በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተደነገገውን የሰዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሀገራችን ኢትዮጵያ የተቀበለችውና በህገ መንግስቷም ያረጋገጠቸው ነው፡፡ በዚሁ መሰረትም ዜጎች ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ያከናውናሉ።
ከዚሁ በተቃራኒ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው እና ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱትም ዜጎች አሉ፡፡ በተለይም ወደመካከለኛው ምስራቅ ሳዑዲ አረቢያ፤ ሊባኖስ፤ ኩዌት፤ ሶርያ፤ የተባበሩት አረብ ኢም ሬት የሚጓዙ ቁጥ ራቸው ከፍተኛ እንደ ሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በህገ ወጥ ስደት ምክንያት ደግሞ ዜጎችን ለመከራና ስቃይ ይዳርጋል፡፡ ክብርንና ሕሊናን የሚያዋርድ መከራን ከመቀበል ጀምሮ እስር፣ እንግልትን፣ የጉልበት ብዝበዛ፤ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት፤ አስገድዶ መደፈር፤ ሞትን ጭምር መጋፈጥን የሚጠይቅ ነው።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከኢትዮጵያ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በህገወጥ መልኩ ከሀገር ይወጣሉ፡፡ አብዛኞቹም ስደተኞች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁና ከገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል የሚፈልሱ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በህገ ወጥ ደላሎች ፤ ‹‹የተሻለ ሕይወት፤ ስራና ኑሮ ታገኛላችሁ›› በሚሉ ተታልለው ለህገ ወጥ ስደት የተዳረጉ ናቸው፡፡
እነዚህ ዜጎች በየደረሱባቸው ሀገራት ሰብዓዊ ክብራቸው ከመነካቱም በላይ በርካታ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ አካል መጉደል፤ መደፈር፤ የመጓጓዣ ሰነዶች መነጠቅና ባልተገባ መልኩ በጠባብ ክፍል ውስጥ መታጎር/መታሰር የመሳሰሉት አስከፊ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል፡፡ የተፈጸሙባቸውን አሰቃቂ ድርጊቶች አሳውቆ ፍትህ ማግኘት እንኳን የሚታሰብ አይደለም፡፡
ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ሰው ተኮር ስራ እየሰራ ያለው እና በውጭ ግንኙነት ስራውም ለዜጎች ክብር ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራው የኢትዮጵያ መንግስትም እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባትና የዜጎቹን ዋስትና ለማረጋገጥ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ እና ባለሙያዎችን በማሰማራት ጭምር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡ በተለያዩ ጊዜዎችም ዜጎችን ከዚህ ችግር እንዲወጡ ያስቻላቸውን ርምጃ ወስዷል፡፡ በቅርቡም ዜጎችን በስደት ከሚደርስባቸው ችግር ለመታደግ በወሰደው ርምጃም ከፍ ያለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በተለይም ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው በሳውዲ ዓረቢያ በእስር ላይና በማቆያ ቦታዎች በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ያደረገው ጥረት እጅግ ፈታኝ ቢሆንም፤ ውጤቱ ግን ለዜጎች ያለውን ክብር በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
መንግስት መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ሕገ ወጥ ስደተኞችን የመመለሱ ተግባር ሲጀመር በሳውዲ ዓረቢያ በእስርና በማቆያ ጣቢያዎች የሚገኙ 102ሺ ዜጎችን ለመመለስ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ሰሞኑን ይፋ በሆነው መረጃ ግን ከ131 ሺህ በላይ ዜጎች ወደአገራቸው መመለስ ተችሏል።
እነዚህ ዜጎች በተለይ በማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ ለበርካታ እንግልትና ስቃይ ተዳርገው የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ ብዙዎችም ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት ገንዘብ ጭምር የሌላቸው መሆናቸው የነበሩበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የመመለሱን ስራ አስቸጋሪና ከፍ ያለ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ያደረገ ነበር፡፡
መንግስት የሁኔታውን አስከፊነትና የሚጠይቀውን ቁርጠኝነት በአግባቡ በመረዳት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን 16 መንግስታዊ ተቋማት በማስተባበር፤ ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በ131ሺ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ አድርጓል። ከሳውዲ አረቢያ በተጨማሪም በተለያዩ አገራት በተመሳሳይ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ስምንት ሺ ዜጎችን የመመለስ ሥራም አከናውኗል፡፡
መንግስት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ያከናወነው ይህ ተግባር ለዜጎቹ እና ለሀገር ያለውን ከፍተኛ ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ፤ ለዜጎቹ ከሚቆረቆር አንድ መንግስት የሚጠበቅ፣ ሊበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ፤ ከዛም በላይ የሚደነቅ ተግባር ነው፡፡
በተለይም ከለውጡ ወዲህ በተዘረጋው ዜጋ ተኮር ፖሊስ አማካኝነት እየተከናወነ ያለው ስራ የዜጎችን በሕይወት የመኖር ዋስትና ጭምር እያረጋገጠ የሚገኝ በመሆኑ፤ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ለመታደግ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ በቀጣይም ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም