ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወቅቶች ለውጥ ፈላጊነታቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል። ከፍ ባለ መስዋዕትነትም ለለውጥ ያላቸው ቁርጠኝነት በተጨባጭ አስመስክረዋል። ለዚህም ከ1950ዎቹ በታሪክ ከሚታወቀው የመንግሥቱ ንዋይ ግርግር ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የተስተዋሉ የተለያዩ የለውጥ ንቅናቄዎች ማሳያ ናቸው።
በተለይም በ60ዎቹ የነበረው ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ ከያዛቸው ፤ ሕዝባዊ ዓላማዎች፣ ተልዕኮዎች እና ሀገራዊ ራዕይ ፤ከዚያም ባለፈ የወቅቱ ትውልድ ለለውጥ ከነበረው ከፍተኛ መነሳሳት እራስን እስከመስጠት የደረሰ ቁርጠኝነት እና ሕዝባዊ ድጋፍ አንጻር ብዙ ተስፋ የተጣለበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያረጋገጡት ነው።
ይህ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሻግራል ተብሎ የታመነበት የለውጥ ንቅናቄ የለውጡ ባለቤት በሆነው ትውልድ መካከል በተፈጠረ አለመደማመጥ፣ አለመረጋጋትና ስክነት ማጣት ወደ ችግርና ጥፋት ተለውጦ ፤ ትውልዱን ያልተገባና አስከፊ ዋጋ አስከፍሏል። በሃገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥም ትልቅ ጥቁር ጠባሳ ሆኖ ተመዝግቧል።
ሌላው በ1997 ዓ/ም በተመሳሳይ መልኩ በሕዝባችን ብዙ ተስፋ የተጣለበት ለውጥና የለውጥ ንቅናቄ ነው፤ ይህ በወቅቱ ሀገሪቱን ያስተዳድር ከነበረው ገዥ ፓርቲ /ኢሕአዴግ/ የፖለቲካ ስህተት በተፈጠረ ክፍተት የተከሰተ ነው። ይህም ቢሆን ለብዙዎች ሞትና ስደት ከመሆን ባለፈ ፤ ለሕዝቡ የለውጥ መሻት ትርጉም ያለው ምላሽ አላስገኘም ።
እንዲያውም የጊዜው ገዥ ፓርቲ /ኢሕአዴግ/ የፖለቲካ ስልት ፈጥሮበት ከነበረው የሕልውና አደጋ በመነሳት፤ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙት፤ ራሱን ፍጹም ወደ ሆነ አምባገነናዊ መንግሥት ለመቀየር የተገደደበት እውነታ ተከስቷል። በዚህም ዕለት ከዕለት እየተዳከመ ወደማይቀር ውድቀቱ ተጉዟል። በውድቀት መንገዱም ሃገርና ሕዝብን ውድ ዋጋ አስከፍሏል።
የኢሕአዴግን ሁለንተናዊ ውድቀት ተከትሎ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቀጣጠለው ለውጥ ከ1960ዎቹ ቀጥሎ በሕዝባዊነቱ የሚጠቀስ ነው። የለውጥ ኃይሉ የዛሬ አምስት ዓመት በተሟላ የሕዝብ ድጋፍ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ አስቻይ ሁኔታዎችን የፈጠረ ፤ ለለውጥ ኃይሉ አቅምና ትምክህት መሆን የቻለ ጭምር ነው።
የለውጥ ኃይሉም ከቀደሙት ሀገራዊ ተሞክሮዎች በመነሳት ለውጡ በሰላማዊ መንደገድ በይቅርታ እና በመደመር መንፈስ እንዲቀጥል ረጅም መንገድ ተጉዟል። ለቀደመው ስህተት ሕዝብን ይቅርታ ከመጠየቅ ጀምሮ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን ፈትቷል ፤በስደት ከሀገር የወጡትን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ተቀብሏል።
በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት በብዙ መልኩ የተሸረሸረው ኢትዮጵያዊነት ደምቆ እንዲወጣ ፤ የሕዝቡም የፖለቲካ ተሳትፎና በሃገር ጉዳይ የወሳኝነት ሚና ከፍ እንዲል ሠርቷል። በሃገሪቱ ፖለቲካ ከተሳትፎ ባለፈ የውሳኝነት ሚና ያልነበራቸውና በሀገራቸው ጉዳይ አጋር በመባል ሲጠሩ የነበሩ ክልሎች በሃገራቸው ጉዳይ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ የሆኑበትን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፍቷል።
ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፤ በሀገራቱ መካከል የነበረውን በጠላትነት መፈላለግ ከማስቀረት ባለፈ ፣በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን የወንድማማችነት መንፈስ የሚያድስ፤ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያገኘ የሰላም ተግባር አከናውኗል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዓለም አቀፍ የኖቬል የሰላም ተሸላሚ የሆኑበት እውነታ ተከስቷል።
ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የነበረውን ታላቁን የዓባይ ግድብ ግንባታ ችግሮች ፈጥኖ በማጥናት ፤ግንባታው በተሻለ መንገድ የሚከናወንበትን ጠንካራ አመራር ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ነው፤ በሁለት ተርባናይኖች ኤሌክትሪክ የማመንጨት ደረጃ ላይም ደርሷል ።
ለውጡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከባዶ ካዝና ተነስቶ ጦርነት የሚሸከምበት አቅም እንዲኖረው አስችለዋል፤ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ፤በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጭ እየሆነ ነው፤ በስንዴ ላይ የተመዘገበው ስኬት የዚህ ማሳያ ነው።
የሀገር ሕልውና መሠረት የሆኑ የፌደራል ተቋማት/የመከላከያና የጸጥታ ተቋማት /ተልእኳቸውን በግልጽ ከማመላከት ጀምሮ ፤ ተልዕኳቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚወጡበትን አቅም እንዲገነቡ እያደረገ ነው። ይህም ቀደም ባለው ጊዜ እንደሀገር ያጋጠመንን የሕልውና ስጋት እንዳይደገም የሚያስችል ከመሆን ባለፈ ፤ዜጎች ዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በሰላም እንዲመሩ ማስተማመኛ የሚሆን ፤ ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግልም ዋነኛ አቅም ነው።
እነዚህ በለውጥ ኃይሉ የተመዘገቡ ሃገራዊ ስኬቶች አልጋ በአልጋ በሆነ ሀገራዊ ዐውድ የተገኙ አይደሉም ፤የመላውን ሕዝባችንን እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ሁለንተናዊ ድጋፍ ፤ የለውጡን ኃይል አርቆ አስተዋይነትና ከፍ ያለ ቁርጠኛነት ከዚያም ባለፈ ቤተ መንግሥት ጥሎ ጦርሜዳ መገኘትን፤ ከሴራና ከሴራ ፖለቲካ ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥንና ኪሳራን አሸንፎ መውጣትን የጠየቁ ናቸው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2015