በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት እንዲሁም የአካዳሚክ ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ገነነ አበበ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርት ብዙ አማራጮችን ይዞ እንደመጣ ይናገራሉ። አንዱ በዚህ ፖሊሲ እንደተቀመጠው ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ማለትም በአጠቃላይ ትምህርት ጭምር እንዲካተት መደረጉ ሲሆን ይህ ደግሞ ሙያንም ሆነ ትምህርቱን ተወዳጅ ለማድረግ ያስችላል። በቴክኒክና ሙያ ዙሪያ ያለውን አመለካከትም ይለውጣል። ተማሪዎች ሙያ ወዳድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ሌላው ፖሊሲው የፈጠረው እድል ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሚማሩበት ደረጃ ልክ በቴክኒክና ሙያም ገብተው እንዲማሩ ማስቻሉ ነው። እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ መማር እንደሚችሉ ግንዛቤ የሚፈጥርና የሚገፋፋቸው ሆኗል። ቴክኒክና ሙያ በባህሪው ሥራ ተኮር ትምህርት በመሆኑ በሙያ ተመርቀው ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚደረግ ትምህርት ይሰጥበታልና አሁን በተፈጠረው እድል ብዙዎች እንደሚገቡ ይታመናል ይላሉ።
አዲሱ ፖሊሲ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርት የጀርባ አጥንት የሆነው የኢንዱስትሪ ተሳትፎን ከማሳለጥ አኳያ ብዙ እድሎችን ይዞ መጥቷል። አንዱ ከዚህ በፊት የነበረውን የኢንዱስትሪዎች ትስስርን በእጅጉ የሚያጠናክርበትና የሚያሰራ ነው። ኢንዱስትሪዎች እንዴት ማሳተፍ ብሎም ትርፋማ ማድረግ እንደሚቻል ያመላክታል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ አመለካከት እንዲሰጠው ያደረገው አሰራሩና ፖሊሲ ነበር፤ በአዲሱ ፖሊሲ ይህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ከዚህ በፊት እስከ ደረጃ አምስት ብቻ የነበረው ሁኔታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲን ብቻ እንዲመለከቱና እንዲመርጡት አድርጓቸው ቆይቷል። አሁን ግን በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ መድረስ የሚቻልበት በመሆኑ ብዙዎች ምርጫቸው ያደርጉታል።
አሁን በወጣው ፖሊሲ አንድ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የከፍተኛ ተቋም የመግቢያ ነጥብ ካገኘ ቴክኒክና ሙያ ውስጥ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን መከታተል ይችላል። ይህ ደግሞ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ አራት ዓመታትን በትምህርት በማሳለፍ ነው የሚገኘው ያሉት ዶክተር ገነነ፤ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ትምህርት የሚጠናቀቀው 12ኛ ክፍል በመሆኑ እንደዚህ ቀደሙ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነ ወደ ቴክኒክና ሙያ አይገባም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሙያን ጥቅም በአግባቡ ተረድቶ ለትምህርቱ ዝግጁ ሆኖ የሚገቡ ተማሪዎችን እንደሚያበራክትም ይናገራሉ።
ዶክተር ገነነ፤ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ መማር ከዚህ በኋላ የምርጫ ጉዳይ እንጂ የውጤት ጉዳይ አይሆንም። ምክንያቱም ቴክኒክና ሙያ ከፍተኛ ተቋም የመግባት ሁኔታው ተመሳሳይነት ያላቸው እድሎችን ይዟል። ከደረጃ ስድስት በላይ ያሉ ትምህርቶችን የሚማሩ ተማሪዎች ልክ እንደከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ዓመቱን ጠብቀው ይመረቃሉ። ደረጃ አምስትን ጨምሮ ያሉት ግን እንደተማሪው አቅምና ፍጥነት ይወሰናሉ። ቴክኒክና ሙያ ላይ ዋጋ የሚሰጠው ዓመታት ማስቆጠሩ ሳይሆን ብቁ ሆኖ መውጣቱ ነውና በትንሽ ጊዜ በጣም ሙያዊ ብቃታቸውን እያሳዩ ከመጡ ደረጃውን መሻገርና የብቃት ምዘና ወስደው ወደ ሥራ መሰማራት እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
በአዲሱ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መሰረት ከቴክኒክና ሙያ የሚወጡ ተማሪዎች በሁለት አይነት መልኩ እንዲሰሩ ተደርገው ይመረቃሉ። የመጀመሪያው በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ተቀጥረው እንዲሰሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል። አንዱ ገበያው የሚፈልገውን እያዩ ማሰልጠን ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር ነው። አሁን አካሄዱ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚል ነው፤ ከራሳችን ተነስተን ነገሮችን እያሰፋን ገበያውን እንይዛለን። በዚህም የአቅርቦትና ፍላጎት ልዩነት እንዳይኖር አምስት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎችን እናሰለጥናለን። በግብርና፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ማዕድን ቁፋሮ(ማይኒንግ)፣ ማንፋክቸሪንግና አይሲቲ የተማሪዎቻችን የሥራ ምንጮች ይሆናሉም ይላሉ።
ተቋማት ስልጠና ሲሰጡ ከአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጋር በተዛመደ መልኩ እንዲሰጡ መደረጉም ሌላው አዲሱ ፖሊሲ ያመጣው መልካም እድል በመሆኑ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም እንደ አካባቢያቸው የተፈጥሮ ሀብት ተለይተው ትምህርት የሚሰጡ ይሆናልና አካባቢያቸውን ለይተው የተመረጡትን ዘርፎች ብቻ አይተው በቀላሉ መስራት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። እድሉ ደግሞ ለተማሪው ብቻ ሳይሆን ለኢንዱስትሪውም ነው።
ታዲያ ይህ ሁሉ ምቹ ሁኔታ ለዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምን አማራጭ ይዞ መጥቷል ከተባለ አንዱ ከ50 በታች ያመጡ 100 ሺ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት እንዲወስዱ በየዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ቢሆንም አንፈልግም ካሉና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን ከመረጡ እድሉ የሚሰጣቸው መሆኑ ነው። ሌላው ከ50 በላይ ያመጡትም ቢሆኑ እድሎቹ እንዳላቸው ያመላከተ ነው። ከዚያም ባሻገር እንዳለፉት ጊዜያት ውጤት ያልመጣላቸውም በተቀመጠላቸው ውጤት መሰረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።
በቅርቡ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 608 ሺ 666ቱ ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ገብተው እንደሚሰለጥኑ ይደረጋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015 ዓ.ም ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት ሊገቡ የሚችሉ ሰልጣኞች ቁጥር 760 ሺህ 832 ሲሆን፤ 20 በመቶ የሚሆኑት ከቴክኒክና ሙያ ውጭ ባሉ ማሰልጠኛ ተቋማት ይገባሉ። በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡት ሰልጣኞች ቁጥር ስፋት ያለው ይሆናል።
በ2015 ዓ.ም የመቁረጫ ነጥብ የሰልጣኞች ድልድል የኢንዱስትሪውን የሰው ኃይል አሰላለፍ መሰረት በማድረግ የተሰላ በመሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የስራ ገበያውን፣ የሰው ኃይል ፍላጎትና የአካባቢውን የልማት ቀጠና መሰረት በማድረግ ቅበላ ያደርጋሉ። መቁረጫ ነጥቡ የ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ለ2015 ዓ.ም ብቻም ያገለግላል። በ2013 ዓ.ም እና በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስደው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓት ያልገቡ ተማሪዎች ደግሞ የሚስተናገዱት በ2014 ዓ.ም በነበረው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት ይሆናል ብለዋል በመግለጫቸው።
እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ታይቶ የቴክኒክና ሙያ እንዲገቡ ይደረጋል። አሁን ግን በአዲሱ ፖሊሲ 10ኛ ክፍል ላይ የሚሰጥ ፈተና ስለሌለ በ10ኛ ክፍል ውጤት መሰረት ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚገባ አይኖርም። በዚህም በ2013 እና በ2014ዓ.ም የተማሩ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚስተናገዱት በሁለት አይነት መንገድ ይሆናል። የመጀመሪያው ትምህርታቸውን 11ኛ ክፍል ገብተው መማር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አጫጭር ሥልጠና ወስደው የቴክኒክና ሙያን ይቀላቀላሉ። በተጠቀሰው ዓመት ውስጥ ያጠናቀቁ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ አጠናቀው የመቁረጫ ነጥቡን የሚያሟሉ ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ውስጥ በሚሰጡ ሁሉም ሙያዎች ላይ እኩል የመወዳደርና የመሰልጠን መብት እንዳለቸው ያብራራሉ።
የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን የማዘመን፣ ተደራሽ የማድረግና በትኩረት መስክ የማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱን ለስራ ገበያው በሁሉም ደረጃዎች የሠለጠነ የሰራተኛ ኃይልና ተስማሚ ቴክኖሎጂ የማቅረብን ተልእኮ ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የተሰጠ በመሆኑ ይህንን ከማስተግበር አኳያ ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል። ተልዕኮውን ውጤታማ ለማድረግም በእውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ ብቁ የሆነ ዜጋ ለማፍራት ከሰልጣኝ ቅበላ እስከ ስራ ማስተሳሰር ያሉ ሂደቶች ጥንቃቄን በሚሹ መልኩ የሚከናወንም ይሆናል።
በ2015 ስልጠና ዘመን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የመግቢያ ነጥብን በተመለከተ እንዳስቀመጡትም፤ በደረጃ አንድና ሁለት ስልጠና የሚሳተፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅት (12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) የተፈጥሮ ሳይንስ የመቁረጫ ነጥብ ለወንዶች 157 ሲሆን፤ ወንዶች ሆነው በታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደሮች አካባቢ ለሚኖሩ ተማሪዎች 156 ነው። ለሴቶች ደግሞ 156 የተወሰነ ሲሆን፤ ሴት ሆነው በታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደሮች አካባቢ ለሚኖሩ መቁረጫ ነጥቡ በአንድ ነጥብ ዝቅ ተደርጎ 155 እንዲሆን ተወስኗል። ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 130 ካመጡ ደረጃውን ያሟላሉና ትምህርቱን መከታተል ይችላሉ።
በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ያሉ በደረጃ አንድና ሁለት ስልጠና የሚሳተፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅት (12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) ተማሪዎች የመቁረጫ ነጥብ ደግሞ ለወንዶች 148 ነው። ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለሚኖሩ ወንድ ተማሪዎች ደግሞ 142 ካመጡ ትምህርቱን መከታተል ይችላሉ። በተመሳሳይ ሴቶች 144 ማምጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ 141 ማምጣት ግዴታቸው ይሆናል። ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 130 ካመጡ በቂ እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል።
ደረጃ ሦስትና አራት ስልጠናን የሚወስዱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅትነ (12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) በተፈጥሮ ሳይንስ የመቁረጫ ነጥባቸው ለወንዶች ከ158 እስከ 245 ሲሆን፤ በታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢ ለሚኖሩ ወንዶች ደግሞ 157 እስከ 202 ማምጣት ግድ ነው። ወደ ሴቶቹ ሲገባ 157 እስከ 217 ድረስ ማምጣት ይኖርባቸዋል። በታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደሮች አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ 156 እስከ 201 ሲያመጡ ነው ደረጃውን የሚያሟሉትና ትምህርቱን መከታተል የሚችሉት ተብሏል። በዚህ ደረጃ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች የተሰጠ የመቁረጫ ነጥብ ደግሞ ከ131 እስከ 148 ነው።
በማህበራዊ ሳይንስ ደረጃ ሦስትና አራት ስልጠናን የሚወስዱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅት (12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) የመቁረጫ ነጥብ ደግሞ ለወንዶች ከ149 እስከ 202 ሲሆን፤ በታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢ ለሚኖሩ ወንዶች 143 እስከ 172 ሆኗል። ሴቶቹ ደግሞ 145 እስከ 178 ማምጣት ይኖርባቸዋል። በታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደሮች አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ 142 እስከ 170 ነው ተብሏል። ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች ከ131 እስከ 148 ድረስ ካመጡ ትምህርቱን መከታተል እንደሚችሉ ተቀምጧል።
በተፈጥሮ ሳይንስ ደረጃ አምስትን የሚቀላቀሉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅት(12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) ተማሪዎች ደግሞ ወንዶቹ 246 ያመጡ ሲሆኑ፤ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደሮች አካባቢ ለሚኖሩ ወንዶች ደግሞ 203 ማምጣት ግዴታ እንደሆነ በመግለጫው ተነስቷል። በተመሳሳይ ለሴቶቹም የተቆረጠ ነጥብ አለ። ይህም 218 ማምጣት ነው። ታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደሮች አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ 202 ማምጣት እንዳለባቸው ተወስኗል። ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች ደግሞ 149 ዝቅተኛ የመግቢያ ውጤታቸው እንደሆነ ተነግሯል።
ደረጃ አምስትን የሚቀላቀሉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያና ቅድመ ዝግጅት(12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ) የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ወንዶቹ 203 ያመጡ ሲሆኑ፤ ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደሮች አካባቢ ለሚኖሩ ወንዶች 173 ማምጣት ግዴታ ነው። በዚህ ደረጃ የሚሰለጥኑ ሴቶች ደግሞ 179 ማምጣት ይኖርባቸዋል። በታዳጊ ክልሎችንና አርብቶ አደሮች አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ማምጣት ያለባቸው ውጤት 171 ነው። ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች ደግሞ 149 ዝቅተኛ የመግቢያ ውጤታቸው ሆኗል።
የመቁረጫ ነጥቡ ይፋ እንደተደረገ በነጥቡ መሰረት ተቋማቱን ለመቀላቀል ዝግጅት ካደረጉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፤ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲሁም ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮዎች በ2015 የትምህርት ዘመን ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ለሚገቡ አዲስ ሰልጣኞች የተማሪ ቅበላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብርን አዘጋጅተዋል። መርሃግብሩ የነበረው በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነበር።
የተማሪ ቅበላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንዳሉትም፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በተጨባጭ ተግባር የታገዘ በቴክኒክ ትምህርት መሰልጠን ለሚፈልጉ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር ለሚሹ ሰዎች የሚሰጥ የፈጠራ ክህሎትን ለማስተማር የሚያስችል ተመራጭ የትምህርት ዘርፍ ነው። ተማሪዎች በሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ እና ደረጃ ላይ መማር የሚችሉበት እድል ስለሚሰጣቸውም ሊጠቀሙበት ይገባል።
በመርሀ ግብሩ የታደሙት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ተቋማት ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም 108 የሙያ አይነቶች በስምንት ኮሌጆች ስልጠና ይሰጣል ሲሉ አብስረዋል። እናም እነዚህን ለመጠቀም ተማሪዎች ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ ቋጨን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም