በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት መቋጫ አግኝቷል፤ ይህንንም ተከትሎ አገርና ህዝብ የሰላም አየር መተንፈስ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉ ርብርርቦችም ሰላሙ የበለጠ አቅም እንዲያገኝ የተሻለ እድል እየፈጠሩ ነው።
”የራሳችንን ችግር በራሳችን የመፍታት አቅም አለን ” በሚል መርሕ የተጀመረውና አሁን ላይ ውጤታማ እየሆነ ያለው የሰላም ስምምነቱ፤ በብዙ መልኩ በችግሮቻችን ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለን መነጋጋርና መወያየት ከቻልን መፍትሄዎቻቸው በእጃችን እንዳሉ በተጨባጭ ያመላከተ፤ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብም ይህንኑ እውነታ እንዲረዳ ያስቻለ ነው።
ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ሂደትም በመንግስትም ሆነ በሕወሓት በኩል የሚታየው ቁርጠኝነት፤ ሰላም የቱን ያህል የአገርና ሀዝብ ዋነኛ አጀንዳ እንደሆነ፤ ከዛም ባለፈ የህዝቦቻችን/ የአገራችን ቀጣይ እጣ ፈንታ በሰላምና በሰላም ላይ የተመሰረተ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ አይነቱ ሰናይ ተግባር በሁለንተናዊ መልኩ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
አሁን ላይ በትግራይ ክልል የሽግግር ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቷል፤ መንግስቱን የሚመራ ፕሬዚዳንትም ተሰይሟል፡፡ ጊዚያዊ አስተዳደሩም ከሰላምና ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ውይይቶችንና ምክክሮችን እያካሄደ ይገኛል፡፡
የክልሉን ሕዝብ የሰላም፤ የልማትና ሌሎች ጥያቄዎች በመመለስ፤ በክልሉ ያለውን ሰላም በተሻለ መሰረት ላይ ለማጽናት፤ የመንግስትና የህዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፤ የክልሉ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ሊያደርጋቸው የሚችሉ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉም ድጋፍ ወሳኝ ነው።
በተለይም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ዲሞክራሲያዊም በሆነ መልኩ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ርእሰ መስተዳድር አድርገው እንዲሰየሙ የመረጧቸው እና በፌደራል መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው ርስሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ቀጣይ ስራቸው ስኬታማ እንዲሆን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አቅም ሊሆኗቸው ያስፈልጋል።
የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ ምክንያት ካለበት አሁነኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ፈጥኖ እንዲያገግም፤ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነታቸውን ወደኋላ በመተው ተባብረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የሚሆን ግልጽነት መፍጠርንም ትልቁ የሽግግር ወቅቱ የፖለቲካ እሴት አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
ይህን ማድረግ በቀጣይ በክልሉ አዲስ የፖለቲካ ባህል እንዲያብብ፤ ህዝቡም የዚህ ባህል ተጠቃሚ እንዲሆን እድል የሚፈጥር፤ ከዚህም በላይ በክልሉ ያለውን አሁነኛ ሰላም በተሻለ መልኩ በማጽናት ወደ ልማት የሚደረገው ጉዞ ስኬታማ የሚያደርግ እንደሚሆንም ይታመናል። ይህን ማድረግ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ አሳቢና ተቆርቋሪ ነኝ ከሚል የትኛውም የፖለቲካ ቡድን የሚጠበቅ ትንሹ ኃላፊነት ነው።
የትግራይ ሕዝብ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከከፈለውና እየከፈለ ካለው ዋጋ አንጻር፤ አሁን ላይ ከሁሉም በፊት ዛሬ ላይ እፎይ ያስባለውን ሰላም የሚያጸናለት እና የሚያስቀጥልለት ተጨባጭ የፖለቲካ ቁርጠኛነት ነው። ይህንን ደግሞ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ማግስት ጀምሮ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየገለጸው ያለው እውነታ ነው።
ይህ የህዝቡ የሰላም መሻት ቀደም ሲል ከፌደራል መንግስት ጋር ተፈጥሮ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን፤ በትግራይ ፖለቲከኞች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶች፤ ወደ ግጭት እንዳይለወጡ፤ ግልጽ በሆነ ውይይትና ድርድር ብቻ መፍትሄ እንዲያገኙ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ጭምር ነው።
የሽግግር አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ወደ ስልጣን መምጣትም ይህንኑ የሕዝቡን ፍላጎት በተደራጀ መንግስታዊ መዋቅር ፈጥኖ እውን ለማድረግ የሚያግዝ፤ በቀጣይ በክልሉ አዲስ የፖለቲካ ስርአት በመፍጠር ሕዝቡን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለመካስ የሚያስችል በመሆኑ፤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአዎንታዊ መልኩ ሊመለከቱትና ለውጤታማነቱ ባላቸው አቅም ሁሉ ሊተባበሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም