እግር ጥሎት አሊያም የጤና እክል ገጥሞት ወደ ጤና ተቋም ጎራ ያለ ሰው ብዙ ነገሮች ሊታዘብ ይችላል። እኔም አንዱ ነበርኩ። ጤናቸውን ሊታዩ አጎቴ ከክፍለ ሀገር መምጣታቸውን ሰምቼ ልጠይቃቸው በሀገሪቱ ሥመ ጥር በሆነ አንድ የመንግስት ሆስፒታል ጎራ አልኩ። በተራ መጠበቂያው አግዳሚ ወንበር ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ታካሚዎች ተኮልኩለዋል። በርካቶቹ በቀጠሮ መምጣታቸውን አረጋግጠውልኛል።
ተራው የደረሰ ታካሚ በክፍሉ ገብቶ ሲወጣ ከተራ ጠባቂዎቹ ታካሚዎች መካከል ‹‹ዶክተሩ ማን ነው? እከሌ ናቸው? ያኛው ወጣቱ? አይ! ዶክተር እከሌ እሳቸው የት ሂደው ነው?›› የሚሉ ከሦስት በላይ ታካሚዎች ተመለከትኩ። አንዳንዶቹ ታካሚዎች ወጣት ዶክተሮችን ‹‹ስህተት ፈጻሚ›› አድርገው የሚያዩበት የተንሸዋረረ እይታ ላይ ብዙዎች አይስማሙም፤ በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶችስ ምን አመላከቱ? መልሱን ከፅሁፉ።
በዚህ መነሻነት በወጣት የሕክምና ባለሙያዎች ዙሪያ ታካሚዎች፣ ሕብረተሰቡ፣ራሳቸው ሙያተኞቹ እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አስተያየት አካትተን በዚህ መንገድ አቅርበነዋል።
በደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ከተማ አሠፋ እንዳሉት፤ ‹‹የሕክምና ስህተቶች በየደረጃውና በየዘርፉ የሚከሰቱ ናቸው። ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዶክተሮች ድረስ ስህተት ሊፈጠር ይችላል። በወጣት ዶክተሮች ዘንድ የሰፋ ነው ማለት አይቻልም። በጣም ጠንቃቃ ወጣት ዶክተሮች ሞልተዋል። በሥፋት በማህበረሰባችን ዘንድ የሚስተዋል አንድ ልማድ አለ፤ ይኸውም ‹ዶክተር እከሌ ያድነኛል› ብሎ ደምድሞ ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣት ይስተዋላል።
‹‹አጋጣሚ ሆኖ ይሄ ታካሚ በአዕምሮው የጠበቀውን ካላገኘ በሌሎች ዶክተሮች ለሚያገኘው አገልግሎት እምብዛም እርካታ የለውም። ካልተሻለውም ‹ዶክተር እከሌ ሥላላከመኝ ነው› ማለቱ አይቀርም። ምናልባት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዶክተሮች ለታካሚው የሚያሳዩት አቀራረብ የተሻለና ጥሩ ሊሆን ይችላል። ከረዥም ልምድ የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና ያውቁታል።›› ዶክተር ከተማ ይናገራሉ።
በሚፈልገው መንገድ አቀራረባቸውን ሲያሳምሩለት በመጠይቅ የሚሟሉ ለሕክምናው እገዛ የሚያደርጉ እውነተኛ መረጃዎችን በማግኘት
በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በዚህ ረገድ ትዕግስተኛ ሆኖና ጊዜ ሰጥቶ ከማዳመጥ ይልቅ ፈጥነው ካፉ በመረዳት በአጭር ጊዜ የሚያክሙ ወጣት ዶክተሮች አሉ። በዚህ ወቅት ታካሚው በተገቢው እህ ብሎ መቼ አዳመጠኝ ሊል ይችላል።
እንደ ዶክተሩ ገለጻ ከሚስተናገደው ታካሚ ብዛት አኳያ ጊዜ ለመቆጠብ ስትል የምትጠይቀውን ብቻ በአጭሩ እንዲነግርህ ልታደርግ ትችላለህ። በዚህ ወቅት ወጣት ዶክተር ከሆነ ‹‹ትዕግስት የለውም፣አልሰከነም….ወዘተ ልትባል ትችላለህ። ረጋ ብለህ አናግረኛ! የት ልትደርስ ነው? የሚሉና ሌላም ሌላም ሥድብ ጭምር የሚናገሩ ታካሚዎች ይገጥሙሃል፤እነሱን አብርደህ ማግባባት ይኖርብሃል።›› ሲሉም ዶክተሩ ይገልፃሉ።
ታካሚውና ማህበረሰቡ ከአቀባበል ሰላምታ ጀምሮ እያንዳንዷን ተግባር ስታከናውን በጥንቃቄ ይከታተልሃል። የዚህ አይነቱን ባህሉንና ወጉን ተላብሶ በጥንቃቄ በመተግበር በኩል ነባር ዶክተሮች የተሻሉ ናቸው የሚሉት ዶክተር ከተማ ረዥም ሰዓት አገልግሎት በሚሰጥባቸው ክፍሎች የሚሰሩ ወጣት ዶክተሮች የመድከም አለያም የመሰላቸት ሥሜት ሊታይባቸው ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በአጠቃላይ የሕክምና ሥህተት ወጣቶቹም ሆኑ አንጋፋዎቹ ዶክተሮች ሊሰሩ ይችላሉ። በእነዚህ ይብሳል ብለህ የምትወስነውና የምትደመድመው አይደለም ብለዋል።
ከልምድ የሚገኘው እውቀት እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው ጉዳይ ግን ለሙያው ሥነምግባር ተገዥ ሆኖ አገልግሎት መስጠቱ ላይ ነው። በሌላ በኩል የማህበረሰቡ አስተሳሰብ እንዲለወጥና እንዲሻሻል ማስተማር ተገቢ ነው። ይህ ከሆነ ወጣት ሐኪሞች ሰርተው በቀላሉ የሚረኩና የሚደክሙ አይደሉም። መምራት፣ መደገፍ፣ማብቃትና ብሎም አውቅና መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
በየአካባቢው የሚገኝ ማንኛውም የጤና ተቋም ለማህበረሰቡ እኩል አገልግሎት የሚሰጥ ነው። በዚያ አገልግሎት ለመስጠት የተሰማራ የሕክምና ባለሙያም እኩል አገልጋይ ነው። ለሕክምና የሚመጡ ሰዎችም ታክመው ከህመማቸው ማገገም እና መዳን እንደሚችሉ ሙሉ እምነት ሊያሳድሩ ይገባል።ይህ ካልሆነና በጥርጣሬ የተሞሉ ከሆነ የታዘዘውን መድሃኒት የመጨረስ ወኔ ያጣሉ ሲሉም ይመክራሉ።
ቀጥሎም ደግሞ በታከሙበት ጤና ተቋም ከዚያም አገልግሎት በሰጣቸው ዶክተር ላይ ጭምር ጥርጣሬን ያሳድራሉ። ማህበረሰቡ መብትና ግዴታውን በተገቢው መወጣትና መጠየቅ ሲጀምር ችግሩ የሚቀረፍ ይመስለኛል ሲሉ ዶክተር ከተማ አሰፋ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ዘርፍ ረዳት መምህርና የራዲዮሎጂ ባለሙያው ወጣት የኑስ ሞላ በበኩላቸው፤ የሕክምና ሥህተቶች በሀገሪቱ እምብዛም ትኩረት የተሰጣቸው ጥፋቶች አልነበሩም ብለዋል።
አሁን አሁን ግን በቂም ባይሆን የዚህ አይነት ሥህተቶች ተጠያቂነት ማስከተል ጀምረዋል። በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም ምክንያቱም የሥህተቶቹ የመጨረሻ ማረፊያቸው ሕይወት ማጥፋት አለያም አካል ማጉደል በመሆኑ ነው።
ስለዚህ ከዚህ በኋላ በሚፈጠሩ ሥህተቶች በየትኛው እድሜ እና ልምድ ውስጥ በሚገኙ ባለሙያዎች እንደተፈጠሩ ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል። እስከ አሁን ባለው ሂደት ግን የተጠያቂነት ልምዱና አድማሱ ከፍተኛ ባለመሆኑ የተደራጀ መረጃ በውል ተለይቶ የመያዝ ክፍተትም ይኖራል።
በመሆኑም የሙያውን ሥነምግባር በማይጠብቁና በማያከብሩ በወጣትነትም ሆነ በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ሥህተት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚሉት ወጣት የኑስ በርካቶቹ ችግሮች በእንዝህላልነት የሚፈጠሩ ናቸው። በእርግጥ በሙያው የብቃት ውስንነት ያለባቸው ሐኪሞች አይኖሩም ማለት አይደለም ይላሉ።
እነዚህ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው የማህበረሰቡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ደረጃም ሊሰፋና ሊያድግ የሚችልበት መንገድ መታሰብ አለበት። የሰለጠነና በምክንያት የሚሞግት ማህበረሰብ በተፈጠረ ቁጥር የህክምና ባለሙያዎች ጥንቃቄ እየጨመረ ይሄዳል። ከዚህ ባለፈ አገልግሎት በሚሰጧቸው የሕክምና ተቋማትና የሕክምና ባለሙያዎች ላይ እምነት ማሳደር መለመድ አለበት። ባህላችን ሊሆን ይገባል
ሲሉም አብራርተዋል።
በማህበረሰቡ የሚንጸባረቁትን ወጣት የሕክምና ባለሙያዎች በአብዛኛው ለሕክምና ሥህተት ተጋላጭ የሚሆኑ አድርጎ የማየት ዝንባሌን የሚያረጋግጥና የሚያሳይ የጥናት ውጤት ድምዳሜ የለም። በዚህ ዙሪያ ከተደረጉና ለሕትመት ከበቁ የቅርብ ጊዜ ጥናትና ምርምሮች ‹‹በአዲስ አበባ የሚገኙ ዶክተሮች የሙያ ሥነ ምግባር ደንቡን የመተግበር ልምዳቸውና ተያያዥ ችግሮች (practice of code of ethics and associated factors among medical doctors in Addis Ababa) በሚል በመስፍን አበጀ ተጠንቶ በ2010 ዓ.ም የታተመው በአስረጅነት ይጠቅሳሉ።
ፅሁፉ በዓለም አቀፍ ጆርናል ለሕትመት የበቃ ነው። የዚህ ጥናት ድምዳሜ የሚያሳየው በሥነምግባር ግድፈት በርካታ የሕክምና ሥህተቶች ይፈጸማሉ። የሥነምግባር ችግሮቹም በየትኛውም የእውቀትና የእድሜ ደረጃ ላይ በሚገኙ የሕክምና ሙያተኞች የሚስተዋልና የሚፈጠር ነው።
በጥናቱ ሶስት የመንግስት ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ከመንግስት እና ከግል ሆስፒታሎች 500 ዶክተሮች በናሙናነት ተካትተዋል፤ በቃለመጠይቅና በተለያዩ መንገዶች ተዳሰዋል። ከዚህ ውስጥም 152(30 ነጥብ 4 በመቶ) የሆኑት ዶክተሮች የሙያው የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው ማረጋገጥ ተችሏል።
በእድሜ ረገድ ደግሞ በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ ከ25 ዓመት እስከ 34 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ዶክተሮች በተሻለ መንገድ የሙያ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው የመስራት ልምድ እንዳላቸው ያሳየ ሲሆን በእድሜ ከ25 እስከ 29 የሆኑት በእድሜ ከ30 እስከ 34 ከሆናቸው ዶክተሮች በ2 ነጥብ 7 በመቶ በሙያ ሥነ ምግባራቸው የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ጥናቱ አሳይቷል። በሌላ በኩል የረዥም ጊዜ ልምድ የሚያስገኛቸው ትሩፋቶች እንዳሉም ጥናቱ አመላክቷል።
ጥናቱ እንዳመለከተው የህክምና ስህተት በስራ ህይወት ውስጥ ያለ ቢሆንም ስህተቱ ግን እድሜን ወይም ደግሞ ወጣቶች ይበልጥ ጥፋት ፈፃሚ እንዳልሆኑ አረጋግጧል። በመሆኑም ከ25 ዓመት እስከ 34 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ዶክተሮች በተሻለ መንገድ የሕክምና ሙያ ሥነምግባራቸውን አክብረው የተገኙ ናቸው። ይህ ማለት የሚፈፅሙት ስህተት ከእድሚያቸው ጋር የተያያዘ አለመሆኑን
በእርግጥም ጥናቱ አረጋግጧል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በሙሐመድ ሁሴን