በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭና አትራፊ ሊግ መመስረትን ዓላማው ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር 4ኛ መደበኛ እና 2ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው ቅዳሜ አከናውኗል። ከተመሰረተ አጭር ጊዜ የሆነው ማህበሩ አዳዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድንም አስመርጧል። ማህበሩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ይሁን እንጂ ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ መልካም የሚባል ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛል።
ውድድሩ በዘመናዊ መልክ እንዲመራ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዕይታን እንዲያገኝም የማህበሩ ሲሰራ ቆይቷል። ይህንን ሁኔታ ለማስቀጠል እንደሚሰራም በተመራጭ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላቱ በኩል አስታውቋል። ከካምፓኒው ምስረታ አንስቶ ያለፉትን ዓመታት በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤ በዚህ ምርጫ ላይም በኢትዮጵያ ቡና እጩ በመሆን ቀርበዋል። በምርጫውም 11 ድምጽ በማግኘት በድጋሚ ለአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ምርጫ ውስጥ በመግባት በድጋሚ በሰብሳቢነት እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል።
ለረጅም ዓመታት በስፖርት አመራርነት የቆዩት አንጋፋው ባለሙያ፤ ሊግ ካምፓኒው ከተቋቋመ ሶስት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ይሁን እንጂ በርካታ ነገሮች የተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። በቅድሚያ የተደረገው በአፍሪካ ትልቅ ከሚባል ተቋም ጋር አብሮ ለመስራት ከስምምነት መድረስ ስኬት ነው። ቀጣዩ ደግሞ ይህንን ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ፣ ክፍያውን እንዲጨምር ማድረግ፣ ሜዳዎች ብቁ የሚሆኑ ከሆነ ደግሞ እንደሌሎች ሀገራት ማስታወቂያዎችን በዘመናዊ መንገድ ማስተላለፍ እንዲሁም ጨዋታዎችን ስፖንሰር የሚያደርጉ ባለሀብቶችን በመጋበዝ ሊጉን ማሳደግ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ይሁንና አሁንም ድረስ ያልተፈታውና በስፖርቱ የጎላ ተግዳሮት በመሆን የቀጠለው ከክለቦች ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በተለይ ራሳቸውን በገንዘብ አለመቻል ተጠቃሽ ነው። መንግሥት በዚህ ወቅት ከመሰረተ ልማት ተርፎ እግር ኳሱን በማስተዳደር አላግባብ የሆነ ወጪ የሚያወጣበት እንዳልሆነ ሰብሳቢው አብራርተዋል። በውጤት ከበርካታ ሀገራት ኋላ የሚገኘው የሀገሪቷ ስፖርት በክፍያ ግን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው። በመሆኑም ክለቦች ሊፈተሹና በተጨባጭ ራሳቸውን ወደሚችሉበት ሁኔታ መመለስ ያስፈልጋቸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፤ ካምፓኒው አዳዲስ ነገሮችን ይዞ የመጣ መሆኑን ገልፀው፣ በስፖርት ንግድ ዘርፍ የተቋቋመ እንደመሆኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተው በአሁኑ ወቅት መልካም በሚባል አቋም ላይ ሊገኝ መቻሉን አብራርተዋል። እንደ አቶ ሰይፈ ገለፃ፣ ሊግ ካምፓኒው በእግር ኳስ ስፖርት ለመሰል ተቋማት መሰረት ሊሆን
የሚችል ስኬታማ ተቋም ነው። ምክንቱም በየዓመቱ 4 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪም በየዓመቱ 250ሺ ዶላር እየጨመረ አሁን ላይ 4 ነጥብ 5ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፤ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 5 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። ይህንን ሁኔታም በቀጣይ አሻሽሎ ስፖንሰር ለሚሆኑ ድርጅቶች መገኘት ይገባዋል። በመሆኑም በማዘውተሪያ፣ በተመልካቾች እና መሰል ነገሮች ላይ በመስራት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይችላል። ለዚህ ደግሞ አዲስ የተመረጠው ቦርድ ከባድ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፤ ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ ከንግድ ሕጉ ጋር ተያይዞ የታዩ ክፍተቶችንም መድፈን አስፈላጊ ነው።
በሌሎች ሀገራት የእግር ኳስ ሊጎች ከሚያገኙት ገቢ መንግሥትን ከመደገደፍ አልፈው በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ተደጋፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ በመሆኑም ይህ መቀየር ይኖርበታል። ይህንን ለመቀየርም አክሲዮን ማህበሩ ከሱፐር ስፖርት ጋር ባለው ስምምነት ጋር በተያያዘ እስካሁን ለማሟላት ያልተቻለው ጥራትን በሚመለከት ነው። ደጋፊ ላይም በተመሳሳይ ተጨማሪ ስራ አስፈላጊ በመሆኑ ስታዲየም ላይ መስራት የግድ ይሆናል።
በጉባኤው ላይ የታደሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራም ምርጫውን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ካምፓኒው ከተመሰረተ ጥቂት ዓመታትን ብቻ ቢያስቆጥርም ያካሄደው ጉባኤና ምርጫ ግን በግልጸኝነቱ ለሌሎችም አርዓያ ሊሆን የሚያስችለው መሆኑን ጠቁመዋል። አዲስ ለተመረጡት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም በተለይ በክለብ ላይሰንሲንግ፣ በሴቶችና ታዳጊዎች ስፖርት እንዲሁም በእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2015