3ኛው አገር አቀፍ የፓራሊምፒክ ቻምፒዮና ከመጋቢት 20/2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ነው፡፡ በውድድሩ በዓለም ቻምፒዮናና በፓሪስ ፓራሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ይመረጣሉ።
ቻምፒዮናው ከ2011 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችን ከመምረጥ እንደሆነም በተጨማሪ ለአትሌቶች የውድድር ዕድል በመፍጠር ተሳታፊ ወቅታዊ አቋማቸውን እንዲፈትሹ ለማስቻል ነው።
የፓራሊምፒክ ስፖርት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ ተጠቃሽ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። አገር አቀፍ ውድድሩ የሚካሄደውም ለአትሌቶች ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር በዓለም ቻምፒዮናና በፓራሊምፒክ ውድድር የሚገኙ ድሎችን በማስጠበቅ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መሆኑን የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ቻምፒዮናው የሜዳ ተግባራትና የመም ውድድሮችን በማካተት ጠንካራ ፉክክሮችን ያስተናገደ ሲሆን፣ ስምንት ክልሎች፣ ሁለት ማሰልጠኛ ማዕከላትና አንድ ክለብ ተሳታፊ መሆን ችለዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ200 በላይ አትሌቶችም ተሳትፈውበታል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ለፓራሊምፒክ ስፖርት ትኩረት በመስጠት ልዩ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን አትሌቶች በመያዝ ስልጠና እየሰጡ ሲሆን ሁለት አትሌቶችን ከዚህ በፊት ለብሔራዊ ቡድን አስመርጠዋል። በዚህ ቻምፒዮናም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው በርካታ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችለዋል።
ከነዚህ ማዕከላት ስልጠና ወስደው የሚወጡ አትሌቶች ክለቦችንና የውድድር ዕድልን ከማግኘት አኳያ ብዙ ሥራ እንደሚቀርም ተጠቁሟል። በዚህ ረገድ የክለቦች አደረጃጀት የአካል ጉዳተኞችን ስፖርት ታሳቢ አለማድረጉ ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የውድድር ዕድልን ለመፍጠር ከአካዳሚዎች አትሌቶችን ወደ ውጭ ለመውሰድ እየተሞከረ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም ለሁለት አትሌቶች የውጭ ውድድር ዕድል መፍጠር መቻሉ ተገልጿል። የፓራሊምፒክ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አደረጃጀትም ለተወዳዳሪዎች የማይመች በመሆኑም ዓለምአቀፍ ውድድሮች ላይ እንደልብ ለመሳተፍ ከባድ ሆኗል።
በኢትዮጵያ ለፓራሊምፒክ ስፖርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ ከሌሎች ስፖርቶች በተሻለ በዓለም መድረኮች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል። ለዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በጥቂት ውድድሮችና ትንሽ ቁጥር ባላቸው አትሌቶች በተሳተፈችባቸው መድረኮች የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ ውድድር የተሳተፈችው እሥራኤል በቴል አቪቭ ላይ እኤአ 1968 ላይ በተካሄደ ውድድር ላይ ነው። ይህም በሁለት አትሌቶች በአትሌቲክስ እና በጠረጴዛ ቴኒስ የውድድር ዘርፍ እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ ለአስርት አመታት ውድድር ላይ አልተሳተፈችም።
እኤአ በ1976 ግን በአትሌት አብርሃም ሃብቴ ስትወከል በአትሌቲክስ፣ ቴኒስና በላውን ቦውሊንግ ውድድር ተሳትፏል። ከዚያ በኋላ በ2004 በአንድ አትሌት መሳተፍ ችላ ነበር። ከአራት አመታት ቆይታ በኋላም በ2008 በሁለት አትሌቶች ተወክላ የነበር ቢሆንም የተመዘገበው ውጤት አመርቂ አልነበረም።
እኤአ በ2012 ለንደን በተዘጋጀው የፓራሊምፒክ ውድድር ግን ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸውና ውጤት ካስመዘገበችባቸው ውድድሮች መካከል ቀዳሚው ሆኗል። ይህም ወንድዬ ፍቅሬ በተባለ አትሌት አማካኝነት በወንዶች 1,500 ሜትር ሩጫ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበችበት ነው።
በቀጣይ ከአራት አመታት በኋላ በብራዚል ሪዮ ከተማ በተዘጋጀው የፓራሊምፒክ ውድድር በመክፈቻ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለበ የገባው ታምሩ ደምሴ በ1,500 ሜትር ለኢትዮጵያ በታሪክ ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በትዕግስት ገዛኸኝ አማካይነት ያገኘችው ባለፈው ቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ነበር። የአፍሪካ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ትዕግስት፣ በጭላንጭል የሚያዩ የ1,500ሜ ሩጫ፣ የራሷን ምርጥ ሰዓት 4:23.24 በማስመዝገብ ነው ለፓራሊምፒክ አሸናፊነት የበቃችው፡፡ ኢትዮጵያ ቶኪዮ ላይ ከትዕግስት ባሻገር፣ በተመሳሳይ 1,500 ሜትር ርቀት በእጅ ጉዳት በገመቹ አመኑና በጭላንጭል የሚያዩ ወንዶች ታምሩ ደምሴ ተወክላ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም