ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደጉ ስራ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለዚህም መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ እያደረገ ያለውን ድጎማ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በ2014/15 የምርት ዘመን ሀገሪቱ 15 ቢሊዮን ብር ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ድጎማ አድርጋለች፡፡ በተያዘው 2015/16 የምርት ዘመን ደግሞ ይህ አሀዝ ወደ 21 ቢሊየን ብር ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ምርትና ምርታማነቱን ይበልጥ ለማሳደግ እንዲሁም አርሶ አደሩ ከአፈር ማዳበሪያ እየተወደደ መምጣት ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳይገጠመው በሚል የተወሰደ ርምጃ ነው፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎም የግብርናው ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ አንድም ማሳ ጦም እንዳያድር በሚል እየተከናወነ ባለው ተግባር፣ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እየተሰፋፋ መምጣት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቃም መስፋፋትና የመሳሰሉት ለለውጡ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ከዘርፉ ተግዳሮት አንዱ በመሆን የሚታወቀውን የአርሶ አደሮች ማሳ የተበጣጠሰ መሆን ችግርን አርሶ አደሩን በማሳመን ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ግብርናውን ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምቹ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም በትራክተር መጠቀምን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ መዋል እየተቻለ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደጉት ሀገሮች እንደሚስተዋለው አንድ አይነት ሰብል የለማባቸው ሰፊፋ የእርሻ ማሳዎችን ማየት የተቻለው አንድም የኩታ ገጠም እርሻ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ ሁሉም ጥረቶች የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ወደፊት እያራመዱት ይገኛሉ፡፡
በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ሌላው የዘርፉን ምርትና ምርታማነት በወሳኝ መልኩ ማሳደግ ያስቻለ ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡ በአንዴ ከማምረት ሁለቴና ሶስቴ ማምረት ውስጥ መግባት ብቻውን ትርጉሙ ሰፊ ነው፡፡ ልማቱ ቴክኖሎጂን በሚገባ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት እንደመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ፋይዳው ከፍተኛ እየሆነ ይገኛል፡፡ በሀገሪቱ ዓመታዊ የግብርና ምርት ላይ እስከ 26 ኩንታል ተጨማሪ ማግኘት የተቻለበት ሁኔታ የተፈጠረበት የምርት ዘመን ለምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣት ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ አሀዝ በዚህ የምርት ዘመን ወደ 52 ሚሊየን ኩንታል እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
ይህ እድገት እየተመዘገበ ያለው ለምርትና ምርታማነት እድገት ብዙ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ እምቅ አቅሞች ገና ብዙም ባልተነኩበት ሁኔታ ነው፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሀገሪቱ በግብርና ኢንቨስትመንት በኩል ሊደረስበት የሚፈለገውን ርቀት ተጉዛለች ባይባልም በአንዳንድ ክልሎች በተወሰነ መልኩ እየሄደችበት ትገኛለች፡፡ በዚህ ብቻም የግብርና ኢንቨስትመንትን ፋይዳ መቅመስ ተችሏል ማለት ይቻላል፡፡
ይህን ኢንቨስትመንት አሁን ወደ ማስፋት መግባት ያስፈልጋል፡፡ እየተስፋፋ የመጣው የኩታ ገጠም እርሻ፣ የሜካናይዜሽን ተጠቃሚነትና አገልግሎት ለግብርናው ዘርፍ መቅረብ የጀመረው የፋይናንስ አገልግሎት ሲታሰቡ የግብርና ኢንቨስመንትን ማስፋፋትን ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት ማሰቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ ኢንቨስትመንት ለዚህች ሀገር የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ጥርጥር የለም፤ ያደጉት ሀገሮች ተሞክሮም ይህንኑ ያስገነዝባል፡፡
በቅርቡ ‹‹የመሬት አስተዳደርና የአካታችነትና ዘላቂ ልማት ጎዳና›› በሚል የተካሄደ መድረክን ዋቢ ያደረገ መረጃ እንዳስገነዘበው፤ የእርሻ ኢንቨስትመንትን በዘመናዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የግብርና ኢንቨሰትመንት ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ ኢኮኖሚውን ሊያሸጋግር ይችላል፡፡ የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምንና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የግሉ ዘርፍም እንዲሳተፍበት ማድረግ እንደሚገባና ለእዚህም ማበረታቻ እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡ የእርሻ መሬትን በዘመናዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በሚገባ ለመጠቀም ደግሞ የግብርና ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ ለግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት የግብርና ኢንቨስትመንት አስፈላጊ ስለመሆኑ የምጣኔ ሀብት እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎችም ያስገነዝባሉ፡፡
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች መረዳት እንደሚቻለውም ዘርፉ አዋጭ መሆኑን ነው፡፡ ይሁንና ከለውጡ በፊት እንደ ጋምቤላ ባሉ አካባቢዎች ለግብርና ኢንቨስትመንት በሚል የገቡ ባለሀብት ተብዬዎች በፈጠሩት ችግር ሳቢያ ልማቱን ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ ሀገርም በእነዚህ ለግብርና ኢንቨስትመንት በሚል ብድር በወሰዱ ባለሀብቶች ለኪሳራ ተዳርጋለች፡፡ ይህ ሁኔታ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከመሬት አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር በተያያዘም የግሉን ዘርፍ በግብርና ኢንቨስትመንት መሰማራት የሚችልበት ሁኔታ ጠባብ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በመማር ኢንቨስትመንቱን ማስፋፋት ግን ይገባል፡፡ ባለሀብቱ በዘርፉ ሊሰማራ የሚችልበትን ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንት ሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገች ካለችው ጥረት እንዲሁም ዘርፉ ኢኮኖሚውን ለማሻገር ካለው ፋይዳ አኳያ ለግብርና ኢንቨስትመንት ትኩረት የመስጫው ጊዜ አሁን መጀመር ይኖርበታል፡፡ ይህች ሀገር ለግብርና ኢንቨስትመንት ሊውል የሚችል ሰፊ ለም መሬትና ለመስኖ ሊውል የሚችል በቂ የውሃ ሀብት አላት፤ በቂ የሰውም ኃይልም እንዲሁ፡፡ ሀገር ይህን ሁሉ ሀብት ይዛ ስለምግብ ዋስትና ችግር መነጋገሩ ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው በግብርና ኢንቨስትመንትም ላይ ሲሰራ ጭምር ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያሉ ህጎችን መፈተሽ፤ ኅብረተሰቡን ማስገንዘብ፣ የግብርና ኢንቨስትመንትን ፋይዳ ማስረዳት፣ የግሉ ዘርፍ ከአርሶ አደሮች ጋር በጥምረት ሊሰራ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንት በሌሎች ሀገሮች እያስገኘ ያለውን ጥቅም፣ በምን አይነት መልኩ እየተፈጸመ ስለመሆኑ ተሞክሮዎችን መቀመርና በሥራ ላይ ማዋልም ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2015