ለሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ የሕብራዊት ገጿ የሆኑት ሕዝቦቿ በአንድም በሌላ መልኩ የሚያስተሳስሯቸው አያሌ ጉዳዮች አሏቸው:: የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የአመለካከትና ሌሎችም የበዙ ማንነቶች ያላቸውን ያህል፤ በቋንቋ ያልተገደበ፣ በሃይማኖት ያልተከለለ፣ በባህል ያልተጋረደ፣ በነገድ ያልታጠረ፣ በጥቅሉ የበዙ ልዩነቶቹ አጥር ያልሰሩበት፣ ወሰን ያላበጁበት የእርስ በእርስ መስተጋብርና የጠነከረ አንድነትን የፈጠሩ ሕዝቦች ናቸው::
ኢትዮጵያዊነት በአማራነት፣ በኦሮሞነት፣ በትግሬነት፣ በሶማሌነት፣ በአፋርነት፣ በወላይታነት፣… ተለክቶ የሚቀርብ ሳይሆን፤ አማራው ከትግሬው፣ ኦሮሞው ከሶማሌው፣ አፋሩ ከአማራው፣ ወላይታው ከሲዳማው፣ በሕብር ተደምሮ በአንድነት የሚደምቅበት ሕያው የማንነት ሰገነት ነው:: በዚህ ሰገነት ላይ የሚገለጡ ኢትዮጵያውያንም ተናጥላዊ ማንነታቸው ሳይሆን ሕብረ ብሔራዊ መጠሪያቸው፤ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና ሌሎችም ወሰን አላባ የጋራ ማንነቶቻቸው ገዝፎ የሚስተዋልባቸው ናቸው::
“ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን እልፍ ጉዳዮች አሉን” እንዲል ብሂሉ፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም ዛሬ ላይ ሊያለያዩን እና ላያግባቡን የሚችሉ መስለው ገዝፈው የሚታዩን አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ ቢታሰብም፤ እውነቱ ግን በትናንት ሂደት፣ በዛሬ ኑረትና በነገ ተስፋችን ውስጥ ገናን የሆኑ አብሮነቶች፣ ሃያል የሆኑ መስተጋብሮች፣ ወሰን አልባ የጋራ ተስፋዎች ባለቤቶች መሆናችን ነው::
ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ቡድኖች የሴራ መስመር ሳይፈቱ፤ በጥቅመኞች የከፋፋይነት አጀንዳ ሳይጠለፉና እጅ ሳይሰጡ፤ በለውጥ ለበስ ነውጥ አራማጆች ነፍጥ እንዲማዘዙ ሲደረግ እንኳን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ቂምና ቁርሾን ከመቋጠር ይልቅ የአብሮነታቸው ገጽ በዝቶ ሲገለጽ የሚስተዋለው:: ለዚህ ደግሞ ለጠብና ቁርሿቸው ይቅርታና እርቅን ያበጁ፤ ለዘላቂ ሰላማና አብሮነታቸው ካሳና የላቀ መተሳሰርን ያሰናዱ ሕዝቦች መሆናቸውን በተግባር እየገለጡ ከትናንት ዛሬ ደርሰዋል፤ ከዛሬ ተሻግረው ነገን በአብሮነት ለመዝለቅ ቃልኪዳን አስረዋል::
ይሁን እንጂ ይሄ የሕዝቦች አብሮነት እና ጠንካራ ትስርስ በየዘመናቱ በተለያዩ ምክንያቶች መፈተኑ አልቀረም:: ለምሳሌ፣ በቅርቡ የተካሄደው በሰሜኑ ጦርነት በተለይ የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ላይ በትሩን ያሳረፈ እንደመሆኑ፤ በእነዚህ አከባቢ ያሉ ሕዝቦች ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ በማህበራዊ እና ሕዝባዊ መስተጋብሮች ላይ ማሳረፉ አይቀሬ ነው:: ይህ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያው እና መለያየትን ሰባኪ በሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች እሳት ቆስቋሽነት ሲታገዝ በህዝቦች መካከል መለያየትና ጸብን የመፍጠር አቅሙ ከፍ ያለ ነው::
ነገር ግን የእነዚህ ሕዝቦች አብሮነት፣ በደምና በአጥንት ተሳስሮ የተገነባ ማንነት በምንም መልኩ ሊላላም ሆነ ሊበጠስ እንደማይችል በጦርነቱ ወቅት ጭምር ታይቷል:: ምክንያቱም ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተሰደዱ ሕዝቦችን የአማራ እና አፋር ክልል ሕዝቦች በወንድማዊ ፍቅር ተቀብለው የችግር ጊዜን እንዲሻገሩ አድርገዋል:: በትግራይ ክልል ያሉ ሕዝቦች በወቅቱ በቦታው የነበሩ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሞና ሌላም ብሔር ተወላጆችን ችግር እንዳይደርስባቸው ከልለው አቆይተዋል፤ ነፍሰጡር አዋልደው ለእናትነት ክብር አብቅተዋል::
እነዚህና መሰል የህዝቦች እውነተኛ ገጽ የሆኑ ተግባራት ”ውቅያኖስን በጭልፋ ”እንዲሉት አይነት ለማሳያነት ተቀንጭበው ቀረቡ እንጂ፤ ኢትዮጵያውያን ለአብሮነታቸው መጽናት መሰረት የሆኗቸው አያሌ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል:: ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያውያን የሚያተርፉት በመለያየት ሳይሆን በአብሮነት መሆኑን የተገነዘቡ፤ መበልጸጋቸው በሕብር ሲሰሩ እንጂ ሲናጠቁ አለመሆኑን፤ ወደ ከፍታና ልዕልናቸው የሚደርሱት ፍቅርና አብሮነታቸውን አጽንተው ሲዘልቁ መሆኑን ቀድመው በመረዳት እየተጓዙ ያሉ ሕዝቦች ናቸው::
እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ይሄን የሕዝቦች አብሮነት፣ አንድነትና በጋራ ሆኖ ስለ ነገ የጋራ ተስፋቸው በሕብር ቆመው መራመዳቸው ያልተዋጠላቸው በርካታ አካላት ይሄንን የአብሮነትና አንድነት መሰረት ለመናድ የማይቆፍሩት ጉድጓድ አለመኖሩን ነው:: ዛሬም በአማራ እና በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሞ፣ በኦሮሞ እና በሲዳማ፣ በኦሮሞ እና በሶማሌ፣ በሶማሌ እና በአፋር፣… ሕዝቦች መካከል ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፤ ከይቅርታ ይልቅ ቂምን፤ ከመተሳሰብና በጋራ ከመቆም ይልቅ መነጣጠልና መከፋፋትን… እየሰበኩ ጦር ለማማዘዝ የሚሰሩ የጥፋት ቡድኖች ማህበራዊ ሚዲያውን ሞልተው የጥላቻና የመከፋፈል መርዛቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ::
ሕዝቡ ሰላም ሲል፣ ጦርነት መስበክን፤ ሕዝቡ ፍቅር ሲል፣ ለቂም ማነሳሳትን፤ ሕዝቡ አብሮነት ሲል፣ በሃሰት ትርክት ታግዞ መለያየትን፤ ሕዝቡ በይቅርታ መሻገርን ምርጫው ሲያደርግ፣ የቂምና ቁርሾ ስብከትን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ማስተጋባቱን የሕልውናቸው መሰረት አድርገው ይዘውታል::
የእነዚህ ኃይሎች ግብ ዛሬ ላይ ከቅዠት የዘለለ ሊሆን ባይችልም፤ ኢትዮጵያውያንን መለያየት እና በተለያየ ማንነት ውስጥ የተዳከመች (ከተቻለም የተበታተነች) እና በቀላሉ የምትዘወር ኢትዮጵያን መፍጠር ነው:: ይህ የሚሆነው የኢትዮጵያዊነትን ገመድ መበጠስ፤ የኢትዮጵያውያንን አብሮነት መናድ ሲቻል እንደሆነም ተረድተው እየሰሩ ነው::
የነዚህን ሀይሎች ለመቀልበስ፣ ኢትዮጵያውያን የቀደመውን የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን አጠንክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፤ የሴረኞች የሴራ መረብ እርሱ ጋር ሳይደርስ እንዲበተን፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በሕብር በደመቀውና በጸናው ማንነታቸው እንዲዘልቁ፤ የሕዝቦችን አብሮነት በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም