ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የዕጸ ጣዕም ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ምቹ የአየር ሁኔታና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ይታወቃል።ይህ እምቅ ሀብት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋ ተጥሎበት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ላይ እየተሰራም ይገኛል።ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ተጠቃሽ መሆን የቻለም ሲሆን፣ ከግብርና ምርቶች ከቡና በመቀጠል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ያለም ነው።
አገሪቷ ለዘርፉ ካላት ተፈጥሯዊ ሃብት በተጨማሪ የሆርቲካልቸር ዘርፍ አነስተኛ በሆነ ቦታ መልማት የሚችልና ሰፊ የእርሻ ቦታን የማይጠይቅ መሆኑ ደግሞ ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ።ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ አበባ አምርታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከጀመረች ከሁለት አስርት ዓመታት ያልበለጠ ዕድሜ ብቻ ያላት ብትሆንም፣ ባላት ዕምቅ ሃብት የተነሳ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡
አገሪቷ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንድትችል መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።የሆርቲካልቸር ዘርፍ በዋናነት ኤክስፖርት ላይ ያተኮረ በመሆኑ የገበያ መዳረሻ የሆኑ አገራት በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ምርቱ ተመርቶና ተዘጋጅቶ እንዲላክ ይሠራል።
ምርቱ በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፤ አብዛኞቹ አምራቾችም የውጭ አገር ባለሃብቶች ናቸው። በመሆኑም አምራችና ገዥ አገራትን በማገናኘት የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲቻል የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ማህበሩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም የተለያዩ ኤክስፖዎችን ማዘጋጀት አንዱ ነው።ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው ኤክስፖዎች አማካኝነትም አገሪቷ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሆነች ከማስተዋወቅ ባለፈ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል።በቅርቡም የሆርቲካልቸር ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ለስምንተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቶ እንደነበር ይታወሳል።ኤክስፖው ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን በማሳደግ እንዲሁም የተወዳዳሪነት አቅምን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው የኤክስፖው ተሳታፊዎች ይናገራሉ፡፡
ወጣት ጃለኔ አበበ የማርጅን አበባ ልማት የኢንቫይሮመንት ባለሙያ ናት።እሷ እንደምትለው፤ ማርጅን የአበባ ልማት የሆላንድ ዜግነት ባላቸው የውጭ ባለሃብት የተመሰረተ ሲሆን፤ ድርጅቱ በኬንያም ሰባት የአበባ እርሻ ቦታዎች አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሶስት የአበባ እርሻ ቦታዎች አሉት።
ማርጅን የሚያመርታቸው አበቦች ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ በመሆናቸው በውጭ ምንዛሬ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።ወጣት ጃለኔ የገበያ መዳረሻቸውን በተመለከተ በዋናነት ሆላንድ ላይ ተደራሽ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ላይም ተደራሽ እንደሆኑና ማርጅን አበባ በዓለም ገበያው እጅጉን ተፈላጊ እንደሆነ ነው ያስረዳችው።የማምረት አቅማቸውን በተመለከተም በዓመት ከ30 ሚሊዮን በላይ የአበባ ግንድ (ስቲም) ወደ ውጭ ገበያ እንደሚላክም ወጣት ጃለኔ አመላክታለች።
የሬድፎክስ ኢትዮጵያ አበባ ልማት ሲኒየር ኳሊቲ አሹራንስ ማናጀር አቶ ሞሲሳ ተፈሪ እንዳሉት፤ ሬድፎክስ ኢትዮጵያ ፔንሴቲያ እና ፔላርጎን የተባሉ ሁለት የአበባ ዝርያዎችን እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል።ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡት እነዚህ የአበባ ዝርያዎችም አራት ሴንቲሜትር ቁመትና ሶስት ቅጠል ብቻ እንዲኖራቸው ሆነው ይዘጋጃሉ።ለገበያ የሚቀርቡትም የአበባ ቁራጮቹ ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የአበባ እርሻው ከአዲስ አበባ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቆቃ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ 2500 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከልም አምስት በመቶ የሚያህሉት ባለሙያና በተመሳሳይ ሙያ ተመርቀው በዘርፉ ውስጥ ያሉ ናቸው።
ድርጅቱ ወደ ሥራው ከገባ 19 ዓመታትን ያስቆጠረና በዘርፉ ልምድ ማካበት የቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ መሰል ኤግዚቢሽኖችም ተሳታፊ በመሆን ምርቱን የማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር የቻለም መሆኑን ይገልጻሉ።ትልቁ ገበያቸው በኢንተርኔት እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
በሬድፎክስ ኢትዮጵያ የሚመረቱት አበቦች ሮዝ ከሚባለው የአበባ ዝርያ እንደሚለዩ በመጥቀስም፤ አበባውን ከማልማታቸው አስቀድመው የደንበኞችን ፍላጎት እንደሚቀበሉም አቶ ሞሲሳ ተናግረዋል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ገበያ መኖሩንም ይገልጸሉ።ዋናው መስሪያ ቤት ኔዘርላንድ ላይ ያለው በመሆኑ ገበያውን እዛ ያለው የማርኬቲንግ ባለሙያ ይቆጣጠረዋል ያሉት አቶ ሞሲሳ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ደግሞ አምርቶ መላክ ብቻ እንደሚጠበቅበትና የገበያ ችግር እንደሌለም ይናገራሉ።
በዓለም አቀፍ ገበያ በስፋት የሚታወቀው ሬድፎክስ ኢትዮጵያ አበባ አምራች አሜሪካና ካናዳ በየዓመቱ ሰፊ ገበያ ያለው ነው።በተጨማሪም አውሮፓ ላይ ብዙ ቦታዎች ላይ የአበባ ምርቶቹን ይሸጣሉ።በኤክስፖርት ላይ ያተኮረው የሆርቲካልቸር ዘርፍ ሻጭና ገዢም ቢሆን በውጭው ዓለም እንደሆነ ይታወቃል።
ዘርፉ ትልቅ ገበያን የሚፈልግ እንደመሆኑ ዕድሜ ጠገብ ገበያ ያለው ስለመሆኑ በኤግዚቢሽኑ ያገኘናት ወይዘሪት ሳባ ሰይድ አጫውታናለች።መቶ ዓመት ባስቆጠረው ሮያል ፍሎራ ሆላንድ ገበያ አካውንት ማናጀር በመሆን የምታገለግለው ሳባ፤ ሮያል ፍሎራ ሆላንድ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ዓለም አቀፍ የሆነ ትልቁ ገበያ እንደሆነ ትናገራለች።
እሷ እንዳለችው፤ ዓለም አቀፉ ሮያል ፍሎራ ሆላንድ ኩባንያ አምራችና ገዢዎችን የሚያገናኝ እንደ ህብረት ሥራ አይነት ነው።ትልቅ የገበያ ቦታ ነው።ይህ ገበያም ዓለም አቀፍ ገዢዎችና ዓለም አቀፍ ሻጮችን የሚያገናኝ የገበያ ቦታ ነው።ዕድሜ ጠገቡ የገበያ ቦታ በአፍሪካ ዋናው ቢሮ ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ቢሮ አለው።በአሁኑ ወቅትም ገዢና ሻጭ በቀላሉና በፍጥነት መገናኘትና መገበያየት የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት እየሠራ ነው።
በዓለም ላይ ያሉ አበባ አምራቾችን እና አበባ ገዢዎችን በማገናኘት የሚሠራው ሮያል ፍሎራ ሆላንድ፣ በዘረጋው የገበያ ስርዓት በየትኛውም ዓለም ያለ ማንኛውም አበባ ገዢ በዲጅታል ሲስተም ባለበት ሆኖ አበባውን መግዛት ይችላል።ለተመረተው ለእያንዳንዱ አበባ እንደ አይነቱ የዋጋ ተመን ይቆረጥለታል።የገበያ ሂደቱም በቀጥታ መግዛትን ጨምሮ በጨረታ የሚሸጥ ይሆናል።በዚህም አምራቹም ሆነ ገዢው ባለበት ሆኖ መገበያየት ይችላል።
ሮያል ፍሎራ ሆላንድ ዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አበባ አምራቾች 70 በመቶ ከሚሆኑት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሆነ የጠቀሰችው ሳባ፤ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላትም ትናገራለች። ዓለም አቀፍ የገበያ ቦታ የሆነው ሮያል ፍሎራ ሆላንድ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀሉም በዚሁ ምክንያት ነው ትላለች።በሆርቲካልቸር ማለትም አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ኬንያ ከዓለም ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሳ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ፣ ኢኳዶር ደግሞ ሶስተኛ እንደሆነች ነው የገለጸችው፡፡
ኢትዮጵያ ጥራት ያለውና የተለያዩ የአበባ ዝርያዎችን አምርታ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን ጠቅሳ፣ አገሪቱ ከዚህ በበለጠ ዕምቅና ጥልቅ የሆነ አቅም እንዳላት ነው ሳባ የጠቀሰችው።ኬንያውያን ቀድመው ወደ ዘርፉ በመግባታቸው የቀዳሚነቱን ቦታ እንደያዙ ነው ያስረዳችው።
ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ እንዳላት በመጥቀስም፣ ከዚህ በበለጠ መሥራት የሚጠበቅባት እንደሆነ ገልጻለች።ከማምረት ባለፈ እንዲህ ባሉ ኤክስፖዎች ምርቶችን ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር በመፍጠር ዓለም አቀፍ ገበያውን ይበልጥ በማስፋት አገሪቷ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን እንድትጠቀም ማድረግ ይገባል ብላለች።
የሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ለስምንተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የሆርቲካልቸር ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ሁለት ዓላማዎችን ይዞ መዘጋጀቱን ይናገራሉ።የመጀመሪያው በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያለውን የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ገዢዎችና አምራቾችን እንዲሁም በዘር የተለያየ አበርክቶ ያላቸውን አካላት ማገናኘት ነው ይላሉ።ይህም እጅግ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቅ እንደቻለ ነው ያስረዱት፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ከ30 በላይ አገራት ወደ አገር ውስጥ መጥተው የኤክስፖው ተሳታፊ መሆን ችለዋል።አምራችና ገዢውን ጨምሮ ግብዓት አቅራቢዎች፣ የሎጅስቲክስ አቅራቢ ኩባንያዎችና የተለያየ አገልግሎት አቅራቢዎች በኤክስፖው መገናኘት መቻላቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም እጅግ ውጤታማ የሆነ ስምምነት ማድረጋቸውንና ይህም ለዘርፉ ዕድገት የሚኖረው አበርክቶ የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ማህበሩ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላትን ዕምቅ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያስተዋውቅ እንደቆየ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።አያይዘውም ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ማለትም አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ እምቅ አቅም እንዳላት አስታውቀው፣ ይህን እምቅ አቅም ደግሞ ትርጉም ወዳለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።ለዚህም ኢንቨስትመንቱ እንደሚያስፈልግ፣ በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎች መፈታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አቶ ቴዎድሮስ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ኤክስፖ በየሁለት ዓመቱ ይካሄድ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤክስፖው ውጤታማ በመሆኑ በቀጣይ በየዓመቱ ለማድረግ ማህበሩ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።በአበባ ምርት ብቻ ሳይሆን በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በዕጸጣዕም ምርትም እንዲሁ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሰራ አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከአበባ በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬን እንዲሁም ዕጸጣዕምን የሚጨምር ቢሆንም በስፋት ተመርቶ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው የአበባ ምርት ነው።ይሁንና ካለፉት ዓመታት ይልቅ በዘንድሮ ዓመት የተሻለ የአትክልት፣ ፍራፍሬና ዕጸጣዕም ምርት ተገኝቷል።በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ዕጸጣዕምን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ ብቻ ትልቅ ኤክስፖ ይዘጋጃል።
የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ ቢመጡ ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውን ይጠቅማሉ፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ የውጭ ምንዛሬን ማምጣት ይችላሉ።የተለያዩ የፖሊሲዎች አሉ።በተለይም ለዘርፉ የተሰጡ የኢንቨስትምት ማበረታቻዎች አሉ።እነዚህም በልማት ባንክና በሌሎች ባንኮች በኩል እየተቀረጹ ነው።ይህም የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ በስፋት ቢሰማሩ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም