ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ለበርካቶች ሞትና፤ የአካል ጉዳተኝነት፤ ለሚሊዮኖች ስደት ምክንያት ሆኗል፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ላይም ያስከተለውም ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አገር ለዘመናት በበርካታ ጦርነቶች ውስጥ እንደማለፋችን የጦርነትን ጉዳት ከማንም በላይ ጠንቅቀን የምናውቅ ህዝቦች ነን፡፡ ከጦርነት ጋር በተያያዘም ስንከፍል የኖርነውም ዋጋ ለግምት የሚከብድ ነው፤ አሁን ላለንበት ኋላቀርነት ዋነኛ ምክንያት ስለመሆኑም ታሪካችን በተጨባጭ የሚናገረው እውነታ ነው።
በሰሜኑ የተከሰተው ጦርነት ቀድሞውኑም አገሪቱ ከነበረችበት ውስብስብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ በህዝባችን የእለት ተእለት ሕይወት ላይ ያስከተለው ተጽእኖ ከፍያለና እስካሁንም በተጨባጭ የሚታይ ነው፡፡
ጦርነቱ በአገር ውስጥ ካስከተለው ውድመትና ጥፋት በተጨማሪ፣ በአገሪቱ መልካም ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል፤ ዜጎችን አንገት ከማስደፋት በተጨማሪ፤ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚኖረው ህዝብ ስነልቦና ላይም ጥላት ያለፈው ጠባሳም በቀላሉ የሚሰላ አይደለም፡፡
ችግሮችን ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ በመነጋጋር ለመፍታት ባለመቻሉ፤ በተከሰተው ግጭት እንደ አገር ያልተገባ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል፡፡ በተለይም ለራሱ ቀርቶ ለግጭቱ አካባቢ ለነዋሪ የነበረው ሰላማዊ ህዝባችን የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የመሆኑ እውነታ ሁኔታውን አስከፊ አድርጎታል።
በርግጥ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ባልተስማማንባቸው ጉዳዮች ሁሉ የጦር መሳሪያ ማንሳታችን ከማንም በላይ የጎዳው እኛኑ ነው፡፡ በተለይም የአገሪቱ ህዝብ ግጭቶችን የሚፈታበት የራሱ የሆነ ጥንታዊ ባህላዊ ስርዓት ያለው ሆኖ ሳለ በማያግባቡ ነገሮች ይህንን የኖረ እሴት መጠቀም ያለመቻሉ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
እርግጥ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅምሩ ጀምሮ ችግሮች በሰላማዊ ውይይትና ድርድር መፍትሄ እንዲያገኝ ሲወተውት ቆይቷል። መንግሥት ሳይወድ ከገባበትን ከዚህ ጦርነት ለመውጣትም ብዙ ዋጋ መክፈሉ እሙን ነው፡፡
አሁን ከሁለት ዓመት የእርስበርስ ግጭት በኋላ የመንግሥት ሰላማዊ ውጥን በደቡብ በአፍሪካ ፕሪቶሪያ በሰላም ስምምነት እልባት አግኝቶ፤ የሰላም አየር መንፈስ ከጀመረ ጥቂት ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም አገራዊ እፎይታ ሰፍኗል፤ ሕይወትም ወደቀደመው ስፍራው በመመለስ ላይ ነው።
ከስምምነቱ ጋር የተያያዙ የውሳኔ ሀሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ በኩልም ሁኔታዎች በተጠበቀው መልኩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆኑም፤ አፈጻጸማቸው ግን ከችግሩ ውስብስብነት አኳያ ተስፋ ሰጭ ነው። መንግሥትና ሕወሓት ለሰላም ደጆቻቸውን ክፍት ማድረጋቸው እንደትልቅ እምርታ የሚታይ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀራርበው በመነጋገር፤ የህዝቡን ህይወት ለመታደግ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴም አበረታች ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሟል፤ የሚመራውም ርእሰ መስተዳድር ይፋ ተደርጓል። ይህ ሂደት ለቀጣይ የስምምነቱ አፈጻጻም ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የክልሉን አሁንም ካሉበት ችግሮች ለመታደግ ጥርጊያ መንገድ ያበጃል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በክልሉ ጦርነቱ የወለዳቸው በርካታ ችግሮች አሉ፤ እነዚህ ችግሮች በክልሉ መንግሥት ቀርቶ በፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም። በክልሉ በሚገኙ የመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ድርሷል። ሌላው ይቅርና የጤና መሰረተ ልማቶቹና አገልግሎቶችም በጦርነቱ ሳቢያ በመውደማቸው ህክምና ሳያገኝ ለተጨማሪ የጤና እክል የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ትናንት ብዙዎችን ቀጥሮ ያስተዳድር የነበረው ባለሃብት፤ ከተሜውን ሳይቀር ሲመግብ የኖረው አርሶአደር፤ አገሪቱ ብዙ ከፍላ ያስተማረችው ምሁርና ባለሙያ ጭምር የሰው እጅ ጠባቂ ሊሆን ተገድዷል፡፡ ታዲያ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች በመንግሥትና በአዲሱ አስተዳደር ጫንቃ ላይ የወደቁ ቢሆንም የህዝቡ፤ የፖለቲከኞችና የአጋሮችን ድጋፍ የሚሹ ናቸው፡፡
በተለይም ደግሞ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉና በክልሉም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በክልሉ ስለሰላም የሚከናወኑ ተግባራትን /የሽግግር መንግሥት ምስረታን ጨምሮ ሌሎችንም/ከመንቀፍ ይልቅ የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
በእርግጥም እነዚህ ድርጅቶች የሚሰሩት ለህዝብና ስለህዝብ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነቱ መርሆዎች ያለመሪ/ያለ አስፈጻሚ/ መሬት ሊወርዱ እንደማይችሉ ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የጦርነቱ ሰለባ የነበሩ የክልሉም ሆነ የአጎራባች ክልሎች ህዝቦችን ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚሹ ናቸው።
ይህንን እውን ለማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊና አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ዛሬ ላይ በችግር ውስጥ ያለውን ህዝብ ህይወት መታደግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
በብዙ ጥረት የመጣው ሰላም እና መረጋጋት ዘላቂነት የሚኖረው የህዝቡ ተሳትፎ ሲታከልበትና ፍላጎቱም ሲሟላለት ነው። በተለይ ደግሞ ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን እንደማንኛውም ዜጋ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት የሚመሰረተው ጊዜያዊ የአስተዳደር ኃላፊነቱ ትልቅ ነው። ለዚህ እራሱን በሁለንተናዊ መንገድ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።
ለአገሪቱና ለህዝቦቿዋ እናስባለን የሚሉ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች አሁን የተገኘው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ያልተገቡ አጀንዳዎች ህዝቡን ከመከፋፈል ወጥተው፤ ለአገር አንድነትና ሰላም ማሰብ ይገባቸዋል።
አገራችን የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤ ቋንቋ እና ሃይማኖት እንዲሁም አመለካከቶች ያሉባት ነች፡፡ እነዚህን ልዩነቶች እንደመልካም እሴትና ውበት በመያዝ ለአገር ጥቅም ማዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ፅንፍ የወጡ ናቸው የሚባሉ አመለካከቶችን አንድ ማድረግ ባይቻልም እንኳን በማቀራረብ ሊመጣ ከሚችለው የከፋ ጉዳት አገርና ህዝብን መታደግ ይገባል፡፡
በተለይም አሁንም ላይ በአገሪቱ ነፍጥ አንግበው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ኃይሎች ከሰሜኑ ጦርነት መማርና ለውይይት እድል መስጠት፤ ጦርነት የሚፈታልን ችግር አለመኖሩን ካለፈው ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፤ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ የተጀመረውን አገራዊ ሰላም በማጽናት ወደ ልማት በሙሉ አቅማችን የምንመልስበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅብናል።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015