ገንዘብና ጊዜ ስላጠፋህ ወደ ግብህ አትደርስም። ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ አለብህ። መድረሻህ ምስራቅ ሆኖ አንተ ወደ ምዕራብ በተቃራኒ አቅጣጫ ለአስር ዓመት ብትጓዝ ምን ያደርጋል? ጀርባህን አዙረህ ወደ ትክክለኛው መንገድ መጓዝ ነው ያለብህ። አስር ዓመት ተጉዣለሁ ብትል ስህተት ስህተት ነው። ስህተትን በስህተት ልታርመው አትችልም። በነቃህ ሰዓት ቆራጥ ሆነህ ማስተካከል አለብህ።
ይህ አመለካከት በተለያየ የሕይወት አቅጣጫ ውስጥ ይፈትነናል። እንደ አዲስ መጀመር የምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሥራችንን፣ ትምህርታችንን፣ ትዳራችንን፣ የፍቅር ግንኙነታችንን ሁሉንም እንደ አዲስ ስለመጀመር መፍራት የለብንም።
2ኛ.መወሰን ለምን እንደሚጠቅምህ እወቅ!
አንድ ነገር ለምን እንደሚጠቅምህ ካወክ ጀምረህ አታቁም። ብዙ ሰው ታነቃቃለህ፣ ሰዎች እኮ አዕምሮዬን አነቃቁት ብሎ ስፖርት ይጀምራል። ግን በሳምንቱ ያቆመዋል። በጠዋት መነሳት ይጀምራል። ካዛ ግን ሲቆይ እንዲህ የምሰቃየው ለነብሴ ነው ለሥጋዬ ብሎ አርፍዶ መነሳቱን ይቀጥላል። አዲስ ቋንቋ ለመልመድ ወይም አዲስ ሞያ ለመማር ተመዝግቦ በጥሩ ስሜት መማር ይጀምራል። ከሳምንታት በኋላ ግን አዬ! ዝም ብዬ ነው የለፋሁት፤ ገንዘቤን አወጣሁ፤ ጊዜዬን አባከንኩ ብሎ ያቆማል።
አየህ! አንድን ነገር ለምን እንደምታደርገው ማወቅ አለብህ። አላማ ሲኖርህ ከወሰንክ ወሰንክ ነው። ወደኋላ ማለት የለም። ስለዚህ ለምንድን ነው የምወስነው?፤ ለምንድን ነው የምቀየረው? የሚለውን ማወቅ አለብህ። ካልወሰንክ ቆመህ ትቀራለህ። እውነቱን እወቅ፣ የምታጣውን አስብ፣ ራስህን የዛሬ አምስት ዓመት ባለህበት ታገኘዋለህ። ሁሌም ልታማርር ነው። እድለ ቢስ ነኝ፤ አልታደልኩም እያልክ ልትኖር ነው። ብትወስን ግን ብዙ ነገር ትቀይራለህ። በስብእና፣ በአመለካከት፣ በገቢ፣ በደስታ ማደግ ትጀምራለህ። ፍጥረት ሁሉ ለማደግ ነው የተፈጠረው። ዛፍ እስከምን ያድጋል ብትለኝ? ማደግ እስከሚችለው ድረስ እልሃለሁ። አንተም እንደዛው ነው የተፈጠርከው። እንድትበዛ፣ ምድርን እንድትቆጣጠራትና የተመኘኸውን እንድታሳካ ነው የጠፈጠርከው።
መወሰን ስትጀምር ልዩ ስሜት ውስጥ ትገባለህ። የመርከብህ ካፒቴን አንተ መሆን አለብህ። በነገራችን ላይ ከአምስትና አስር ዓመታት በፊት የወሰንካቸው ውሳኔዎች ናቸው ዛሬ ላይ ያደረሱህ። ድሮ ያነበብካቸው መጻሕፍት፣ ያየሃቸው ፊልሞች፣ አብረሃቸው ትውላቸው የነበሩ ሰዎች አሁን ለደረስክበት ቦታ ዋና መሰረት ናቸው። ነገ ቀጣዩን የሕይወትህን ምዕራፍ የሚወስኑት ዛሬ የምትወስናቸው ውሳኔዎች ናቸው። ወዳጄ! ከመወሰንህ በፊት ግን ለምን እንደምትወስን ለራስህ ንገረው።
3ኛ. ከሰው መጠበቅን አቁም!
ብዙ ሰው የሆነ ነገር እስኪቀሰቅሰው ይጠብቃል። የሚያግዘው ሰው እስኪመጣ ወይ ጥሩ ሁኔታ እስኪፈጠር እየጠበቀ አይወስንም። አሳስሮ ያስቀመጠህ፣ ጥንካሬ ያሳጣህና ልፍስፍስ ያደረገህ ሰውን መጠበቅ ነው። ሁኔታዎች እስኪቀየሩ መጠበቅ ነው። ለውጥ ትፈልጋለህ። ግን አትጀምርም። መዋኘት እያማረህ መርጠብ አትፈልግም። መለወጥ ትፈልጋለህ። መጀመር ግን አልቻልክም። ተኝተህ ፈጣሪ ያውቃል ብትል ፈጣሪ የሚያውቀው እንቅልፋም እንደሆንክ ነው። ተነስተህ ለውጡን መፍጠር አለብህ።
አንተ እንድትለወጥ ማን እስኪመጣ ነው የምትጠብቀው? ማንንም አትጠብቅ። ማንም አይመጣም። እድሎች እንኳ የሚመጡት በራስህ የምትችለውን ያህል ስትንቀሳቀስ ነው። ቁጭ ብለህ ስትጠብቅ ያልመጡ እድሎች መንቀሳቀስ ስትጀምር ግን በላይ በላይ ይደራረባሉ። ፍቅረኛ ሳይኖርህ ዞር ብለው ያላዩህ ሰዎች ፍቅረኛ ስትይዝ ግን አላስቆም አላስቀምጥ ይሉሃል። ቆመህ ስትጠብቅ ያልመጣው ታክሲ እንኳን በእግርህ መንገድ ስትጀምር የሞላ አንድ ሰው ይልሃል።
ይህች ዓለም የምታደላው ቁጭ ለሚል አይደለም። ለሚሮጥ ነው። ከሰው ለሚጠብቅ አይደለም። ለራሴ አላንስም ብሎ ለሚታገል ነው። ከሰው መጠበቅ ልብህን ይሰብረዋል። እድል እስኪመጣ ቁጭ ማለት ብኩን ያደርግሃል። መሮጥ አለብህ። መታገል አለብህ። ለሚመጣው መዘጋጀት አለብህ። ካልተዘጋጀህ እድሉ ቢመጣ ራሱ ታባክነዋለህ። ከሰው መጠበቁን፣ ሁኔታ እስኪስተካከል መጠበቁን አቁምና በራስህ ወስን። ለውጡን ጀምረው።
4ኛ. እንዳትቀየር የሚጎትትህን ነገር አቁም!
አየህ! እንዳትለወጥ የጎተተህ ምናልባት ውሎህ ሊሆን ይችላል። ጓደኞችህ ሊሆኑ ይችላሉ። በዙሪያህ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዳትወስን፣ ቆመህ እንድትቀር ያደረገህን ነገር ለይተህ እውቀው። አትችልም፣ የትም አትደርስም፣ ይቅርብህ፣ አርፈህ ቁጭ በል ከሚሉ ሰዎች የምትርቀው ስለማትወዳቸው አይደለም። ነገር ግን ህልምህን ቆፍረው እንዳይቀብሩት ነው። አንድ ጥግ አስቀምጠው እንዳያስሩህ ነው። ቆራጥ ስትሆን ግን የሚተቹህ ሰዎች እንኳን ያከብሩሃል። እሱ እኮ ከወሰነ ወሰነ ነው ይሉሃል። በራስ መተማመንህ ይጨምራል።
ወደኋላ ያስቀረህ ምንድን ነው? እወቀው። ሰበብ ነው፣ ምክንያት ነው? ሰበብ ከሆነ ሰበበኛውን ቅበረው። ‹‹ለራሴ ቃለ የገባሁትንና ያልኩት ሁሉ አደርጋለሁ›› በልና ወደ ተግባር ግባ። በሕይወት ከባዱ መጀመር አይደለም። መጨረስ ነው። ቆራጥ ሆነህ እስከ ፍፃሜው መጓዝ ከፈለክ ወደኋላ የሚጎትቱህን ነገሮች፣ ሁኔታዎች፣ ሰዎች ሁሉ ከሕይወትህ አስወግዳቸው።
5ኛ. ኃላፊነት ውሰድ!
አሁን አንተን የገጠመህ ችግር የሆነን ሰው ይገጥመዋል። ትምህርት ናላውን ያዞረዋል። ኑሮ፣ ገንዘብ ማግኘት፣ ሥራ ማጣት አብዝቶ ያስጨንቀዋል። ከወር እስከ ወር ሕይወት አልገፋ፤ ኑሮ አልጨበጥ ይለዋል። ፈተናው ይለያይ እንጂ ሁሉም ይፈተናል። ልዩነት ፈጣሪው ግን የገጠመህ ችግር አይደለም። ያንተ ቆራጥነት ነው። ያንተ ምላሽ ነው። ስለዚህ ኃላፊነቱን ውሰድ። ከፈጣሪ ቀጥሎ ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ በል። ሕይወቴን የማስተካክለው እኔ ነኝ በል።
ከእኛ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሕይወታቸውን እስከ መጨረሻው የቀየሩ ብዙ ሰዎች አሉ። እድለ ቢስ አይደለህም። ስለማትችል ወይም ሰነፍ ስለሆንክም አይደለም እንደምትችል ስላላመንክ ነው። ፈጣሪ ባንተ ውስጥ ተአምር እንደሚሰራ ስላላመንክ ነው። አንተ ምን ደርሶብህ ነው፤ ምን መአት ወርዶብህ ነው እንደዚህ ጭንቅ ጥብብ ያለህ? ዓይንን ቀና አድርጎ ጣራ ከማየት ውጭ ለአስር ዓመት ከቤቱ ያልወጣ አንድ ህመምተኛ ምን ይበል ወዳጄ! በምድራዊ ችግር ተስፋ መቁረጥ የለብህም። ምክንያቱም አንዱ በር ሲዘጋ ሌላው ይከፈታል። ኃላፊነቱን ውሰድ። ሕይወቴን እኔ ቆራጥ ሆኜ ከዛሬ ጀምሮ አስተካክለዋለሁ በል።
6ኛ. ከወሰንክ በኋላ ወደ ተግባር ግባ!
አስበህበት፣ አምነህበት ከወሰንክ ወደ ተግባር ግባ። ጀምረው ለውጡን መወሰን በቂ አይደለም። ድርጊት ያስፈልጋል። ለመብላት ብትወስን ምን ያደርጋል ሆድህ አይጠግብም። ባለህበት የምትቀረው ወስነህ ወደ ድርጊት ካልገባህ ነው። መወሰን አንድ ነገር ነው። ወደ ተግባር መግባት ግን ሌላ ነው። መድኃኒቱ ቢኖርህ ምን ያደርጋል ካልዋጥከው አትድንም።
7ኛ. መፅናት አለብህ!
ጀመርክ ማለት ደረስክ ማለት አይደለም። ግን ደግሞ የ42 ኪሎ ሜትር ማራቶን ሩጫ በአንድ ርምጃ ነው የሚጀመረው። ቶሎ ለውጥ ካላየሁ አትበል። አንድ ሰው የዓመቱን ስፖርት አጠራቅሞ ለአንድ ቀን ቢሰራ ጡንቻ አያወጣም። ስትራፖ ነው የሚይዘው። በየቀኑ ጊዜውን ከፋፍሎ ለአንድ ዓመት ስፖርት ቢሰራ ግን ጡንቻ ያወጣል። ለውጥ ያያል። ውሳኔ አቅጣጫህን ነው የሚቀይረው። ሕይወትህን አይቀይርም። ሕይወትህን የሚቀይረው የማይቆም ድርጊት ነው። አየህ! የማይቆም ጥረት ከፍፃሜው ያደረስሃል። መጀመር ግን አለብህ።
መለወጥ ከፈለክ ወሳኙ ጊዜ የባነንክበት፣ የነቃህበት ቅፅበት ነው። እሱም አሁን ነው። በቃ! አሁን ለውጡን ጀምር። እሺ ወስኛለሁ፤ እጀምራለሁ፣ እለወጣለሁ ካልክ ለውጥህን የሚያበረታ፣ ከፍርሃት የሚያወጣህ አንድ ድንቅ መጽሐፍ አለ። መጽሐፉ አይቤን ማን ወሰደው? ወይም /who moved my cheese/ ይሰኛል። ደራሲው ደግሞ ዶክተር ስፔንሰር ጆንሰን ይባላል። አንብበው። ብዙ ቁም ነገር ታገኝበታለህ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም