አሁን አሁን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መረጃን በፍጥነትና በጥራት መለዋወጥ የተለመደ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም ለመንግሥት ተቋማት ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት በመስጠት በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። ከመንግሥት ተቋማት መካከልም ከፍተኛ መጠን ያለውን የመንግሥት ገንዘብ ለሚያንቀሳቅሰው የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመንግሥት የግዥ ስርዓትን በኤሌክትሮኒክስ ማከናወን በመቻሉ የፌዴራል ተቋማት ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ከማግኘታቸው ባለፈ የግዢ ስርዓቱ ከሙስና የጸዳ እንዲሆን በማስቻል የአገር ኢኮኖሚን ከብክነት እየታደገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ የፌዴራል ተቋማት የፋይናንስ ግዥ ስርዓታቸውን በኤሌክትሮኒክስ መፈጸም በመቻላቸው ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ከሙስና የጸዳ ሥራ በመሥራት በኩል ለውጦች እያመጡ እንደሚገኙ መረዳት ተችሏል።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን እንዳስታወቀው 74 የሚደርሱ የፌዴራል ተቋማት የመንግሥት ግዥ ስርዓትን በኤሌክትሮኒክስ ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል። ይህን ስርዓት በመተግበር አራት የፌዴራል ተቋማት የተሻለ አፈፃፀም ማሳየታቸው ተጠቁሟል፤ እነሱም የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ከእነዚህ አራት የፌዴራል ተቋማት መካከልም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ተሞክሮዎቻቸውን በውይይት አቅርበዋል።
ኢ-ጂፒ የመንግሥትን ግዢ በቴክኖሎጂ አስደግፎ ዲጅታላይዝድ በማድረግ፤ አጠቃላይ ግዢ ሲፈጸም በኦን ላይን መፈጸም ማለት መሆኑን ያስረዱት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የግዢና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈጠነ ናቸው። ፍርድ ቤቱ፤ ኢ-ጂፒን ተቀብሎ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት እንደቻለና በዚህም ተጠቃሚ መሆኑን አቶ ሰለሞን ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዳኝነት አገልግሎትን በአግባቡ በመደገፍና በማሳለጥ አገልግሎት ፈላጊውን ማርካት የሚል ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው።
ተቋሙ በራሱ ተነሳሽነት የመንግሥት ግዢን በኤሌክትሮኒክስ ለማድረግ ወደ ሲስተሙ ገብቷል። በዚህም ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለና አገልግሎቱም ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ምቹ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል። በተለይም ለዳኝነት አገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በተገቢው ጊዜ በጥራትና በመጠን መድረስ እንዲችሉ በማድረግ ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር እና የአጠቃቀም ስርጭትን አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሰራሩ ዕቅድን መሰረት ያደረገ የግዢና ንብረት አጠቃቀም ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ያደርገዋል። በሲስተሙ ያላለፈና ከዕቅድ ውጭ የሆነ ማንኛውም አይነት ግዢ በኢ-ጂፒ አይፈጸምም። በመሆኑም ኢ-ጂፒ አስቀድሞ ማቀድን የሚያስገድድ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በተቋሙ ውስጥ በዘፈቀደ የሚገዛ ግዢ በከፍተኛ መጠን መቀነስ ችሏል። ማንኛውም ጥያቄ ሲስተም ውስጥ ከሌለ ኢ-ጂፒ በፍጹም ሊያስተናግደው አይችልም፤ ይህም በእጅጉ ተመራጭ አድርጎታል።
ኢ-ጂፒ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር በተለይም የዘርፉን አደረጃጀት፣ የአሰራር ውጤታማነት ለማሻሻልና ለማዘመን አይነተኛ ድርሻ እንዳለውም ነው የተናገሩት። በዚህም ኪራይ ሰብሳቢነትን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም መቀነስና ማቀጨጭ መቻሉን ያነሱት አቶ ሰለሞን፤ ይህም በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለ ነው የተናገሩት።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት የግዢ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደቻለ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ በተለይም የተቋሙን የግዢና ንብረት ዕቅድ ለማዘጋጀት ያለው አቅም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል። በዚህም ተቋሙ ዲጂታል የግዢና ንብረት አስተዳደር የአሰራር ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው፣ ይህም በተግባር የሚታይ እንደሆነ ነው ያስረዱት። በአሁኑ ወቅትም ከሲስተም ውጭ የሚገዛ ንብረት በተቋሙ እንደሌለ ጠቅሰው፣ ዕቃ ሲገዛም ሆነ ሲወጣ በሲስተሙ አማካኝነት ግልጽ በሆነ መንገድ ነው ይላሉ።
