ለውጥ ድንገት የሚፈጠርና በሆነ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተጠናቆ የሚያበቃ ክስተት አይደለም። በጊዜ ሂደት ውስጥ ሲብላሉ በቆዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ገፊ ምክንያት የሚፈጠር፤ እንደየባህሪው በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት መመራትን የሚጠይቅ ትልቅ ግለሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ አገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ እውነታ ነው።
ለውጥ ከሁሉም በላይ ከትናንት እና ከትናንት ከሆኑ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ ከወለዷቸው ድርጊቶች የመውጣት መነሳሳት የሚታይበትና ለዚህም የሚሆን ቁርጠኛነት የሚስተዋልበት፤ ከውስጥ የሚመነጭና በአስተሳሰብና በድርጊት እየገዘፈ የሚሄድ፤ በኋላም ገዥ ሆኖ ማኅበረሰብን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሻግር ነው።
በተለይም ድህነት ውስጥ በሚኖሩ ሕዝቦች ውስጥ የሚካሄዱ ለውጦች እና ለውጦቹ ሊገዙላቸው የሚገቡ አስተሳሰቦች፤ በዋነኛነት ድህነትን አሸንፎ መውጣትን ታሳቢ ያደረጉ፤ ድህነትን ከፈጠሩ እና ዕድሜውን ከሚያራዝሙ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ ከወለዷቸው ማህበራዊ ድርጊቶች የራቁ ሊሆን ይገባል። የስኬት አቅምም መመዘኛቸውም ይኸው ነው።
በእኛም አገር የዛሬ አምስት ዓመት የተጀመረው ለውጥ ከመነሻው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች የነበረው፤ በየዘርፉ ለውጥ አምጪ ሪፎርሞችን በመተግበር ድህነትን ታሪክ የማድረግ ዓላማና ተልዕኮ ይዞ የተነሳ ነው። እስካሁን ባለው ሂደትም በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ ተስፋ ሰጪ በሆነ የጉዞ ሂደት ላይ ይገኛል።
አገር እንደ አገር በከፍተኛ የመፍረስ ስጋት ውስጥ በነበረችበት፤ በዚህም ዜጎች ባልተረጋጋ ስሜትና መንፈስ በጭንቀት እና ግራ መጋባት ውስጥ በነበሩባቸው በነዚያ ክፉ ቀናት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ኃይሉ፤ በጊዜው የነበረውን አገራዊ ምስቅልቅል ፈር ለማስያዝ የሄደበት ብስለት የተሞላበት መንገድ፤ የዛሬዋን የተረጋጋች አገር እውን ከማድረግ አልፎ በብዙዎች ዘንድ ለነገ ተስፋ የተጣለባትን አገር መፍጠር እየቻለ ይገኛል።
ባዶ ካዝና፣ በብዙ ክፍተቶች የተሞሉ የጸጥታ ተቋማት፣ ማዕከላዊነት የጎደለው የፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት በእጅጉ እየተገዳደሩት አገር የመታደግ ታሪካዊ ጉዞውን በአገር ፍቅር ስሜት በሕዝብ ታምኖ የጀመረው የለውጥ ኃይሉ፤ ብዙም ሳይራመድ ግልጽ በሆነ ጦርነት፤ በየአካባቢው ታቅደው በሚከሰቱ ግጭቶች፤ በኢኮኖሚ አሻጥር፣ ዓለም አቀፍ ጫና፣ ፋታ በሌለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተፈትኗል።
በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ የሚገኙ የሕዝቡን የለውጥ መሻት የመቆመሪያ ካርድ ማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች፤ ዛሬ አልበቃ ብሏቸው ወደ ትናንቶች ተጉዘው፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ፤ የታሪክ ጠባሳዎችን በመምዘዝ ፤ ለለውጡ ተግዳሮት ሆነዋል። በዚህም የለውጡን ኃይል ብቻ ሳይሆን መላውን ሕዝብ ውድ ዋጋ አስከፍለውታል።
እነዚህ ፈተናዎች ለውጡ ከነበረው ሕዝባዊ ድጋፍ አንጻር፤ የታሰበለትን ያህል በፍጥነት እንዳይጓዝ ተግዳሮት ሆኗል። በተለይም የለውጥ ኃይሉ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማምጣት ገና ከጅምሩ የመጣበትን ትናንቶችን በይቅርታ፤ ዛሬዎችን በውይይትና በድርድር የመሻገር መሻት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈታትነውታል፤ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍልም አስገድደውታል።
ይህ ሁሉ በሆነበትና እየሆነ ባለበት አገራዊ አውድ የለውጥ ኃይሉ በአገርና በመንግሥት ላይ የታወጀውን ግልጽ ጦርነት መላውን ሕዝብ ከጎኑ አሰልፎ ከማምከን ጀምሮ፤ አገርን እንደ አገር በጸና መሠረት ላይ ሊያቆሙ የሚችሉ የፌዴራል ተቋማትን /የመከላከያ፣ የደህንነት .ወዘተ / ዘመናዊ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየገነባ፤ በዚህም የብዙዎችን አድናቆት እየተቸረ ነው።
በዴሞክራሲ እና ፍትህ ተቋማት ግንባታ ዙሪያም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን ጨምሮ ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት የሚሠሩበትን አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ፤ በቀጣይም በመላው ሕዝብ ተሳትፎ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊሸጋገር የሚችል እንደሚሆን ይታመናል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየወቅቱ ያጋጠሙትን ውስጣዊና ውጪያዊ አሻጥሮች/ ሴራዎች ተሻግሮ አሁን ላይ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል፤ ይህም አሁን ካለው አገራዊ ሰላም አንጻር በቀጣይ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን፤ በዚህም ዜጎች የለውጡን ትሩፋት የሚያጣጥሙበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።
የለውጥ ኃይሉ በአምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞው፤ በተለይም ከለውጡ ውስብስብ ባህሪ አንጻር፣ አንድም ለውጡን በአግባቡ ካለመረዳት፣ ከዚያም ባለፈ ከለውጡ ያልተገባ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ከለውጥ ኃይሉ ጋር ሰልፍ ባሳመሩ እና ባልተለወጡ ግለሰቦችና ቡድኖች፤ የለውጡን ዓላማና ተልዕኮ የሚፈታተኑ፤ በዚህም ሕዝብንና አገርን ዋጋ ያስከፈሉ ችግሮች ተከስተዋል።
ተመሳሳይ ችግሮች በለውጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ቢሆኑም፤ ከእንግዲህ ባለው ቀጣይ የለውጥ ጉዞ ለችግሮቹ ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ለውጥ ሂደት ከመሆኑ አንጻር የለውጥ ኃይሉ በአስቸጋሪ ወቅቶች ከአቅም በላይ በሆኑ ገፊ ምክንያቶች ተከስተው በሕዝቡ ውስጥ ቅሬታ የፈጠሩ ጉዳዮችን በማረም፤ ለውጡ በሕዝቡ ውስጥ የነበረውንና ያለውን አመኔታ ማደስ ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015