የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ለ2023 አፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛና አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከጊኒ ጋር አድርገው አንድም ነጥብ ማሳካት ሳይችሉ ከሞሮኮ ተመልሰዋል። ዋልያዎቹ ባለፈው አርብ 2ለ0 ከትናንት በስቲያ ደግሞ 3ለ2 መሸነፋቸውን ተከትሎ ከወሳኝ ስድስት ነጥቦች አንድም አለማሳካታቸው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው ተስፋ ከሰበሰቡት ነጥብ አኳያ የመነመነ ሆኗል። ከአራቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ አሸንፈው በሌሎቹ በመሸነፋቸው ቀሪ ሁለት ጨዋታ ቢኖራቸውም ወደ ኮትዲቯር ለማቅናት ያላቸውን እድል እጅግ የጠበበ አድርጎታል።
ዋልያዎቹ ከሰበሰቡት ዝቅተኛ ነጥብና እግር ኳሳዊ ምክንያቶች በተለየ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳቸው ውጪ ማድረጋቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚኖራቸውን እድል የጠበበ እንዲሆን ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሚሆን ቀላል ግምት ማስቀመጥ ይቻላል። ዋልያዎቹ የምድቡ ጠንካራ አገር የሆነችው ግብፅን በገለልተኛ ሜዳ ማሸነፍ ቢችሉም የመልሱ ጨዋታ በፈርኦኖቹ ሜዳ እንደመሆኑ ያለፈውን ሽንፈት በድል ለመካስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ግልፅ ነው።
ከማላዊ ጋር የሚኖረው ቀሪው አንድ ጨዋታም ቢሆን እንዳለፉት ሁሉ በገለልተኛ ሜዳ የሚከናወን እንደመሆኑ ዋልያዎቹ ቀላል ፈተና እንደማይገጥማቸው እውን ነው። ሁለቱን ቀሪ ጨዋታዎች ቢያሸንፉ እንኳን ምድቡን ቢያንስ በስድስት ነጥብ ልዩነት አንደኛና ሁለተኛ ሆነው እየመሩ የሚገኙት ጊኒና ግብፅ በቀሪ ሁለት ማጣሪያ ጨዋታዎች ተሸንፈው ዋልያዎቹ በግብ ክፍያ መብለጥ ይኖርባቸዋል። በዚህ ቀላል ስሌት መሰረት የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ አክትሞለታል። ዋልያዎቹ ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበው ተስፋ አልፈው ለአፍሪካ ዋንጫ ይበቃሉ ብሎ ተስፋ ማድረግም ተአምር እንደሚሆን የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው።
በርካታ የዋልያዎቹ ደጋፊዎችም በቀጣዩቹ ጨዋታዎች ላይ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ከጊኒ ጋር በነበረው ፍልሚያ ቢያንስ አንድ ነጥብ ማግኘት የሚቻልበት እድል እግር ኳሳዊ ባልሆነ ምክንያት መምከኑ እያስቆጫቸው ነው። ይህም ዋልያዎቹ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም ባለመኖሩ በገለልተኛ ሜዳ መጫወታቸው ሲሆን፣ የምእራብ አፍሪካ አገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሲጫወቱ የአየር ፀባዩ የሚከብዳቸው እንደመሆኑ ቢያንስ ከጊኒው የደርሶ መልስ ጨዋታ አንድ ነጥብ የሚገኝበት እድል ጠባብ አልነበረም የሚል ቁጭት በብዙዎች ዘንድ አድሯል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ዋልያዎቹ በጊኒ 3 ለ 2 ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋቸው ጠባብ መሆኑን በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል። “ፍላጎታችን ቀጣይ አፍሪካ ዋንጫ ላይ መገኘት ነው። በፍላጎት ደረጃ ይሄ ነው። በነጥብ ደረጃ ግን ይሄንን የሚያመላክት ነገር አይደለም እያየን ያለ ነው። ያ እንዳይርቅ መስራት ነው ያለብን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በየሁለት ዓመቱ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ስትገኝ የነበረች ሀገር እንዳልሆነች ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ ያ የራቀውን ነገር ለማሳጠር መሞከር ነው” በማለት አሰልጣኙ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አክለውም፣ “አፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመካፈል የምንፈልግ ከሆነ ውጤት መያዝ አለብን። ቢበዛ ነጥቡ ደግሞ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ነበር ፤ ይህ አልሆነም። ለዚህ ግን እንደ መሠረታዊ ነገር አድርጌ የምቆጥረው የመጀመሪያውን ጨዋታ በምንፈልገው መንገድ አለመቆጣጠራችን ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ያለን ዕድል በጣም ጠባብ ነው። በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይም የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል። ከውድድር አንጻር አስቸጋሪ ነገር ውስጥ ነው ያለነው። እርግጥ 100% የማለፍ ዕድላችን አክትሟል ማለት አይቻልም። በሂሳባዊ ስሌት ሙሉ ለሙሉ ውጪ አይደለንም፤ ግን ዕድሉ የጠበበ ነው” ብለዋል።
እንደ አሰልጣኙ ገለፃ፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አይነት ብሔራዊ ቡድን በወጥነት ለረጅም ጊዜ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማግኘት ከባድ ነው። ከግብፁ ጨዋታ በኋላ እንኳን የተወሰነ የተጫዋች ልዩነት አለ። በወጥነት የሚጫወቱ ተጫዋቾችንም ማግኘት አንዱ ክፍተት ነው። እንደ ሌሎች ቡድኖች በወጥነት አምስት እና ስድስት ዓመት የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማግኘት አልተቻለም።
“ከእኔ በብዙ እጥፍ አቅም ያለው ሰው በዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ ያሉት እነዚሁ ተጫዋቾች ናቸው፣ እኛ ካልቻልን ደግሞ የሚችል አካል በቅርብ ጊዜ ወደዛ እንዲመለስ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፣ ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ያለን ዕድል በጣም ጠባብ ነው፣ ዞሮ ዞሮ የፈለከው አይነት አቅም ቢኖርህ ፤ ከእኔ በብዙ እጥፍ አቅም ያለው ሰው በዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ ያሉት እነዚሁ ተጫዋቾች ናቸው። ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን የማፍራት ስራ ላይ እንደ ሀገር መትጋት ያለብን ይመስለኛል ፤ ባለው ነገር ግን የምንችለውን ነገር ለማሳየት ሞክረናል” ሲሉም አብራርተዋል።
“እኛ ካልቻልን ደግሞ የሚችል አካል በቅርብ ጊዜ ወደዛ እንዲመለስ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ” በማለት ስለቀጣዩ ጉዞ ፍንጭ የሰጡት አሰልጣኙ በቅርቡ ተጨማሪ ሁለት ዓመት ኮንትራት ሲሰጣቸው ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ሃላፊነት እንደተጣለባቸው ይታወሳል። ይህንን ማሳካት ካልቻሉም የመሰናበት እድላቸው ሰፊ እንደሚሆን ከፌዴሬሽኑ ጋር ውል ባሰሩበት ወቅት ተጠቁሞ ነበር። የአሰልጣኙ አስተያየትም ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፋቸው ነገር ጠባብ መሆኑን ከመግለፁ በተጨማሪ እሳቸውም ከቡድኑ ጋር የመለያየታቸው ጉዳይ ሩቅ እንደማይሆን ጠቋሚ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015