ኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እየጨመረ ቢመጣም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመባል የሚታወቀው ግብርና አሁንም የጀርባ አጥንትነቱን ይዞ ቀጥሏል፡፡ ግብርናው የአገሪቱ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ነው፤ ጉርስ ብቻም አይደለም፤ ጥሪትም ሀብትም በመሆን ለኢንዱስትሪውና አገልግሎቱ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
መንግሥት ይህ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ የበለጠ እንዲያድግ ይፈልጋል፤ ግብርናው እያደገም፣ ገና ማደግ የሚችልና ማደግ አለበት ብሎ በትኩረት እየሠራ ነው፡፡ ለዘርፉ ክፍተኛ ሀብት እየመደበ የሚገኘውም ለዚህ ነው፡፡ ዘንድሮ ለአፈር ማዳበሪያ መግዣ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን ለዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርሶ አደሩ ዘንድ ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ፣ ምርጥ ዘር በሚፈለገው ልክ እንዲቀርብ፣ የግብርናው ዘርፍ ምርምር ይበልጥ እንዲጠናከር እያደረገ ነው፡፡ ግብርናውም በዚያው ልክ አጸፋውን እየመለሰ ነው፤ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይገኛል፡፡
መንግሥት ሁሉም ባለድርሻ አካል የግብርናውን ዘርፍ እንዲደግፍም ሁሌም ያሳስባል፡፡ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የፋይናንሱ ዘርፍ የብድር አቅርቦት እንዲያደርግ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ ለግብርናው ዘርፍ ቅርበት ያላቸው የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የሚመሩ አካላትም ኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት የማይሰጥባት ብቸኛ አገር አድርገው ሲጠሯትም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበትም ሲያሳስቡ ኖረዋል፡፡
መንግሥት የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች) በከተሞች ሕንፃ ለሚገነቡ ባለሀብቶች ብቻ ድጋፍ እያደረጉ ያሉበትን ሁኔታ በመተቸት ለአርሶ አደሩም ብድር በማቅረብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የገንዘቡ ባለቤት መላው ሕዝብ ሆኖ እያለ ባለሀብቶች ብቻ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መስተካከል እንደሚኖርበት ሲጠቆምም ነበር፡፡
የፋይናንሻል ዘርፉ በበኩሉ በመያዣ፣ በመሬት አስተዳደርና በመሳሰሉት በኩል ችግሮች መኖራቸውን በመጥቀስ ለግብርናው ዘርፍ ብድር ለማቅረብ እንደሚቸገር ሲጠቅስም ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለውጦች መምጣታቸውን መገንዘብ ተችሏል፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ተከትሎ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከተናገሩት መረዳት እንደሚቻለው የፋይናንሻል ዘርፉ ለግብርናው ዘርፍ ብድር መስጠት መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ የሚሰጠው የብድር መጠንም እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ባንኮች ዘንድሮ ለግብርናው ዘርፍ 92 ቢሊዮን ብር አበድረዋል፤ ይህም ከአምናው በ29 በመቶ እድገት የታየበት ነው፡፡ ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትም እንዲሁ 30 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል፤ ይህ ደግሞ በ36 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡
ዘርፉ ለግብርናውና ለአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፉ ብድር መስጠት መጀመሩ አልፎም ተርፎ እየሰጠ ያለው ብድር ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ፣ የፋይንናስ ዘርፉ የገንዘቡን ባለቤቶች ተጠቃሚ ወደ ማድረግ እየተሸጋገረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የብድር አቅርቦቱ ፋይዳም ብዙ ነው፡፡ ዘርፎቹ የያዙት ማህበረሰብ ብዛት፣ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፣ በሥራ ዕድሎቹ የሚፈጠረው አገልግሎት መስፋፋት ሲታሰብ የብድር አገልግሎቱ ያለውን ተደራሽነት ስፋትም ይጠቁማል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ በተለይ ወደ ግብርናው ዘርፍ ፊቱን ማዞሩ ትልቅ ለውጥ ሆኖ አብዛኛው ብድር ከተማ አካባቢ ወይም ከግብርናው ዘርፍ ውጪ መሆኑ አሁንም ብዙ መሠራት እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ግብርናው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሰፊ ድርሻ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ግብአት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደመሆኑ የፋይናንስ ዘርፉ ይህን የግብርናውን ሚና በአጽንኦት መመልከት ይኖርበታል፡፡
አቅርቦቱን የግብርና ልማቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ ግብርናው መዘመን ጀምሯል፤ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ለመውጣት፣ በመስኖ ለማልማት እየተጣጣረ ነው፡፡ ለዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ለውጥ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተፈላጊ የሆነውን ስንዴ በመኸር ብቻ ሳይሆን በበጋ መስኖም በስፋት የማልማቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህ ግብርና ደግሞ እንደ ቀድሞው በተለምዷዊ መንገድ የሚካሄድ አይደለም፤ ቴክኖሎጂና ሜካናይዜሽንን በእጅጉ ይፈልጋል ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ የብድር አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ትራክተር ኮምባይነር የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መግዛት ይፈልጋል፤ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን በማቅረብ አርሶ አደሩ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች እንዲያገኙ እያደረገ ነው፤ ፍላጎቱ ግን ከመንግሥት አቅርቦትም በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ክፍተት መሙላት ላይ የፋይናንስ ዘርፉ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቆይታቸው ‹‹የፋይናንሻል ዘርፉ እንዳለፈው ዓመት ዘንድሮም በጣም ጥሩ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ዘርፉ ካበደረው 311 ቢሊዮን ውስጥ ወደ 172 ቢሊዮን ብር ብድር ሰብስቧል›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ዘንድሮ የሰጠው ብድርም አምና ከሰጠው መቶ በመቶ ማደጉን ገልጸዋል፡፡
ዘርፉ የሚሰጠው ብድርም፣ ያስመለሰው ብድርም በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቱ አንድ ስኬት ሆኖ አገርን ይበልጥ ለሚያሳድጉ ዘርፎች በተለይም ለግብርናው የሚሰጠውን ብድር ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ሊሠራ ይገባል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ስኬት መለኪያው ለአርሶ አደሮች የሚያቀርበው የብድር መጠን ከፍተኛነት እንዲሆን ተደርጎ መሠራት ይኖርበታል፡፡
ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ይሸጋገራል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፉ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የግብርናውን ጫና ከመቀነስ ውጪ የተባለውን ሽግግር እውን በማድረግ በኩል ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የሚናገሩት፡፡
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም