የአዕምሮ እድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ያለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግራቸው በትክክል ባለመታወቁ የተነሳ ከፍተኛ እክል ሲገጥማቸው እንደነበር መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው። በሽታው ማንኛውም ሰው የሚገጥመውና ሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ የጤና እክል ቢሆንም፤ የጤና እክሉ ያለባቸው ዜጎች ይህንን ባለመገንዘብ ለዓመታት ብዙ በደል እንዲደርስባቸው ሆነዋል። ከበደሉ ዋነኛውም የጤና እክሉ የተለያየ ትርጉም መስጠቱ ነው። አንዱ ደግሞ ከፈጣሪ የመጣ ቁጣና እርኩስ መንፈስ ተደርጎ መወሰዱ ነው።
በዚሁ የተዛባ የሕብረተሰቡ አመለካከትና እሳቤ ሳቢያ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች በተለይም ህፃናትና ታዳጊ ልጆች ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸዋል። ማሰር፤ በር በላያቸው ላይ መቆለፍና ከዚሁ ጋር በተያያዘም እንዲሰቃዩ ማድረግ በዋናነት የሚጠቀሱ እንግልቶች ናቸው። ይህ ነገር ዛሬም ቀንሷል ለማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም ይህንን ግንዛቤ የሚፈጥሩ የሕክምና፤ የትምህርትና የሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አልሰፉም።
ጅማሮውም ቢሆን ሥራ ከመቃብር በላይ እንደሆነ ያስመሰከሩት አሻራቸውን በሰው ልብ ውስጥ ያስቀመጡት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ባይሆን ኖሮ እንደአገር ተግባሩ ይነሳል፤ እንቅስቃሴው ይሰፋል ለማለት ያስቸግራል። እርሳቸው በገጠማቸው ችግር ምክንያት ለአገር ልጆች ተስፋ ለመስጠት ይህንን ማህበራዊ የሆነ ውስብስብ ችግር መስበር ችለዋል። የጆይ ኦቲዝም ማዕከልን በአገር ደረጃ በመመስረትም በርካታ ልጆችን ታድገዋል።
የበሽታው ተጠቂ በሆነው በልጃቸው ስምም ለመጀመርያ ጊዜ የ‹‹ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል››ን መስርተዋል። ሕይወታቸው እስካለፈበት ድረስም የዚሁ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን የብዙዎችን ተስፋ አለምልመዋል። ምንም የኦቲዝም መረጃም ሆነ አገልግሎት ባልነበረበት በ1994 ዓ.ም ጀምሮ በኦቲዝም ጉዳይ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ዓይን ገላጭም ነበሩ።
ዘሚ አብዛኛው የሕይወታቸውን ዘመን ያሳለፉት በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በጤና፣ በትምህርት፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በአካታችነት፣ በአካቶ ትምህርት በያገባኛል ስሜት ህብረተሰብ አቀፍ የማህበራዊ ንቅናቄ ላይ በመሥራት ነው። የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን፤ በሮተሪያንነት፣ በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና አገር አቀፍ ፖሊሲ አማካሪ ግብረ ኃይል አባልነት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል እና ሌሎች በርካታ ተቋማት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል እንዲሁም በበርካታ አገር አቀፍ የበጎ አድራጎት ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጾ በማድረግ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ ስለ ኦቲዝም ሰብከዋል፤ ብዙዎችን ከስህተታቸው መልሰዋል።
ይሄ የዘሚ የህይወት ዘመን የላቀ የመሪነት አስተዋጽኦ እና ሁሉ አቀፍ የማህበራዊ አገል ግሎትም መጋቢት 22/2015 ዕውቅና ማግኘት ችሏል። እውቅናው ከፍተኛ ተፅዕኖ ለፈጠሩ ሴቶች የሚበረከት ሲሆን፤ “The African Womens Award” የሚል ነው። አሸናፊ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ይህ ስራቸው ደግሞ እርሳቸው ባይኖሩም ቀጣይነቱ ግድ ነውና ከእውቅናው ባሻገር በቅንጅት እንዲሰራ እድል ተሰጥቶታል። ይህም ፋውንዴሽኑ የሚያከናውናቸውን በርካታ ተግባራት ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል፣ ከአዲስ አበባ ነህሚያ ኢቲዝም ማዕከል፣ ከአዲስ አበባ፤ ምሉዕ ፋውንዴሽን፣ ከአዲስ አበባ፤ ቤቴል አዳማ ኦቲዝም ማዕከል፣ ከአዳማ ብራይት ኦቲዝም ማዕከል፣ ከሀዋሳ ተረክበው በቅንጅት እንዲያሰሩት መደረጉ ነው። በተለይም አካቶ ትምህርት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሁሉም ህጻናት እና ወጣቶች ተደራሽ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ዋነኛ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩም ሆነዋል።
በየዓመቱ መጋቢት 2 የሚከበረው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ወር ‹‹አካቶ ትምህርት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሁሉም ህጻናት እና ወጣቶች!” በሚል መሪ ሀሳብ እንዲከበር የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። እናም ቅንጅቱ እንደ አገር የኦቲዝም ተጠቂዎችን ተደራሽ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። የተለያዩ እንቅስቃሴዎችንም እያከናወነ ይገኛል። ከሚያከናውናቸው ውስጥ ‹‹ጥራት ያለው አካቶ ትምህርት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሁሉም ሕፃናትና ወጣቶች›› የሚለው አንዱ እንደሆነ የ16ኛው ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀን የኦቲዝም ማዕከላት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋየ ገብረማርያም ይናገራሉ።
የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀን በዓለም ለ16ኛ ጊዜ ይከበር እንጂ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው። በዓሉ መከበሩ ኦቲዝም ያለባቸው ዜጎች በማህበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚያግዝ ነው። እንቅፋት የሚሆኑባቸውን ተግዳሮቶች ይቀንሳልም ተብሎ ይታሰባል። ስለሆነም አውቲስስቲክ ሰዎች በአካቶ ትምህርት ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብና መስራት ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈጣሪ በጎ ለሰሩ ሁሉ አስታዋሽ አያሳጣቸውምና የዘሚን ሥራ እያስታወስን የበለጠ ለኦቲዝም ተጠቂዎች እንድረስ በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015