በንጉሠ-ነገሥቱ ዘመነ-መንግሥት ልሂቃን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመመስረት ሙከራ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ በዘመኑ ትኩረት ከሚደረግባቸው የደህንነት ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የፖለቲካ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ልሂቃኑ በጣም የሚቀራረቡና በሚስጥር የሚገናኙ መሆን ነበረባቸው፡፡ ሚስጥር እየሾለከ በሚወጣበት ጊዜ ግን የፖለቲካ ሴረኞች ተብለው የተጠረጠሩ ሲያዙ ከባድ የእሥራት ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ ሴረኞቹ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በሚሆኑበት ጊዜ ወደ ጠቅላይ ግዛት (ክፍለ ሀገር) ወይም ዳር አገር በሹመት ስም ግዞት ይላካሉ፡፡ ግዞት ማለት የተሾመው ባለሥልጣን በዓይነ-ቁራኛ የሚሰለልበት የእሥራት ስልት እንደማለት ነው፡፡
የግዞቱ ወሬ በሰፊው እንዲናፈስ ይደረጋል፡፡ የወሬው ዓላማ ሌሎች በማሴር ላይ ያሉ የፖለቲካ ሥራቸውን እንዲያቆሙ፤ ወደፊት ለማሴር ያሰቡ ካሉ ደግሞ እንዲጠነቀቁ በተዘዋዋሪ ለማስገንዘብ ነበር፡፡ የደህንነቱ ሥራ መጠነ ሰፊ ስለነበር በይፋ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ ሊፈጠር አልቻለም፡፡ በየዕለቱ በውድቅት ሌሊት ታማኝ የደህንነት ኃላፊዎች ልዩ ካቢኔውን ጨምሮ በየተራ በሚስጥር ቤተ መንግሥት እየገቡ ስለፖለቲካው አየር ለንጉሡ ሪፖርት ያደርጉላቸውም ነበር፡፡
ተጨባጭ ማስረጃ የሚቀርብባቸው የፖለቲካ አክቲቪስቶች ፍርድ ቤት ቀርበው ለእሥራት ይዳረጋሉ፤ የቀሩት ደግሞ ይጠፋ ወይም ወደ ውጭ አገር ይሰደዳሉ፡፡ በመሆኑም በንጉሡ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ መመስረት አልተቻለም ነበር፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በደህንነት አፈና ምክንያት ሊመሰርቱ ባለመቻላቸው የፖለቲካው ምህዳር ሊፈነዳ ደረሰ፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ምሁራንን ጨምሮ የፖለቲካ ቀዳዳዎች መፈላለግ ነበረባቸው፡፡ ከነዚህም ቀዳዳዎች ሁለቱን ማስታወስ ይቻላል፡፡ አንዱ የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ነው፡፡ በ1953 ዓ.ም. በወንድማማቾቹ በጄኔራል መንግሥቱና በገርማሜ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ይካሄዳል፡፡
ዓላማውም መሬትን ላራሹ ማድረግና የብሔሮችን እኩልነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ በቅንጅት ጉድለት ምክንያት መፈንቅለ መንግሥቱ ከሽፎ ወንድማማቾቹ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በፍርድ ቤት ትእዛዝ በአደባባይ በስቅላትና በእስር መስዋዕትነት ቢከፍሉም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ዓይን ገላጭ መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ንጉሡና የፊውዳሉ ሥርዓት ከመፈንቅለ-መንግሥቱ ምንም ሳይማሩበት 13 ዓመት ቆይተው በ1966 ዓ.ም. በሕዝባዊ አብዮታዊ እርምጃ ተወግደዋል፡፡ በዚህም የታፈነ ፖሊቲካ ሊፈነዳ እንደሚችል አንድ ትምህርት ተገኘ ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው የፖለቲክ ዓይን ገላጭ የሆነው የወንድማማቾቹን የፖሊቲካ ትምህርት ያጠኑት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ወገኖች መሬትን ላራሹ ለማድረግ ሲሉ የፊውዳሉን ሥርዓት ታግለዋል፤ በዚህ የተነሳም ታስረዋል፤ ተገድለዋል፡፡ እነዚህ ትግሎች የተካሄዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ እንዲመሰረቱ ባለመፈቀዱ ነበር ማለት ስህተት አይመስለኝም፡፡
ከፊውዳሉ ሥርዓት መወገድ በኋላ የተማሪውን የትግል ዓላማ አስታኮ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በ1967 ዓ.ም.ሥልጣን ያዘ፡፡ ደርግ ሥልጣን ከመያዙ ጥቂት ቀደም ብሎ በውጭ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰረቱ ልሂቃን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበር፡፡ ከነዚህም ከፊሎቹ ከደርግ ጋር ለጊዜው የታክቲካ ትብብር ማድረግ ነበረባቸውና ሕዝባዊ መንግሥት መመስረት አለበት በሚል የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀመሩ፡፡ በመጀመሪያ ሥልጣን ለመያዝ በሚል ዕርስ በራሳቸው ተላለቁ፡፡ ከደርግ ጋር ባደረጉት ፍልሚያም ተሸነፉ፤ ታሰሩ፤ ተሰው፡፡ በመሆኑም ሕዝባዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደብዛቸው ጠፋ፡፡
ደርግ ሥልጣን በያዘ በአስረኛው ዓመት ገደማ የወታደር መንግሥትንና የሶሻሊስት መንግሥትን ማዋሃድ ውስጣዊ ተቃርኖ ስለሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረት አስፈላጊ ነው ተባለ፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች ሕብረት (ኢማሌድኅ) እንዲመሰረት ተደረገ፡፡ የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች ዓላማቸውና ስትራቴጂያቸው አንድ በመሆኑ አማራጭ ፓርቲዎች ባለመሆናችው ይህም ትርጉም የለሽ ሕብረት ሆኖ ቀረ፡፡
ቀጥሎም የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) የሚባል ድርጅት ተመሰረተ፡፡ ኮሚሽኑም የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲን (ኢሠፓ)ን አዋለደና ተልዕኮውን አሳካ ተብሎ ፈረሰ፡፡ የደርግ ሊቀመንበር የነበሩት ወታደር የኢሠፓ ሊቀመንበር ሆነው ቁጭ አሉ፡፡ እዚህ ሁሉ ትርክት ውስጥ የገባሁት በደርግ ዘመንም ልክ እንደንጉሡ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እንደተጨናገፉ ለማሳየት ነው፡፡
ከደርግ ቀጥሎም ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ የተከተለው ፓለቲካ የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብት እስከ መገንጠል መከበር አለበት የሚል በታኝ ስልት ሆነ፡፡በዚህ መሰረት የዘውግ (ብሔር) እና የዜግነት(ሕብረ ብሔራዊ) የፖሊቲካ ፓርቲዎች በሕግ እንዲመሰረቱ አደረገ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ጫጩት እየተፈለፈሉ በፈንግል በሽታ እንዴት እንዳለቁ ባጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ለጊዜው መጠናቸውን በትክክል ባላስታውስም ከሰማንያ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመስረታቸውና በምርጫ ቦርድ መመዝገባቸው ትዝ ይለኛል። አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጥቂት ግለሰቦች ፓርቲዎች ናቸው ሲባል ሀቀኛ አባላት ይኑራቸው አይኑራቸው በሕዝቡ ዘንድ አይታወቅም ነበር፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ሚናም የገዥው ፓርቲ አጫፋሪነት እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህ ሚናቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ሰፊ አስመሰለውታል፤ ለዚህም ተግባራቸው ዳረጎትና ምስጋና በገዥው ፓርቲ ቁንጮ ተችረዋል፡፡ በዚህም የጥቅም ጥገኛ አድርጓአቸው ቆይተዋል፡፡
እነዚህ ፓርቲዎች እስከ አሁን ድረስ ይህን ቅንነት የጎደለውን በሕዝብ ስም የመነገድ አሳፋሪ ድርጊታቸውን ግንባራቸው ላይ ለጥፈው ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ ለሕዝብ የቆሙ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባሎች ከመጋቢት 2010 በፊት በነበሩት በገዥው ፓርቲ በኢህአዴግ መሪዎች አማካኝነት ፍዳቸውን አይተዋል፤ ተሰደዋል፤ ታስረው ተሰቃይተዋል፡፡
እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባሎች ለታላቅ ሰቆቃ ከተዳረጉባቸው በርካታ ውስጣዊና ውጭያዊ ምክንያቶች መካከልም ጥቂቶችን ለመጥቀስ እሞከራለሁ፡፡ በመጀመሪያ ውስጣዊ ምክንያቶች ላይ አተኩራለሁ፡፡ አንደኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ኢህአዴግ አስሮ በሚያሰቃይበት ጊዜ ተለጣፊዎች ፓርቲያቸውን መክዳታቸው፤ በታሰሩት ምትክም ሥልጣን ለመያዝ መስገብገባቸው ዋናው ይመስለኛል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የሚተዋወቁ ግለሰብ ልሂቃን አንድን ፓርቲ በአባልነት ከመቀላቀልና ከማጠናከር ይልቅ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው በምርጫ ቦርድ በቀላሉ መመዘገብ መቻላቸው ነው፡፡ እንዲሁም የሚተዋወቁ ልሂቃን ከፓርቲ ተገንጥሎ ሌላ ፓርቲ የመመስረት ፍላጎት ነበረባቸው፡፡ የፓርቲ አመራሮች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የልምድ አስፈላጊነትን ሰበብ በማድረግ ወጣቶች ወደ ፓርቲ አመራር ደረጃ እንዳያድጉ ማድረጋቸው ነው፡፡ የአባሎች በፓርቲዎቻቸው እምነት ማጣትና በዚህም ምክንያት የገንዘብ መዋጮ ማነስ ፓርቲዎቹን አሽመድምዷቸዋል፡፡
ልሂቃን ከአገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በልዩ ልዩ ምክንያት በተይም በችሎታቸው ማነስ አብረው ከሚሠሩ ይልቅ በብሔርና ብሔረሰቦች ፓርቲዎች መደራጀት ስለሚቀላቸው በኢትዮጵያ በሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቁጥር ልክ በምርጫ ቦርድም በቀላሉ መመዝገባቸው ፓርቲዎቹን ኮሳሳና ደካማ አድርጓአቸዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ቁጥራቸው የአገሪቱ አቅም ከሚችለው በላይ በመሆኑ የሀብት ብክነት አስከትለዋል፡፡
ለፖሊቲካ ፓርቲዎች መዳከምና መጠቃት ምክንያት ከሆኑት በርካታ ውጫዊ መካከል ጥቂቶቹን እጠቅሳለሁ፡፡ በመጀመሪያ መጠቀስ ያለበት ገዥው ፓርቲ ተለጣፊ ባልሆኑ ሀቀኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃ ነው፡፡ ሀቀኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ጥቃት እንዲደርስባቸው ተደርገዋል፡፡ በሀሰት ተከሰዋል፤ ሕገ መንግሥቱን በመናድ፤ ሀገር በመክዳት ሰበብ ንብረታቸው ተወርሷል፤ ቤተሰቦቻቸው ታስረዋል፤ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ በፈጠራ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውለው እንዲሰቃዩ ተደርገዋል፡፡
የደረሰባቸውን ስቃይ በጽሑፍ መግለጽ ፍፁም አይቻልም፡፡ ከዚህ ሁሉ ሰቆቃ የተረፉት ሀቀኛ አመራሮች ደግሞ በጥቅም እንዲከፋፈሉ ይደረጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ መዓት በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባሎች ላይ ካወረደ በኋላ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሚቆጣጠረው ሚዲያ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በጋዜጣ በሀሰተኛ ቃሉ የሕዝቡን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በማስከበር ላይ ነኝ በማለት ይለፍፍም ነበር፡፡
ባለፉት ሥርዓቶች የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ጥረት በማድረጋቸው የኢትዮጵያ ምሑራን የደረሰባቸውን ፈተና በጥቂቱ ጠቃቅሻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በሕዝብ ትግል መነሻነት የኢህአዴግን ቁንጮ በሞት አፋፍ ላይ ቆመው በታገሉት በአቶ ለማ መገርሣ፤ በዶ/ር አብይ አህመድ፤ በአቶ ደመቀ መኮንን፣ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ደጋፊዎቻቸው ቆራጥ አመራር አማካኝነት በኢትዮጵያ የለውጥ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡ ይህን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብትን ማስከበር የሕዝቡና የልሂቃኑ ኃላፊነት ነው፡፡
ታፍኖ የቆየው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታ በአዲሱ ለውጥ ምክንያት ተነቃቅቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሰማንያ በላይ ፓርቲዎች ተመስርተው በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ የፓርቲዎቹ ቁጥር እጅግ ስለበዛ በመራጩ ሕዝብ ላይ ውዥንብር ከመፍጠር ያለፈ ጥቅም ስለማይኖረው የፓርቲዎች ቁጥር ከአምስት መብለጥ እንደሌለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል፡፡
ይህንን ሀሳብ በመደገፍ የረጂም ጊዜ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው ዶ/ር ዲማ ነገዎና ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በመገናኛ ብዙኃን ገለፃ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በዴሞክራሲ ስም ኢህአዴግ ወደ ሰማንያ የሚጠጉ የጎሣ ፓርቲዎችን ፈልፍሎ ዕርስ በራሳቸውና ከአገር አቀፋዊ ፓርቲዎች ጋር በጥቅማ ጥቅም በማጋጨትና በማዳከም የጠነከረ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይወጣ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት በምርጫ ወቅት ሕዝቡ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ስለሚበዙበት አንዱን ከሌላ መለየትና መምረጥ እንዳይችል ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተለይም በብሔር የተደራጁት ፓርቲዎች ለመራጩ የህሊና እረፍት የሚነሱ ሆነዋል፡፡ አንድ ዜጋ በእናቱ የአንድ ብሔር በአባቱ ደግሞ የሌላ ብሔር ተወላጅ ከሆነ በምርጫ ወቅት ከሁለት አንዱን ሳይወድ በግድ ሲመርጥ ቆይቷል፡፡
ይህን አሳዛኝ ሁኔታ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም መወገድ ያለበት መሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ አበክሮ አስገንዝቧል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው እንዳብራራው፤ በቋንቋ ላይ በተመሰረተ የብሔር ፓርቲ ውስጥ ከሌላ ብሔር የመጣ ቋንቋውን የሚችል የፓርቲ አባል ይዋል ይደር እንጂ በደም በዘር ቆጠራ ከፓርቲው መወገዱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የብሔር ፓርቲ አደረጃጀት በቋንቋ ማር የተሸፈነና የተከሸነ ስለሆነ ሥር ሳይሰድ መነቀል ይኖርበታል፡፡
ይህ የሚወገድበትን ስልት ሁለቱ ልሂቃን ዶ/ር ዲማና ዶ/ር አረጋዊ ጠቁመዋል፡፡ አንዱ ስልት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ተከፍለው መደራጀት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ የሚመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሦስት ብቻ ይሆናሉ፤ አንደኛው ቀኝ-ዘመም፤ ሁለተኛው ግራ-ዘመም፤ ሦስተኛው ደግሞ መሃል-ዘመም ይሆናሉ፡፡ በእኔ ሃሳብም ለመራጩ የሚቀለው ሦስት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ቢወዳደሩ ነው፡፡
የፓርቲዎች ምደባ ስልቱም በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስመዘገቡት የፓርቲ ፕሮግራም መሰረት በሦስት መመደብ ነው፡፡ ለዚህም የፓርቲዎች ምደባ ተግባር በፓርቲዎች ምክክር የተመረጡ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁራን፤ የፍልስፍና ምሑሮች፤ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እነዚህን ባለሙያዎች ያካተተ ግብረ ኃይል ሊመሰርቱ ይችላሉ፡፡ ግብረ ኃይሉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በሦስት የሚመድብበትን መስፈርት አዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል፤ መስፈርቱ ሲጸድቅም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምደባ ያከናውናል፡፡
በምደባው መሰረት በሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰባሰቡት አባላት መሪዎቻቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ እንዲመርጡ ይደረጋል፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ አባላቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች የተውጣጡ እንዲሆኑ በማስደረግ ሕዝባዊነቱን ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዜግነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራማቸውን አጠናቀው ለሕዝቡ አቅርበው ያስረዳሉ፡፡ ሕዝቡ እንዲመርጣቸውም በየጎጡ በምስጢር ሳይሆን በአደባባይ በፈለጉት ሚዲያ በአካል ተገኝተው ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ መራጭ ግለሰብም የሦስቱን ፕሮግራሞች የዓላማ ልዩነቶች አጢኖ ከህሊናው ጋር ተማክሮ ምርጫውን በምስጢር ያደርጋል፡፡
የምርጫ ቦርድም ራሱን አድሶ በቴክኖሎጂና በባለሙያዎች በመታገዝ የሕዝቡን ምርጫ ውጤት የሦስቱ ፓርቲዎች ተወካዮች በተገኙበት አረጋግጦ በሀቅ ለሕዝብ ያሳውቃል፡፡ ከዚህ በኋላ አውራ የፖለቲካ ፓርቲ 100 በመቶ ድምጽ አግኝቷል ተብሎ በዓለም ሕዝብ ፊት የሚነገርበት ጊዜ ያከትማል፡፡ ለዚህም የዴሞክራሲያዊና የሰብኣዊ መብት ተቋማት ተጠናክረው ሕዝብን በቅንነት ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡
በመጨረሻም እስከዛሬ በመሪዎች በሥልጣን የመቆየት ፍላጎት ምክንያት ለደረሰብን ሰቆቃ ተጠያቂዎቹ መሪዎቹ ብቻ ሣይሆኑ እኛም ራሳችን ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች ታሪክ እንደምንማረው ከሆነ ከሕዝብ ሰቆቃ ውስጥ መድኅን ይወለዳል፡፡ በኢትዮጵያም መድኅኑ ተወለዷልና ተንከባክቦ ማሳደግ የሕዝብ ኃላፊነት ነው፡፡
ሌላው ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻው ውሱን የጎጥ አመለካከቶችን ወደ አገራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ መቀየር ነው፡፡ ለዚህም የሚሆኑ ሕጎችና አስፈፃሚ ተቋሞች ያስፈልጋሉ፡፡ ሕጎቹ የሚያተኩሩባቸው ቁም ነገሮችም በነፃነት መጻፍ፤ መናገር፤ ከስፍራ ወደ ስፍራ መንቀሳቀስ፣ የሰው መብት አለመድፈር፤ ዕርስ በዕርስና በአገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ መተባበርና መረዳዳት ናቸው፡፡ የሰውን ልጅ ደካማነት መገንዘብና በይቅርታ ጠያቂነትና-ይቅርባይነት መርሆዎች ለአገራችን አስፈላጊውን እርምጃ የመንወስድበት ጊዜ አሁን ነው፡፡
እነዚህን መርሆዎች ለማስፈፀምም ደግሞ የሣይንስ፤ የትምህርት፤ የማኅበራዊ ተቋማት፤ የሚዲያ፤ የዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ድርጅቶች፤ ጠንካራ መንግሥትና በሕግ የሚመራ ነፃ ገበያና ኢንቨስትመንት ወ.ዘ.ተ. አስፈላጊና ወሳኝ ናቸውና ልዩና ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግባቸው ይገባናል፡፡
መጋቢት 24/2010 የተባረከች ቀን ትሁን
አመሰግናለሁ
በጌታቸው ሚናስ