የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን በተለይም የመንግሥት ሠራተኞችን ሕይወት ፈታኝ ካደረጉ ጉዳዮች ግንባር ቀደሙ የመኖሪያ ቤት ችግር ነው።የቤት ኪራይ የከተማዋን ኢኮኖሚ እስከመዘወር፣ በከተማዋ የመኖር እና ያለመኖር ሁኔታን እስከመወሰን እንደደረሰ ሁላችንም የታዘብነው ሐቅ ነው።
መጠለያ ምግብና ልብስ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ናቸው፡፡ በድሮው አስተሳሰብ አንድ ሰው መኖሪያ ቤት አለው ሲባል ከሶስቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱን አሟልቷል የሚል ትርጉም ይሰጠው ነበር፡፡ አሁን ግን አንድ ሰው በተለይም ሰፋ ባለ ከተማ ውስጥ ቤት አለው ከተባለ የሚሰጠው ትርጉም ማረፊያውን ወይም መውደቂውን አመቻችቷል ከሚለው ይልቅ ኢኮኖሚ አፍርቷል ወደሚለው ያመዝናል።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በሚሊዮኖች ደረጃ የሚከራዩ የንግድ ቤቶች አሉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚያከራዩ መኖሪያ ቤቶችም ይገኛሉ። በቤት ኪራይ የሚተዳደረው ሰው በደመወዝ ከሚተዳደረው ሰው የማይተናነስ መሆኑን የምንረዳው አብዛኛው ደመወዝተኛ በአከራዮች ቤት የሚኖር በመሆኑ ነው፡፡
በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ባይሆንም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ የሚዘዋወረው ኢኮኖሚ ከሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛው ደመወዝ ጋር ሲነጻጻር የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይመስልም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑን በየአካባቢው ተገንብተው ለንግድ ሥራ የሚከራዩት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች፣ ለመኖሪያነት የሚከራዩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ በየመንደሩ እየተከራዩ ያሉ ቪላ ቤቶችና ትንንሽ ክፍሎች ናቸው።
በዚህ የተነሳ መኖሪያ ቤት ባላቸው እና በሌላቸው ነዋሪዎች መካከል ያለው የኑሮ ደረጃ የሰማይና የመሬት ያህል ተራርቋል፡፡ በከተማዋ የሚስተዋለው የቤት ኪራይ ውድነት ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ ከሚመጣው የሸቀጦች ዋጋ ጋር ተዳምሮ ነዋሪውን ግራ ማጋባቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች ዋጋ በጨመረ ቁጥር ቤት አከራዮች በዚያ በኩል ያወጡትን ወጪ በዚህ በኩል ለማካካስ ሲሉ በሚያከራዩት ቤት ላይ ዋጋ መቆለልን እንደ ትክክለኛ መፍትሔ እየተመለከቱ የቤት ኪራይ ዋጋን ሰማይ አድርሰውታል።
እዚህ ጋር አንድ እውነት አለ፡፡ በዓለም አቀፍም ይሁን በአገር አቀፍ ተለዋዋጭ ምክንያቶች የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ ሊጨምር ይችላል፡፡ እነዚህን ለዕለት ፍጆታ የምንጠቀማቸውን ሸቀጦች መግዛት የወዴታ ግዴታ ስለሚሆንብን እየተቸገርንም ቢሆን በተባለው ዋጋ ከመግዛት ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖረንም፡፡ ከዚህ አንጻር የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ምክንያታዊ ነው ሊባል ይችላል፡፡
የሸቀጦች ዋጋ በጨመረ ቁጥር አከራዮች ያንን ለማካካስ በቤት ተከራዮች ላይ የሚጭኑት ጭማሪ ግን ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ለምን ቢባል የዋጋ ንረቱ በአከራዩም በተከራዩም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ ቤት አከራዮች በሸቀጦች ላይ ዋጋ በተጨመረ ቁጥር እነርሱም በፊናቸው በሚያከራዩት ቤት ላይ ዋጋ እየጨመሩ የሕዝቡን ኑሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማድረጋቸው ተገቢነት የለውም።
ቤት አከራዮች፣ ነጋዴዎች እና አገልግሎት ሰጪዎች አንዳንድ ጊዜ በምክንያት አንዳንድ ጊዜም ያለበቂ ምክንያት በሚያደርጉት ረፍት የሌለው የዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰነዘረው ዱላ የሚያርፍበት ደግሞ የወር ደመወዝ ጠብቆ በሚኖረው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ ላይ ነው።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አንዲት ሶስት በአራት የሆነች ክፍል በአማካይ ከአራት እስከ አምስት ሺህ ብር ትከራያለች፡፡ አንድ ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት (እንደ የቦታው ሁኔታ ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ) ከአስር እስከ አስራ ሁለት ሺህ ብር ይከራያል፡፡
