
ሰሞኑን አንዲት የቤት ሰራተኛ ሕጻን ልጅ ይዛ ጠፍታ በፖሊስ ጥበባዊ የምርመራ ስልት ተገኝታለች፡፡እንዲህ አይነት የፖሊስ የምርመራ ጥበቦች ያስደምማሉ። መኖር ማለት እንዲህ ህሊናን የሚያረካ ሥራ ሲሰራ ነው ያሰኛል፡፡ ‹‹አሁን እኔም አገሬን አገለገልኩ ነው የምል!›› ብለን ራሳችንን እንድንታዘብ ያደርገናል፡፡በእርግጥ ለመቆርቆርም የአገር ስሜት ሊኖር ይገባል፡፡
እንዲህ አይነት አገርንም፣ የግል ህሊናንም የሚያኮሩ ሥራዎች የሚሰሩት ሙያን ከልብ መውደድ ሲኖር ነው። ሦስት ገጠመኞችን ለማሳያነት ልጥቀስ፡፡የመጀመሪያው ከፖሊስ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ከሦስት ይሁን አራት ዓመት በፊት ከመስክ ሥራ በአንድ አነስተኛ ተሽከርካሪ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ እሄድን ነው፡፡ ደጀን ስንደርስ ሁለት ፖሊሶች ቦታ መኖሩን ፈቃድ ጠይቀው ገቡ፡፡የሚሄዱት ዓባይ ድልድይ ነው፡፡ደጀንን አልፈን ቁልቁለቱን እየወረድን ሳለ ከርቀት የሆኑ ወጣቶች ሲሯሯጡ ተመለከቱ፡፡ ከፖሊሶች ውጭ ማንም አላስተዋለም ነበር፡፡
ሙያውን የሚወድ ፖሊስ የንሥር ዓይን ነውና ያለው ከርቀት ተመልክተዋል፡፡ አሽከርካሪውን እንዲያቆም ላቸው ጠይቀው ዱብ ዱብ አሉ፡፡ ያንን ጥሻ እና ወጣ ገባ በእግራቸው ማቆራረጥ ጀመሩ፡፡እኛም ሁኔታውን ለማየት ዓይናችን ማየት እስከቻለው ድረስ መከታተል ጀመርን፡፡
ከውስጣችን፤ አንዳንዶች መጀመሪያውኑም የመጡት የሚፈልጉት ሰው ቢኖር ነው እንጂ ዓባይ ድልድይ ሊወርዱ አልነበረም ማለት ጀመሩ፤ ሊሆን ይችላል ብለን ተቀበልናቸው፡፡ቁልቁለቱን ወርደን ታች ስንደርስ ሁነቱን የተመለከቱ በየመንገዱ ዳር የነበሩ ሰዎችን ጠየቅን፡፡ነገርየው ድንገት የተፈጠረ ነበር፡፡ከታች ሲመጣ የነበረ ቢራ የጫነ ተሽከርካሪ በድንጋይ ሊመቱ ሲሉ በአሽከርካሪውና በአካባቢው ሰዎች የሚሯሯጡ ናቸው፡፡ታች ስንደርስ ተሽከርካሪውንም አገኘነው፡፡
ስለዚህ ፖሊሶች ከደጀን የመጡት ይህን አስበው አልነበረም፤ ሲጀመር ለተራ የመንገድ ዳር ሌባ የፖሊስ ዝውውርም ሊደረግ አይችልም፡፡በእነዚያ ፖሊሶች የሙያ ታማኝነትና ልባዊ አገልጋይነት እየተገረምን መጨረሻውን ሳናውቅ ተሻገርን፡፡
ይህን ለማለት ያስገደደን ብዙ ጊዜ በአንዳንድ የፀጥታ አካላት ‹‹ምድቤ አይደለም›› ሲባል ስለምንሰማ ነው፡፡ እነዚያ ፖሊሶች ያ ቦታ ምድባቸው እንዳልሆነ ይታወቃል። ግን የፖሊስነት ሥራቸውን ገደብ አላደረጉበትም፡፡ ህሊናቸው አልፈቀደላቸውም፡፡ የሚሰ ሩት ለሥራ ብለው ሳይሆን ለሙያዊ ህሊናቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ሲጠቀመው ያየሁት ጥበብ ነው፡፡ይህን ጥበብ ብዙ የትራፊክ ፖሊሶች ቢጠቀሙት ብልሹ አሰራር ይቀረፍ ነበር፡፡ ከልብ ከሰሩ እንዲህ ነው!
