ልጅነቷ በሳቅ ጨዋታ የተዋዛ አይደለም:: እናትዋን በሞት ያጣችው በሕጻንነት ዕድሜዋ ነው:: የእናት ወግ ፣ የልጅነት ቅብጠት ይሉትን አላየችም:: ባደገችበት የገጠር ቀዬ በታላቅ ወንድሟ መዳፍ ሥር ቆይታለች:: ነፍስ ማወቅ ስትጀምር ግን ክፉ ደጉን ለየች:: ደግ ወንድሟ እንደ እናት አባት መከታ ሆኗታል:: እየደገፈ፣ እየሰሰተ አሳድጓታል::
አበራሽ ደገፋ በዕድሜ ከፍ እስክትል ከመንደር ቀዬው አልራቀችም:: አቅም ከቻለው፣ ቤት ካፈራው ሳትነፈግ አስር ዓመቷን ደፈነች:: ከዚህ ዕድሜዋ በኋላ ግን ብዙ ዓይኖች ከዓይኖቿ ላይ በረከቱ:: መውጫ መግቢያዋን የሚያዩ፣ አረማመዷን የሚቃኙ ሁሉ ከጀርባዋ ተከተሏት:: ልጅነቷን የሻቱ ፣ ዝምድናዋን ፈለጉት:: ፍላጎታቸው ለጋብቻ ፣ ለትዳር ሆነ::
አበራሽ በዕድሜ ገና ልጅ ናት:: የሰዎቹ ፍላጎት ግን ገብቷታል:: ልጅነቷን አሳበው በግዳጅ ሊድሯት መሆኑን አውቃለች:: እሷ ባለችበት ዕድሜ ባል ማግባትን ፣ትዳር መያዝን አትሻም::
ሰዎቹ በአትኩሮት ክትትል ይዘዋል:: እሷ ሀሳባቸው እንዳይሰምር፣ ትመኛለች:: አጋጣሚው መልካም ሆነላት:: የእሷ ስጋት የእነሱ ዕቅድ ዕውን ሳይሆን ቀረ:: አበራሽ በአንድ የቀን ሙሉ ጫንጮን ድንገት ለቃ አዲስ አበባ ገባች::
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ እንደ ገጠር አይደለም:: ድምቀቱ ፣ መብራቱ፣ ኑሮው፣ ከምታውቀው መንደር ይለያል:: ሁሉም ነገር ደስ አላት:: በዚህ ስፍራ አክስቷና ሌሎች ዘመዶቿ አሉ:: ለእንግድነት አልከበደችም:: መልካም ፊቶች በደስታ ተቀበሏት:: የነበረችበትን ረሳች፣ያሳለፈችውን ዘነጋች::
አበራሽ በአክስቷ ቤት ኑሮን ጀመረች:: የከተማ ሕይወት አላስከፋትም:: ሁሉን መስላ ከሁሉ ተግባባች:: ውሎ አድሮ በእሷ ላይ አዲስ ሀሳብ ተመከረ:: ቤት ከምትቀመጥ ሠርታ ብታድር እንደሚበጅ ነገሯት:: ሀሳቡን አልጠላችም:: እየሠራች፣ገንዘብ ብታገኝ፣ አዲስ ልብስና ጫማ ብትገዛ ወደደች:: እጇን ይዘው ከሥራው ጋር አገናኟት:: በእሷ ዕድሜ የተገኘው ሙያ ሞግዚትነት ሆነ::
አበራሽ ጥቂት የቆየችበትን የአክስቷን ቤት ትታ ሥራውን ጀመረች:: አልከበዳትም:: ከእሷ የሚያንስ ሕጻን አዝላና አቅፋ ትውላለች:: የሰጧትን በልታ፣የታዘዘችውን ሠርታ ታድራለች::
ትንሽዋ አበራሽ ከወር በኋላ የወር ደሞዝ ይኖራታል:: እሱ ሲደርስ የልቧ ይሞላል:: የዛኔ ያሻትን ትገዛለች:: ይህን ስታስብ ፈገግታዋ ይደምቃል:: የልጅነት ልቧ ይሞላል:: ደስ እያላት ሥራውን ቀጠለች:: ሕጻኑ ወደዳት፣ ቤተሰቦቹ መረጧት :: መሽቶ ነጋ፣ ቀናት አለፉ::
አሁን አበራሽ የአዲስ አበባ ልጅ ነች:: ዕድገት ውበቷ ጨምሯል:: ድንቡሼ ሰውነቷ ልጅነቷን ይናገር፣ ያሳብቅ ይዟል :: እንዲህ መሆኑ ከዓይን ጥሏታል:: አሁንም በተለየ የሚያይዋት፣ የሚያስተውሏት አልጠፉም::
አንድ ቀን አበራሽ ልጁን አዝላ‹‹እሹሹ..››ስትል ዋለች:: መሸት ሲል ሕጻኑን ለእናቱ አስረክባ ወደ ማረፊያዋ ሄደች:: እንዲህ ማድረግ አዲሷ አይደለም:: ሥራው ሲያልቅ ክፍሏን ዘግታ ጎኗን ታሳርፋለች:: የዛን ቀንም ልክ እንደወትሮው አረፍ ልትል ገብታለች:: ከአፍታ በኋላ ተስፋዋን እያለመች ዕንቅልፍ ይጥላታል:: አበራሽ የዛን ቀን በመስኮቱ በኩል አንድ ድምፅ የሰማች መሰላት:: ደንገጥ ብላ በእርጋታ አጤነችው:: በትክክል መስኮቱን ለመክፈት የሚታገል እጅ አለ:: የልጅነት ልቧ ደነገጠ:: ደግሞ ደጋግሞ ደለቀ::
ጥቂት ቆይቶ መስኮቱ ብርግድ ብሎ የውጭው ብርሃን ወለል አለ እንደፈራችው ነው:: አንድ ሰው ከፊት ለፊቷ ቆሞ ዘሎ ለመግባት ይታገላል:: አውቀዋለች:: የአሠሪዎቿ፣ልጅ የቤቱ ጎረምሳ ነው:: ፈጥና ጩኸቷን አሰማች:: ድምፅዋን የሰሙ ጩኸት ያስደነገጣቸው እየሮጡ ደረሱ:: የሆነውን ሁሉ ሳትደብቅ ተናገረች::
‹‹ውሸታም…››
አሠሪዎቿ ከእሷ የሰሙትን ሐቅ አልተቀበሉም:: የእነሱ ልጅ እሷን ለመድፈር መስኮት ዘሎ እንደማይገባ አምነዋል:: የልጁ ድርጊት ፈጽሞ ከክፋት አልታየም:: አበራሽ ግን ጥፋተኛ ተደርጋ መወቀስ ይዛለች:: ‹‹ውሸታም›› ተብላለች:: ይህ እውነት እሷን ከእነሱ አስታርቆ የሚያዘልቃት አልሆነም:: አፍታ አልቆየችም:: የእጇን ጥላ፣ የያዘችውን ትታ ቤቱን ለቃ ወጣች::
አበራሽ የለፋችበትን፣የጉልበቷን ዋጋ አልጠየቀችም:: ስትገባ በትንሸዋ ቦርሳ ያኖረቻትን ገንዘብ ጭምር ትታ ወጥታለች:: የሆነባት ክፋት ሳይታሰብ ነገሮች በእሷ መሳበባቸው አስከፍቷታል:: ወደ ቤት ስትመለስ አክስቷ ፊት አልነሷትም:: ጥቂት ቀን ተረጋግታ ሌላ አማራጭ ፈለገች:: በየቤቱ እየዞረች ልብስ አጠባ ጀመረች::
አሁን አበራሽ ዕድሜ ጨምራለች፣ ከአምናው ዘንድሮ፣ ውስጧ በስሏል:: የአዲስ አበባን ሕይወት እየገባት፣ እያወቀችው ነው:: ከዚህ በኋላ በአክስቷ ቤት መኖር አትሻም:: ራሷን መቻል ፈልጋለች:: ያሰበችው አልቀረም:: ቤት ተከራይታ ኑሮ ጀመረች::
ሕይወት ራስን በመምራት ቀጠለ:: በገቢዋ ኪራይዋን ከፍላ ቤት ጓዳዋን ትሞላለች:: የቀራትን ጥቂት ይዛ ስለ ነገ ታስባለች:: አከራይዋ ሴት ይወዷታል:: ጨዋነቷን ፣ የዕለት ብርታቷን ያደንቁታል:: አበራሽ ግቢው ‹‹አባዬ›› ብሎ ለሚጠራቸው ወይዘሮ ልዩ ፍቅር አላት:: እንደ እናት ትወዳቸዋለች:: ሁሌም ያሏትን ትሰማለች፣ ቃላቸውን ታከብራለች::
የአባዬ ምክር
አንድ ቀን አባዬ ማልደው ተነሱ:: አበራሽን እያስተዋሉም እንደሚፈልጓት ነገሯት:: አክባሪያቸው ናትና ከፊታቸው ቆመች:: አባዬ ኮስተር ብለው ንግግር ጀመሩ:: የብቸኝነት ኑሮ እንደማይበጅ ደጋግመው ነገሯት:: ከልብ ሰማቻቸው:: በዚህ ብቻ አልቆሙም:: ያሰቡትን፣ለእሷ የተመኙትን ዕቅድ ዘረዘሩላት፣ለጊዜው ግራ ገባት:: ቀስ እያሉ አስረዷት:: አልተቃወመችም:: በዝምታ አንገቷን ደፍታ ሰ ማቻቸው::
ወይዘሮዋ ለአበራሽ ለእሷ ትዳርን አስበዋል:: ያጩላት ደግሞ ከዕድሜዋ የሚልቅ፣ ምራቁን የዋጠ ሰው ነው:: ሰውዬው ከአበራሽ፣ እሷም ከእሱ እውቂያ የላቸውም:: የአክባሪ እናቷን እጅ አልገፋችም:: ባሏት ተስማምታ ቃላቸውን አከበረች:: ካጩላት ሰው ተዋውቃ ቤት ጎጆ መሠረተች::
አበራሽ የትዳር አጋሯን ካገኘች ወዲህ ብቸኝነቷ ቀርቷል:: ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት›› ይሉት ብሂል እውነት መሆኑ ገብቷታል:: አንዳንዴ ባለቤቷ ሀገሩ መግባት እንደሚፈልግ ይነግራታል:: ይህ እውነታ ለእሷ ያስጨንቃታል :: በትዳር ሁለት ዓመታት አልፈዋል:: ከዚህ በኋላ ለብቻ መኖርን አትሻም:: ይህን ስታስብ ታዝናለች፣ ትተክዛለች::
በድንገት
አንድ ማለዳ አበራሽ እግሯ ከሆስፒታል አደረሳት:: የመረመራት ሐኪም በእጁ የያዘውን ወረቀት እያስተዋለ ነፍሰጡር መሆኗን አበሰራት:: ደነገጠች፣ተደሰተች:: ይህ አጋጣሚ ለባለቤቷ እጥፍ የምሥራች ሆነ:: የእሷ ማርገዝ ሀሳቡን አስለወጠ:: መንገድ ያሰበው ልቡ ወደ ቤቱ ተመለሰ::
ከወራት በኋላ አበራሽ የሴት ልጅ እናት ሆነች:: የጥንዶቹ ሕይወት በልጅ በረከት ታድሶ ቤታቸው ሞቀ:: ልጅቷ ማደግ፣መሮጥ ስትጀምር ተጨማሪ ገቢ አስፈለጋቸው:: የቤቱ አባወራ በጥበቃ ሥራ ጥቂት ገቢ ያመጣል:: መኖሪያቸው በኪራይ ነውና ተጨማሪ አቅም ያሻል::
አበራሽ ትንሽዋን ልጅ አዝላ ልብስ አጠባ ትውላለች:: በላብ በወዟ የምታገኘው ጥቂት ገንዘብ የልብ አያደርስም:: ከባለቤቷ ገቢ ተዳምሮ ለጎጇቸው ይውላል::
የቀን ጎዶሎ
አበራሽ ለኑሮ፣ትዳሯ መልፋቷን ይዛለች:: የትም ስትሄድ ልጇን አዝላ፣አስከትላ ነው:: በየሰው ቤት ልብስ ታጥባለች ፣ ሥራ አትንቅም:: ገንዘብ የሚያስገኘውን ሁሉ ትሠራለች:: አንዳንዴ የልብስ አጠባው ጊዜ አይሰጣትም:: ቀኑን ይይዝባታል:: ሁሌም በድካም ውላ ስትመለስ ቤቷን ታስባለች:: ጎጆዋ እንዳይጎድል፣ እጇ እንዳያጣ፣ልጇ እንዳትራብ የማትሠራው የለም ::
ወርሐ ጥቅምት ውርጩ አይሏል:: የጠዋት ማታ ቅዝቃዜው አልተቻለም:: አበራሽ ጊዜ አትመርጥም:: ልብስ አጠባ ባለበት ሁሉ ማልዳ መገኘት ግዴታዋ ነው:: ዕለቱን ከሥራዋ ውላለች:: ካጠበችው የልብስ ክምር የደረቀውን ለይታ አስገብታለች:: ጸሐይ የሚያሻውን አስጥታ ያጠበችበትን ዕቃ መላልሳለች:: ጣጣዋን እንደጨረሰች ልጇን አዝላ መንገድ ጀመረች:: ዛሬ ከወትሮው በተለየ አልቻለችም:: በጣም ርቧታል:: ቤት ገብታ እህል ካፏ እስኪደርስ እየናፈቀች ነው::
ብዙ እያሰበች ከግቢው ወጣች:: ልጇ ከጀርባዋ ተኝታለች:: የእናቲቱ ሆድ ይጮሀል:: አይምሮዋ እንደልማዱ ያስባል:: ቤት ገብታ ማድረግ ያለባትን ታቅዳለች:: ስለነገው ታልማለች:: በዚህ መሐል የረገጠችውን አታውቅም:: በድንገት እግሮቿ ፈጥነው ሸርተት አሉ:: በዋዛ መቆም አልቻለችም:: ከፊቷ ያደናቀፋት ድንጋይ ወደፊት አንሸራቶ በልቧ ድፍት አለች:: አንድ እግሯ ተገንጥሎ የወደቀ መሰላት:: በከባድ ስቃይ ውስጥ ሆና ያዘለቻትን ሕጻን አሰበች:: ከጀርባዋ እንዳለች ናት፣ አልወደቀችም::
የአበራሽን አወዳደቅ ያስተዋሉ መንገደኞች ፈጥነው ሊረዷት፣ ሊያነሷት ሞከሩ:: ቀኝ እግሯ ክፉኛ ተጎድቷል:: ሰውነቷ ይብረከረካል:: ትጮኃለች፣ ታቃስታለች:: ሰዎቹ ምኗን እንደሚይዙ ቸገራቸው:: ልጇን ከጀርባዋ አውርደው፣ እሷን እንደምንም ተሸክመው ከቤቷ አደረሷት::
ጠንካራዋ ሴት እንደዋዛ ከቤት ዋለች:: ስቃይዋ በረከተ፤መንቀሳቀስ መራመድ ተሳናት:: ውሎ አድሮ የወዳጅ ዘመድን ምክር ሰማች:: ከሕክምናው ወጌሻው እንደሚሻል አመነች:: ገጠር ከሚገኘው ወንድሟ ዘንድ መሄድ ግዴታዋ ሆነ::
‹‹እምቢኝ፣አሻፈረኝ››
ሁለት ወራትን ሀገር ቤት ያሳለፈችው አበራሽ ሁነኛ በተባለ ወጌሻ ስትታሽ ከረመች:: ተመልሳ አዲስ አበባ ስትመጣ እግሯ እንደታሰበው አልዳነም:: መሥራት መንቀሳቀስ ተሳናት:: መልሳ ከቤት ብትውል ሆስፒታል መሄድ ግድ አላት:: ሐኪሞች የእግሯን ስር የሰደደ ጉዳት አይተው መቆረጥ እንዳለበት አሳወቋት:: ምላሽዋ ‹‹እምቢኝ ፣ አሻፈረኝ ››ሆነ::
አበራሽ በወጌሻ መታሸቷ እያስቆጫት ነው:: ሕክምናው እግሯ አላግባብ በመታሸቱ እንደቀድሞው እንደማይሆን ጠቁሟታል:: አሁን ሮጣ አታድርም፣እርምጃ ጠፍቷታል፣ አቋሟ ተቀይሯል:: ሁለት ዓመት ያስቆጠረው የሕክምና ክትትል በእንጨት ክራንች ቆማ እንድሄድ አገዛት::
አበራሽ እንደቀድሞው በየሰዉ ቤት ልብስ ማጠብ፣እንጀራ መጋገር ፣መሮጥ መላላክ አልቻለችም:: ቤት ተቀምጦ መዋል ዕጣ ፈንታዋ ሆነ:: በየቀኑ ባለቤቷ ሀገሬ ካልገባሁ፣ ካልሄድኩ ይላታል:: ሁኔታው እያስጨነቃት ታስባለች:: መካሪዎቿ አሁንም ዝም አላሉም:: ‹‹ይበጃል›› ያሉትን ጠቆሟት:: ልጇን ይዛ ልመናውን እንድትሞክር ነገሯት:: አበራሽ ግን አሁንም ‹‹እምቢኝ አሻፈረኝ›› አለች ::
ለመኖር
እሷ ለሕይወቷ ዝም አላለችም:: አልጋዋ ላይ ሆና የሽሮሜዳን ነጠላና ጋቢ መቋጨት ጀመረች:: ቁጭቱ ሲያልቅ ደንበኞቿ ለአንድ ነጠላ ሰባ አምስት ሳንቲም ይከፍሏታል፣ ሳታማረር በምስጋና ትቀበላለች:: ውሎ አድሮ ሥራውን ለመደችው :: ሳንቲሙ ጨምሮ አንድ ብር ከሀምሳ፣ ሁለት ብር፣ እያለ አምስት ብር ሆነላት:: የምታገኘውን ይዛ ለ ልጇ ዳቦ ደረሰች ::
ከዓመታት በኋላ
የትናንቷ ብርቱ ሴት ዛሬ አካል ጉዳተኛ ሆናለች:: በእጆቿ መሐል ክራንች ተደግፋ ኑሮን ለመግፋት ትጓዛለች:: ሩቅ ለመሄድ፣ ካሰበችው ለመድረስ ባትሮጥም ጉዳቷ ብቻውን ሰበብ አልሆናትም:: ዛሬም ጎጇዋን ለማቆም፣ ጓዳዋን ለመሙላት ትጥራለች:: በመልካም ሰዎች በጎነት ከጨረቃ ቤት ተላቃ የቀበሌ ቤት ገብታለች:: ምስጋናዋ ልቋል::
አበራሽ ከሌሎች አካል ጉዳተኛ ወገኖች ጋር ተደራጅታ ጫማዎችን ትሠራለች:: ሁሌም ከቤቷ ተነስታ ከሥራዋ ለመድረስ የትራንስፖርት ውጣ ወረድ እንደፈተናት ነው:: አንዳንዴ ክራንች አጥብቃ የምትይዘበት ብብቷ ይላጣል፣ አውቶቡስ ጥበቃ የምትቆምበት እግሯ ይዝላል:: እሷ ግን የዛሬን ብቻ አታይም:: ትናንት ሳንቲም ለማግኘት የለፋችበትን ጊዜ ታስታውሳለች ፣ የዛሬውን ጥቂት ብር አስባም በበዛ ምስጋና ትውላለች::
አበራሽ አንዳንዴ በሥራ ጉዳይ መርካቶ መሄድ ግድ ይላታል:: መንገዷ ፈተና አያጣውም:: መኖሯን የማያስቡ፣ ስለእሷ የማይጨነቁ እግረኞች ገፍተው ይጥሏታል:: በዚህ አጋጣሚ እጇ ተሰብሯል፣ እግሯ ጉዳት ገጥሞት ተሰፍታ ታክማለች::
አሁን ወይዘሮዋ አንድዬ ልጇ አድጋላታለች:: የዕድሜዋ መጨመር፣የወጣትነቷ ማበብ ያስደስታታል:: አንዳንዴ ደግሞ እንደ እናት ይህ ውበቷ ከሀሳብ ይጥላታል:: የአበራሽ መኖሪያ ቤት ከወንዝ ዳር ነው:: ጠዋት ወጥታ ማታ እክስትመለስ የልጇ ጉዳይ እንዳስጨነቃት ይውላል::
አንገት ሰባሪ
አንድ ቀን አበራሽ ሥራ ውላ ቤት ደረሰች:: እግሯ ደጃፏን እንደረገጠ የሰማችው መርዶ ግን ልቧን ሰበረው:: ልጇ በጎረቤት ጎረምሳ ተደፍራለች:: አካባቢው ወንዝ ዳር በመሆኑ ጩኸቷን ሰምቶ ጎረቤት አልደረሰም:: ይህ የሆነው ‹‹የእኔን አካል ጉዳት በሚያውቁ ሰዎች ነው›› ስትል አመነች:: ይህ እውነት ይበልጥ አንገት አስደፋት:: ጉዳዩን ለሕግ ልታሳውቅ ጣረች:: ውጤቱ እንዳሰበችው አልሆነም:: ሁሉን ለፈጣሪዋ ትታ በነገ ላይ ተስፋ ጣለች::
ከትናንት ዛሬ
አሁን አበራሽ በሥራ ተግታ ትውላለች:: ከትናንት ዛሬ ሕይወቷ መልካም ሆኗል:: የተጎዳው እግሯ በሚያመች ጫማ ታግዞ ይራመዳል:: እጆቿ ክራንች ጨብጠው አካሏን ይደግፋሉ:: ከምንም በላይ ግን በአንድ ልጇ ጉዳይ አዝና አልቀረችም:: ብዙ ያየችባት፣ፈተና የተሻገረችባት ፍሬዋ ዛሬ ኃዘኗ ቀርቶ፣ አንገቷ ቀንቷል:: በወግ ማዕረግ ለሌላ ሰው ተድራለች:: ይህ አይነቱ እውነት የእናት አበራሽን የልብ ቁስል አክሞ ፊቷን ለፈገግታ፣ አንደበቷን ለምስጋና አብቅቷል::
አበራሽ ሁሌም የእግሯን እንጂ የውስጧን ጉዳት አታስብም:: ያሳለፈችው ታሪክ የሕይወቷ አሻራ ነው:: በዛሬው ማንነቷ ጠባሳዋ ሽሯል:: ቁስሏ ጠጓል:: እሷ እግሯ እንጂ ልቧ እንዳልተሰበረ በጽኑ ታምናለች:: ጠንካራዋ ወይዘሮ አበራሽ ደገፋ ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015