“እያረርሁ እስቃለሁ እንደ ማሽላ” ይላል የአገሬው ሰው ሰብሉን ተጠቅሞ በምሳሌያዊ አነጋገር ሀሳቡንና የውስጡን ስሜት ሲገልጽ። ከተረት ማሳመሪያነት ባሻገር ማህበረሰቡ ባህላዊ የአልኮል መጠጦችንና የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ለማዘጋጀት ማሽላን እንደዋነኛ ግብዓት ይጠቀማል፤ ተረፈ ምርቱ ለከብቶች መኖ የሚውልና ሰብሉ በትንሽ ዘር ከፍተኛ ምርት የሚያስገኝ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ ፈርጀ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።
በተጨማሪም በሳይንሳዊ ዘዴ ለሽሮፕ መስሪያነት በመዋል ለህክምና አገልግሎት እንደሚውል በሳይንስ ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ ቆላማ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ደግሞ ከዓመት ጉርስ ባሻገር የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ የማሽላ ምርትን ለማግኘት ገበሬው ከሦስት ጊዜ በላይ እርፍና ሞፈርን በማንሳት መሬቱን ማረስና ማለስለስ ግድ ይለዋል። በተደጋጋሚ ሲያርስ፣ ሰብሉን ሲጠብቅ ዓመቱን በሙሉ የሚያሳልፈው አርሶ አደር በዓመቱ መጨረሻ የሚያገኘው ምርት ከድካሙ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የአርሶ አደሩን ድካም የሚቀንስ፣ የተሻለ ምርት የሚያስገኝና አንዴ ተዘርቶ እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ምርት የሚሰጥ የማሽላ ምርምር ውጤታማ መሆኑን የድሮው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአሁኑ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለፈው አመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ አድርጎ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የምክር ቤቱ አባላት ምርምሩ በሚካሄድበት ቦታ ተገኝተው የመስክ ምልከታ ማድረጋቸው ይታወሳል። የዘሩ የምርምር ስራ ተጠናቆ በሙከራና ዘር በማባዛት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአርሶ አደሩ የሚከፋፈል መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሳወቀ ሲሆን ተመራማሪው አቶ ታለጌታ ልዑል ስለ ምርመር ስራቸው የሚሉት አለ። በሙያቸው የጥርስ ሀኪም የሆኑት ተመራማሪው በጤፍ፣ በማሽላ ፣በገብስ እና ባቄላ ባሉ ጥራጥሬዎች ላይ ምርምር ሲያካሂዱ የቆዩት በንባብ ባገኙት ዕውቀት ነው።
በአጫጭር ስልጠናዎች እና የሌሎች ተመራማሪዎችን አሰራር በመመልከት ዕውቀታቸውንም አጎልብተዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመንዝ ቀያ ገብርኤል ወረዳ ዘረት በተባለች አነስተኛ መንደር የተወለዱት አቶ ታለጌታ ከአርሶ አደር ቤተሰብ መገኘታቸውና የአርሶ አደሩን ችግር በተግባር ያዩ መሆናቸው ወደዚህ ምርምር እንዲያዘነብሉምክንያት ሆኗቸዋል ። «በግብርና ስራ ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች መገኘቴ ችግሩን በሚገባ እንዳውቀው አደርጎኛል፤ የአገራችን ገበሬ በሳይንሳዊ ምርምርና በቴክኖሎጂ ተደግፎ የግብርና ስራውን ስለማያከናውን የጥረቱንና የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ አይደለም ከዛ ይልቅ በረሃብ መሞት፣ መቸገር አገር ጥሎ መሰደድ የተለመደ ነው »። አቶ ታለጌታ እንደሚሉት የእርሳቸውን ቤተሰቦች ጨምሮ ገበሬው ህይወቱ መቼ ነው የሚቀየረው? አርሶ አደሩ ከችግርና ከልፋት እንዴት ይላቀቅ? የሚል ቁጭት ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ እንዳደረባቸው ቁጭት ባዘለ አንደበት ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ከ30 ዓመታት በላይ በግላቸው በነዚህ ዘሮች ላይ ጥናትና ምርምር ሲያደርጉ ቢቆዩም፤ ከባለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ ምርምሩን እያከናወኑ ይገኛሉ፤ «አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ የማሽላ ምርት ለማግኘት መሬቱን ሁለትና ሦስት ጊዜ ከማረስ ባሻገር ሰብሉን ለመጠበቅ ጉልበቱን በማፍሰስ ብዙ ይደክማል በዓመቱ መጨረሻ የሚያገኘው ምርት ግን አጥጋቢ አይደለም። ችግሩን ለመቅረፍና አርሶ አደሩ ድካሙን ቀንሶ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ ለማድረግ በማሽላ ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር በማድረግ አንድ ጊዜ በተዘራ የማሽላ ዘር እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ማለትም ለ 20 ትውልድ የተሻለ ምርት ሊሰጥ የሚችል ውጤት ማግኘት ችያለሁ» ይላሉ።
የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር ያለሙት አቶ ታለጌታ ለምርምራቸው የገበሬውን ዕውቀት እና አገር በቀል ዘር በግብዓትነት ተጠቅመዋል። ምርምር ሲያደርጉባቸው ከቆዩባቸው የማሽላ ዝርያዎች በስድስቱ አጥጋቢ ውጤት ያገኙ ሲሆን ከዝርያዎቹ ውስጥ ቢጫማ፣ ነጭ፣ ጥቁር እና የዘንጋዳ ዝርያዎችን በስም ጠቅሰዋል። እንዲሁም ይሄን ጥናት መሰረት በማድረግ በጤፍ፣ በገብስ፣ በባቄላና በሌሎችም የሰብል አይነቶች ተመሳሳይ ጥናት በማድረግ ውጤታማ መሆኑ በሙከራ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል። ተመራማሪው እንደሚሉት፤ በርካታ ሰብሎች ዓመታዊ ምርት ብቻ የሚሰጡ ናቸው።
ማሽላም ዓመታዊ ምርት ከሚሰጡ ሰብሎች አንዱ ነው ምርምሩ የተደረገው ማሽላን እንደ ቡና፣ ማንጎ፣ ሙዝና የመሳሰሉት ቋሚ ተክሎች ለዘለቄታው ምርት እንዲያስገኝ ለማድረግ ሲሆን፤ ውጤታማ ማድረግም ተችሏል። በምርምር የተገኘው የማሽላ ዘርም አንዴ ከተዘራ በኋላ ራሱን የሚያባዛ ስለሆነ አርሶ አደሩ በየዓመቱ ዘር የሚፈልግበት አግባብ አይኖርም። የአካባቢው ሁኔታ የተመቻቸ ከሆነበዓመት ሦስት ጊዜ ምርት እየሰጠ ለስምንት ዓመታት የሚዘልቅ የአርሶ አደሩንም ድካም የሚያቀል ነው ።
ዝርያው በመጀመሪያው የምርት ዑደት ላይ በሄክታር 72 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን፣ በሁለተኛ የምርት ዑደት ላይ በሄክታር 125 ኩንታል ምርት መስጠቱ በምርምር ተረጋግጧል ብለዋል። አቶ ታለጌታ በምርምር አገኘኋቸው ስለሚሏቸው የማሽላ ዝርያዎች ሲያብራሩ፤ አንዴ ተዘርተው ከበቀሉ በኋላ መሬቱን ዳግም ማረስም ሆነ ሌላ ዘር መዝራት ሳያስፈልግ ምርት ይሰጣል። የተለመዱትን ዘሮች ስንዘራቸው ወቅታቸው ወይም ዓመታዊ ዑደታቸው ሲያበቃ ይደርቃሉ። ደግመው ህይወት መስጠት አይችሉም።
እነዚህኞቹ በጥናት የተገኙት ዝርያዎች ግን አንዴ ተዘርተው ሰብላቸው ከተሰበሰበ በኋላ ይታጨዳል። ከታጨደ በኋላ ውሃ በሚያገኙበት ጊዜ ራሳቸውን በማባዛት አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ፣ ስድስተኛና ከዚያ በላይ ትውልድ ድረስ ያለምንም ዘር ከፍተኛ ምርት ይሰጣሉ። እነዚህ በምርምር የተገኙት ዘሮች ቶክሲክ አሲድ የሚባል ንጥረ ነገርን በብዛት ማመንጨት የሚችሉ ዝርያዎች ስለሆኑ፤ ዋናው ዘር ሲሞት ራሱ ዘሩን ከውስጡ አውጥቶ ሌሎችን ትውልዶች እየተካ በትውልድ ቅብብሎሽ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ናቸው። እንዲሁም ዘሩ ተገቢ እንክብካቤ ከተደረገለት በሚፈልገው የአየር ጸባይ ውስጥ የበቀለ ከሆነ እና አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ ውሃ ካገኝ አንድ የማሽላ ፍሬ ዘራን ብንል ሲበቅል አስር፤ ሃያ፤ ሰላሳና ከዚያ በላይ እግሮችን ይዞ ሊወጣ ይችላል።
