የእንሰት ተከል በሀገራችን በርካታ አካባቢዎች በስፋት ይለማል። ከተክሉ የሚመረቱት ቆጮ፣ ቡላና የመሳሰሉትም በዋና ምግብነት ይታወቃሉ። የእንሰት ተክል በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በኦሮሚያ ክልሎች አንደሚለማ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከተክሉ የሚገኙት ቆጮና የመሳሰሉት ምግቦች ሲመረቱ የኖሩት በባህላዊ መንገድ ሲሆን፣ በማምረቱ ሥራም የሚሳተፉት ሴቶች ናቸው። ባሕላዊ የአመራረት ሂደቱ እጅግ ኋላ ቀር በመሆኑ የእናቶችን ጊዜ ያባክናል፤ ጉልበታቸውን የሚበላና አድካሚ ነው።
ይህንን የአመራረት ዘዴ በማሻሻል ዘመናዊ ዘዴን እንዲከተል ማድረግ የእነዚህን እናቶች ድካም ከማቅለልና ጊዜያቸውን ከመቆጠብ በላይ ምርታማነትንም መጨመር መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያመለክታል። ከእንሰት ቆጮና የመሳሰሉትን በዘመናዊ ዘዴ ማምረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ አስታውቋል። የዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችንም ይህንኑ አዲስ ቴክኖሎጂና ፋይዳውን የተመለከተ ነው።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና ተመራማሪ ዶክተር አዲሱ ፍቃዱ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የእናቶችን ድካም የሚያቃልሉ፣ ጊዜያቸውን የሚቆጥቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂን በመሥራት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። አዲሱ ቴክኖሎጂ ከእንሰት ቆጮና የመሳሰሉት በባሕላዊ መንገድ የሚመረቱበትን ሂደት ሙሉ ለሙሉ ያዘምናል። ቴክኖሎጂው የምግብ ጥራትን ከማሻሻል እና ከእንሰት የሚገኘውን ጥቅም ከመጨመር አንጻር ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከታል።
ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የማኅበረሰቡን ችግሮች በመለየት ሳይንሳዊ መፍትሔ መስጠት ነው የሚሉት ዶ/ር አዲሱ፤ በዚህም ከእንሰት የሚገኙ ምርቶችን በዘመናዊ መልኩ ማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በማበልጸግ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲሞከሩ በማድረግ የተሻለ የተባለው ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመት በፊት ከተለዩ ችግሮች አንዱ ከእንሰት የተለያዩ ምርቶች አመራረት፣ ማብላላት፣ የመፋቅ ሂደት እና ምግብ የማዘጋጀት ሂደት እጅግ በጣም ጉልበት የሚጠይቁ እና ጊዜ የሚፈልጉ ከመሆናቸው ባሻገር ከእንሰት የሚገኘው ምግብ ወጥ ያልሆነ፣ ጥራቱ ከቦታ ቦታ የሚለያይ መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ ተመራማሪው ያብራራሉ። ቆጮው ገበያ ላይ ሲውል የተሻለ ዋጋ የማያወጣበት ሁኔታ እንዳለም ይገልጻሉ።
ለእነዚህ ችግሮች በተቀናጀ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት ጥናቶች መካሄዳቸውንም ጠቅሰዋል። ጥናቶቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ የሕትመት ውጤቶች ላይ ለሕትመት እንዲበቁ መደረጋቸውን ዶ/ር አዲስ ይናገራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለህትመት ከበቁት ቴክኖሎጂዎች ውስጥ ቃጫውን በቀላሉ የሚለይ መፋቂያ ማሽን፣ የሚያደቅ ማሽን፣ የሚጨምቅ ማሽን እና ሌሎች አዳዲስ የማብለያ ዘዴዎችን የያዙ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም እንሰት በዘመናዊ መልኩ ከተመረተ ከእንሰት የሚገኘው ምግብ ጤንነቱ የተጠበቀ ይሆናል።
ከእንሰት ከሚመረቱት ምግቦች መካከል በተለምዶ ከምናውቃቸው ከገንፎ እና ከቂጣ በተጨማሪ ውስን ምግቦች ብቻ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፣ በቴክኖሎጂ በመጠቀም በዘመናዊ ዘዴ የእንሰት ምርቶች ሲመረቱ ግን ከተክሉ በጣም ብዙ የምግብ አይነቶችን መሥራት ይቻላል ይላሉ።
‹‹ቀደም ሲል እንሰት ቆጮ ሆኖ ተጋግሮ የሚበላ ባህላዊ ምግብ እንደሆነ ነው የሚታወቀው›› የሚሉት ዶ/ር አዲሱ ፤ ከባህላዊ ምግብነቱ ባሻገር በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሲመረት ደግሞ ጥራቱ በጠበቀ ሁኔታ ስለሚመረት ነጭ፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ቆጮ ማግኘት እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ማሽኑ ቆጮውን በቀላሉ ወደ ዱቄት እንደሚቀይረው ተናግረው፣ ከዱቄቱ ደግሞ ዳቦ፣ ኬክ፣ ኩኪስ እና የመሳሰሉትን ሌሎች ምግቦች ማምረት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
እስካሁን በአብዛኛዎቹ ቦታዎች እንሰት የሚፋቀውና ቆጮውም የሚለየው በእንጨት ወይም በአጥንት እና በቀርከሃ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር አዲሱ፤ ቆጮው እንዲብላላ የሚደረገውም በጉድጓድ በመቅበር ረጅም ሂደቶችን እንዲያልፍ በማድረግ መሆኑን ይገልጻሉ። አዲሱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግን ይህንን ሁሉ ድካም በማስቀረት በዘመናዊ መልኩ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን ማግኘት ማስቻሉን ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በተለመደው መንገድ ሁለት እናቶች በአንድ ላይ ሆነው አንድ እንሰት ለመፋቅ ከአንድ ቀን በላይ ሊፈጅባቸው ይችላል። በአዲሱ ቴክኖሎጂ ግን እንሰት የመፋቁ ሥራ በአብዛኛው አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። ይህም ጊዜንም ይቆጠባል፤ የምግብን ጥራትንም ያረጋግጣል። እናቶች እንሰት ለመፋቅ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ ይቆጥባል፤ ጉልበታቸውን ለሌላ ሥራ እንዲያውሉ ያስችላል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሚገባ የተበላላ ቆጮ ማግኘት እንደየአካበቢው ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም፣ በትንሹ ከሁለት ወር እስከ ስድስት ወር ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ መቆየት አለበት ይላሉ። በዩኒቨርሲቲው ቤተ ሙከራ የበለጸገው እርሾ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ግን ከሰባት እስከ አስር ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ በቀላሉ የተፋቀው እንሰት ተብላልቶ ለምግብነት መዋል እንደሚችል ነው ያመለከቱት።
እናቶች መጀመሪያ የተፋቀውን እንሰት በጉድጓድ ይቀብራሉ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከጉድጓዱ አውጥተው ያገላብጡትና መልሰው ይቀብሩታል። ከዚያም እንደገና ያወጡትና ቦታ ይቀያይራሉ። ይህ ሂደት ረጅም ጊዜ ይወስዳል፤ ጉልበት ያባክናል። አዲሱ ቴክኖሎጂ ይህንን ሂደት የሚያሳጥር በመሆኑ የበለጸገ እርሾ በመጠቀም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ተቀላቅሎ ይገባል፤ ከዚያም በአጭር ቀን ውስጥ አውጥቶ ለምግብነት ማዋል እንደሚቻል ይገልጻሉ። ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አሠራሮችን ከማዘመን በተጨማሪ ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ የምግቡን ጥራትና ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር መሠራቱን ተናግረዋል።
እንሰት አልሚ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ የመግዛት አቅምን በተመለከተም በስፋት ጥናት መካሄዱን ነው ዶ/ር አዲሱ የጠቆሙት፤ እንሰት የሚያለሙ አርሶ አደሮች እንሰቱ የሚፍቁት በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ መሆኑን ተመራማሪው ተናግረው፣ እንሰት የሚፋቅበት ጊዜ በጣም አጭር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓመት አንድ ጊዜ ለሚደረገው የመፋቅ ፕሮግራም ቴክኖሎጂው ያስገኘውን ማሽን መግዛት አዋጭ አይደለም ይላሉ።
ለዚህም ጥናቱን መሠረት በማድረግ እንሰት ባለበት አካባቢ በየሰፈሩ ማኅበረሰብ አቀፍ የእንሰት መፋቂያና ማብላያ ማዕከላት መገንባታቸውን ይገልጻሉ። ለአብነት በዶርዜ አካባቢ በተገነባው ማዕከል ቴክኖሎጂዎቹ እንዲገቡ ተደርጎ ሥራ መጀመሩን ይናገራሉ። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ልክ እንደ ወፍጮ ቤት እንሰቱን በጋሪ ይዞ ወደ በማዕከሉ በመሄድ አስፍቆ ወደ ቤቱ የሚመለስበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ይጠቁማሉ።
እሳቸው አንዳሉት፤ አንድ አርሶ አደር ማሽኑን ለመግዛት የአቅም ውስነት ሊኖርበት ይችላል፤ በመሆኑም ቴክኖሎጂው በማዕከል በኩል ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፤ ተመራጭም ነው። በዚህም ጥሩ ለውጦች እየታዩ ናቸው። ማዕከሉ እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል። አርሶ አደሮች ማሽኑን ገዝተው ለመጠቀም ከፈለጉም በኅብረት በመሆን ብዙም ኪስ በማይጎዳ ዋጋ ገዝተው መጠቀም ይችላሉ።
ዶ/ር አዲሱ እስካሁን ዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። ማዕከላት የመገንባቱ ሂደት ከኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከሌሎችም አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የማዕከላቱ ግንባታ በዶርዜ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ላይ ውሏል የሚሉት ዶ/ር አዲሱ፣ ‹‹ክርስቲያን ኤድ›› ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በወላይታ ሁለት ማዕከላት መገንባታቸውንም ይጠቁማሉ። በማዕከላቱም ለ1ሺ280 አርሶ አደሮችና ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን ይጠቁማሉ።
በቅርቡ ደግሞ ሦስት ማዕከላት በጋሞ ለመገንባት በሰፊው እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። ማዕከላቱ ሲገነቡ ይሰጣሉ ተብሎ ከተገመተው በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ሊሰጡ እንደሚችሉም ዶ/ር አዲሱ የሚናገሩት።
‹‹ ከእንሰት ቆጮንና የመሳሰሉትን ለማምረት የኬሚካል ፣የማዳበሪያ እና የመሳሰሉ ምንም አይነት ዶላር ውጭ አናወጣም ›› ሲሉ ዶ/ር አዲሱ ይናገራሉ፤ እንሰት ሙሉ ለሙሉ ሀገር በቀል እጽዋት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ‹‹እንደ ሀገር በምግብ ራሳችንን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ላይ አጋዥ በመሆን ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
