
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል።ድርጅቱ በሄግ ባካሄደው ጉባዔው፤ አባል ሀገራቱ እ.አ.አ በ2035 ሀገራቱ ከጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው ውስጥ አምስት በመቶ ለመከላከያና ደህንነት ዘርፋቸው ለመመደብ ተስማምተዋል።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ የአባል ሀገራቱን ውሳኔ አድንቀዋል።ለውሳኔው እውን መሆን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ የተነገረላቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በአባል ሀገራቱ መሪዎች አድናቆት ተችሯቸዋል። ትራምፕ የድርጅቱ አባል ሀገራት ለመከላከያና ደህንነት ዘርፋቸው የሚመድቡትን በጀት እንዲጨምሩ በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል። ከውሳኔው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ “ፈጽሞ የማይሳካ ይመስል ነበር። እንዳሳካሁት ነግረውኛል። በእርግጥም ያሳካሁት ይመስለኛል” ብለዋል።
አንዳንዶቹ የድርጅቱ አባል ሀገራት ግን የአምስት በመቶ ውሳኔ ለማሳካት እንደሚቸገሩ አሳውቀዋል።የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ሀገራቸው በሁለት በመቶ የመከላከያ በጀት ላይ እንደምትቆይ ገልጸዋል። ትራምፕ የስፔንን አቋም “መጥፎ” ሲሉ ተችተዋል። ቤልጂየም በበኩሏ የአምስት በመቶ እቅድ እንዲሳካ የተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ማሳካት አጠራጣሪ እንደሆነ ስትገልጽ፤ ስሎቫኪያ ግን የመከላከያዋን በጀት ራሷ እንደምትወስን አቋሟን አሳውቃለች።
ዋና ጸሐፊው ከሦስት ሳምንታት በፊት በብራሰልስ በተካሄደው የድርጅቱ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ የአምስት በመቶ የመከላከያ በጀት እቅድ እ.አ.አ. በ2032 ሙሉ በሙሉ እንዲሳካ ሃሳብ አቅርበው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሃሳባቸው በአባል ሀገራቱ መካከል ክፍፍልን ፈጥሮ ነበር። አንዳንዶቹ አባል ሀገራት የተቀመጠው ጊዜ ረጅም እንደሆነ ሲገልጹ፤ ሌሎቹ ደግሞ አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እቅዱን ለማሳካት የተቀመጠው ጊዜ አጭር እንደሆነ ገልጸዋል።
ሊቱዌኒያ ለ2032 ተብሎ የተቀመጠው ጊዜ በጣም የዘገየ እንደሆነ ገልጻ፤ እቅዱ እንዲሳካ የሚቀመጠው የጊዜ ገደብ ከ2030 ማለፍ እንደሌለበት አቋማን አሳውቃ ነበር። ስዊድን የአምስት በመቶ እቅዱን እ.አ.አ በ2030 እንዲያሳካ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች። የጥምረቱ ባለሥልጣናት በበኩላቸው፤ አባል ሀገራቱ እቅዱን ለማሳካት ከጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው ውስጥ ከሦስት ነጥብ አምስት እስከ ሦስት ነጥብ ሰባት በመቶውን ሊጠይቃቸው እንደሚችል አስረድተው ነበር።
አሜሪካ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮቿ የመከላከያ በጀታቸውንና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉ ስትጠይቅ ነበር። ለባለብዙ ወገን ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ብዙም ግድ የላቸውም ተብለው የሚወቀሱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ በሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ትብብር ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ያቀርባሉ። ፕሬዚዳንቱ የድርጅቱ አብዛኛው ሥራና ኃላፊነት በአሜሪካ ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ብለው ያምናሉ። አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ እንዳልሆነና ለድርጅቱ የሚያደርጉትን መዋጮ እንዲያሳድጉም ደጋግመው ይናገራሉ።“አሜሪካ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች አውሮፓን የምትጠብቀው በምን እዳዋ ነው?” እያሉ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ታዲያ ይህን የአሜሪካ ዛቻ ችላ ማለት ያልፈለጉት የአውሮፓ ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል። ለአብነት ያህል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ለመከላከያ ኃይላቸው የሚመድቡትን በጀት እንደሚጨምሩ አሳውቀዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ርምጃዎች ያሰጓቸው አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች፤ አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት ደጋግመው እየተናገሩ ነው።ለአብነት ያህል በቅርቡ ጀርመንን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት መራኄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ፤ አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት በፅኑ የሚያምኑ ፖለቲከኛ እንደሆኑ ተገልጿል።
ከአሜሪካ ጫና የተላቀቀ አውሮፓን መገንባት ከዋና ዋና እቅዶቻቸው መካከል አንዱ እንደሆነና ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሚወስዷቸው ርምጃዎች በእጅጉ መበሳጨታቸውን የሚናገሩት ሜትስ፤ የአሜሪካ መንግሥት የአውሮፓ መፃኢ እድል ግድ እንደማይሰጠው በግልጽ ማሳየቱንና አውሮፓ በፍጥነት የራሱ የሆነ መከላከያ ሳያስፈልገው እንደማይቀር ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ውስጥ ያላትን ሚና በአውሮፓ ኃይሎች ለመተካት የሚያስችል እቅድ ስለማዘጋጀታቸው ከሁለት ወራት በፊት ይፋ የሆነ አንድ መረጃ አመልክቷል። እቅዱ ለአውሮፓ ደህንነትና መከላከያ አህጉሩ ራሱ የበለጠውን ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያደርግ ነው ተብሏል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና የኖርዲክ ሀገራት የጦር ኅብረቱን ቅርጽ የሚለውጠውን እቅድ ካዘጋጁት ሀገራት መካከል እንደሚጠቀሱ “ፋይናንሻል ታይምስ” (The Financial Times) ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል።ይህ እቅድ ስኬታማ ከሆነ በትራንስአትላንቲክ ትብብር እጣ ፈንታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያስከትል ይሆናል ተብሏል።
ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የአውሮፓ ፖለቲከኞች የሩሲያ ቀጣይ የወረራ ኢላማ አውሮፓ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ለእዚህም አውሮፓ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት ያሳስባሉ። አውሮፓ በአስተማማኝነት ራሱን መከላከልና ማስከበር የሚችለው በራሱ የመከላከያ ኃይል እንደሆነ የሚያምኑት እነዚህ የአውሮፓ ፖለቲከኞች፤ ከአሜሪካ ጥላ ነፃ የወጣ አውሮፓዊ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ውስጥ ግዙፍ ሚና አላት።ከድርጅቱ ዓመታዊ ወጪ ውስጥ ከ16 በመቶ የሚበልጠውን የምትሸፍነው አሜሪካ ናት። በመላው አውሮፓ እስከ100ሺህ የሚደርስ ጦርም አሰማርታለች። ይህ የሚያሳየው አሜሪካ በአውሮፓ ጸጥታና ደህንነት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላት ነው። ከእዚህ ወሳኝና ግዙፍ የአሜሪካ ሚና አንጻር “አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እያደረጉ ስላልሆነ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፤ አለበለዚያ አሜሪካ ከጥምረቱ አባልነት ልትወጣ ትችላለች” የሚለው የፕሬዚዳንት ትራምፕ ማሳሰቢያ ለድርጅቱ ሕልውና በቀላሉ የሚታይና እንደዋዛ የሚታለፍ ማስጠንቀቂያ አይደለም ተብሏል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም