17ኛው አገር አቀፍ የክለቦችና ከተማ አስተዳደሮች የዳርት ስፖርት ቻምፒዮና ከመጋቢት 21 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ ከትላንት በስቲያ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ፉክክሮችን ያስተናገደው ይህ ቻምፒዮና በአዲስ አበባ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ቻምፒዮናው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በስልጠናና ውድድሮች ሲያደርጉ የቆዩት እንቅስቃሴ ምንደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመለካትና ብሄራዊ ቡድን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል። አምስት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በቻምፒዮናው የተሳተፉ ሲሆን አራት የሚደርሱ ክልሎች በጀትና ባለሙያ ባለመመደብ መሳተፍ እንዳልቻሉ የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በቀጣይ ግን ክትትል በማድረግ ያልተሳተፉ ክልሎች እንዲሳተፉ እንደሚሰራ ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡
በቻምፒናው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 456 ነጥቦቸን በመሰብሰብ በሁለት የወርቅ፣ ሶስት የብርና በአንድ የነሐስ ሜዳለያ ቀዳሚ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል፡፡ አማራ ክልል በበኩሉ 337 ነጥቦችን በመያዝ በሶስት የወርቅና በአንድ ብር ሜዳሊያ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል። ደቡብ ክልል ደግሞ 319 ነጥቦችን ሰብስቦ በሶስተኝነት አጠናቋል፡፡
ውድድሮቹ በአራት የተለያዩ ምድቦች ተከፍለው በመካሄድ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ፤ በነጠላ ወንድና ሴት ውድድር፣ ጥንድ ወንድና ሴት ውድድር፣ የቡድን ወንድና ሴት ውድድርና የድብልቅ ፉክክሮችን በማድረግ አሸናፊዎች ተለይተዋል።
በነጠላ ወንዶች ምድብ ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ ሳላዲን አብዲ ከሐረሪ ክልል የወርቅ ሜዳለያ አሸናፊ ሲሆን፣ በዚሁ ምድብ ጥሩ ፉክክር ያደረገው ሀብታሙ ዳግም ከአማራ ክልል የብር ሜዳለያ ተሸላሚ ሆኗል። እርቅይሁን አዲሱ ከአዲስ አበባ የነሐስ ሜዳሊያውን ያጠለቀ ተወዳዳሪ ሆኗል።
በነጠላ ሴቶች ምድብ በተካሄዱ ውድድሮች ማስተዋል ነፃነት ከአማራ፣ ከበቡሽ አሎንጆ ከደቡብና መክሊት ጎንፋ ከሲዳማ በተጋጣሚዎቻቸው ላይ በወሰዱት የበላይነት የወርቅ የብርና የነሐስ ሜዳለያ አሸናፊዎች ሆነዋል።
በወንዶች ምድብ የወርቅ ሜዳለያ አሸናፊው ሳላዲን አብዲ፤ ለውድድሩ ጥቂት ዝግጅት ማድረጉንና ለማሸነፉ ልምዱ እንደጠቀመው ለአዲስ ዘመን ገልጿል፡፡ ሳላዲን በዳርት ስፖርት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሲወዳደር መቆየቱን ያስታውሳል። ለመጀመርያ ጊዜ ድሬዳዋ ላይ የተሳተፈ ሲሆን በ2005 ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደ ውድድር ተመልሶም ዘንድሮ ተሳታፊ ሆኗል።
“ደስ የሚልና የሚያዝናና ጨዋታ ቢሆንም ያስጨንቃል፣ ዛሬ እድል ከኔ ጋር በመሆኗ አሸንፌ ወርቅ ለማጥለቅ በቅቻለው” ሲልም ስለዘንድሮው ቻምፒዮና አስተያየቱን ሰቷል፡፡ የዳርት ፌዴሬሽን ለክልሎች የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግና ፕሮጀክቶችን በማብዛት ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች ወክለው ውጤታማ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንደሚቻል መልዕክቱን አስተላ ልፏል፡፡
የጥንድ ምድብ ውድድሮች በሁለቱም ጾታዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ፤ በጥንድ ወንዶች ብርሃኑና ደሳለኝ የወርቅ፣ አማኑኤልና እርቅይሁን የብር ሜዳሊያዎችን ለአዲስ አበባ አስመዝግበዋል። በጥንድ ሴቶች ምድብ ኬሪያና እስከዳር ከደቡብ የወርቅ፣ ሲትራና ተስኒም ከሐረሪ የብር፣ ከበቡሽና ብዙአየሁ ከደቡብ የነሐስ ሜዳለያ ማሳካት ችለዋል።
በድብልቅ ፆታ ምድብ በተካሄዱ ውድድሮች ደግሞ አማኑኤልና ፍሬወይኒ ከአዲስ አበባ የወርቅ፣ እስከዳርና በጎስጦታ ከደቡብ የብርና እዮብና ሮዛ ከአማራ የነሃስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችለዋል። የሴቶችና የወንዶች የቡድን ምድብ ውድድር በአጓጊ ፉክክሮች ታጅቦ ሲጠናቀቅ፣ በሴቶች የቡድን ውድድር አማራ 1ኛ፣ አዲስ አበባ 2ኛ እና ሲዳማ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። በተመሳሳይ በወንዶች የቡድን ምድብ ውድድር አማራ የወርቅ፣ አዲስ አበባ የብርና ሐረሪ የነሃስ ሜዳለያ ባለቤት በመሆን ውድድራቸውን ፈጽመዋል፡፡
በቻምፒዮናው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተጫዋቾች የማጣርያ ውድድር በማድረግ በቀጣይ መስከረም በሚካሄደው የዓለም ዳርት ቻምፒዮና ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ የዳርት ስፖርት ብዙ ቦታን የማይፈጅ የአእምሮ ስፖርት መሆኑን ጠቁመው የእጅና የአይን ቅንጅትን በማስተሳሰር እርግጠኝነትን የሚያሰፍን የስፖርት ዓይነት ነው በማለት ይናገራሉ።
ስፖርቱ በሁሉም ቦታዎች ማለትም በሆቴሎች፣ በማሰልጠኛ ማዕከላት፣ በመዝናኛ ስፍራዎች በቀላሉ ሊከወን የሚችል ስፖርት ዓይነት ነው የሚሉት አቶ ቢልልኝ፣ ስፖርቱ ለማዘውተር የቁሳቁስ አቅርቦት ችግርና ብዙ ወጪን የማይጠይቅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለወጣቶችና ለአዋቂዎች እድል በመስጠት በውድድሩ እየተሳተፉ የተሻሉና አገርን መወከል የሚችሉ ተወዳዳሪዎችን ማበርከት እንደቻሉ አስረድተዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ የዳርት ፌዴሬሽን ከበጀት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ተደጋጋሚ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ይቸገራል። ያምሆኖ በየጊዜው ታዳጊዎችን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን የሚያሳትፍ ውድድር ማዘጋጀት ግዴታ ነው።
ዳርት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዘወትር ስፖርት በመሆኑ ተወዳዳሪዎች ከታች ጀምሮ የውድድር እድል ሊኖራቸው ይገባል። ስለዚህም ከኢትዮጵያ ቻምፒዮና በተጨማሪ ወደፊት ስፖንሰሮች ከተገኙ ፌዴሬሽኑ ሌሎች ውድድሮችን ለማዘጋጀት እቅድ እንዳለው ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። አዳዲስ ስልጠናዎችን የመስጠትና ከዚበፊት በተሰጡት ላይም የማነቃቂያ ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015