
አዲስ አበባ፡- የሌሶቱ ፓርላማ በደቡብ አፍሪካ ስር ገብተውብኛል ያላቸውን ሰፋፊ ግዛቶች እንዲመለሱለት በሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ሊወያይ ነው።
በግዙፏ ደቡብ አፍሪካ ተከባ የምትገኘው የትንሽዬዋ አገር ፓርላማ በግዛት ጥያቄው ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ የሚጠበቀው በትናንትናው ዕለት ነው።
ለፓርላማው የቀረበን የውሳኔ ሃሳብ ሰነድ የጠቀሱ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባል እንዳሉት፣ ሌሶቱ በዙሪያዋ ያሉ በደቡብ አፍሪካ ስር የሚገኙ በርካታ ግዛቶች ላይ የይገባኛል ጥያቄን አንስታለች።
ሕግ አውጪዎቹ የደቡብ አፍሪካ “ፍሪ ስቴት ግዛትን በሙሉ፣ የሰሜን እና ኢስተርን ኬፕ ግዛቶችን በከፊል፣ ፑማላንጋን በከፊል እንዲሁም የክዋዙሉናታል ግዛትን የተወሰነ ክፍሎችን” የሌሶቱ ግዛት አድርገው እንዲወስኑ ሃሳብ ቀርቧል።
ሌሶቱ ይገባኛል በሚል ከደቡብ አፍሪካ ለመጠየቅ የተነሳችው አካባቢዎች ደቡብ አፍሪካ ካሏት ዘጠኝ ግዛቶች በአምስቱ ላይ ነው።
የውሳኔ ሃሳቡ ሰነድ እንደሚለው ይህ የሌሶቱ የግዛት ይገባኛል ጥያቄው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ 1962 ያሳለፈው ውሳኔን መሠረት ያደረገ ነው።
በንጉሣዊ አስተዳደር ስር ያለችው ሌሶቱ በደቡብ አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ ተከባ የምትገኝ ትንሽዬ አገር ስትሆን፣ አጠቃላይ እንቅስቃሴዋ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተያያዘ ነው። የሌሶቱ ሕዝብ በተጠቀሱት እና አሁን በደቡብ አፍሪካ ስር በሚገኙት ግዛቶች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር በታሪክ ይነገራል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2015