የአንድ ሃገር እና ሕዝብ ብሩህ ነገዎች የሚወሰኑት በዚያ ሃገርና ሕዝብ ውስጥ ባሉ ተራማጅ /ያደጉ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ ባላቸው ሕዝባዊ መሠረት/ተቀባይነት ነው። ከዚህ ውጪ ያሉ የትኛውም አይነት አማራጮች የሃገርን ነገዎች ከማጨለም ባለፈ ሊፈጥሩ የሚችሉት አንዳች ነገር እንደሌለ የሀገራት ተሞክሮ በግልፅ የሚያመላክተው እውነታ ነው።
በተለይም በኃይል ፤ በሴራ እና በጽንፈኛ አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የአንድ ሀገርን ነገዎች ብቻ ሳይሆን የብዙ ትውልዶችን ዕጣ ፈንታ ጽልመት የሚያለብሱ ፤ ትውልድ ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ እንዲኖር የሚያስገድዱ ፤ ሃገርን በማያቋርጥ የግጭት ማዕበል ውስጥ በመጨመር ዜጎች በነገዎቻቸው ላይ ተስፋ እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ናቸው።
ለዚህ እውነታ አስረጅ ፍለጋ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። እንደሃገር የመጣንበት የፖለቲካ ባሕላችን ተጨባጭ ማሳያ ሊሆነን የሚችል ነው፤ በተለይም የኃይል እና የሴራ ፖለቲካ እንደሃገርና ሕዝብ ያስከፈለንና ዛሬም እያስከፈለን ያለው አላስፈላጊ ዋጋ የአደባባይ ሚስጥር ነው፤ በዚህ ዘመናት ባስቆጠረ አሮጌ የፖለቲካ ባሕል መከፈል የማይገባው ውድ ዋጋ እንደተከፈለም ሊደበቅ የሚችል አይደለም ።
ችግሩ እንኳን በቀደሙት ዘመናት ቀርቶ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ የሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈታተን፣ ሃገርንና ሕዝብን በከፋ መልኩ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ላለፉት አምስት ዓመታት የመጣንበትን የፖለቲካ መንገድና መንገዱ የተገዛበትን የፖለቲካ አስተሳሰብ በአግባቡ መመርመር ተገቢ ነው ።
ኃይል አለኝ ፤ የፖለቲካ መሻቴን በኃይል አስፈጽማለሁ የሚል ቡድን በሀገር ላይ ግልፅ ጦርነት እስከ ማወጅ የደረሰበት ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍላጎቱን በኃይል በሀገር በሕዝብ ላይ ለመጫን አቅም ያጣ ደግሞ በሴራ ፖለቲካ ሌት ተቀን ሲተጋ ፤ በዚህም የሃገር ደህንነት አደጋ ላይ እስከመውደቅ ደርሷል። የንጹሐን ዜጎች ደምም ለፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ ሆኖ በከንቱ ፈሷል።
ይህ ከትናንት ታሪኮቻችን ቆም ብለን ለመማር ካለመፍቀዳችን የሚመነጨው ስህተታችን፤ ሃገራዊ ፖለቲካው ዘመኑንና የሕዝባችንን ፍላጎት በሚዋጅ መልኩ እንዳይታደስ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። ከዚያም በላይ ተራማጅ/የለውጥ አስተሳሰቦች ሕዝባዊ መሠረት ኖሯቸው ሃገር እንደ ሃገር ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዳትሸጋገር ጎታች ፈተና ሆኗል።
ከዚህም ባለፈ የኃይል እና የሴራ ፖለቲካ አቅማችንን እየተፈታተነ ባለበት ሀገራዊ የፖለቲካ ዐውድ ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ጽንፈኛ ኃይሎች እንደሀገር እውን ለማድረግ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ባለው አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ/ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ/ተጨማሪ ፈተና ሆነዋል። በዚህም እየፈጠሩት ያለው ግራ መጋባት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በሕዝብ መካከል አለመተማመንን ከመፍጠር ጀምሮ በየአካበቢው ለተፈጠሩና ለሚፈጠሩ ግጭቶች ፤በግጭቶች ለተከሰቱ የዜጎች ሞት፣ ስደት እና የንብረት ውድመት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ሃገራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍንም ትልቅ ተግዳሮት ሆነዋል። ለውጡ በተጀመረበት ፍጥነት እንዳይጓዝም ፈተና ሆነዋል።
እነዚህን ሃገርን እንደ ሃገር ለረጅም ዘመናት ሲፈታተኑ የቆዩ አሮጌ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በአግባቡ መግራት ካልተቻለና በተለይም የዘመኑ የፖለቲካ ኃይሎች ከዚህ ትውልድን ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍል ከኖረ የአስተሳሰብ ባርነት ራሳቸውን ነፃ ማውጣት ካልቻሉ፤ የሀገርን ነገዎች ብሩህ ወደሚያደርግ ወደ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ማሻገር የሚቻል አይሆንም።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ፤በኃይል፤በሴራ እና በጽንፈኛ አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ማንንም ተጠቃሚ የማያደርጉና ሃገርን እንደሃገር ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ ስለመሆናቸው አበክረው የተናገሩት።
ከዚህ ይልቅ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ባህል በመገንባት የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ ነገዎች ብሩህ ማድረግ እንደሚገባ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት ከሁሉም እንደሚጠበቅ፤ ይህ ዝግጁነት በሚፈጥረው የፖለቲካ ስብዕና ብቻ ሀገርን ማሻገር እንደሚቻል ያስገነዘቡት ።
በርግጥም ለአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላምና ከሰላም ለሚመነጭ ዕድገት/ብልጽግና በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረትና ባሕል አድርጎ ማስቀጠል ወሳኝ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ካለንበት የታሪክ ምዕራፍ የተሻለ አጋጣሚ /ጊዜም ሊኖር አይችልም።
ስለሆነም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመኑንና የሕዝብን ፍላጎት ለሚዋጀው በሀሳብ ልዕልና/የበላይነት ላይ ለተመሠረተ የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሳቸውን ተገዥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህንንም ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ በተግባር ማሳየት ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2015