ከአንድ የገጠር አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እየሄድኩ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የገጠር አካባቢዎች ከታሪፍ በላይ ነው የሚያስከፍሉት፡፡ ትራፊኩ ይህን ያውቃል። ትራፊኮች ሆን ብለው ያሳልፏቸዋል የሚባል ሀሜት አለ፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ገንዘብ እየተቀበሉ ዝም ይሏቸዋል ይባላል፡፡ብዙ ጊዜ እንደታዘብኩትም በር ላይ ሆነው ለይምሰል ‹‹በታሪፉ ነው የከፈላችሁ?›› ይላሉ። ደፍሮ የሚናገር ስለሌለ የተወሰነ ሰው ‹‹አዎ!›› ይላል። ላይቀጧቸው ለምን ትዝብት አስተርፋለሁ በሚል ጭምር ማለት ነው፡፡
ይህ ትራፊክ ግን እንደሌሎች ማድረግ አልፈለገም። ምን አይነት ሰዎች እንደሚዋሹም ያውቃል፡፡ወጣቶች፣ በአለባበስም ሆነ አነጋገር የተማሩ የሚመስሉ፣ ከተማ ቀመስ ሰዎች ‹‹አራዳ›› ለመምሰል በሚል ሀቁን አይናገሩም። ይህ የገባው ትራፊክ ተሽከርካሪውን አስቁሞ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ቀለል እና ፈገግ ባለ አነጋገር ስለጉዞ ጠየቀ፡፡ በር አካባቢ ያሉ ሊዋሹ የሚችሉ ሰዎችን አልፎ ወደ መሐል ዘለቀ፡፡ አንዲት ነጭ ሻሽ ያደረጉ ሴትዮ (መነኩሴ ሊሆኑ ይችላሉ) ጠጋ ብሎ ‹‹ጉዞ እንዴት ነው?›› ብሎ ቀለል አድርጎ የከፈሉትን ጠየቃቸው፡፡ ሀቁን ተናገሩ። ወደ ሾፌሩ ሄዶ ተገቢውን ቅጣት ሰጠው!
ይህን ያነሳሁት ትልቅ ‹‹ኦፕሬሽን›› ሆኖ አይደለም። ዳሩ ግን ብዙዎች የይምሰል ሥራ ስለሚሰሩ እንዲህም ከልብ የሚሰሩ አሉ የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ ሦስተኛው ገጠመኝ ከዓመት በፊት አንድ መምህር ሲያደርገው ያየሁት ነው፡፡ኮከበ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በር ላይ ነው፡፡ሰዓቱ ረፈድ ብሏል፡፡ተማሪዎች ስላረፈዱ ክፍል ውስጥ አትገቡም ተብለው ይሁን ስለረፈደ መግባት ፈርተው አላውቅም በር አካባበቢ ተማሪዎች ቆመዋል፡፡
አራት ይሁኑ አምስት ተማሪዎች በትራንስፖርት መጠበቂያ መጠለያው በኩል ከጀርባ ዞረው የደንብ ልብሳቸውን በሌላ ልብስ ይቀይራሉ፡፡አንድ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ግን ዝም ብሎ ታዝቦ ማለፍ አልቻለም፡፡ጠጋ ብሎ አናገራቸው፤ መምህር መሆኑንም ነገራቸው፡፡መምህራዊ ተግሳጽ ገሰጻቸው፡፡ደስ የሚለው ተማሪዎችም በትህትና ነበር የተቀበሉት፡፡
ያ መምህር የዚያ ትምህርት ቤት መምህር አይደለም። እነዚያ ልጆች ያንን በማድረጋቸው ዝም ብሎ ቢያልፍ ተጠያቂ የሚሆንበት ምንም ነገር የለም፡፡ግን የሚሰራው ለደሞዝ ብቻ አልነበረም፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ብቻ አልነበረም፡፡ የሚሰራው ለሙያውና ህሊናው ነው! ለአለቃ ተጠያቂነት ሳይሆን ለህሊና ተጠያቂነት ነው የሚሰራው፡፡ሙያን ሲወዱ ደግሞ እንዲህ ነው!
ከላይ የገለጽኳቸው ሦስቱም ገጠመኞች ሙያን ከመውደድ የሚመጡ ናቸው፡፡ከልብ በመሥራት የሚገኙ ናቸው፡፡ ተቆጥሮ ለተሰጠ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ቃል ለገቡለት ሙያ ከልብ መታመንን የሚያሳዩ ናቸው፡፡የሰዓትና የቦታ ገደብ የሌላቸው ናቸው፡፡
ሙያን መውደድ ሌሎችን መጥቀም መሆኑ ግልጽ ነው፤ ከዚያ በላይ ግን ራስንም ጤነኛ ማድረግ ነው። አንድ ሰው ሙያውን ሲወድ ደስተኛ ይሆናል፡፡የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማውም፤ ነጭናጫ አይሆንም። በትንሽ ትልቁ አያማርርም፡፡
ለምሳሌ ከላይ የገለጽኳቸው ፖሊስም ሆነ መምህር በሙያቸው ልክ ክፍያ የሚከፈላቸው አይደሉም፡፡ለእነዚህ ባለሙያዎች ግን ሙያቸው ከዚያ በላይ ነው። ለእንጀራ ብቻ አይደለም እየኖሩ ያሉት፡፡ ያ መምህር የኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት መምህር አይደለም፤ ቢሆን እንኳን ተማሪዎችን ውጭ ለውጭ የመከታተል ግዴታ የለበትም፤ የህሊና ግዴታ ግን አለበት፡፡የህሊና ግዴታ ደግሞ በቅንነትና ሙያን በመውደድ የሚመጣ ነው፡፡
እነዚያ ፖሊሶች ልግመኛ ቢሆኑ ኖሮ ምድባችን አይደለም ብለው ማለፍ ይችሉ ነበር፤ ቃል የገቡለት ሙያቸው ግን ይህን ልግመት አልፈቀደላቸውም፡፡ ሁላችንም ቃል ለገባንለት ሙያና ኃላፊነት እንዲህ በቅን ልቦና ብንሰራ አገራችን የት በደረሰች ነበር! ሙያን መውደድ ለራስም ለአገርም ነው፡፡አገርንም ራስንም የሚጎዱ ችግሮች የሚፈጠሩት ሙያን ካለመውደድና ያልተገባ ጥቅም ከመፈለግ ነው፡፡
ስለዚህ ሙያችንን እንውደድ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015