ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ሲነሳ የማንዘነጋው አንድ ክለብ አለ። ክለቡ ታሪካዊ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስና ሀዋሳ ከነማ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ከ1990 ጀምሮ ሲካሄድ ሁለት ጊዜ ቻምፒዮን ከሆኑ ጥቂት ክለቦች አንዱ ነው። የቀድሞው መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ክለብ በቀደሙት ዓመታት ታሪኩ በርካታ ተጫዋቾችን ለአገር በማፍራት ይታወቃል።
ምስረታው ከታዳጊዎች የሚጀምር ሲሆን አንዋር ትንሹና ኤሊያስ ጀዋርን የመሳሰሉ ታሪካዊ ተጫዋቾችን በማፍራት ተጠቃሽ ነው። በክለቡ ተጫውተው ካለፉ ታላላቅ ተጫዋቾች መካከልም ዮርዳኖስ አባይ፣ ሙሉዓለም ጥላሁን፣ ረዲ አብረሃና በረከት ተሰማን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። ለበርካታ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን በማበርከትም በወርቃማ ዘመኑ ‹‹የኢትዮጵያው ላማስያ›› እስከ መባልም ደርሷል።
ከአዲስ አበባ ክለቦች መካከል አንዱ ሆኖ በ1953 ዓ.ም ሲመሰረት፣ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለሶስት ጊዜያት ከፍ ማድረግ ችሏል። ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮም በታሪኩ 13 ዋንጫዎችን በማንሳት ትልቅ ዝናና ስም ገንብተል። በአፍሪካ ደረጃም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች ደጋግሞ መሳተፍ ችሏል።
ይህ ታሪካዊ ክለብ ለዓመታት ብርቱ ተፎካካሪ ከሆነበት ፕሪሚየር ሊግ ወርዶ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ዘንድሮ መመለስ ቢችልም የስሙንና የታሪኩን ግዝፈት ያህል በጠንካራ ተፎካካሪነት ለመዝለቅ እየተቸገረ ይገኛል። ከከፍተኛ ሊግ ባደገ በዓመቱ ተመልሶ እንዳይወርድም አሁን እየተጓዘበት ያለው መንገድ ለደጋፊዎቹ የሚያሰጋ ነው። ክለቡ አሁን በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አስራ ስድስት ጨዋታዎችን አድርጎ ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው። 26 ግቦች ሲቆጠርበት ማስቆጠር የቻለው 16 ግቦችን ነው። በ8 ነጥብና በ10 የግብ እዳ 15ኛ ደረጃን በመያዝም የመውረድ ስጋት ተጋርጦበታል።
ከዚህ ስጋቱ ለመውጣት ግን አሁን ወደራሱ የሚመለከትበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል። የፕሪሚየር ሊጉ የመጫወቻ ሜዳ በዝናብ ምክንያት መቆራረጡና ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ተቋርጧል። ይሄንንም አጋጣሚ ክለቡ ባገኘው ፋታ እራሱን አርሞ ከመውረድ ለመዳን እንደሚጠቀምበት ጠቁሟል።
ክለቡ በጥር የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾችን በመጨመር ለሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጠንካራ ዝግጅት አድርጎ በሊጉ ለመቆየት በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በዝውውር መስኮቱ እራሱን መፈተሹንና ብቃታቸው የወረደ ሰባት ተጨዋቾችን አሰናብቶ ስድስት አዳዲስ ተጫዋች ክለቡን እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ጠቁሟል።
ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካሳደገው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በውጤት መጥፋት ምክንያት ከተለያየ በኋላ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩ ይታወሳል። በአዲሱ አሰልጣኝ ስርም የቀጠለው የውጤት መጥፋት በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ውድድር ለመቅረፍና በሊጉ ለመቆየት ከአሰልጣኙና ተጫዋቾች ጋር መግባባቱን ጠቅሷል።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ለማ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት ከተጨዋቾችና ከአሰልጣኝ ቡድኑ ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ተችሏል። የክለቡ አመራር ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይቶችን አድርጎ ቅሬታዎችን እንደግብዓት መወሰዱን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፣ በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ግምገማ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ቀሪ 14 ጨዋታዎች እንደ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች እንደሚመለከቱም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል። በቀጣይም ችግሩን ለመፍታት ከደጋፊ ማህበሩ ጋርም ውይይት እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከፌዴሬሽንና ከዳኞች ማህበር ጋር ያሉትን ችግሮች ለማቃለል መሰል ውይይት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።
ክለቡ ኢፍታዊ በሆኑ የዳኝነት ክፍተቶች ምክንያት ውጤት እንዳያጣ ብቃት ያላቸው ዳኞች እንዲመደቡ ለማድረግ እንደሚታገል የገለፁት ስራ አስኪያጁ፣ በአጠቃላይ በእያንዳንዱ ጨዋታ የክለቡ አመራር ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሚታወቅበት ታዳጊዎችን የማፍራት ባህል እንዳይቀጥል የሌሎች ክለቦች ውጤትን ትኩረት ያደረገ የአስተዳደር ስርዓት መከተሉ ተጎጂ እንዳደረገው አቶ ሲሳይ ያምናሉ። ለዚህም የውጭ ተጫዋቾችን ማስፈረም ለታዳጊዎች የሚሰጠውን ትኩረት መቀነሱንና ክለቡንም ተጎጂ ማድረጉን ያብራራሉ። እነዚህና ሌሎች መሰል ነገሮችም ለክለቡ ውጤት ማጣት ተጠቃሽ መሆናቸውን ያስቀምጣሉ።
ክለቡ አሁንም ታዳጊዎችን የማፍራት ባህሉን ጠብቆ ለመጓዝ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን ወጣቶችን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም ክለቡ የውጭ ተጫዋችን ከማምጣት ይልቅ ቅድሚያ ለሀገር ውስጥ ተጫዋቾች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ‹‹ክለቡ የቀድሞ ባህሉንና ፍልስፍናውን በማስቀጠል በሊጉ መቆየት ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ለመሆን መስራት ይጠበቅብናል›› ሲሉም ተናግሯል።
የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በበኩሉ፣ ቡድኑን ለመታደግ ያስፈረሟቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች በማካተት ለሁለተኛ ዙር ዝግጅት በማድረግ ውጤት እንደሚያስመዘግቡም ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ክለቡን ከወራጅ ቀጠናው ለማውጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ክለቡ ታሪካዊ በመሆኑ በሚገባው ቦታ መቀመጥ እንደሚገባውም ይናገራሉ። ተጫዋቾቹ በተነሳሽነት ረገድ ያለውን ጫና ስለሚያውቁ በስነልቦና ረገድ በባለሙያ የተደገፈ ዝግጅትን በማድረግ ላይ እንደሚገኙም አክለዋል። በክለቡ ተጫዋቾች ላይ የሚታየውን መነሳሳት ተጠቅመውም ክለቡን ከመውረድ ለመታደግ እየሰሩ ይገኛሉ።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2015