በሚቀጥለው ትውልድ ላይ ደግሞ እንደ ሁኔታው 50፣ 60፣ 70 እና ከዚያ በላይ እግሮችን ሊይዝ ይችላል። ስለዚህ እነዚህን ዘሮች አንድ ገበሬ ሲጠቀም ድካሙን ቀንሶ ምርትና ምርታማነቱን የሚጨምር መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ።የዝርያው የምርምር ውጤት በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የተመዘገበ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘሩን የማባዛት ስራውን ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተደረገ የሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በግማሽ ካሬ ሜትር ላይ እየተከናወነ ይገኛል። እናት ዘሩ ለምርት ደርሶ ሰብሉ የተሰበሰበ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሁለተኛው ትውልድ በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተያዘለት እቅድ መሰረት በያዝነው አመት ዘሩን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ አስር ኩንታል የሚደርስ አራት አይነት የማሽላ ዝርያዎች ተዘጋጅቷል ያሉት ተመራማሪው፤ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ውይይት በማድረግ ዘሩን ለአርሶ አደሩ በቅርቡ ለማሰራጨት ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል።
ነገርግን እነዚህ ዘሮች ከገበሬው ዘንድ ለአመታት አብረው የነበሩና ተፈጥሯዊ ባህሪያቸውን የያዙ በመሆናቸው በማንኛውም አካል በኩል ዘሮቹ ለአርሶ አደሩ ቢከፋፈል ምንም አይነት የጎንዮሽ ችግሮችን በገበሬውና በማሳው ላይ እንደማያስከትሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም አንዳንዶች ለረጅም ጊዜ ሌላ ዘር ሳይፈራረቅ አንድ አይነት ዘር ማሳው ላይ መቆየቱ የመሬቱን ለምነትና የሰብሉን ምርታማነት ይቀንሳል የሚል ስጋት ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታለጌታ፤ ሆኖም ይህ የምርምር ውጤት የመሬቱን ለምነት ጠብቆ በመያዝ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር ነው።
ምክንያቱም ዘሩ ከተዘራ በኋላ የመጀመሪያው ትውልድ ምርት ሰጥቶ ቀጣዩ ትውልድ በሚመጣበት ወቅት የመጀመሪያው ትውልድ ስሩ በስብሶ ለመጪው ትውልድ ተጨማሪ ምግብና ማዳበሪያ ስለሚሆን ከመጀመሪያው ትውልድ ምርቱ በዕጥፍ እንዲጨምር ያደርገዋል ብለዋል። ማሽላው አፈሩ በውሃና በነፋስ እንዳይሸረሸር በማድረግ የመሬቱን ለምነት የሚጠብቅ ነው። የአካባቢውን አየር ንብረት የተስተካከለና የተዋበ ያደርገዋል። በተጨማሪም ያለምንም ድካምና ወጪ በትንሽ ውሃ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር፣ አገዳውና ተረፈ ምርቱ በድርቅ ወቅት ለእንስሳት መኖ የሚውል በመሆኑ፤ ዘሩ ለአርሶ አደሩ ስጦታ እንጂ ስጋት እንደማይሆን በጥናታቸው እንዳረጋገጡ ተመራማሪው ገልጸዋል።
በመሆኑም በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የማሽላ ዘር ሲቆይ ነቅዞ ስለሚበላሽ ዘሩ ሳይበላሽ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ምርምሩ ውጤታማ እንዲሆን የተደረገላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ ፤ «ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅቶት በነበረው የፈጠራና የምርምር ስራ ውድድር በምርምራቸው አሸናፊ በመሆን የ50 ሺ ብር፣ የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ያገኘሁ ሲሆን ሚኒስቴሩ ለዘር ምርምር ማካሄጃ የ99 ሺ ብር ድጋፍ አድርጎልኛል። በተጨማሪም ምርምሩ በአይነቱ ልዩና ለሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፤ የአቢሲኒያ ሽልማት የሎሬትነት የማዕረግ ክብርን አቀዳጅቶኛል ።ለዚህ ሁሉ እንድበቃ ግን ያደረጉኝ የቤተሰቦቼ እርዳታ ነው» ይላሉ። አቶ ታለጌታ የአርሶ አደሩ ችግር አሳስቧቸው ለበርካታ ዓመታት ምርምሩን በሚያደርጉበት ወቅት የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርምሩ እንዲሳካ ተገቢውን እገዛ እንዳደረጉላቸው ገልጸው፤ የጥናቱን ሀሳብ ለባለሙያዎች በሚያቀርቡበት ጊዜ ሀሳቡን ተረድቶ ወደ ተግባር እንዲገባ ከማበረታታት ይልቅ የማንቋሸሽና ጥናቱን የማጣጣል ሁኔታ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከአመታት በፊትም 18 ጊዜ ሀሳቡን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ለሚመለከታቸው የቴክኒክ ኮሚቴዎች አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸው እንደነበር ጠቁመው፤ አሁን ላይ የተቋሙ ሚኒስቴር የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ሀሳቡ የሀገሪቱን የሰብል ምርት ከፍ የሚያደርግ ነው ብለው በማመን ለጥናቱ ቦታ ሰጥተው እንዲሰራ አድርገዋል ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል። ነገርግን አንዳንድ ብልሹ አሰራሮች በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስገኘት ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦች ስኬታማ፣ ችግር ፈቺና የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚያቀሉ ጥናት እንዳያከናውኑ ያደርጋል።
አገሪቱ ከያዘችው ግብርናውን በጥናት የማዘመን አቅጣጫ ጋርም ይቃረናል ይላሉ። የአገሪቱ ግብርና እየተፈተነ ያለው ምርታማነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። መንግሥት ምርታማነት እንዲጨምርና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሰብሎች በበቂ ሁኔታ እንዲኖር ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ የአገሪቱን የአየር ጸባይ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በሰብሎች ላይ ጥናት በማካሄድ ምርምርን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን መስራት ካልተቻለ ውጤት አይመጣም። ድካምን የሚቀንሱና በአጭር ጊዜ ሰፊ ምርት የሚያስገኙ የምርምር ሥራዎች መሰራት አለባቸው ፤ ችግር ፈቺና የተሻለ የምርምር ውጤት እንዲያስገኙ ተመራማሪዎችን ማገዝ ያስፈልጋል። ለተመራማሪውም አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላትም ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
ሶሎሞን በየነ