የቴክኖሎጂ ማስፋፊያዎች ለመሥራት ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከአጋር አካላት ጋር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውም ጠቅሰው፣ እስካሁን ሥራ የጀመሩና ወደ ሥራ እየገቡም ያሉ ማዕከላት መኖራቸውም አስታውቀዋል። በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ማዕከላትን በመገንባት በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገቡ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ዶ/ር አዲሱ እንደሚሉት፤ አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂው ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት አለው። በተለይ ቴክኖሎጂዎቹ ተሞክረው ያመጡትን ውጤት ሲያዩ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ። የማዕከሉ ተጠቃሚዎችም በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናቸው ለውጥ ማምጣታቸውን ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንደቆጠበላቸው እንዲሁም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሆነላቸው ይገልጻሉ ።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያገኙት ቆጮ ጥራቱን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ ገበያ ላይ የተሻለ ዋጋ ያገኙበታል የሚሉት ዶ/ር አዲሱ፤ ቴክኖሎጂ ሕይወታቸውን በመቀየር ረገድ ለውጥ መምጣት መቻሉን አይተናል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂው ያልደረሰባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው ቴክኖሎጂውን በማስፋፋት በኩል ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እነዚህን ማዕከላት በየቦታው በማስፋፋት ጥቅም ላይ በማዋል አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል።
ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ለሙከራ ብዙ አይነት ማሽኖች መሥራታቸውን የሚገልጹት ተመራማሪው፣ እነዚህ ማሽኖች ሙያዊ እውቀትን የሚጠይቁ በመሆናቸው እናቶች እንዲጠቀሙበት የሚያስችሉ አልነበሩም ይላሉ። አሁን ጥቅም ላይ ውለው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ማሽኖች ለአጠቃቀም ምቹ የሆኑ በትንሽ ስልጠና እናቶች ራሳቸው እንደፈለጉ ሊሠሩባቸው የሚችሉ መሆናቸውን ያብራራሉ ።
በዶርዜ ማዕከል የተገኘው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በባሕላዊ መንገድ እንሰት ይፍቁ የነበሩ እናቶች፤ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በአጭር ጊዜ የማንንም እገዛ ሳይፈልጉ በማሽኖቹ በቀላሉ ራሳቸው እየሠሩ መሆናቸው አመላክተዋል። ይህም ለመጠቀም ምቹና ቀላል ማሽኖች ተደራሽ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል ።
ዶ/ር አዲሱ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በመሥራቱ ሀገር አቀፍ ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ እውቅናም አግኝቷል። የማኅበረሰቡን ሕይወት ከመለወጥ ፣የምግብ ዋስትናን ከማሻሻል አንጻር ብዙ እውቅናዎች እንዲኖሩት አድርጓል። የቴክኖሎጂ ውጤቶቹንም በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በማስመዘገቡ አምስት የሚደርሱ ቴክኖሎጂዎች የአዕምራዊ ንብረት ጥበቃ እንዲደረግላቸው መደረጉን አስታውቀዋል። ቴክኖሎጂዎቹ በሰፊው ተመርተው ሁሉም እንሰት አልሚ ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን እንደሚጠይቅ ዶ/ር አዲሱ አስገንዝበዋል።
እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንሰት በአራት ክልሎች (በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እና ኦሮሚያ ) ይለማል፤ በእነዚህ ክልሎቹ ሁሉ ቴክኖሎጂዎቹ ተባዝተው በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ ቢደረግ በተለይ ለወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው። ከዚህም ባሻገር እንደሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረትም አንድም የውጭ ምንዛሪ ሳይወጣበት ማሳካት ይቻላል።
አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው ካለው የሀብት ውስንነት አንጻር ቴክኖሎጂውን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አይችልም ያሉት ዶክተር አዲሱ፤ በተለይ አጋር አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተባብረው ቢሠሩ ቴክኖሎጂዎቹን ለበርካታ እንሰት አልሚ አርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ በርካታ ወጣቶችንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም