የሰላም ጉዳይ ቀልሎ የሚታያቸው አካላት ስለሰላም የሚከፈሉ ከፍ ያሉ ዋጋዎችን አሳንሰው ቢመለከቱ ወይም ትርጉም ባይሰጧቸው ብዙም የሚያስገርም የሚያነጋግር አይሆንም። ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን ተገንዝበው የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የተዘጋጁና የሚከፍሉ ግን በሁለንተናዊ መልኩ የትውልዶች ባለውለታ የመሆናቸው እውነታ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
በተለይም ሀገርና ሕዝብ መስቀለኛ በሆነ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በሚገኙባቸው ወቅቶች የሰላም ሀዋሪያ የሆኑ፣ ስለ ሰላም አበክረው የሚሰሩና የሚሰብኩ እንዲሁም ለዚህም ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ ኃይሎች ሀገርና ሕዝብን በመታደግ ለአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ በር ከፋች የመሆናቸው እውነታ በብዙ ሀገራት ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ነው።
ይህም ሆኖ ሕዝብ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች አሮጌ አስተሳሰቦች እና የእነርሱ መገለጫ የሆኑ ድርጊቶችን ተቃውሞ ንቅናቄ በሚፈጥርበት፤ ንቅናቄውም ፈጣን ለውጥ በሚሻበት ወቅት፤ ይህንን አጋጣሚ ለጥፋት ተልዕኮ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ኃይሎች፤ ግጭቶችን እንደ አንድ የትግል ስትራቴጂ አድርገው መጠቀማቸው የተለመደ ነው።
በአንድ በኩል የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት ተረድቶ ፍላጎቱን ተጨባጭ ለማድረግ የሚንቀሳቀሰውን የለውጥ ኃይል ፋታ በመንሳት ሕዝቡ በለውጥ ኃይሉ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጣ ለማድረግ፤ በሌላ በኩል የለውጥ ኃይሉ ራሱ ከተነሳበት የለውጥ አስተሳሰብ አፈንግጦ ባልተገባ መንገድ እንዲሄድ፤ በዚህም አጠቃላይ ለውጡ ትርጉም አልባ እንዲሆን ግጭትን የትግል ስትራቴጂ አድርገው ይሰራሉ።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን በተጨባጭ የሆነውም ይሄ ነው። ሕዝባችን ብዙ ዋጋ ከፍሎ እውን ያደረገውን ለውጥና ለውጡን የሚመራውን ኃይል በየአካባቢው በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በተፈጠሩ ግጭቶች፤ ግጭቶቹ በሚፈጥሩት ሞት ፣ መፈናቅልና የንብረት ውድመቶች ተስፋ በማስቆረጥ “ለውጥ ድሮ ቀረ ” ወደሚል ትርክት ለመመለስ ብዙ ርቀት ተሄዷል።
ሰላምና የሰላም ጉዳይን በየትኛውም መልኩ የትግል ስትራቴጂ ማድረግ የማይችሉና ተፈጥሯዊ ማንነታቸው የማይፈቅድላቸው አንዳንድ ኃይሎች ስለሰላም የሚከፈል ዋጋ የቱን ያህል ውድ መሆኑን፣ ይህንን ዋጋ ለመክፈል ከፍ ያለ ስብዕና እንደሚጠይቅ መረዳት ሲያቅታቸው ይታያል።
ከሰላም የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ፍሬዎች ሀገርን እንደሀገር ወደ ቀጣይ ያደገ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ዋነኛ አቅሞች መሆናቸውን፤ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻችው፣ ለልጅ ልጆቻቸው የተሻለች ሀገር በመፍጠር ሂደት ውስጥ ሰላም አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ለመቀበልና ለሰላም ተገቢውን ትርጉም ለመስጠት የተዘጋጀ አዕምሮ የላቸውም። ግጭት ግጭትን እየወለደ እነሱንና የእነሱ የሆነውን ጭምር እንደሚበላ ለአፍታ ለማሰብም ፍቃደኛ አይደሉም።
በእነርሱ የተዛባ አስተሳሰብ ዋጋ እየከፈለ ስላለው ዜጋም ሆነ እየወደመ ስላለው የሕዝብ ሀብት የሚያስጨንቃቸው አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ግጭት የትግል ስትራቴጂያቸው ከማድረጋቸው አንጻር፤ የዜጎች ሞትም ሆነ የሀገር ሀብት ውድመት እንደ ስኬት የሚቆጥሩ ናቸው። ለዚህም ነው በሚፈጥሯቸው ግጭቶች ሰለባ የሚሆኑ ዜጎችን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ለማድረግ የሚተጉት።
መንግሥት ዜጎችን ለሞትና መፈናቀል የዳረጉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለማስቆም እያደረገ ያለውን ጥረት ከማንቋሸሽ ጀምሮ ያልተገባ ትርጉም በመስጠት፤ ግጭቶች ዘላቂ ሆነው እንዲቀጥሉ ባላቸው አቅም ሁሉ ከፍ ባለ ድምጽ የሚጮሁትም ከዚህ ባህሪያቸው በመነጨ ነው።
መንግሥት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ያለበትን የሕግና የሞራል ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ አንድም ሰላም ከሁሉም በላይ የሕዝባችን ጥያቄ በመሆኑ፤ ከዚህም ባለፈ የሕዝባችን የመልማት መሻት /ብልጽግና/ ስኬታማ የሚሆነው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት የፖለቲካ ባህልን ስናዳብርና ዘላቂ ሰላም ስናረጋግጥ መሆኑን ከመረዳት ነው። ይህ ደግሞ ሀገርን ለማጽናት ከሚሰራ አመራርና ሀገሩን ከሚወድ ሕዝብ የሚጠበቅ ቀና መንገድ ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2015 ኣ.ም