በተቋሙ የግዢ ስርዓት ላይ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በ2013/14 ዓ.ም ጥናት ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፤ በዚህም ከጥቂት ጉድለቶች በስተቀር አበረታች ውጤት ማምጣት የቻለ ተቋም መሆኑን ማመላከቱን ተናግረዋል። ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ኢፍሚስ እና ኢ-ጂፒን መጠቀም በመቻሉ በግዢ ስርዓቱ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት ችሏል። በተለይም ባለሙያዎች በግዢ ዘዴ መረጣ ላይ ያላቸው ዕውቀት በመጨመሩ ሥራውን በሚገባ መሥራት የሚችሉ ባለብቁ ባለሙያዎች አድርጓቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።
ባለሙያዎቹ የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት፣ በመገምገምና በመተንተን አጠቃላይ የግዢ ስርዓቱ ደረጃውን ያሟላ መሆን እንዲችል አድርገዋል። በዘርፉ የግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅ፣ መመሪያ፣ የጨረታ ሰነዶች፣ የአሰራር ሥርዓቶችን በማሻሻል ዓለም ወደ ደረሰበት የዲጅታላይዜሽን ወይም ኢፍሚስ፣ ኢ-ጂፒ፣ ኢገቨርመንት የሚባሉ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ በቀጣይም ፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታዩ በርካታ ችግሮችን መቅረፍና የገጽታ ግንባታውን መቀየር የሚቻለው በአገር ልጆች የለማውን ኢ-ጂፒ ቴክኖሎጂን መጠቀም ሲቻል ነው ብለዋል።
በተለይም ፈጣንና ጥራት ያለው እንዲሁም ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት የጀርባ አጥንት የሆነውና ትልቁ የአገሪቷ በጀት የሚውለው ግዢ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ግዥ ላይ መሥራት አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአፍሪካ 13 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር ለግዢ ብቻ ወጪ የሚደረግ መሆኑን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ይህን ከፍተኛ የአገሪቷን ወጪ የሚጠይቀውን ግዢ በአግባቡ፣ በስርዓትና በዕቅድ ለመመራት በቴክኖሎጂ መደገፍ የግድ ነው ይላሉ። ያ ካልሆነ ግን የሚመጣው ኪሳራ ከባድ መሆኑን ጠቁመው፣ በመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ስርዓት ያልገቡ የፌዴራል ተቋማት በፍጥነት ወደ ሲስተሙ ገብተው ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር አገሪቷን ከሀብት ብክነት መታደግ እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የግዢና ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ማሞ አሸብር በበኩላቸው የባለስልጣኑ ዋና ሥራ ቅርሶችን መመዝገብ፣ መጠበቅ፣ መንከባከብና ለትውልድ ማስተላለፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ተግባራዊ ለማደረግም በቴክኖሎጂ የታገዘና ቀልጣፋ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ወሳኝ ነው ይላሉ። ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልጽ የሆነ የአሠራር ስርዓትን መከተል የሚያስችለው የኢ-ጂፒ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ባለስልጣኑ ሥራውን እያሳለጠ እንደሆነም አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የተቋሙን የግዢ ስርዓት ቀልጣፋና ፈጣን ከሰው ንክኪ ነጻ ለማድረግ የመጀመሪያው ሥራ የዕቅድ ዝግጅት ነው። ከዕቅድ ዝግጅት ውጭ የሚደረግ ግዢ አይኖርም። ይሁንና ከዚህ ቀደም በነበረው የአሰራር ስርዓት ከዕቅድ ውጭ በሆነ መንገድ የተለያዩ ግዢዎች በዘፈቀደ ይከናወኑ ነበር። በመሆኑም ዛሬ አንዱ ዳይሬክተር አንድ ነገር እንዲገዛለት ይጠይቃል። ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ ሌላው የፈለገውን ዕቃ የሚያስገዛበት ሂደት ነበር። ይህም የሀብት ብክነትን ከማስከተሉም ባለፈ ለከፍተኛ ኪራይ ሰብሳቢነት ሲዳርግ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ግዢ የሚከናወነው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢ-ጂፒን ተግባራዊ በማድረግ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። ኢ-ጂፒ ደግሞ በዕቅድ ያልተያዘና ያልታቀደ ግዢን የማይቀበል በመሆኑ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የመንግሥት ግዢው በኢ-ጂፒ እንደሚከናወን ይናገራሉ። በቅድሚያ በተቋሙ ውስጥ ያሉ የሥራ ክፍሎችን በሙሉ በየዘርፉ በመከፋፈል ስለትክክለኛነቱ በማጥራት ለግዢ ኮሚቴ እንደሚቀርብ፣ የቀረበው የግዢ ፍላጎትና የሥራ ክፍሎቹ ትክክለኛ ስለመሆናቸውም በኃላፊዎች እንደሚረጋገጥ ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ቅርስን ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ለሚያከናውናቸው ተግባራት አሸዋ፣ ድንጋይና አፈር ሳይቀር ይገዛል። ይሁንና እነዚህ ግብዓቶች ከዚህ ቀደም በማኑዋል ሲገዙ የነበረ ሲሆን፤ የግዢ ስርዓቱም ለከፍተኛ የሀብት ብክነትና ለብልሹ አሰራር ተጋልጦ ነበር።
በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ግብዓቶች በመንግሥት የግዢ ስርዓት ውስጥ መካተታቸውን ጠቅሰው፣ ማንኛውንም ግዢ በኢ-ጂፒ መግዛት እንደሚቻል መረጋገጡን ተናግረዋል። ወደ ሥራው በመግባት ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኢ-ጂፒ ሲስተምን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ በዘርፉ ያካበተውን መልካም ተሞክሮ ለሌሎች ተቋማት እያካፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኢ-ጂፒን ተግባራዊ ሲያደርግ የተለያዩ ፈታኝ የሚባሉ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር ያነሱት አቶ ማሞ፤ ነገር ግን ችግሮቹን ያለመታከት የማንዋሉን የግዢ ዘዴ ለማስቀረት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የኢ-ጂፒ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ እንደቻሉ ነው ያስረዱት።
የመንግሥት ሥራን ለመሥራት አንዱና ዋነኛው ክንፍ ግዢ እንደሆነ የገለጹት የፌዴራል ግዢ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወልደአብ ደምሴ፤ በበኩላቸው ከግዢ ውጭ የሚሠራ ሥራ የሌለ መሆኑን ይናገራሉ። ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርሰው የመንግሥት ገንዘብ ለመንግሥት ሥራ የሚውል መሆኑን ያመለክታሉ። ለመንግሥት ሥራ የጀርባ አጥንት የሆነው የመንግሥት ግዢ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓትን ተከትሎ እንዲሰራ የሚደረገው ጥረት የመንግሥትና የሕዝብን ሀብት ከብክነት ከመታደግ ባለፈ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ያስችላል። የመንግሥት ግዢን በቴክኖሎጂ ሲታገዝና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን ሙሉ ለሙሉ ሲከተል በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ድርሻ የጎላ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ግዢ የሚፈጸምባቸው የአሰራር ስርዓቶች አሉ። ከእነዚህ የአሰራር ስርዓቶች አንዱ ግልጸኝነት ነው። ግልጸኝነቱ የሚረጋገጠውም አራተኛው መንግሥት ተብሎ በሚታወቀው በሚዲያው በመሆኑ በተለይም ሚዲያው ግዢ ላይ የሚታዩ ለውጦችን ወደ ሕዝቡ በማድረስ በኩል ጉልህ ድርሻ አለው። ስለሆነም ሚዲያው እንደ አራተኛ መንግሥትነቱ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ መደገፍና ማጋለጥ ይጠበቅበታልም ብለዋል።
የመንግሥትን ግዢ በቴክኖሎጂ አስደግፎ ዲጂታላይዝድ በማድረግ ግዢ ሲፈጸም በኦን ላይን መፈጸም ከተቻለ በመልካም አስተዳደር በኩል ያለውን ከፍተኛ ችግር ማቃለል እንደሚቻልም አስታውቀዋል። የመንግሥት ግዢን በኢ-ጂፒ መተግበር ያስፈለገበት አንዱ ዓላማም መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ለሚወጣው ወጪ ተመጣጣኝ ውጤት ማስገኘትና ለአገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ድጋፍ ማድረግ ነው ይላሉ።
መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ዋነኛ የሥራ ዘርፎች አንዱ የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት በመተግበር ከአፍሪካ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኑን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት አሁን ላይ 74 የፌዴራል ተቋማት የፋይናንስ ግዥ ስርዓታቸውን በኤሌክትሮኒክስ መፈፀም ችለዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 726 ጨረታዎች በኤሌክትሮኒክስ ተፈጽመዋል። ጨረታዎችን ለመሳተፍ ከክልል ከተሞች ወይም ከሌሎች አገራት የሚደረገውን ጉዞ በማስቀረት ዜጎች የሥራ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ወጪያቸውን ማዳን ችለዋል። ከሁሉም በላይ በዘርፉ የሚካሄደውን የሙስና ሰንሰለት ቆርጦ መጣል ያስቻለ እንደሆነም ተገልጿል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም