
ሰው ጠፋ፤ መልካምነት ራቀ፤ በትውልዱ ክፋት ነገሰ፣ ራስን መውደድ ተመለከ፤ ወዘተ የሚሉ ሃሳቦች በዚህ ዘመን በተደጋጋሚ የምንሰማቸው ሃሳቦች ናቸው። በዚህ መሀል ግን የቸርነትና የደግነት እንዲሁም ሰው የመሆን ጥግንም አይተናል። «ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው» ብሎ የተነሳውን የዘመናችንን የደግነት ተምሳሌት ድርጅት በሁለት እግሩ ለማቆም ሌሎች ደጋጎች ከጎኑ ተሰለፉ።
ራስንና ወጣትነቱን ያሸነፈ ትውልድ መጣ፤ የዚህ ትውልድ ቅኖች ዘመኑን ሊዋጁ ተገኙ። ባለ ደግ ልቦች ባልተዋለላቸው ውለታ፣ ውለታ ከፋይ ሆኑ። የየትውልዱን ዕዳ በመልካም እጆቻቸው አፍሰው መለሱ። የበጎነት ሰንደቅ የጥሩ መሆን አርማ ሆኑ። ከነዚህ መሀል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመልካም ተግባሩ የብዙዎችን ቀልብ የገዛው የበጎነት ተምሳሌቱ ቢንያም በለጠ ተጠቃሽ ነው።
የክቡር ዶክተር ቢንያም በለጠ ነገር ብዙ ተብሎለታል። የተባለውም ያልተባለውም መልካም ቃል ያልገለፀው የክፍለ ዘመኑ ባለ ቅን ልብ ነው። ሰዎች እሱን ለመግለፅ ሊሉት ሽተው አፋቸው ባልታዘዘላቸው ቃላት ብዛት ደክመዋል። ቢንያም ብዙዎች ሊሆኑት ሊያደርጉት የሚመኙትን እርሱ በመኖር አሳይቷል። የመልካምነት ዋሻ የጥሩነት መጠለያ ነው። ጧሪ ለሌላቸው ደጋፊ ለእራሳቸው የደከሙትን ረጂም ጭምር። መፀዳዳት ላልቻሉት ንፅህና መመገብ ለተሳናቸው ምግብ ሰጪ ነው። መንቀሳቀስ አቅቷቸው አልጋ ለተቆራኛቸው አልባሽ አጉራሽ ነው።
የቢንያም ጉዳይ ብዙ የተባለለት፤ ነገር ግን ገና ወደፊትም ብዙ ሊነገርለትና ተሞክሮውም ሊቀመር የሚገባው ትልቅ ዋርካ ነው። ለዛሬ ግን ከዚሁ ጀግና ጎን ተሰልፎ ምርኩዝ ሆኖ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ስለሚገኘው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ ልናወጋችሁ ነው።
ኮሜዲያኑ አቅሙን በአምላኩ ትከሻ ላይ ጥሏል። ቀን አዘንብሎበት የሰው ፊት አጥቁሮት ያውቃል። በሰው ፊት መነሳትን የድህነትን ጓዳ ጎድጓዳ አበጥሮ ያውቀዋል። ለእግሩ ጫማ ለዓይኑ ሰው ርቦት ያውቃል።
ኖሮት ያውቃልና ሰው ማጣት ምን ይመስላል ቢባል መልስ አለው። የድህነትን ጎልያድ በመልካምነት ጠጠር መጣል ችሏል። ዛሬ ላይ ፈላጊ ሳይሆን ለሌሎች የሚደርስ ነው። እግዚአብሔር የሚታዘዝ አጥቶ እንጂ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ነው፤ መፍቀድ ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው ይላል። በመቄዶንያ ሥራ ፈጣሪ እኔን አከበረኝ እንጂ መቄዶንያማ መጀመሪያም ግዙፍ ተቋም ነው ብሏል። ክብርና ሞገስ በችግርና መከራ መልክ እንጂ በካባ በወርቅ ሀብል መልክ አይመጣም ይላል በተለያየ ጊዜያት ሲናገር።
ኮሜዲያን እሸቱ የዘመኑን መልካም አጋጣሚ ዲጂታሉን ዓለም በመጠቀም ለብዙዎች ደረሰ። ሃይማኖትን ሳይለይ ፆታ ብሔር ሳይገድበው ሊደረስላቸው ለተገባ ሁሉ በቻለው ሁሉ ደረሰ። የቅን አሳቢዎችን ኪስ በመልካምነት እጁ ፈተሸ።
መቄዶንያ በአዲስ አበባ አያት ፀበል መድኃኒዓለም ላይ ከትሟል። በዚሁ ግቢ ውስጥ የሆነ ዘመናዊ ሆስፒታልና ምቹ የአረጋውያን መኖሪያ ሕንፃ እየገነባ ነው። የዚህ ሕንፃ ጉዳይ ነው ኮሜዲያን እሸቱን አገር ጉድ ያሰኘ የመልካምነት ተግባር እንዲከውን ዕድል የሰጠው።
በመቄዶንያ ምክንያት ከ7ሺህ 500 በላይ ነፍሶች ከመኖር ተዋወቁ። እንደ ሰው ተቆጥረው ከጅብ ራትነት ተረፉ። መቄዶንያ ማንኛውም የሕይወት ክፉና ደግ ገጠመኞችን ከአረጋውያኑ ጋር ማሳለፊያ ዕድልን ፈጥሯል። ቤት፣ መኪና፣ የንግድ ተቋም፣ የቤት ዕቃ ማንኛውንም ማውረስ የሚቻልበትን መንገድም ጭምር። በማዕከሉ በመገኘት ተጫጭተው የተጋቡ ወልደው የልጆቻቸውን ልደት ያከበሩ እልፎች ናቸው።
መቄዶንያ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞችን ምቾት ከግምት ያስገባ አዲስ ሕንፃ እገነባለሁ አለ። በዚህም የተረጂዎችን ቁጥር ሃያ ሺህ ለማድረስ ቆርጦ ተነሳ። ሕንፃው የ15 ወለሎች ባለቤት ነው። ለሕክምና ብቻ አንድ ሺህ 200 አልጋዎች አሉት። አዳራሹ አምስት ሺህ ሰው ይይዛል። 120 መኪናዎችን ማቆም ይችላል። ሰውን ከሚፈልገው ስፍራ የሚያደርሱ ሰባት አሳንስሮች ይኖሩታል። በሦስት ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ያለእረፍት በመሥራት 70 በመቶ ማጠናቀቅ ቻለ።
የዚህ ሕንፃ መጠናቀቅ ከ7 ሺህ 500 በመነሳት 20 ሺህ ነፍሶች እንዲደረስላቸው መንገድን ይጠርጋል። ለተጀመረው ሕንፃ 888 በሮችን እና 739 መስኮቶችን ለመግጠም ከቅን አሳቢዎች ጋር ተቃጠረ። ይሄኔ ኮሜዲያን እሸቱ ቀበቶውን ታጠቀ። እውቅ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን የሆኑ አርቲስቶችም አጠገብህ ነን አሉ። የቀናት እንቅልፉን ሰውቶ አላማውን አሳካ። በአንድ መድረክ ቆራጥነት መልካም መሆንና ለአላማ መቆም በኮሜዲያኑ ደጅ ደምቀው ተሞሸሩ።
በኢትዮጵያ የእርዳታ ታሪክ ውስጥ ተአምር ተፈጠረ። ያለፈው የካቲት 26 ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ሌሊት 7፡30 የቆየ በዶንኪ ቲዩብ (Donkey tube) አማካኝነት በቀጥታ ገቢ ማሰባሰቢያ 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በመሰብሰብ የተሳካ ሥራ ተሠርቷል።
መቄዶንያም እሸቱን የማመስገን ግዴታውን አልረሳም ነበር። በወቅቱ አረጋውያንም ከአፋቸው የምስጋና ዜማ ተደመጠ። እንደ ስምህ እሸት እሸት ብቻ ያብላህ፣ ዘርህ ይብዛ፣ ክፉህ ይራቅ፣ ደግ ይከተልህ፣… ብቻ ብዙ መልካም ቃላት ተሰሙ።
ዶንኪ ቲዩብ (Donkey tube) ኮሜዲያን እሸቱና በስሩ ያሉ ሠራተኞች በመቄዶንያ ምስጋና ተችሯቸዋል። በቀጥታ ስርጭቱ ላይ አዳራቸውን በመሰዋት ያስተባበሩ እውቅ አርቲስቶች እና የሃይማኖት አባቶችም በቢንያም ተመስግነዋል።
ሕንፃው አሁንም አላለቀም። የፊኒሺንግ ሥራው ብቻ 800 ሚሊዮን ብር ይፈልጋል። በሁሉም ክልል 34 ከተሞች ላይ የሚገነቡ መኖሪዎችም ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣሉ። መቄዶንያ ዛሬም በአጠቃላይ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ከፍተኛ ወጪ አለበት። ለዚሁ አላማም የቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሁም በቀጣይም ሚሊኒየም አዳራሽ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ ይዘጋጃል።
ከዚህ ቀደም ድርጅታችን መቄዶንያን በጎበኘበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፣ መቄዶንያን መደገፍ የነገ ቤትን መሥራት ነው። ይህን ቤት መገንባት ደግሞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሰጠ አደራ ነውና መቄዶንያን ይርዱ ይደግፉ እንላለን።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2015