ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ መልስ ከ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከጅምሮ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የ17ኛ ሳምንት ቀሪ መርሃ ግብሮችን ተስተካካይ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት ያስተናገደው ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ በ18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡
በዚህም ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡ 9፡00 ሰዓት ላይ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ለማጠናከር፤ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በሊጉ ያላቸውን ቆይታ ለማረጋገጥ የሚደረግ ጨዋታ መሆኑ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድል መልስ ሲዳማ ቡና ደግሞ ከሽንፈት መልስ የሚያደርጉት ፍልሚያም ነው፡፡ ፈረሰኞቹ በ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነታቸውን ማጠናከራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሀዲያ ሆሳዕና ከደረሰበት የ1 ለ 0 ሽንፈት ማግስት ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ዛሬ አርባ ምንጭ ከተማን ከመቻል የሚያገናኘው ጨዋታም የሚጠበቅ ሲሆን፣ አዞዎቹ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ በማግኘት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት፤ መቻል ደግሞ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ፍልሚያ ይሆናል፡፡ አርባ ምንጭ በተስተካካይ መርሃ ግብር አዳማ ከተማን አስተናግዶ የ3ለ2 ሽንፈት ማስተናገዱ የሚታወስ ሲሆን አርባ ምንጭ በበኩሉ በኢትዮጵያ መድን የ2 ለ 1 ሽንፈት እንደደረሰበት ይታወቃል፡፡
የሳምንቱ መርሃ ግብር ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ቀጥለው የሚካሄዱ ይሆናል፡፡ ነገ 9፡00 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ከወልቂጤ ከተማና፣ 12፡00 ሰዓት ደግሞ ፋሲል ከነማን ከባህር ዳር ከተማ የሚገናኙ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ያለምንም ግብ ወልቂጤ ደግሞ በባህር ዳር ከደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ የሚያደርጉት መርሃ-ግብር ነው። በደረጃ ሰንጠረዡም ቢሆን ኢትዮጵያ ቡና ወደ መሪዎቹ ለመጠጋትና ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ተጠባቂ ነው፡፡
የጣና ሞገዶቹ በተስተካካይ መርሃ ግብራቸው ወልቂጤ ከተማን 4ለ0 በመርታት ከጣፋጭ ድላቸው መልስ ነገ ጎረቤታቸውን ሲገጥሙ፣ አፄዎቹ በበኩላቸው ወላይታ ድቻን 2ለ1 በረቱ ማግስት በዚህ የውድድር ዓመት ጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙት የጣና ሞገዶች ጋር ይፋለማሉ፡፡ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ከድል ማግስት የሚደርጉት ጨዋታ በመሆኑም በጉጉት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ባህር ዳር ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ነጥብ ለማጥበብ፤ አፄዎቹ ደግሞ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚያደርጉ ፍልሚያም እንደመሆኑ ተጠባቂ ነው፡፡
እሁድ 9፡00 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ይገናኛሉ፡፡ አዳማ በተስተካካይ ጨዋታው መቻልን አሸንፎ፣ ሃዋሳ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቶ የሚያካሄዱት ጨዋታ ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዥም ሃዋሳ ከተማ አራተኛ ሲሆን መቻል ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡ ሁለቱም ውጤት በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ለማለት የሚያደረጉት ጨዋታም ይሆናል።
በተመሳሳይ እሁድ 12፡00 ሰዓት ላይ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ከውጤት ማጣት በኋላ የሚገናኙ ክለቦች ናቸው፡፡ በ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በመሪው ቅድስ ጊዮርጊስ የደረሰበትን የ2ለ0 ሽንፈት ለማካካስ ወላይታ ዲቻ ደግሞ በፋሲል ከነማ ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ ነው፡፡ ውጤቱ በተለይም ለኢትዮ-ኤሌክትሪክ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ክለቡ በአሁኑ ወቅት በወራጅ ቀጠና ግርጌ ስለሚገኝ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማሳካት ይኖርበታል፡፡
የ18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ሰኞ ቀጥለው ሲደረጉም ሀዲያ ሆሳዕና ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ፡፡ ሁለቱም የሚገናኙት ከሽንፈት መልስ ነው። ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣትና ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ፍልሚያ በመሆኑም ተጠባቂ ነው፡፡
ሰኞ 12፡00 ሰዓት ላይ በሚያስተናግደው የለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ የ18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሚያጠናቅቅ ይሆናል፡፡ ለገጣፎ ከ15 ጨዋታዎች በኋላ አሸንፎ እና ኢትዮጵያ መድን እንዲሁ ከድል መልስ ነው የሚገናኙት፡፡ ለገጣፎ ያለበትን የውጤት ቀውስ ለመቅረፍና ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ኢትዮጵያ መድን ወደ መሪው ለመጠጋት የማይሆኑት እልህ አስጨራሽ ጨዋታ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዡን ቅድስ ጊዮርጊስ በ38 ነጥቦችና በ26 የግብ ክፍያ ይመራል፡፡ ባህርዳር ከተማ ከጊዮርጊስ በ5 ነጥቦች አንሶ 33 ነጥቦችን በመያዝ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ የሊጉ ክስተት ኢትዮጵያ መድን እንዲሁ በ33 ነጥቦች በግብ ክፍያ አንሶ 3ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 8፣ ለገጣፎ በ9 እና አርባምንጭ ከተማ በ18 ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015