የአንድ ሀገር ህልውና የሚጸናው በሕዝቦቿ የሀገር ፍቅር ጽናትና በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ተቋማት ጥንካሬ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ሲባል ሀገራት በሀገር ፍቅርና በተቋማት ግንባታ ዙሪያ ሁሌም ያለመታከት ይሰራሉ፤ በድካማቸውም ፍሬ ጠንካራ ሀገር እና ሕዝብ በመመስረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተሰሚነትና ተጠቃሚነት ያጎለብታሉ።
በዚህ ረገድ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሆነውን ውጪያዊና ውስጣዊ ሰላም እና ሀገራዊ መረጋጋት እውን ለማድረግ ትልቁን ድርሻ የሚይዙትን፤ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ተቋማትን በጠንካራ መሰረት ላይ የማዋቀሩና በቴክኖሎጂ የማዘመኑ ተግባር ከሁሉም በላይ ትኩረት የሚሰጠው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
በተለይም እንደኛ ባሉ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው በልማትና በልማት ላይ ብቻ መሰረት ላደረጉ ሀገራት፤ ለልማታቸው መሰረትና ቀጣይነት ዋነኛ አቅም የሆነውን ውጪያዊና ውስጣዊ ሰላማቸውን እውን ለማድረግ የግድ ይላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ተቋሞቻቸውን አቅም መገንባትና አስተማማኝ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትም ያስፈልጋቸዋል።
እኛም እንደ ሀገር “ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን” በሚል እሳቤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ እያደረግነው ያለነውን ልማት በአስተማማኝ የሰላምና የጸጥታ መሰረት ላይ ለማዋቀር በመከላከያና በጸጥታ ተቋማት ላይ ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረናል። የለውጥ አመታት እንደ ሀገር በብዙ ፈተናዎች የታጠሩ ቢሆኑም፤ የሪፎርም ስራዎቹ ግን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
ለዚህም የሀገሪቱን የፌደራል የደህንነት እና የፖሊስ ተቋማትን ከተልእኮ ጀምሮ በሰለጠነ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አቅማቸውን ለማሳደግ የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት፤ ለጎረቤት ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል ደረጃ ላይ ደርሷል። እንደ ሀገርም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ያጋጠሙንን ውስብስብ ፈተናዎች በስኬት እንድንሻገር ትልቅ አቅም ሆነውናል።
በመከላከያና በጸጥታ ተቋማት ላይ የሚሰሩ የሪፎርም ስራዎቹ ቀጣይነት ባለው መልኩ ያለማቋረጥ በከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚከናወኑ የብሔራዊ ጥቅማችን ማስፈጸሚያ ስትራቴጂክ ከመሆናቸው አንጻር፤ አሁን ላይ በዘርፉ እያስመዘገብነው ያለው ስኬት የምንዘናጋበት ሳይሆን ለበለጠ ስራ እራሳችንን የምናዘጋጅበት ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው።
በተለይም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ በተለያየ የእዝ ሰንሰለቶች የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ ኃይሎችን በአንድ የእዝ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባት አንድ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ኃይል የመፍጠሩ ሂደት፤ አንድም ሀገራዊ የጸጥታ ኃይሉን በሁለንተናዊ መልኩ ለማብቃት፣ ከዛም ባለፈ አንድ ሀገራዊ ተልእኮ ይዞ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል ካለው የማይተካ አስተዋጽኦ አንጻር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ሕገ መንግስታዊ በሆነ ስርአት ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ባለፈ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ራሱ ከየትኛውም አይነት አደጋና ስጋት የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ኃላፊነታቸውን የሚወጡት ከህገ መንግስቱ በሚመነጭ ስልጣንና ኃላፊነት ነው፡፡ በአንድ ወጥ የእዝ ሰንሰለት የመመራታቸው እውነታም ለተልእኳቸው ስኬት ወሳኝ አቅም የሚፈጥርላቸው ይሆናል።
በተለይም ሕገ መንግስታዊ የሆኑ የጸጥታ አካላት አቅም እየገነቡ ሲመጡና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል ቁመና ሲላበሱ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሕጋዊ መሰረት ሳይኖራቸው የጸጥታ ኃይሉን ሲደግፉ የነበሩ አደረጃጀቶች ሕጋዊነት የሚላበሱበትን አሰራር መፍጠር ያስፈልጋል።
እነዚህን በአገር ሰላምና ሕልውና ማስጠበቅ ከፍ ያለ መስዋእትነት በመክፈል የድርሻቸውን ሲወጡ የነበሩ አደረጃጀቶችን በሕገ መንግስታዊ ስርዓትና ተልዕኮ በመግራት፤ የተሻለ ስልጠና እና የተልእኮ ዝግጁነት በመፍጠር ህጋዊ በሆኑ አደረጃጀቶች እንዲታቀፉ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ አደረጃጀቶቹ ለሀገር ሰላም እና ለሕዝቦች ደህንነት ከቀደመው የተሻለ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሕብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ ወጥ ጠንካራ የጸጥታ እና የመከላከያ ኃይል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015