ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በተፈጠሩ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ሪፎርሞች በርካታ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ይሄን ተከትሎ አስደማሚ ውጤቶች የመገኘታቸውን ያህል፤ ከለውጡ መንፈስ ጋር መራመድ ያልቻሉ ተግዳሮቶችም አልጠፉም፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ደግሞ ለውጡን ከመገዳደር አልፈው በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከፍ ያለ ችግርን የጋረጡ፤ ሲከፋም ጦርነትን የጋበዙ ነበሩ፡፡
በዚህ ረገድ ሁለት ዓመታትን የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት አያሌ ዜጎችን አፈናቅሏል፤ ሀብት ንብረታቸውን አውድሟል፤ አካላቸውን አጉድሏል፤ የማይተካ ሕይታቸውንም ነጥቋል፡፡ በዚህ መልኩ በዜጎች ላይ ከሚገለጸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊና ሌሎችም ጉዳቶች በዘለለ፤ ሀገርን ከፍ ያለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ችግር ውስጥ አስገብቷት እንደነበርም የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት እንደ መንግሥት ችግሩን ከጅምሩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እና ጦርነትን ለማስቀረት ብዙ የለፋ ከመሆኑ ባለፈ፤ የአገርን ሕልውና በማስጠበቅ ጦርነት ውስጥም ሆኖ ስለ ዜጎቹ ሰላምና ደህንነት ሲል ተደጋጋሚ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
መጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ፤ ኋላም ኬንያ ናይሮቢ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረትም፣ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት በኩል ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይሄ ተግባር አድጎም ሕወሓት “አሸባሪ” የሚለው ስም እንዲነሳለት ከመደረጉም በላይ፤ የትግራይ ክልል በጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመራ እና የጊዜያዊ አስተዳደርን ፕሬዚዳንት በመሾም ስምምነቱን መሬት የማስያዙ ጉዞ በመልካም ደረጃ እንዲራመድ እየተደረገ ይገኛል፡፡
እነዚህ ተግባራት ጦርነት ለከረመበት አካባቢ፣ በተለይም ለትግራይ ክልልና ሕዝብ ትልቅ እፎይታንና ተስፋን የሰጡ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ከግማሽ ምዕተዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ ኖሯል፤ ልጆቹን በተደጋጋሚ ለመስዋዕትነት አቅርቧል፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶቹ በጦርነቶች እየተናጉበት ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ እናም የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት ሳይሆን ከሰላም እንደሚያተርፍ ከማንም በላይ ይገነዘባል።አሁን የተደረሰው የሰላም ስምምነት እና የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችም ይሄንኑ የሕዝቡን ስሜት እና ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚከወኑ መሆናቸውን ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ሃቅ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የሕዝቡ ፍላጎት በግልጽ ታይቷል፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት እና በሕወሓት በኩል ያለው ጥረትም ተገልጧል፡፡ ሌሎች ባለ ድርሻዎችም ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ይሄንኑ ተከትሎ በሚያሳዩትና በሚያሰሙት አቋም እየተለየ ይገኛል፡፡ ስለ ሰላም የሚናገሩ አንደበቶች የእውነት ሰላም ፈላጊ ስለመሆን አለመሆናቸው፤ ስለ ሕዝብ ጥቅምና ደህንነት የሚደሰኩሩ ምላሶች የእውነት ይሄንን ከልባቸው ያደረሱ ስለመሆን አለመሆናቸው፤ ስለ ትግራይ ሕዝብ ጥቅምና እድገት የሚሰብኩ አንደበቶች ይሄንኑ ፈልገው የሚናገሩ ስለመሆን አለመሆናቸው፤… ለሁሉም ግልጽ እየሆነ ይገኛል፡፡
ይሄን መሰሉ ጉዳይ ጊዜና ሁኔታዎች የሚያጠሩት ቢሆንም፤ ሊዘነጋ የማይገባው ግን የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ታስቦ እየተተገበሩ ያሉ ስራዎች ማጠንጠኛቸው አገርና ሕዝብ መሆናቸው ነው፡፡ ምክንያቱም አገር ከፓርቲም፣ ከቡድንም በላይ ናት፤ ሕዝብም ከግል ጥቅምና ፍላጎት የላቀ ነው፡፡ ስለ ቡድን እያሰቡ፣ ስለ ግል ጥቅም እየተጨነቁ አገርና ሕዝብን እንደ ካባ ደርቦ የሚደረግ ሩጫ ካለ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ሊሆን የሚገባው ከቡድን ፍላጎት የተሻገረ፣ ከግል ጥቅምና ምኞት የተፋታ ስለ ሀገር እና ሕዝብ ደህንነት፣ ሰላምና ከፍታ የሚገለጽ ተግባር ነው፡፡
በዚህ ረገድ አሁን በትግራይ ክልል እየተደረገ እና በፌዴራሉ መንግሥት ይሁንታ እየተሰጠው እየተጓዘ ያለው የስምምነቱ አካል የሆነው ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ተግባር፤ በዋናነት የትግራይ ክልልን ሕዝብና አጎራባች ሕዝቦችን፤ በጠቅላላው ደግሞ መላው ኢትዮጵያውያንን ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማታቸው ፊታቸውን እንዲያዞሩ የሚያስችል ታላቅ ርምጃ ነው፡፡ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሀገርና ሕዝብ ይሄ እንዲሆን ትልቅ ዋጋ የከፈሉበት ውድ ነገር ነው፡፡ ይሄን ውድ ነገር ለማራከስ መሞከር፣ ይሄን የሰላም አየር ለመበከል መጣጣር ደግሞ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይገባው ብቻ ሳይሆን በእንጭጩ ሊገታ የሚገባው ነው፡፡
የሰላም ስምምነቱ እውን መሆን አገር በብልጽግና መስመሯ ፈጥና እንድትራመድ፤ መንግሥትም ለሕዝቡ ሁለንተናዊ ደህንነትና ዕድገት በሙሉ ልብ እንዲሰራ፤ ሕዝብም ስለ ሰላሙ እውን መሆን በሕብረት እንዲቆም እድል የሚፈጥርለት ነው፡፡ በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ በሙላት እንዲፈጸም እና ከሰላም ስምምነቱ ሕዝብ እንዲያተርፍ በቅንነት መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ይሆናል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም