ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለውጡን ለመቀልበስ፤ ለአገርና ለህዝብ ይዞት የመጣውን ተስፋ ለማክሰም ማቆሚያ የሌላቸው የጥፋት ተልእኮዎች በተቀናጀ መንገድ ታቅደው ሲተገበሩ ቆይተዋል፤ ዛሬም እየተተገበሩ ነው። በዚህም ሕዝባችን አላስፈላጊ የሆኑ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገድዷል።
ግልጽ ጦርነትን ያካተቱት እነዚህ የጥፋት ተልእኮዎች፤ በፈጠራ ወሬዎች፣ በተዛቡ መረጃዎችና በተሳሳቱ ትርክቶች አቅም እየገዙ የለውጡ ዋነኛ ኃይል የሆነውን ህዝባችንን ግራ በማጋባትን እና በማደናገር፤ ለውጡ በተነሳበት ፍጥነት እንዳይጓዝ፤ ሂደቱም በብዙ ተግዳሮቶች እንዲፈተን አድርገውታል።
በተለይም ለተወሰነ ህዝብ /ብሄር፣ ብሄረሰብ/ እና ለአገር ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ የለውጡን ሂደት ተከትለው በየወቅቱ የሚፈጥሯቸው የጥፋት አጀንዳዎች፣ ሂደቱን ወደኋላ መቀልበስ የሚያስችል አቅም ባይኖራቸውም፣ ለጊዜው ለለውጡ ተግዳሮት መሆናቸው አልቀረም።
እነዚህ ኃይሎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት በጥቅሉም የፌዴራል የጸጥታና የደህንነት ኃይል መፈጠር ሲገባው የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት መኖሩ ለአገርም ሆነ ለህዝብ ደህንነት አደጋ ስለመሆኑ አብዝተው ሲጮሁ፤ ”መበተን ” አለበት እያሉ በአደባባይ ሲሞግቱ፤ መንግስት ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ሲኮንኑ፣ ሲከስሱና ሲያብጠለጥሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
አሁን ላይ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ጥናት አድርጎ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሮ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት አንድ ጠንካራ የተማከለ ሕብረ ብሄራዊ የመከላከያና የጸጥታ ኃይል ለመገንባት መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ የትናንት ጩኸታቸውን ሁሉ ዘንግተው በሌላ ዜማና በተለመደው የሕዝብ ማደናገሪያ ጩኸታቸው ተከስተዋል።
በርግጥ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራው ዋና አላማ የጥፋት ኃይሎች እንደሚሉት፤ ኃይሉን ትጥቅ በማስፈታት ወይም አንድን ብሔር ለይቶ ለማዳከምና ለጥቃት አሳልፎ ለመስጠት አይደለም ።
ከዚህ ይልቅ ልዩ ኃይሉ ትጥቁን ይዞና የተሻለ ዐቅም ተፈጥሮለት በምርጫው መሠረት የክልል ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስን ወይም የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ማድረግ የሚያስችል ነው። በዚህ ሂደት መካተት ያልፈለገም ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገባ በመንግሥት በኩል አስፈላጊ የማቋቋሚያ ሥራዎች እንዲከናወኑ የሚያመቻች ነው።
ይሄም በአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ነው፤ የልዩ ኃይል አባላቱን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜም በክልሎች አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የአገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ቦታዎች ሥምሪት ወስዷል።
ሕወሓትን በተመለከተም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰበት የሰላም ስምምነት መሠረት ትጥቁን ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ የሚደረግ መሆኑ በሂደቱ እንደ ስጋት ሊያስቆጥረው የሚችል አይሆንም። ከዚህም በላይ የመከላከያ ሰራዊት በሁሉም ቦታ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር መሰማራቱ ስጋቶችን ለማስወገድ አስተማማኝ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
የመልሶ ማደራጀት ሥራው አሁን ላይ በሁሉም ክልሎች በሰላማዊ መንገድ በጥንቃቄ እየተከናወነ ባለበት ሁኔታ፤ በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ተስተውለዋል። ችግሮቹ አንድም የመልሶ ማደራጀት ስራን ዓላማ በአግባቡ ካለመረዳት፤ ካልሆነም የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ ከመጠለፍ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
የሥራውን ዓላማ ካለመረዳት ሆነ በጥፋት ኃይሎች የፈጠራ ወሬ፣ የተዛባ መረጃ እና የተሳሳተ ትርክት ሰለባ የሆኑ እነዚህ የልዩ ኃይል ክፍሎች፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀት ሥራ አላማና ተልእኮ በአግባቡ ሊረዱት፣ ለተግባራዊነቱም በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሰላም እና ደህንነት አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው የአገሪቱን የመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች ሕብረ ብሄራዊ በሆነ ጠንካራ መሰረት ላይ ሲዋቀሩ፤ ጊዜውን ሊዋጅ በሚችል አቅምና ዝግጁነት ሲገነቡ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገው ያለው ትልቁና ዋነኛው የሪፎርም ስራው ነው።
አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራም ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ የመከላከያና የጸጥታ ተቋማት የመገንባት ሂደት አካል ነው፤ የህዝባችንን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የሚደረገው አገራዊ ጥረት ስኬት ዋነኛ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ፤ ሕዝባችንን ከትናንት እና ከዛሬ የጸጥታ ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመታደግ የሚያስችል ነው። ይህንን በአግባቡ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ ስኬት መንቀሳቀስ ደግሞ የልዩ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015