በማኅበረሰባችን ውስጥ ልክ እንደሌሎቹ ባሕሎቻችን የምንገለፅበት አልያም ብዙዎቻችንን የሚያመሳስለን ነገር ነው፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ courtesy ይሰኛል፡፡ ትርጉሙ ይበልጥ ሲብራራ ደግሞ መልካም እርዳታ ይባላል፡፡ ሆኖም የሚደረገው መልካም እርዳታ ከራስ ሙሉ ፍላጎት ሳይሆን ሰዎች ምን ይሉኛል ብሎ ከመጨነቅ አልያም ከማፈር ይመነጫል ይለናል የይሉኝታ ጭብጥ ሀሳብ፡፡
ይሉኝታ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ትልቅ ቦታ እንደመስጠት አልያም እንደማክበር ተደርጎ ይወሰዳል። ለረጅም ጊዜ ተለማምድነው የኖርነው ባሕሪ ውጤትም ነው። ይሉኝታ የሚያጠቃው ሰው በማኅበረሰብ ውስጥ ምስጉን፣ የመልካም ባሕሪ ባለቤትና ትሑት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን ነገሩን ከዚህ አስተሳሰብ ወጣ ብለን ከተመለከትነው ‹‹ይሉኝታ ማንን ይጠቅማል?›› ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡
ምክንያቱም ይሉኝታ መልካም እርዳታ ከሚለው አጭር ማብራሪያ በዘለለ እኛ በምንሠራው ፣በምንናገረው፣ አለፍ ሲልም በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ሌሎች ሰዎች ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀድ ወይም በሌሎች ሰዎች ተፅዕኖ ስር ራሳችንን መጣል ከሚለው ትርጓሜ ውጪ ሌላ ማብራሪያ ስለሌለው ነው።
ይሉኝታ ሰዎች ገና አስተያየት ሳይሰጡን ምን ይሉን ይሆናል በሚል ስጋት የምንፈፅመው ድርጊት ወይም የምናሳየው ባሕርይ ነው፡፡ ይህ ባሕርይ ታዲያ በአብዛኛው እኛ ከምንኖርበት አካባቢ በተለያየ ጊዜ እና ሁኔታ በአኗኗራችን ውስጥ በመላመድ ይመጣል፡፡ ለሌሎች ሰዎች ካለን ክብር የተነሳ ስለሌሎች ሰዎች ስሜት እና ባሕሪ ያልተሰጠንን ኃላፊነት ከመሸከምም ይሉኝታ ይመነጫል፡፡
ሰዎች ይሉኝታ የሚያጠቃቸው መቼ ነው?
በተደጋጋሚ የተሠሩ የማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናቶች የሰው ልጅ ተወልዶ ካደገ በኋላ የሚኖረው ባሕሪ ፣ ስብዕና በአብዛኛው የሚገነባው ከውልደቱ እስከ አስር ዓመቱ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን እነዚህ ባሕሪያት ለቀሪ ሕይወቱ የሚጠቀምበት እና ከዛ በኋላ ለመቀየር አስቸጋሪ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ አንድ ሰው በወጣትነቱ /አስር ዓመታት ውስጥ/ የሚያዳብረው ስብዕና በሚቀጥለው ሕይወቱም የእርሱ ማንነት ሆኖ የሚዘልቅ ማለትም እሱነቱን የሚገልፅ እንደሆነ እነዚሁ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ወላጆች የልጆቻቸውን ሕይወትን እንዲረዱ ሥነ-ምግባር የሚያስተምሩበት መንገድ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያሳያል ።
በሀገራችን ደግሞ በሁሉም ጫፍ ተመሳሳይ የልጆች አስተዳደግ መንገድ አለ፡፡ ለምሳሌ ልጆች በልጅነታቸው ለሚያቀርቡት ሀሳብ ተቀባይነት የሌለው ከነተረቱ ‹‹ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም›› እንደሚባለው እንግዳ ሲመጣ ልጆች ቦታ ይለቃሉ፡፡ ልጆች የወላጆቻውን ቁጣ እንዲሁ ከዓይናቸው ብቻ ተረድተው እነርሱ የሚፈልጉትን የሚያደርጉበት ጊዜም አለ፡፡ ‹‹ሰው ቤት ተኺዶ ምግብ አይበላም›› ፣ ‹‹ታላቅ ሲያዝ እምቢ አይባልም›› ፣ ቀደም ቀደም አትበል/አትበይና መሰል አነጋገሮች የልጅነት ትዝታዎች ናቸው።
ልጆች በቤተሰቦቻቸው ተወዳጅ ለመሆን እና እነሱን ለማስደሰት ሲሉ እነዚህንና ሌሎች የተግሳፅ አዘል ትምህርቶችን ያለፍላጎታቸውና ስሜታቸው ሳይፈቅድ ይለምዷቸዋል እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ከሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሲሉ የሚያደርጉት ቀላል ጥበብ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ውስጥ ድብቅ መሆንንና ማስመሰልን ባሕሪያቸው ያደርጉታል፡፡
አንድ ሰው በውስጡ ለሚገነባው የስብዕና መገለጫዎች መጥፎም ይሁን ጥሩ ባሕሪን ለመገንባት ከወላጆች ቀጥሎ ኅብረተሰቡ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን ትውልድን በመቅረፅ ረገድም ሚናው የጎላ ነው። ለአብነትም በማኅበረሰብ ውስጥ ተወዳጅ እና የሚከበር ሰው ብዙውን ጊዜ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ የሚመስል አልያም ሕጉን የሚያከብር ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ በባሕሪው ሙገሳን አብዝቶ የሚወድ በተቃራኒው ደግሞ ነቀፌታንና ትችትን አብዝቶ የሚጠላ በመሆኑ በዚህ አሳሪ ባሕል ውስጥ ራሱን ያገኘዋል፡፡
ይሉኝታ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ በተለያየ መንገድ ከመገለፁ በፊት የአንድ ሰው ባሕሪ ፣ ማንነት ውስጥ እንዲገነባ የሚያደርጉ ሌሎች ባህሎች እና ልማዶች በውስጡ ይይዛል፡፡ ይህም ለታላላቆች ካለን ክብር፣ ልጆች ለቤተሰቦቻቸው ፣ ወጣቶች በእድሜ ለሚበልጧቸው ከሚሰጡት ክብር ይመነጫል፡፡ በአጠቃላይ ለሌሎች የምንሰጠው ቦታ እንደግለሰብ እያደገ ሲመጣ እና ከአቅራቢያችን ባሉ ሰዎች ጫና ሲደረግበት በውስጣችን ካለው በተጨማሪ ሌላ ባሕሪ እንድንገነባ ያደርገናል፡፡ ይህም ይሉንተኛ ያስብለናል፡፡ ከዚህ በሁላችንም ዘንድ ቀስ በቀስ የተገነባው መነሻው አክብሮት የሆነ ባሕል ቢሆንም መድረሻው ግን ወደ ይሉኝታ ተቀይሮ ባሕሪው በሰዎች ላይ የራሱን ጉዳት ያስከትላል፡፡
በዚህ ጊዜ ለምንወዳቸውና ለሚቀርቡን ሰዎች ለሚጠይቁን ነገር ሁሉ እሽታን እንመርጣለን፤ አልያም ለምንጠየቀው እርዳታም ሆነ ሌላ ነገር ሳናውቀውም እያወቅን በራሳችን እምቢተኛነትን እናጣለን፡፡ ሰዎችን ላለማስቀየም ስንል ማድረግ የማንፈልገውን ነገር ለነዛ ሰዎች እናደርጋለን፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ የራሳችን የሆነን ነገር አሳልፈን እስከመስጠት እንደርሳለን፡፡ በዚህም የይሉንተኝነት ባሕሪ እናዳብራለን፡፡ እየበሰልን ስንመጣ ደግሞ ነገሩ በተደጋገመና ይህንን ችግር በራሳችን ላይ ባስተዋልነው ቁጥር ለራሳችንን ያለን ቦታ ዝቅ ይላል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ራሳችንን ወደመውቀስ እንገባለን፡፡ ይህ ደግሞ ለከፋ የሥነ-ልቦና ችግር ያጋልጠናል ።
የይሉኝታ ውለታው/ጥቅሙ/
የምንኖርበት ዓለም የራሷ ሕግ እንዳላት ሁሉ ሀገርም የሚመራበት ሕግ አለ፡፡ በተመሳሳይ ቤተሰብ ከፍ ሲል ማኅበረሰብም አብሮ የመኖር ምክንያት የሆኑ፤ ያልተፃፉና በሰነድ ያልተመዘገቡ ሕጎች አሉ፡፡ እነዚህ ሕጎችም ናቸው በአብሮነት እንድንቆይ የሚያደርጉን። እንግዲህ በዚህ ውስጥ ያን ያህል የማንለውጠው ምናልባትም የማንፈልገው አልያም ደግሞ የማንጎዳበት ነገር ሲያጋጥመን በይሉኝታ እንተወዋለን፡፡
አንዳንድ ጊዜ ጊዜያቸውን ካልጠበቁ እና ጉንጭ አልፋ ብቻ ለሆኑ ክርክሮች ቦታ መስጠት ስለማይኖርብን አልያም ደግሞ ያለንን በጎ ነገር ከማጠልሸት ውጪ የሚጨምሩት ነገር ሳይኖር ሲቀር እንዲሁ ነገሮቹን እንተዋቸዋለን። ይህ ደግሞ በአንድ ሆነን የመኖራችን ሚስጥር ተደርጎ ሊታይ እና ጠቀሜታ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ለዚህ አስረጂ ሊሆን የሚችል ሀሳብ ላቅርብላችሁ፡፡
ሥራ ለመሥራት ወይም ጥናት ለማካሄድ አልያም ለጉብኝት ወደ አንዱ የሀገራችን ክፍል ወደሆኑት ሐመር ወይም አፋር ብትጓዙ የነርሱን ባህልና አኗኗር ማጣጣል አልያም ስህተት ነው ብሎ ለማስረዳት መሞከር ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ጥናት አድራጊው ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን እነርሱን ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከመጥፎ ይልቅ ጥሩ ጎኑ ያመዝናል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ ከብዙ አዳዲስ ሰዎች ጋር እንገናኛለን፤ እንተዋወቃለን። የተለያዩ ሀሳቦችንም እንለዋወጣለን፡፡ በዚህ የግንኙነት ሂደት ለጓደኝነት የምንመርጣቸው ሁሉ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ምናልባትም ፍፁም የማንስማማበት እና የማንቀበለው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ከብዙ አልፊ ክርክሮች በኋላ ሀሳቡን ለማይቀይረው ጓደኛችን ስንል ሀሳቡን ሳይቋጭ እናልፈዋለን፡፡ ታዲያ በዚህ ውስጥ መቻልን እና መተውን ተማርን ማለት አይደል! ነገር ግን ይህም ቢሆን ሊሆን የሚችለው እንዲህ ማድረጉን ላወቀበት ነው።
ሌላኛው ይሉኝታ
ከላይ ከተጠቀሰው በተለየ መልኩ ደግሞ የሰዎች ባሕሪ የሚገነባበት መንገድ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከገጠማቸው ችግር አልያም መጥፎ አጋጣሚ ተነስተው ጥሩ ነገርን ሲቀስሙ ሌሎች ግን እሾህን በእሾህ የሚለውን መርሕ ይከተላሉ ። በሕይወት ጉዟችን ውስጥ ካወቅናቸው ሰዎች መካከል ቦታ የሰጠናቸው በምላሹ ትኩረት ሳይሰጡን ሲቀር እኛም የተከተልነው መንገድ እንደማይሠራ ስናውቅ እነርሱ ያደረጉትን በማድረግ አፀፋውን እንመልሳለን፡፡ ይህ ነው እንግዲህ እሾህን በእሾህ የሚያሰኘው፡፡
በዚህ ሩጫ በበዛበት ዘመን እንዲህ አይነቱ ባሕሪ የሚታይባቸው ሰዎች ከሰዎች ጋር ማውራትንና ትኩረትን ይሻሉ፡፡ እናም በጊዜ ሂደት ትኩረት ሲነፈጉ ይህን ባሕሪ በመላበስ ለነገሮች ትኩረት የማይሰጡ፣ አይተው እንዳላየ የሚያልፉና ግዴለሽ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ‹‹አርፈህ ኑሮህን ኑር ፣ ምን አገባኝ ፣አልደረሰብኝ!›› በሚሉ መሸንገያ ቃላት ተሸፍነው ቆይተው የአንድ ሰው ቋሚ ባሕሪ ከመሆን አልፈው የማኅበረሰብ ችግር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ ሰው ሆይ በአንድ የመኖሪያ መንደር ውስጥ ባልተገባ ቦታ ላይ የተጠራቀመ ቆሻሻ ብትመለከት ‹‹ምን አይነት ሰፈር ነው?›› ከማለትህ በፊት እንድ ቀን በዚያ አካባቢ ስታልፍ ከኪስህ ወይም ከቤትህ ያወጣኸውን ቆሻሻ አለመጣልህን አረጋግጥ። ይህ ደግሞ የሚያመጣቸው የማኅበረሰብ ጣጣዎች በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የአካባቢ በቆሻሻ መበከል፣ የስርቆት ወንጀል ከቀን ወደቀን እየጨመረ መምጣት ፣ በሕፃናት እና በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለ ፆታዊ ጥቃት እና ሌሎችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
ምን ይሻላል?
