ሌባ የማይሰርቀው ትልቅ ሃብት ቢኖር ‹‹የእጅ ሙያ›› ነው፡፡ የእጅ ሙያ ያለው ሰው ምንም ቢያጣ ሙያውን ተጠቅሞ ኑሮን ማሸነፍ እንደሚችል ይታመናል፡፡ በእጅ ያለ ሙያ ከባለቤቱ ጋር አብሮ ያረጀ ይሆናል እንጂ፤ እንደማንኛውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ከእጁ አልያም ከደጃፉ ሌባ ሊሰርቀውም አይችልም፡፡
እርግጥ ነው በቀደመው ጊዜ ሰዎች ለእጅ ሙያ የሚሰጡት ግምት ዝቅተኛ የነበረ መሆኑ ዛሬም ድረስ ለሚታየው የሥራ ባህላችን ደካማነት ዋና ምክንያት ነው። ይሁንና አሁን አሁን ብዙዎች ለእጅ ሙያ ትልቅ ትኩረት ሲሰጡና ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡
ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ የመጣው የእጅ ሙያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ላይ ከዘመኑ ጋር እሽቅድድም የያዘ ይመስላል፡፡ ይህ ሙያ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ መጥቷል፤ የእጅ ሙያ ያላቸው ወገኖች በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በሸክላ፣ በብረታ ብረት ሥራ፣ በአገር ባሕል አልባሳት ማምረት ወይም ማዘጋጀት፣ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችና ጌጣ ጌጥ ማምረት ውስጥ በስፋት ተሰማርተው መታየትም ጀምረዋል ምርታቸውም ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው፡፡
መንግሥት እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ በኩል ሰፋፊ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ መንግሥት በዘረጋው የአሠራር ሥርዓትም ሙያተኞች ከሙያቸው ጋር መገናኘት በመቻላቸው ዘርፉ ለሀገር እና ለሕዝብ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችንም መንግሥት ለተለያዩ የሥራ ዘርፎች በተለይም ለእጅ ሙያ የሰጠውን ትኩረት መሠረት አድርገው እውቀታቸውን ከሙያው ጋር ማገናኘት ከቻሉ መካከል “የኩል ዲዛይን” መሥራቾችን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንዲሉ ኩል ዲዛይን በሁለት ባለሙያዎች ተመሥርቶ ለስኬት በቅቷል፡፡
ባለሙያዎቹ በተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ጥንዶች ናቸው፡፡ ጥንዶቹ ገና ተማሪ እያሉ በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ልምድ አዳብረው ሥራውን የማስፋት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የተማሩትን በሥራ ልምድ ማዳበር ከቻሉ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት ይችላሉ፡፡ ለሌሎችም ይተርፋሉ የሚል ጽኑ እምነት አላቸውና፡፡
ጥንዶቹ እትብታቸው አዲስ አበባ እምብርት ላይ አይቀበር እንጂ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያደጉትና የተማሩት በመዲናዋ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካቴድራል የተከታተለው አቶ እሸቱ ደጉ ኩል ዲዛይንን የመሠረቱት ከባለቤቱ ሳምራዊት አዲሱ ጋር መሆኑን ይገልጻል፡፡ ጥንዶቹ ወደ ዘርፉ ከመግባታቸው አስቀድሞ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ አቶ ደጉ በቴክስታይል ኢንጅነሪንግ፣ ባለቤቱ ወይዘሮ ሳምራዊት ደግሞ በፋሽን ዲዛይን ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ ማግስት ሁለቱም በየፊናቸው በሙያቸው ተቀጥረው ሠርተዋል። ‹‹ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳል›› እንዲሉ ሆነና አቶ እሸቱ፤ በጋርመንትና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ለስድስት ዓመታት ሲሠራ ባለቤቱ ሳምራዊት ደግሞ የፋሽን ዲዛይን መምህርት በመሆን በተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት ውስጥ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት አስተምራለች፡፡
ዕውቀትን በሥራ ልምድ ያካበቱት እነዚህ ጥንዶች ወትሮም ሥራቸውን ማስፋፋት ዓላማቸው ነውና የፋሽን ዲዛይን እና የቴክስታይል ኢንጅነሪንግ ዕውቀትን በሥራ ልምድ አስደግፈው ኩል ዲዛይንን መመሥረት ችለዋል፡፡
ኩል ዲዛይን በጨረታ ተወዳድሮ ከሚያገኛቸው የተለያዩ የደንብ ልብሶች የስፌት ሥራ በተጨማሪ ዘመናዊና ባሕላዊ አልባሳትንም ያመርታል፡፡ ድርጅቱ አልባሳትን አምርቶ ለገበያ ከማቅረብ ባለፈም ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት ባለሙያዎችን እያፈራ ይገኛል፡፡
ዕውቀትና ልምዳቸውን ይዘው ድርጅቱን ለማቋቋም የተነሱት እነዚህ ጥንዶች መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያመቻቸውን ዕድል አሟጠው መጠቀም እንደቻሉና ዕድለኛም እንደሆኑ አቶ እሸቱ ይናገራል፡፡ ሰባት ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የማምረቻ ቦታን ከመንግሥት ያገኙ ሲሆን፤ አዲስ ካፒታል ከተባለ ድርጅት ደግሞ መስፊያ ማሽኖችን በብድር ማግኘት ችለዋል፡፡
በወቅቱ ለዲዛይን ሥራቸው የሚያስፈልግ ሁለት ማሽንና የተመዘገበ 300 ብር መነሻ ካፒታል ይዘው ወደ ሥራ እንደገቡ የሚያስታውሰው አቶ እሸቱ፤ ባለቤቱን ጨምሮ ሙያው በእጃቸው በመሆኑ ከሰው ከሚጠብቁት 100 ብር በራሳቸው ድርጅት ሠርተው የሚያገኙት አንድ ብር የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል ትልቅ ሕልም እንደነበራቸው ይናገራል፡፡
እነ ደጉ ያነገቡትን ትልቅ ሕልም ዕውን ለማድረግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ቀን ከሌሊት በማምረት ለገበያ ማቅረባቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥንዶቹ ሁለት ማሽን ብቻ ይዘው የተለያዩ ዘመናዊና ባሕላዊ እንዲሁም የደንብ ልብሶችን በጥራት ማምረት በመቻላቸው ገበያው ውስጥ በስፋት መግባት ቻሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣውን ሥራ ይበልጥ ማሳደግ የሚቻልበትን መንገድ በመቀየስ ቀድመው የወሰዱትን ብድር መልሰው ተጨማሪ የስፌት ማሽኖችን እና ሠራተኞችን አንድ ሁለት እያሉ አበራከቱ፡፡
ከማምረት ባለፈም አምራች የሆነውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሥልጠና ማዕከል መክፈት ቻሉ። መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሰጠው ትኩረት ለእዚህ ሥራቸው መልካም ዕድል ይዞ መጣ፡፡ ይህን ተከትሎም በርካታ ተቋማት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እየፈለጉ መምጣታቸውን የጠቀሰው አቶ እሸቱ፤ ወደ ሥልጠናው ለመግባት ይበልጥ ያነሳሳቸው ይሄው ምክንያት እንደሆነ ይናገራል፡፡
እነ አቶ እሸቱ በልብስ ስፌት፣ በፋሽን ዲዛይንና በተዛማጅ ዘርፎች ለሙያው ፍቅርና ፍላጎት ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የአጭር ጊዜ ሥልጠና እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ሥልጠናው በዋናነት የሚሰጠው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሲሆን የሦስት ወር፣ የስድስት ወርና የአንድ ዓመት ጊዜን ይፈልጋል፡፡
የአንድ ዓመት ጊዜ ከሚጠይቀው መደበኛ ሥልጠና በተጨማሪም ኦቨር ሎክና ሌሎች ጥቃቅን የሚባሉ የሙያ ዘርፎችን መሰልጠን የፈለገ ደግሞ በ15 ቀናት ውስጥ መሠረታዊ የሆነውን እውቀት ለመጨበጥ መሰልጠን ይችላል፡፡ ለአብነትም አንድ ሰው ወደ ሥልጠና ማዕከሉ መጥቶ የኦቨርሎክ ሙያን ብቻ መሰልጠን እፈልጋለሁ ካለ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሰልጥኖ በፋብሪካዎች መቀጠርና የሥራ ባለቤት መሆን እንደሚቻል አቶ እሸቱ አጫውቶናል፡፡
አቶ እሸቱም ሆነ ወይዘሮ ሳምራዊት አልባሳትን ከማምረትና ከማሰልጠን በተጨማሪም የእጅ ሙያ ባለቤት እንደመሆናቸው ለድርጅቶች የማማከር አገልግሎትም ይሰጣሉ፡፡ በተለይም የቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆነው አቶ እሸቱ፤ በዘርፉ የተሠማሩ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በጥራትና በፍጥነት አምርተው ውጤታማ መሆን እንዲችሉና ሠርቶ መለወጥ የሚያስችላቸውን የክህሎት ሥልጠናና የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። ድርጅቱም በሚያገኘው ሙያዊ የምክር አገልግሎት ማሻሻያዎችን በማድረግ ለለውጥ ይተጋል፡፡ ለአብነትም ኩል ዲዛይን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመንግሥት ተማሪዎች ዩኒፎርምን ከዲዛይን ጀምሮ አማካሪ ወይም ዲዛይነር በሚል የቁጥጥር ሥራ ሠርቷል፡፡
አንድን ልብስ በጥራት፣ በፍጥነትና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ማቅረብ በገበያ ውስጥ ተፈላጊነትን ይጨምራል የሚለው አቶ እሸቱ፤ የገበያ መዳረሻቸው በስፋት መርካቶ እንደሆነም ይናገራል፤ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም ደንበኞቻቸው መሆናቸውም ሌላው ገበያ ውስጥ በስፋት መግባት እንዲችሉ እንዳደረጋቸው ይናገራል፡፡
ሁለት ማሽኖችን ይዞ በሰባት ካሬ ሜትር ቦታ ወደ ሥራ የገባው ኩል ዲዛይን፤ የፋሽን ዲዛይን፣ የስፌት ሥራውንና ሥልጠናውን አንድ ሁለት እያለ ማሳደግ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመስፊያ ማሽኖቹን 65 ማድረስ የቻለ ሲሆን፤ የማምረቻ ቦታውም 80 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታን ይሸፍናል፡፡ 300 ተብሎ የተመዘገበው መነሻ ካፒታልም ዛሬ ላይ ከሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ብር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ለሁለት የተጀመረው ሥራ አሁን 47 ለሚደርሱ ሠራተኞች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ከፋሽን ዲዛይንና ስፌት ሥራው ጎን ለጎን በሚሰጡት ሙያዊ ሥልጠናም በርካቶችን ሌባ የማይሰርቀው የሙያ ባለቤት ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይም ሙያው እንዲኖራቸው ፍላጎት እያላቸው በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ወደ ኋላ የቀሩ የተለያዩ የማኅበረሰቡ አካላትን የሙያ ባለቤት ማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ ለአብነትም ከስደት ተመላሽ የሆኑ ዜጎች፣ የገቢ ምንጭ የሌላቸውና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
አቶ እሸቱ የኩል ዲዛይን ድርጅት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ስለሚገኝ እገዛ የሚስፈልጋቸውን ዜጎችንም ከዚያው ከወረዳው እንደሚያገኝ ያስረዳል። ተደራሽነትን ለማስፋት በቅርቡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ሁለተኛውን ቅርንጫፍ እንደከፈቱም ይናገራል። በዚህ አካባቢ ለሚገኙ አቅም ለሌላቸው ዜጎችም ተመሳሳይ እገዛ እንደሚያደርጉ ይገልፃል፡፡ ከድጋፋቸው ባሻገር ተቋሙ በዲዛይን፣ በስፌትና በሌሎች ዘርፎች መደበኛ ሥልጠናውን በአምስት ፈረቃ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአንድ ፈረቃ 30 ሰልጣኞችን በማሰልጠን በአንድ ቀን እስከ 150 ለሚደርሱ ተማሪዎች ሥልጠናው ይሰጣል፡፡
በኩል ዲዛይን የሰለጠኑ ሠልጣኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ ሥራው ዓለም የሚቀላቀሉ እንደሆነ የገለጸው አቶ እሸቱ፤ በተማሪዎች ዩኒፎርም ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር መሥራቱ ከከተማ ጋርመንቶች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ጋርመንቶች ጋር በመነጋጋር በኩል በዲዛይን የሠለጠኑ ሠልጣኞችን በእነዚሁ ጋርመንቶች ያስቀጥራቸዋል፡፡ በዚሁ ምክንያትም አብዛኞቹ ሠልጣኞች ሥራ የሚይዙ እንደሆነ ነው ያጫወተን፡፡
በተለይም የነጻ ሥልጠና የሚያገኙ ሠልጣኞችን በፍጥነት ወደ ሥራ የሚያስገባቸው መሆኑን ያነሳው አቶ እሸቱ፤ ለአብነትም በ2014 ዓ.ም 34 የሚደርሱ ሠልጣኞች ሠልጥነው የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በነጻ ሠልጥነው ወደ ሥራ ከተሰማሩት 34 ሰልጣኞች በተጨማሪም በመደበኛው የሥልጠና ጊዜ ገንዘብ ከፍለው ከሰለጠኑት 289 ሰልጣኞች መካከል 115 የሚደርሱት ወደ ሥራ የገቡ ስለመሆናቸው ነው አቶ እሸቱ ያስረዳው፡፡
የተለያዩ አልባሳትን አምርቶ ለገበያ ከማቅረብ በበለጠ በሥልጠናው ዘርፍ ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ዜጎች በአጭር ጊዜ የሙያ ባለቤት እንዲሆኑና የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እየሠራ ያለው ኩል ዲዛይን በዘርፉ ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡ የፋሽን ዲዛይን ዘርፍ ብዙ ሊሠራበት የሚችል ዘርፍ በመሆኑ ለውጤት ቅርብ ነው የሚለው አቶ እሸቱ፤ በተለይም ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት አገር እንደመሆኗ የአለባበስ ባሕሉም በዛው ልክ ሰፊ ቁጥር አለው፡፡ ስለዚህ ይህን እምቅ ሃብት አውጥቶ መጠቀም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎችን ከማስገኘት ባለፈ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የማስተዋወቅ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሯል።
የፋሽን ዲዛይን ከሽመና ጀምሮ በአገሪቱ ያለውን ጥሬ ዕቃ አውጥቶ መጠቀም የሚያስችል ዘርፍ እንደመሆኑ ኢትዮጵያን በፋሽን ዲዛይን ኢንዱስትሪው የማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል አለ የሚለው አቶ እሸቱ፤ ዘርፉን ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ ዘርፉ ከቀደመው ጊዜ በተሻለ መንገድ በተማረና በሠለጠነ የሰው ኃይል እየተመራ መሆኑም ለዘርፉ ዕድገት አይነተኛ ድርሻ አለው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ እንደ ቻይና፣ ቱርክና ሕንድ ከመሳሰሉ አገራት ተርታ የመሰለፍና ተወዳዳሪ የመሆን ሰፊ ዕድል አላት፡፡
ኩል ዲዛይን ሱፍ ወይም ሙሉ ልብስን ጨምሮ የሴት፣ የወንድና የሕጻናትን የተለያዩ አልባሳት በተፈለገው ዲዛይን፣ በጥራትና በጊዜ እያመረተ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ በመቻሉ ተፈላጊ ነው የሚለው አቶ እሸቱ፤ የፋሽን ዲዛይን ሥራ የፈጠራ ችሎታን የሚያሳድግ በመሆኑ በቀጣይም ፈጠራ የታከለበት ሥራን በማጎልበት ማራኪ፣ ሳቢና የማኅበረሰቡን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴት የጠበቁ አልባሳትን በማምረት ቀዳሚ ለመሆን ይተጋል፡፡ በዚህም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል በማለት ሀሳባቡን ቋጭተዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015