‹‹ማንበብ ልማዳችን አይደለም›› ሲባል ለመጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት ብቻ ይመስላል፡፡ በአንድ ዓረፍተ ነገር ወይም ሐረግ ወይም በአንዲት ቃል ብቻ የተጻፉ ጽሑፎችንም አናነብም፡፡ አንድን ነገር ምን እንደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍ ተጽፎ ልብ አንለውም፤ ይልቁንም በግምትና በዘፈቀደ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡
ይህን ነገር ያስታወሰኝ ባለፈው እሁድ ከአንድ መምህር ጓደኛዬ ጋር በነበረን ጨዋታ ነው፡፡ አንድ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ገዝተን ወደ ቤት ገባን፡፡ ዋጋውን ከባለፈው ዓመት ጋር እያነፃፀርን ስንገረም ቆይተን ‹‹በዚህ ዋጋ ተገዝቶ ለረጅም ጊዜ ቢያገለግልስ ጥሩ አልነበር!›› በሚል ቶሎ ስለመበላሸቱም ሀሳብ ተነሳ፡፡ ለመበላሸቱ ግን የምርቶች ጥራት እንዳለ ሆኖ የአጠቃቀም ስህተቶችም አሉ፡፡ ይህን ስናስታውስ ከዕቃው ጋር የተሰጠች ዝርዝር መመሪያ የያዘች ወረቀት ማንበብ ጀመርኩ፡፡ በዚያው እግረ መንገድ መመሪያ ባለማንበብ ብዙ ነገር እንደምናበላሽ ስናወራ ቆየን፡፡
በልጅነቴ አንድ ጥሩ ልማድ ነበረኝ፡፡ የፋብሪካ ዕቃዎች የታሸጉበት ሽፋን ላይ ወይም ራሱ ዕቃው ላይ ጽሑፍ አላቸው፡፡ ጽሑፎቹ አብዛኛውን ጊዜ እንግሊዘኛ ናቸው። የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የፋብሪካ ዕቃዎች ላይ ያሉ ጽሑፎችን እያዟዟርኩ ነበር የማነብ፡፡ ችግሩ ግን እኔ የማነበው ስለዕቃው አጠቃቀም ለማወቅ ሳይሆን እንግሊዝኛ ማንበቡ ብርቅ ስለሚሆንብኝ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹን ትርጉማቸውንም አላውቀውም፡፡ ቢሆንም ግን እያዟዟርኩ አነብ ነበር፡፡ የትምህርት ደረጃዬ ከፍ እያለ ሲሄድ ግን በተቃራኒው ሰነፍ እየሆንኩ ሄድኩ፤ ከዕቃዎች ላይ ያሉ ጽሑፎችን ማንበብ ትዝ አይለኝም፡፡
አሁን ላይ ሳስበው የእኔ ችግር ብቻ አይደለም፤ እንደ ቁም ነገር የሚቆጥረው የለም፡፡ በተለይም ትልልቅና በውድ ዋጋ የሚገዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ስንገዛ ወረቀቱን ከታሸገበት ካርቶን ጋር ነው የምንጥለው፡፡ እንኳን ወረቀቱን ከራሱ ከዕቃው ላይ ያለውን ጽሑፍ እንኳን አናነበውም፡፡ አውቀነው ቢሆን እኮ ችግር አልነበረውም! አብዛኞቻችን ግን ሳናውቀው ነው የማናነበው፡፡
አብሮን ያልኖረ የፋብሪካ ዕቃ ስንጠቀም መመሪያውን ከማንበብ ይልቅ ሰዎችን በመጠየቅ ወይም በልማድ በማየት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መመሪያው ከላዩ ላይ እያለ በዘፈቀደ ለመገጣጠም ወይም ለማሰራት እንታገላለን። እንዴት መሰካካት እንዳለበት ጠቋሚ ምልክቶች እያሉ በግድ ለመሰካት እንታገላለን፤ እምቢ ካለ እያዟዟርን መታገል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ዕቃው ለብልሽት ይዳረጋል፡፡ በተለይም የምልክት ጠቋሚዎችን ልብ አንልም፡፡
መመሪያ አለማንበብ ዕቃ ማበላሸትን ያስከትላል ማለት ነው፡፡ የገዛነውን ዕቃ ያለአግባብ አበላሸን ማለት ለኪሳራ ተዳረግን ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ማንበብ አለመውደዳችን በሕይወታችን ላይ ጉዳት እያመጣ ነው ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ ግን አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር አለ። ብዙ የፋብሪካ ምርቶች መመሪያዎቻቸው የሚጻፈው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አብዛኞቹ የሚመረቱት ውጭ አገር ስለሚሆን ነው፡፡ ዳሩ ግን የአገር ውስጥ ምርቶችም ቢሆን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ሲባል መመሪያቸው የሚጻፈው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት የሚገኝ እንጂ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ያለ አይደለም። የማህበረሰቡ ቋንቋ አይደለም፤ በሃይማኖት ተቋማት እና በጎልማሶች ትምህርት የሚማሩ ሰዎች እንግሊዝኛ አንብበው ላይረዱ ይችላሉ፡፡
ይህ ግን ለስንፍናችን ምክንያት አይሆንም፤ ምክንያቱም አፋችንን በፈታንበት ቋንቋ የተጻፉ መመሪያዎችንም አናነብም፡፡ በአማርኛ አፉን የፈታ ሰው የአማርኛ መመሪያዎችን አያነብም፡፡ የእንግሊዝኛ ዜናዎችን፣ የእንግሊዝኛ ልቦለዶችን የሚያነቡ ሰዎች መመሪያዎችን ግን አያነቡም፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ገደብ ብቻ ሳይሆን ልብ አለማለት(ስንፍና) ነው፡፡
መመሪያዎችን አለማንበብ ለወንጀል ሁሉ ይዳርገናል። ‹‹ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም›› የሚባል ተደጋጋሚ መሪ ቃል አለ፡፡ መመሪያዎችን አለማንበብም ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ብዙ ጊዜ መደረግ የሌለባቸው ነገሮች በጽሑፍ ተከልክለው ሳለ ባለማንበብ ብቻ እናደርጋቸዋለን፡፡ ‹‹ማለፍ ክልክል ነው›› የሚል ተጽፎ ባለማንበብ ብቻ ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ እንገጥማለን፡፡ ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያለበት ቦታ ላይ ፎቶ አንስተን ልንጠየቅ እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ ከፍተኛ የፀጥታ ገደብ ያለባቸው አካባቢዎች ላይ መመሪያ ባናነብ ለወንጀል ልንዳረግ እንችላለን፡፡
መመሪያ ማንበብ መለማመድ ያለብን ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፈተና ትዕዛዞች ጥሩ መለማመጃ ናቸው፡፡ አስታውሳለሁ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ አንዳንድ መምህራን ከጥያቄው ይልቅ በመመሪያ(ትዕዛዝ) ይሸውዱን ነበር፡፡ ጥያቄው ሳይከብደን በመመሪያ ስህተት አንድ ትዕዛዝ የሚይዛቸውን ሙሉ ነጥቦች እናጣለን፡፡ የሚገርመው በመመሪያ ስህተት የሚሸወዱት ጎበዝ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ሮጠው ወደ ጥያቄው ስለሚሄዱ በተለመዱት ትዕዛዞች ብቻ ነው መልሱን የሚሞሉት፡፡
ለምሳሌ፤ ትዕዛዙ ‹‹ትክክል የሆነውን ሀሰት፣ ትክክል ያልሆነውን ደግሞ እውነት በማለት መልሱ›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ የተለመደው ትክክል የሆነውን እውነት፣ ትክክል ያልሆነውን ደግሞ ሀሰት ማለት ስለሆነ የጥያቄዎች ይዘት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ ትዕዛዝ ያው ትዕዛዝ ነውና ነጥብ እናጣለን፡፡
አሁን ያለው መመሪያ ያለማንበብ ችግራችን ግን ልብ አለማለት ብቻ አይደለም፤ ጭራሹንም አለማየት ሆነ እንጂ። እንዲህ አይነት ጥቃቅን ስህተቶች እየተለመዱ ሲሄዱ ትልቅ አደጋ ላይ የሚጥሉ መመሪያዎችን አለማስተዋል ይከሰታል። የተሰጠንን ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ያለመመሪያ መሥራት ይመጣል፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የዕቃዎች መመሪያ ለሌሎች ነገሮችም ልምድ ይሆነናል፡፡ የምንጠጣውን የታሸገ ውሃ እንኳን የማዕድን ይዘቶችን ስንቶቻችን እናነባለን? እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ልጨምር፡፡
ከምኖርበት ቤት አጠገብ ካለ አንድ ሱቅ ውሃ እየገዛሁ ነው፡፡ የሶዲየም ይዘቱ መብዛት የለበትም ሲባል ስለምሰማ ሶዲየም እያየሁ ነው የምገዛ፡፡ እንደተለመደው የሶዲየም ይዘቱን ሳይ ‹‹ምንነቱን ነው የምታየው?›› አለችኝ፡፡ የሶዲየም ይዘቱን መሆኑን ስነግራት ተገረመች፤ ማንም እንደዚያ አይቶ እንደማያውቅ ነገረችኝ፡፡ የውሃውን ስም እንኳን ‹‹ይሄኛው ይሁንልን›› የሚሉት አብዛኞቹ በፕላስቲኩ ጥንካሬ እንጂ በውሃው ይዘት አይደለም፡፡ ይቺን እንኳን ትንሿን ነገር ልብ አንልም፡፡
እዚህ ላይ የአንድ ጋዜጠኛ ጓደኛዬን ተሞክሮ ብገልጽ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ ጋዜጠኛ የተጻፈ ነገር አያልፈውም።ካፌ ውስጥ ለተጠቀምነው ነገር ደረሰኝ ሲመጣ ከዋጋው ውጭ ያሉ ቃላትና ቁጥሮችን ሁሉ ያነባቸዋል፡፡ ብዙዎቻችን የምናነበው ድምር ዋጋውን ብቻ ነው፤ ግፋ ቢል ደግሞ ያልተጠቀምነውን ነገር እንዳይጨምሩ(ሆን ብለውም ሆነ ተሳስተው) የተጠቀምነውን ዝርዝር ነው የምናነበው፡፡ እሱ ግን ከላይ ከአናቱ ጀምሮ የንግድ ስሙን ሁሉ ነው፡፡
ለምንድነው ይህን ሁሉ የምታነበው ስንለው ‹‹የሙያ ቃላት አገላለጽ›› የሚለው አለው፡፡ ይሄ ማለት በየዘርፉ ያሉ የሙያ ቃላትን ማወቅ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ የንግድ፣ የህክምና፣ የወታደራዊ… በአጠቃላይ በምን ዘርፍ ምን አይነት አገላለጽ እንዳለ እየተማረ ነው የሚሄድ፡፡
አንዳንዱ ለመማሪያ ጭምር እዚህ ድረስ በትኩረት አድርጎ ሲያነብ አንዳንዶቻችን ግን የግዴታ የሆነውን እንኳን አናነብም! ይህን ልማዳችንን እንቅረፍ፤ መመሪያዎችን እናንብብ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2015