1ኛ. ትኩረት መስጠት
በየትኛውም የሕይወት መንገድ ውስጥ የምንቀሳቀስባቸውና የምንገኝባቸው ቦታዎች ብሎም የምናጋራቸው ሀሳቦች የኛ ውሳኔ የታከለባቸው መሆኑን ባለመርሳት ሃሳባችን እና ልክ ናቸው ከማለታችን በፊት ደጋግመን ማሰብ ይኖርብናል። ይህም ለአንድ አካል ብቻ የተሰጡ እና ነውር የሚመስሉ ነገሮችን ለምን? ብሎ የመጠየቅ ባሕልን እንድናዳብር እና ባመንበት ነገር ላይ ብቻ የመወሰንን አቅም እንድንለማመድ ያደርገናል። መብታችን መሆኑንም ጭምር እንድንረዳ ያደርገናል፡፡
ይህ በራሳችን ሕይወት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳለው ሆኖ ኃላፊነት ለሚሸከሙ ሰዎች ለቁጥር ማሟያ እጃቸውን የሚያወጡ እና በሌሎች ተፅዕኖ ስር ወድቀው የብዙኃኑን ድምፅ የሚቀበሉ ሳይሆኑ ሀሳባቸውን አዋጥተው በበለጠው ላይ ተስማምተው የሚወስኑ መሪዎች በአነስተኛም ሆነ ከፍ ባሉ ዘርፎች ላይ እንዲፈጠሩና እንዲበራከቱ ያደርጋል ።
2ኛ. የድርሻችንን መወጣት
ድርሻን መወጣት ሲባል ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ እስከላይኛው የሥልጣን እርከን ድረስ ያለውን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ድርሻን መወጣት ልጅ፣ አዋቂ፣ ሀብታም፣ ደሃ፣ ሴት፣ ወንድ አይለም፡፡ ለዚህ አስረጂ ይሆን ዘንድ አንድ ታሪክ ላቅርብላችሁ፡-
በአንድ ሀገር የሚኖሩ አንድ ንጉሥ የሕዝቡን የወተት ችግር ለመፍታት አንድ ትልቅ የወተት ገንዳ እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡ የወተት ገንዳውም በታዘዘው መሠረት ተዘጋጀ። ከዚያም በአካባቢው የሚኖረውን ሰው በሙሉ እያንዳንዳቸው አንድ ብርጭቆ ወተት ወደገንዳው እንዲጨምሩ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ሕዝቡም እንደታዘዘው ማድረግ ጀመረ፡፡ በአካባቢው የሚኖር አንድ ሰው ግን ሁሉም ሰው ወተት የሚጨምር ከሆነ የኔ አንድ ብርጭቆ ውሀ ምንም ለውጥ አያመጣም በማለት ሄዶ የወተት ገንዳ ውስጥ አንድ ብርጭቆ ውሀ ይጨምራል፡፡ ሆኖም በመጨረሻ የወተት ገንዳው ሲታይ በውስጡ የነበረው ወተት ሳይሆን ሙሉ ውሀ ነበር።
አንድን ነገር ለመደገፍ አልያም ለመቃወም የሌሎች ሰዎች ተሳታፊነት ወይም የአብላጫው ድምፅ መሰማት ሳይሆን የእኛ በነገሩ ማመን ትልቅ ለውጥ ያመጣልና ይመለከተኛል ለማለት የሌሎች ሰዎችን እግር መከተል አይጠበቅብንም፡፡ ‹‹ሁሉም ከሄደበት ሁሉም የተው›› እንደሚለው ተረቱ ለራሳችን ዋጋ በሰጠን ቁጥር በየትኛውም ቦታ ብንጓዝ የሚኖረንን ዋጋ እንረዳለን፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠበቅብንን፣የምንችለውንና የድርሻችንን እንድንወጣ ያደርገናል፡፡ ይህ አበርክቶ ታዲያ ከእኛ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል፡፡
ሰሚራ በርሄ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015