እንደ አገር የተለያዩ የትምህርት አሰጣጥ ዓይነቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየመጡ ይገኛሉ:: ችግሮች ቢኖሩባቸውም መሠረታዊ የሚባሉ መፍትሄዎችን ማመላከት መቻላቸውን ማንም አይክደውም:: በተለይም ክህሎትን ከማዳበርና እውቀትን ከመጨመር አንጻር የማይተካ ሚናን ተጫውተዋል:: ለአብነት የኦላይን ትምህርትንና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል::
ይህ ዓይነት ትምህርት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው እስከ ባለሀብቱ ድረስ መሠረታዊ እውቀት ያስጨበጠ ነው:: በሁኔታዎች አለመመቻቸት የሚከሰቱ መስተጓጉሎችን በቀላሉ ለመፍታት መንገድን አሳይቷል:: ለምሳሌ፡- ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ ለማይችሉ ግለሰቦች የትምህርት ፍላጎታቸውን በኦላይን ትምህርት ማሳካት የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቷል:: በተመሳሳይ የምግብ አሠራሮችና የቅድመ ሕመም ክትትሎች በዚሁ በኦላይን ትምህርት መፍትሄ ማግኘት ችለዋል::
የኦላይን ትምህርቶች መረጃ ሰጪም ናቸው:: ወቅታዊ መረጃዎችን ለምንፈልጋቸው አላማዎች እንድንጠቀምባቸው ያግዙናል:: ስለዚህም የኦላይን ትምህርት አንድም በመረጃ ሰጪነት በሌላ በኩልም በእውቀትና ክህሎት እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ማለት ነው:: እኛም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኦላይን ሆኖ በትምህርት ቤቶች ላይ ልዩ ትኩረቱን ያደረገ የትምህርት ሥርዓት ይዘንላችሁ ቀርበናል:: የትምህርት ሥርዓቱ ኢ- ስኩል ይባላል:: የሶፍትዌር ሥራን የያዘ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶች የሚሠሩትን አጠቃላይ ሥራዎች በዘመናዊ መንገድ እንዲተገብሩ የሚያስችላቸው ነው::
የኢ- ስኩል መተግበሪያ ሥርዓት እንደ አገር ሥራው ገና ተግባራዊ አልተደረገም:: እንቅስቃሴውም ቢሆን እንዲሁ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው:: እናም ከተማ አስተዳደሩ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል፤ መቼ ወደተግባርስ ይገባልና ጥቅሙ ምንድነው ስንል በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቴክኖሎጂና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ዳኜን አነጋግረናቸዋል:: በጉዳዩ ላይ የሰጡንንም ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበናል::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል 200 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት በ55 ትምህርት ቤቶች ለመተግበር እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴው ተጀምሯል:: ሥራው የሚሠራው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመሆን ሲሆን፤ የቴክኖሎጂውን አጠቃቀም በሚመለከት ለ55ቱ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ስልጠና በተለያዩ ጊዜያት ተሰጥቷል።
ሥራዎቹ ከ40 በመቶ በላይ ተከናውነዋል:: የመተግበሪያ ሥርዓቱ የሚጀመረው በ2015 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፤ የትምህርት ማኔጅመንቱ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው ደግሞ በ2016 ዓ.ም ነው:: ትምህርቱ የሚተገበርባቸው ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከሙአለ ሕፃናት እስከ ኮሌጆች ድረስ የሚዘልቅ ነው:: አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ቴክኒክና ሙያዎችንም ይጨምራል::
የኢ- ስኩል ጥቅም በርካታ ነው:: ዋናው ግን የተቀላጠፈ መረጃ ማግኘት ሲሆን፤ መረጃው ትምህርት ጭምር ሊሆን ይችላል:: ከዚህ ቀደም ሕፃናት በክፍል ደረጃቸው ማወቅ የሚጠበቅባቸውን ዕውቀትና ክህሎት የሚያስጨብጥ አሠራር አልተዘረጋም:: ይህ ደግሞ እንደአገር ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል:: በመሆኑም ይህንን ችግር የተረዳው ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የ «ኢ-ስኩል» ን መተግበሪያ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንቅስቃሴውን ጀምሯል::
በዚህ መተግበሪያ የሕፃናቱ ችግር ብቻ ሳይሆን የቤተሰብንም ሆነ የመምህራንን ክፍተቶች ይደፍናሉ:: የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጉልህ ሚና ይጫወታሉም:: እንዴት ከተባለ ለአገር፣ ለወላጆች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደር ሠራተኞች፣ ለተማሪዎች በሚሰጠው ጠቀሜታ ነው:: ለወላጆች ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ብንነሳ የልጆቻቸውን ውሎ በቀላሉ መከታተል እንዲችሉ ያደርጋቸዋል::
በተጨማሪም ውጤታማነታቸውን በቀላሉ አይተው ለመደገፍና ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል:: ልጆቻቸውን የፈተና ወረቀታችሁን አሳዩኝ ማለትንም ያስቀርላቸዋል:: ምክንያቱም በቀጥታ ዌብሳይቱ ውስጥ ገብተው ያሉበትን ደረጃ ማወቅ ይችላሉ:: ይህንን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ሲስተሙ በራሱ መልዕክት ስለሚልክላቸው ልጃቸው ምን ያህል ውጤት እንዳመጡ ይረዳሉ:: ስለዚህም ሳይወዱ በግዳቸው የልጆቻቸው ተቆጣጣሪ ይሆናሉ:: ለልጆቻቸው የሚያስቡትን ነገር በትምህርቱ ዘርፍ እንዲያገኙ ያስችላቸዋልም::
ለተማሪው ያለው ጥቅም ደግሞ ባለበት ሆኖ መማር መቻሉ ነው:: እርስ በእርስ በመገናኘትም መማማር የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል:: ምክንያቱም ሲስተሙ እርስ በእርሳቸው የሚያወሩበት (ቻት) የሚደራረጉበት ዕድል አለው:: ጉዳያቸው የፌስ ቡክ ወሬ ሳይሆን የትምህርት ነገር እንዲሆንም ያስችላቸዋል:: ይህ ሥርዓት ተማሪው ምን እያወራ ነው የሚለውንም ለመከታተል በቀላሉ ይቻልበታል:: ከዚያ ይህንን ንግግራቸውን መሠረት አድርጎ እነርሱን ለመደገፍ መምህራን እንዲሠሩ፣ ወላጆች ክፍተታቸውን እንዲደፍኑና አስተዳደሩም የጎደሉ ነገሮችን እንዲያስተካክል ያስችለዋል::
ሌላው ተማሪው ያለውን ውጤት አይቶ የት ላይ አቅም እንዳለውና በየትኛው ትምህርት ደከም እንዳለ እንዲለይበት ማስቻሉ ነው:: የቀጣይ ህልሙን የሚያሳካበትን መንገድ የሚቀይስበትም ነው:: ሲስተሙ የሚፈልጉትን ነገር በአንድ ቋት ውስጥ ስለሚያስቀምጥላቸው የፈለጉትን ነገር እያወጡ (አክሰስ) እያደረጉ እንዲማሩም ያበረታታቸዋል:: በቀላሉ የተሰጣቸውን የቤት ሥራ፣ ፈተናና መለማመጃዎች እንዲሠሩም ዕድል የሚፈጥርላቸው ነው:: የሳቱትንም ቢሆን ወዲያው ያሳያቸዋል::
ኢ- ስኩል ሥርዓት ለመምህራንም እንዲሁ ትልቅ ጥቅም አለው:: አንዱ በእቅድ እንዲጓዙ ማድረጉ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በየአቅማቸው ተማሪዎችን ለመደገፍ ያስችለዋል:: የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን ሳይደክሙ በቀላሉ እንዲያከናውኑም ይረዳቸዋል:: ማለትም ሮስተር፣ የዕለት እቅድና ሪፖርትን የመሳሰሉ ሥራዎችን ሲስተሙ ስለሚሠራላቸው እነርሱ ልዩ ትኩረታቸው ማስተማሩ ላይ ብቻ ይሆናል:: ከዚያ ባሻገር የእነርሱ ሥራ መረጃውን ወደ ሲስተሙ ማስገባት ነው:: ይህ ደግሞ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ሁነኛ አማራጭ ነው::
ለርዕሰ መምህሩ የሚሰጠው ጠቀሜታ ደግሞ የእኔ ትምህርት ቤት ምን ይመስላል፤ እንዴት እየመራሁት ነው፤ ተማሪዎቼ፣ መምህራን በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉና ለማስፈተን ምን ያህል ብቁ ነኝ የሚለውን እንዲያውቅ ያግዘዋል:: ለቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ትምህርቱን ለሚመሩት አካላትም እንዲሁ ጠቀሜታም የጎላ ነው:: የተማሪዎችን አቅም፤ የትምህርት ቤቶችን የማስተማር ሁኔታ፣ የአስተዳደር አቅምና መሰል መረጃዎችን ለማግኘትና ወደ ተግባር ለመቀየር ዕድል ይፈጥርላቸዋል:: ለአጥኚዎችና ፖሊሲ አውጪዎችም ቢሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው:: ምክንያቱም እንደአገር ያለውን የትምህርት ስብራት የቱ ጋር እንደሆነ በመለየት ለውጦችን ማድረግ ያስችላል::
ኢ- ስኩል ሌላው ለየት የሚያደርገው ነገርና ያለው ጠቀሜታ የፈተና ባንክ ያለው መተግበሪያ መሆኑ ነው:: በዚህም በሁሉም ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች አንድ ዓይነት ፈተና እንዲፈተኑ ይሆናሉ:: ይህ ሲሆን ደግሞ የእያንዳንዱ ትምህርት ቤት መማር ማስተማር ሥራ፣ የትምህርት ቤት አስተዳደር ሁኔታ፣ የተማሪዎችና የመምህራን አቅም ይለይበታል:: ከዚህ ቀደም የነበረውን የመምህሩን ጫና የሚቀንስም ነው:: ማለትም ማስተማር፣ ፈተና ማውጣትና መፈተን የሚሉት ነገሮች ገደብ ይኖራቸዋል::
በኢ- ስኩል ሥርዓት ልክ እንደማትሪክ ፈተናው የሚወጣው በፈተና ኤክስፐርቶች ሲሆን፤ ትምህርቱን የመስጠትና የመሸፈን ጉዳይ እንዲሁም የተማሪዎች ክትትል ልዩነት ካላመጣ በስተቀር ተማሪዎች ፈተናው እንደልዩነት ተደርጎ አይወሰድም:: ሁሉም በእኩል አንድ ዓይነት የመፈተን ዕድል አላቸው:: ውጤቱ ደግሞ እንደአቅማቸው ሁኔታ የሚታይ ይሆናል:: በዚያ ላይ በኢ- ስኩል ሥርዓት ካሪኩለሙ ተማሪዎች ምን ማወቅ አለባቸው፣ መምህሩ የት መድረስ አለበት የሚለውን በሚገባ ያሳያል:: በምዕራፉ መጨረሻ ላይ የተለያዩ ፈተናዎችም ይሰጣሉ:: እነዚህ ፈተናዎች ተጠራቅመው ደግሞ የሴሚስተሩ ፈተናዎች የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጥራል::
ስለዚህም ተማሪዎች እያወቁ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል:: ሲፈተኑም የመመለስ ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል:: ይህ ደግሞ እንደአገር የታየውን የ12ኛ ክፍል የውጤት ማሽቆልቆልና ያለማወቅ ችግር በእጅጉ የሚፈታ ነው:: ኢ-ስኩል ስድስት መሠረታዊ ፓኬጆችን ተግባራዊ የሚያደርግ ሥርዓት ሲሆን፤ እነዚህም የትምህርት ቤት መረጃ ማኔጅመንት፣ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት፣ የትምህርት ቤት ቤተ- መጽሐፍት ሥርዓት (ስኩል ላይብረሪ ሲስተም)፤ የትምህርት ማኔጅመንት፣ የትምህርት ቤት ፖርታል እና ቢዝነስ ኢንተለጀንስ የሚባሉት ሥርዓቶች ናቸው። እያንዳንዳቸውን ከሚሰጡት ጥቅም አንጻርም አቶ ደረጀ እንደሚከተለው ተንተነዋቸዋል::
የመጀመሪያው የትምህርት ቤቶች መረጃ ማኔጅመንት (School Information Management System) ሲሆን፤ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉትን አጠቃላይ መረጃዎች የምናገኝበት ነው:: የተማሪ ቁጥር፣ የመምህር ብዛት፣ የትምህርት ቤቱ ግብዓቶችንና መሰል አጠቃላይ የትምህርትቤቶች መረጃን የሚይዘው ነው:: በዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ምን እንደሚጎድለው፤ ምን ምን አቅርቦቶች እንዳሉት ማወቅ ይቻላል:: ይህ መሆኑ ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ አሠራሮችን ለማሻሻል ምልክት ይሰጣል:: የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ቢሆን እቅዶቹን አስተካክሎ የጎዶለውን አውቆ እንዲሞላና አስተዳደሩን እንዲያሻሽል ያግዘዋል::
ወደ መምህራን ሲመጣ የቱ ጋር ክፍተቶች እንዳሉ ለይተው ተማሪዎቻቸውን በምን መልኩ ማገዝ እንዳለባቸው እንዲረዱ ያስችላቸዋል:: ተማሪዎችም ቢሆኑ እንዲሁ ትምህርት ቤቱ የሚጎድለውን ነገር ተረድተው በምን መልኩ መማርና በትምህርታቸው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ያመላክታቸዋል:: የራሳቸውን አቅጣጫ ለመቀየስም ዕድል ይሰጣቸዋል:: በወላጆች በኩል ስንመለከት ደግሞ ልጆቻቸውን የተመረጠ ትምህርት ቤት እንዲያስገቡ በሩን ይከፍትላቸዋል:: በአጠቃላይ በትምህርትቤቶች፣ በተማሪዎችና መምህራን መካከል ውድድር እንዲፈጠር ያስችላል::
ሌላው ኢ- ስኩል በውስጡ የያዘው ነገር ተማሪዎች የሚፈልጓቸውን መጽሐፍት ባሉበት ሆነው እንዲያገኙ የሚያስችለው፤ በራሳቸው መማር እንዲችሉ የሚደግፋቸው ፓኬጅ ሲሆን፤ ይህም ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት (Digital Library Systems) የሚባለው ነው:: ተማሪዎች የትኛውም ቦታ ላይ ሆነው መጽሐፍቱን አግኝተው እንዲያነቡ የሚያግዛቸው ነው:: ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸውን ለማገዝ የትኛው መጽሐፍ ለዚያ ደረጃ ይመጥናል የሚለውን ስለሚረዱ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱን ተጠቅመው ማገዝ ይችላሉ:: መምህራንም ቢሆን አቅማቸውን አጎልብተው ለተማሪዎች የሚጠቅም መረጃ ለማግኘት የሚያስችላቸው ነው::
ሦስተኛው ፓኬጅ የትምህርት ቤት ቤተ- መጽሐፍት ሥርዓት(school layeberry system) የሚባለው ሲሆን፤ በሀርድ ኮፒ ያለውን የትምህርት ቤት መጽሐፍ ወደ ሶፍት ኮፒ በመቀየር በየክፍል ደረጃው በማስቀመጥ በቀላሉ ተማሪዎች እንዲጠቀሙበት የምናደርግበት ሥርዓት ነው:: ይህ ሥርዓት ተማሪዎቹ ለየትኛው ደረጃ የትኛውን መጽሐፍ ማንበብ እንዳለባቸው የሚያስገነዝባቸው ነው::
የትምህርት ማኔጅመንት ሥርዓት (learning management system) የሚባለውም አንዱ የኢ- ስኩል ፓኬጅ ሲሆን፤ ይህ ሥርዓት ተማሪዎች በራሳቸው እንዲማሩ የሚሆኑበት ነው:: ማንኛውም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተመዘገበ ተማሪ መምህር ሳይኖር ኦላይን ገብተው መማር የሚችሉበት ነው:: የተሰጣቸውን የቤት ሥራም የሚሠሩበትና የሚከታተሉበት ነው:: የኪውዝ ፈተናዎችን የሚሠሩበትም ነው::
የትምህርት ማኔጅመንት ሥርዓት በሥራቸው ውስጥ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያገኙ ሁሉንም የአሠራር እንቅስቃሴዎችን በማስተዳደር ሁሉንም ሥራዎች እንዲይዙ ይረዳል:: ለተማሪዎች እንዲሁም ለትምህርት ቤት አስተዳደር የተሻለ የመማር ባህልና አካባቢን ይፈጥራል:: የተሻሉ የልማት ዕድሎችን የሚሰጥም ነው:: ለአሠራር እንቅስቃሴዎች የበለጠ ቀላልነትን ያመጣል::
አራተኛው የኢ- ስኩል መተግበሪያ ፓኬጅ የትምህርት ቤት ፖርታል (school portal system) የሚባለው ነው:: ሁሉም የትምህርት ቤት መረጃ በአንድ ቋት የሚሰባሰብበት ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶች የራሳቸው ዌብሳይት ተፈጥሮላቸው በዚያ ገብተው መረጃዎችን የሚለዋወጡበት ነው:: ክፍለከተማው፣ ቢሮው፣ ወላጆች እንዲሁም ተማሪዎች እየገቡ መረጃዎችን ይለዋወጡበታል፤ ያገኙበታልም:: በተጨማሪም ለተማሪዎች ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች ይተላለፉበታል::
የመጨረሻው የኢ- ስኩል ሥርዓት ቢዝነስ ኢንተለጀንስ (Business Intelligence system) የሚባለው ሲሆን፤ ከላይ የተጠቀሱት ሲስተሞችን በአጠቃላይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንት በሆነ መልኩ መረጃዎችን እያጣራ የሚይዝ ነው:: የፈለግነውን መረጃ የሚያቀርብልንም ነው:: በአንድ ጥያቄ የሚፈለገውን መረጃ መውሰድ የምንችልበት ፓኬጅ ነው:: የሁሉንም ሲስተም ሰብስቦ በምንፈልገው መልኩ መረጃ ይሰጣል:: የአንድ ተማሪ ሙሉ መረጃውን ሳይቀር መከታተል የምንችልበት ሥርዓት ነው:: የመምህራንና የትምህርት ቤቱን ሠራተኞች ሳይቀር አስፈላጊ መረጃ እናገኝበታለን::
በዚህ ሥርዓት ውስጥ የገቡ ተማሪዎች የትኛውም ትምህርት ቤት ቢሄዱ ሙሉ መረጃቸውን ማግኘት ይቻላል:: ምን ያህል አቋረጠ፣ ምን ያህል ተፈታኝ አለ የሚሉትንም የትምህርትቤት መረጃ ማንንም ሳንጠይቅ ማወቅ ይቻልበታልም:: ስለሆነም እነዚህ ፓኬጆች ተግባራዊ ከሆኑ እንደ አገር የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ በብዙ መልኩ ያስችላልም ብለዋል ዳይሬክተሩ አቶ ደረጀ:: ይሁንና ሥራው ወደ ተግባር ይገባ ዘንድ የሁሉም ሰው ርብርብ ያስፈልጋልና ከአለው ጥቅም አንጻር ተረድተን ለሚሰጠን ሥራ የበኩላችንን እናበርክት በማለት ለዛሬ አበቃን::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም