ገዳም የገባን ፈጣሪው እንጂ ማን ያየዋል? ይህ መናኝ ግን ከሁሉም የተለየ ነበር። ከሰውም ከፈጣሪውም ያልተሸሸገ የእራሱን የሙዚቃ ገዳም አበጅቶ የመነነ ታላቅ ጥበበኛ ጭምር ነበር። በራሱ ገዳም ውስጥ ቁጭ ብሎ ሙዚቃን እየሰራ ብቻ አልነበረም። ሙሉ ሕይወቱን ለሙዚቃ ሰውቶ እርሱ እንደ ሻማ እየቀለጠ ሙዚቃን እንደ ጧፍ ሲያበራ ኖሯል፡፡ ሙዚቃ በእሱ ላይ ስር አብቅላ እንድትወጣ እራሱን አፈርና ውሃ አድርጎ እየሞተ ሕይወት ዘራባት። ከእርሱ በላይ የበቀለችው ሙዚቃም ጣፋጭ የወይን ግንዷ ስሮች በአፍቃሪዎቿ ልብ ውስጥ ተሰድረው ይኖራሉ፡፡ የእውነትም ለሙዚቃ መኖር ማለት እንዲህ ነው፡፡
ይህ የታላቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካን ሕይወት በትክክል የሚገልፅ ነው። ኤልያስ መልካ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አቀናባሪ ብቻ ሳይሆን የዜማና ግጥም ደራሲ ጭምር የነበረ ሁለገብ ሙዚቀኛ ነበር። አንድ ብሎ የሚጀምረው የሙዚቃ ሕይወቱ ያለምንም ስስት 400 ያህል የሙዚቃ ስራዎችን አበርክቷል። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከሮሐ ባንድ በኋላ በ1980ዎቹ አጋማሽ ገደማ ቀዝቀዝ ብሎ በነበረውን ደብዛዛ ጊዜ ኤልያስ መልካ እንደ ድንገት ብቅ ብሎ ደማቅና ብሩህ አድርጎታል፡፡
ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ የሙዚቃ ስራዎቹ እንደ አበባ የፈካ የሙዚቃ ዓለምን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰገነት ላይ አኑሯል። ከ1990ዎቹ ወዲህ በተሰሩ አብዛኛዎቹ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ ከበስተጀርባቸው ኤልያስ መልካ አይታጣም። በሰራቸው ሙዚቃዎች ፍቅር እየተነደፈ ‘ህይወትን መስጠት ቢቻልና ምን ነበር በሰጠሁት’ እያለ በቁጭት የሚንገበገብለት አድናቂውም እጅግ በጣም ብዙ ነው። ከጆሮው የገቡትን ስራዎቹን በልቡ ያጣጣመ ሁሉ በአንደበቱ ይህንን ቢል አይገርም። እሱም የእዮብ መኮንን በሆነው ድንቅ ስራው ውስጥ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር።
ነገን ላየው እጓጓለሁ
በል ሂድ ዛሬ ጠግቤያለሁ
ከንግዲህ መቼም ላትመጣ
ደህና ሁን በል ሌላ መጣ
እናም አልቀረም ከእሩቁ የታየው ያ ሌላ መጣና ወሰደው። በዚህ ሰዓት ከአፈር በታች ቢሆንም ከመቃብር በላይ ውብ አድርጎ የሰራውን የሙዚቃ መንደር ትውልድ በአይነ ህሊና እየተመለከተ መልከ ብዙ የሆነው የኤልያስ መልካን ህይወትና ስራዎቹን ሲያስታውስ ይኖራል፡፡
ኤልያስ መልካ ተወልዶ ያደገው የብዙ አርቲስቶች መፍለቂያ ከሆነችው የአዲስ አበባዋ አዲስ ከተማ፣ አብነት አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃት ትምህርቱን በኃይሉ ተስፋዬ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከፍተኛ ሰባት ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅትም ጎበዝና ታታሪ ተማሪ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ። በዚያን ጊዜ ጎበዝ ተማሪ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገሮች የተካነ ነውና ጎበዝ የእግር ኳስ ተጫዋችም ጭምር ነበር። የእግር ኳስ ችሎታውን የተመለከቱ ጓደኞቹም ‘ትንሹ ማራዶና’ ሲሉ ይጠሩት ነበር። በልጅነቱም የራሱን ክራርና ጊታር እያበጀ የሙዚቃ ጥሙን ለማርካት ብዙ ይታገል እንደነበር በሕይወት ታሪኩ ተፅፏል።
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ዘመን የማይፍቀውን አሻራ ማኖር የቻለው የዚህ ሰው ስም ለሙዚቃ አፍቃሪዎች እንግዳ አይደለም፡፡ እንዲያው በጨዋታ መሃል ድንገት ስለ ኤልያስ መልካ ሲነሳ ‘እውነት ስለ እሱ አውቃለሁ ብሎ ብዙ ማውራት ባህርን በዋና አቋርጣለሁ እንደማለት ነው’ ቢባል ማጋነን አይሆንም። በእርግጥም የዚህን ታላቅ ከያኒ ከስራዎቹ በስተጀርባ ያለው ረቂቅ ማንነቱና የተለየ የሕይወት ፍልስፍናው ይህን ለማመን ያስገድዳል። ረጋ፣ ሰከን ብሎ ከርቱእ አንደበቱ ከሚያወጣቸው ቃላት ባሻገር፣ ከፊቱ ላይ የሚታየውን ድምጽ አልባ ጥልቅ ስሜቶቹን ገልጾ የሚችል አይኖርም።
ኤልያስ ወደ ሙዚቃው ዓለም ከመግባቱ በፊት የመንፈሳዊው ዓለም የመዝሙር አቀናባሪ ነበር። እድገቱም በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ከጊዜያት በኋላ የሙዚቃ ድምጽ በልቡ ማቃጨል ጀመረና መንገዱን ቀይሮ ዛሬ ወደምንመለከታትና ወደሰራት ወደዚህች ጥበባዊ የሙዚቃ መንደር ጎራ አለ። የመንፈሳዊውን ዓለም ስራ ባይጠላውም እውነተኛውና በህይወቱ የተጠራበት ትክክለኛው ቦታ ይህችው መንደር ስለመሆኗ እራሱ ተናግሯል። በተገኘበት ስፍራ ሁሉ ብቁ ሆኖ የሚታይ፣ የዳበረ ልምድና ክህሎት እንዲሁም ሁለገብ እውቀት ያለው የበሳል አዕምሮ ባለቤትና ወጣ ያለ የአኗኗር ዘይቤን የሚከተል ሰው ነበር።
ከምንም በላይ ለተሰጠን ነገር መሰጠት አለብን የሚልም ትልቅ የህይወት ፍልስፍና ነበረው። ወደ ሙዚቃው የገባው ሙዚቃን እንደ ውሃ ለተጠማችው ነብሱ እንጂ ለእንጀራው አልነበረም። ወደ ሙዚቃው ዓለም ከገባ በኋላ ከአፍሮ ሳውንድ፣ ከዜማ ላስታስ፣ ከደመራና ከሌሎች ባንዶች ጋር እሱን እንደመመልከት የሚያስደስት ነገር አልነበረም።
ከመድረክ ላይ ሊድ ጊታሩን ይዞ ከባንዶቹ ጋር የሚፈጥረው የተለየ ውህደት የሙዚቃን ግሩም ቃና ያሳያል። ሙዚቃን በልምድ ብቻ ሳይሆን በእውቀትም ጭምር እንዲኖራት ያደረጉትን ልዩ ልዩ ክህሎቶችን 1987ዓ/ም ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት ከውጭው ዓለም የሙዚቃ መሳሪያዎች በቼሎና በፒያኖ እንዲሁም ከአገር ውስጥ የባህል መሳሪዎች ደግሞ በክራር ተምሮ ለመመረቅ ችሏል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ የኤልያስ መልካ አሻራ እጅግ ግዙፍ ነው። በአልበም ደረጃ ብቻ 30 የተለያዩ አልበሞችን አቀናብሯል። ሙዚቃን ከማቀናበርም ባለፈ በዘመናዊው ሙዚቃ ውስጥ ስማቸው ገኖ መውጣት የቻሉ በርካታ ሙዚቀኞችን በብቃት እንዲሻገሩ ገርቶ አቅንቷቸዋል። በሙዚቃ ውስጥ የወለዳቸው አባታቸው ነውም ለማለት ያስደፍራል። ከእነዚህ መሃከል ሚኪያ በኃይሉ፣ እዮብ መኮንንን፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኃይሌ ሩት፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ትዕግስት በቀለ፣ ማህሌት ገብረ ጊዮርጊስ እና ጌቴ አንለይ ሁሉም የኤልያስ መልካን የሙዚቃ ጸበል ተጎንጭተዋል።
ኤልያስ በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ሙዚቃ ስጋና ደም ለብሶ በአካል የተገለጠ እስኪመስለን ከፊታችን እንድናይ ካደረገባቸው በርካታ አልበሞች ውስጥ አንደኛው የቴዲ አፍሮ ‘አቦጊዳ’ የተሰኘው አልበም ነው። ማራኪ በሆነው ድምጽ ላይ፣ በተዋጣለት የግጥምና ዜማ ውህደት የቀረበውን አልበም ግሩምና ድንቅ አድርጎ በማቀናበር የብዙዎችን የሙዚቃ ጥም አርክቷል።
በተወዳጁ የሙዚቃ ሰው የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያውጠነጥን አንድ መጽሀፍ ከዓመታት በፊት ለንባብ የበቃ ሲሆን የዚህ መጽሀፍ ርዕስም ‘የከተማው መናኝ’ ይሰኛል። መጽሀፉ ገበያ ላይ ከዋለ በኋላ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ተወዳጅና ተፈላጊ ለመሆን ችሏል። ምክንያቱ ደግሞ ስለ እርሱ የሰማ ሁሉ የእርሱን የህይወት መንገድ ለማወቅ ይጓጓ ስለነበር ነው። ኤልያስ እልም ካለው የከተማ ፎቆች ጫካ ውስጥ ገብቶ የእውነትም መንኖ ነበር። እሱን የሚፈልግ ሰው ሊያገኘው የሚችለው ከከተማው ጎዳናዎች አልያም ሆቴሎች ውስጥ አልነበረም። እሱ ከሁሉም ነገሮች እርቆ እራሱን በሙዚቃ ውስጥ በመደበቅ የነብሱን ጥሪ ሲኖር ነበር።
ኤልያስ መልካ በስራዎቻቸው ላይ ነብስን ዘርቶ ያበቀላቸው ብዙ ድምጻዊያን ቢኖሩም ከእነዚህ መሃከል ሁሌም በልዩነት የሚነሳ አንድ ድምጻዊ አለ። ኤልያስ መልካ ብለን መቼም እዮብ መኮንን አንዘነጋውም። የዚህ ትልቁ ሚስጥር ደግሞ ኤልያስ መልካ እዮብን እንደራሱ አድርጎ በመቅረጹ በትክክልም የእርሱን መንገድ መጓዝና ማየት የቻለ ሰው በመሆኑ ነው። ለዚህም በእዮብ መኮንን ሙዚቃዎች ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ግጥምና ዜማዎች የኤልያስ መልካ ውስጣዊ አሻራዎች ናቸው።
ኤልያስ እራሱን በእዮብ ውስጥ ገንብቷል፣ እንዲሁም ደግሞ እዮብ በኤልያስ ውስጥ ነበር። በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ከእዮብ ሙዚቃዎች ከሶስት ስራዎች በስተቀር ሁሉም የኤልያስ መልካ ስራዎች ናቸው። የሁለቱም ማንነት እጅጉን የተዋሃደ ስለነበር ከስራ ውጭ የነበራቸው ቀረቤታም የተለየ ነበር። ሁለቱም ግን እንደ ወይን እንደጣፈጡ ሳይጠገቡ መሄዳቸው ልብን የሚሰብር ነበር።
ቅጣትና ምህረት ዛሬ ሰው ለያዩ
አንዱን ከፍለው አንዱን አለፉ እንዳላዩ
የኤልያስ አሻራ ካረፈባቸው የእዮብ መኮንን ስራዎች መሃከል ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ እንዳጠፋሽ፣ ደብዝዘሽ፣ የቋንቋ ፈላስፋ፣ ነገን ላየው, ረከዳ፣ ማን እንደቃል፣ የምድር ድርሻዬ፣ ይዘባርቃሉ እና ሌሎች በርካታ ስራዎችም ይገኛሉ።
ይህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ገና በወጣትነቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አጃኢብ የሚያሰኙ ወደርየለሽ ስራዎችን ቢሰራም የዛኑ ያህል ሽልማቶችን አግኝቷል ለማለት ግን ይቸግራል። በጥቂቱም ቢሆን ግን በተለያዩ ጊዜያት እውቅናና ሽልማቶች ተበርክተውለታል። ስራ የማይታክተው ብርቱም ነበርና ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በፋና የድምፃውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ መናኙ የሙዚቃ ሰው ኤልያስ መልካ ከሙዚቃ የተሰወረ ምንም ህይወት አልነበረውም።
ከሙዚቃ አስተርፎ ለራሱ ያኖራት ሽርፍራፊ እድሜም እንኳን አልነበረችውም። የቱንም ያህል ሙዚቃን የሚወድ ሰው ቢሆን ይህን ያህል እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው አለ ለማለት የሚከብድ ቢሆንም፤ ከሰገነቱ በላይ፣ ከምናየው ጥግ ያለውን የእርሱን ሕይወትና የሙዚቃ ፍቅር መመስከር የሚችለው ከመንደሩ ሆኖ እውነታውን መመልከት የቻለ ብቻ ነው። ለዚህ መናኝ ከሙዚቃ ያለፈ ሕይወት አልነበረውምና ትዳር እንኳን አልመሰረተም ነበር።
ለተሰጠው ታላቅ ጸጋ እንደተሰጠ የኖረው ኤልያስ መልካ፣ ከሙዚቃ መሳሪያው ፊት ለፊት ከምትገኘው፣ መንኖ ከተቀመጠባት ወንበር አብዝቶ ከማዘውተሩ የተነሳ ለኩላሊት ህመም ተዳርጎ ነበር። በህክምና እየተረዳ ቢቆይም ስር የሰደደው ህመሙ አይሎ ማንም ሊረታው ያልቻለውን የሙዚቃ ፍቅሩን ሞት ረታው። እናም መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም በ42 ዓመቱ ይህችን ምድር ተሰናብቶ ሄደ። ኤልያስ መልካ ለሙዚቃ መጣ፣ ለሙዚቃ ኖሮ፣ ለሙዚቃም ሞተ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2015