ለኢኮኖሚ እድገት/ብልጽግና ከሁሉም በላይ ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ነው፤ ስለ ሰላም ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠይቃል። ይህ እውነታ በሌለበት ማኅበረሰባዊ ዐውድ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ሕይወት ለመለወጥ የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ረጅም መንገድ የሚጓዝ አይሆንም ።
በተለይም ተፈጥሮ በብዙ በረከት ያደለቻቸው ፤ ይህንን በረከት በአግባቡ ተጠቅመው የሕዝቦቻቸውን ሕይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ የሚችሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ለሰላማቸው በቂ ጥበቃና ትኩረት መስጠት ከቻሉ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ታሪክ ማድረግ የሚችል አቅም እንዳላቸው ላለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሃገር የሄድንባቸው የፈተና መንገዶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው ።
በሀገሪቱ የለውጥ ኃይሉ መንግሥት መሆኑን ተከትሎ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመረው ሁለንተናዊ ጥረት ገና ከጅምሩ ብዙ ተግዳሮቶች አጋጥሞታል። በሃገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተናበበ እና በተቀናጀ መልኩ ከጦርነት ጀምሮ በተለያዩ ግልጽና ስውር ደባዎች/ሴራዎች ተፈትኗል። ድህነትን መታገል የቱን ያህል ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አጀንዳ እንደሆነም በተጨባጭ ማረጋገጥ ችሏል።
በአንድ በኩል የሀገርን ስጋት ውስጥ የከተቱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በመመከት ፤በሌላ በኩል የተጀመረውን ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግል አጠናክሮ በመቀጠል፤ሀገራዊ ኢኮኖሚው ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አድርጓል። ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው ይህ እድገት ፤ለውጡ በተነሳበት መንፈስ በሀገራዊ ሰላም ቢታገዝ፣ እድገቱ በምን ደረጃ ሊሰላ እንደሚችል ማሰብ የሚከብድ አይሆንም።
ሀገራዊ ኢኮኖሚው በጦርነትና በግጭት ውስጥ ያስመዘገበው ዕድገት ፤ በሰከነ መንፈስና አእምሮ ማየት ለሚችል ሰብዓዊ ፍጡር ፣ እንደ ሀገር ያለንን የመልማት እድል በተጨባጭ የሚያመላክት ፤ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው ትግል የዜጎች ቁርጠኝነት/ ሁለንተናዊ ድጋፍ ከታከለበት የሩቅ ጊዜ ተስፋ እንደማይሆን በተግባር የሚያሳይ ነው ።
በተለይም ሃገራዊ ኢኮኖሚው ላለፉት አስርና ከዛም በላይ ዓመታት በዘለቁ ችግሮች ሲፈተን የመጣ ከመሆኑ አንጻር ፤ባለፉት አምስት ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች በተለያዩ ሴራዎች ምክንያት የሚገባቸውን ያህል ትርጉም ተሰጥቷቸው የአደባባይ ግዝፈት ባይሆኑም ፤የመጣንባቸው የፈተና መንገዶች የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ታድገውናል።
በዚህም እንደሕዝብ/ሀገር ከዛሬ ተሞክሯችን በአግባቡ ልናጤነው፣ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው፤ ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግና የተሻለች ሀገር ለመጪዎቹ ትውልዶች ለማስረከብ ከሁሉም በላይ የሰላም ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ነው። በተለይም ዘላቂ ልማት በማምጣት ከድህነት ለመውጣት እያደረግን ያለነው ብሔራዊ ጥረት ያለ ሰላም የተሟላ ትርጉም የሚኖረው አይደለም።
ለዚህም ከሁሉም በላይ የድህነት ገፈት ቀማሽ የሆነው ሕዝባችን ፤ ከዚህ አንገት አስደፊ ችግር ወጥቶ ቀና ብሎ መሄድ የሚያስችለውን ሁለንተናዊ አቅም ለመላበስ ሃገራዊ ሰላሙን ባለው አቅም ሁሉ መጠበቅ ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርበታል።
አብረውት በኖሩት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የሰላም እሴቶቹ ራሱን የሰላም ሐዋሪያ በማድረግ ፤ለራሱ ፣ ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ የተመቸች ሰለማዊና የበለጸገች ሀገር መፍጠር ይጠበቅበታል ።
የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጽንፈኛ ኃይሎች ለሚያዜሙት የጥፋት ዜማ ጆሮ በመከልከል፤በብሔራዊ ሰላሙ ለሚቆምሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ዕድል ባለመስጠት ፤ እንደ ሃገር የተጀመረውን እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር ውጤታማ እየሆነ ያለውን ድህነትን ታሪክ የማድረግ እልህ አስጨራሽ ትግል በንቃትና በባለቤትነት መንፈስ ሊሳተፍ ይገባል ።
እንደ ሕዝብ ይህን ማድረግ ከቻልን የአባቶቻችን የነጻነት የተጋድሎ ታሪክ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያጎናጸፉንን ሞገስ ፤በተመሳሳይ መልኩ ከፍ ባለ ጽናት ድህነትን ታሪክ በማድረግ የተሟላ ማድረግ እንችላለን። ይህም እንደቀደመው ዘመን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች አርአያ መሆን የሚያስችል ታሪክ ባለቤት እንድንሆን ዕድል ይፈጥርልናል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2015