አንድ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በሥራ ዓለም የተሰማራ ጀማሪ የሲቪል ሰርቪስ ደመወዝተኛ ደግሞ በአማካይ ከሶስት እስከ አምስት ሺህ ብር ሲከፈለው ነባር ሰራተኛ የሚባለውም ደመወዙ ከአስር እስከ አስራ አራት ሺህ ብር የሚበልጥ አይደለም፡፡
እንግዲህ ደመወዝና የቤት ኪራይ ዋጋ ባልተመጣጠኑባት አዲስ አበባ ከተማ በተለይም መኖሪያ ቤት የሌላቸው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ምኑን ከምን እያደረጉ እንደሚኖሩ ሲታሰብ ያሳቅቃል።በዚህም ላይ የምግብ፣ የልጆች ትምህርት፣ የአልባሳት፣ የህክምና፣ የትራንስፖርት ወዘተ ወጪዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ።
የሶስት ወርና የአምስት ወር ቅድመ ክፍያ በአንድ ጊዜ ተጠቃሎ እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ አንዳንድ ልበ ደንዳና አከራዮች መኖራቸውም አይረሳም፡፡ ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ ቤት እንዲለቁ የሚገደዱት፤ ጓዛቸውን ጭነው ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት የሚንከራተቱትን እና ለጫኝ እና አውራጆች ሲሳይ የሚሆኑትን ደግሞ ቤቱ ይቁጥራቸው።
መንግሥት የመዲናዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ከግምት በማስገባት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገነብቶ ጥያቄዎችን በተወሰነ መልኩ ለመመለስ ባይሞክር ኖሮ ችግሩ ዛሬ ከምናየውም በላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መረዳት አይከብድም፡፡
ከዚህ ጋር ማንሳት የሚገባን ቁም ነገር አለ። በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በርካታ ባለእድለኞችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ቤቶቹ በችግር ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችን ምን ያህል ተጠቃሚ አድርገዋል ከተባለ ግን አጠያያቂ ነው።
የሚገርመው በርካታ ችግረኞች እያሉ የራሳ ቸውን ሕይወት ያልመሰረቱና በቤተሰብ ጥገኝነት ስር ያሉ ወጣቶች ሳይቀሩ የእድሉ ተጠቃሚዎች መሆን ችለዋል፡፡ በሆነ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማን መታወቂያ አውጥተው የተመዘገቡና ነዋሪነታቸው ሌላ አገር የሆኑ አካላትም የቤት እድለኛ ሆነዋል፡፡
እንደማንኛውም ዜጋ የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው አይከፋም ግን በአንገብጋቢ ችግር ውስጥ ያሉ፣ በርካታ ቤተሰብ ይዘው የሚንከራተቱ ፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው፣ ብዙ ዓመታትን አገራቸውን ያገለገሉ አቅመ ደካሞች እያሉ ሌሎች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው ብዙ አያሳምንም።
በግል አስተያየቴ ቤት እንደሎተሪ እድለኛ ይድረሰው ተብሎ የሚታደል መሆን የለበትም፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ቁልጭ ብለው የሚታዩ የኑሮ እና የአኗኗር ደረጃን ፣ የሥራ ሁኔታን ፣ የቤተሰብ ብዛትን፣ እድሜና የአገልግሎት ዘመንን ወዘተ ከግምት ያስገባ ቢሆን ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል።
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ የሚኖሩ የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ አዲስ መርሃ-ግብር አስተዋውቋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛውን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከነደፋቸው የተለያዩ አማራጮች አንዱ የማህበር ቤት ነው።
የመንግሥት ሠራተኞች በማህበር ተደራጅተው አቅማቸው በሚፈቅደው ልክ እየቆጠቡ በአጭር ጊዜ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ አሠራር ቤትን እንደሎተሪ በእድል ከመስጠት ይልቅ በትክክል የከፋ ችግር ያለባቸው የመንግሥት ሠራተኞችን ታላሚ ያደረገ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም