የኑሮ ውድነት በዓለምአቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን መሰረታዊ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። የገበያን ዋጋ ለማረጋጋት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም የኑሮ ውድነቱ በሚፈለገው ደረጃ አልወረደም፡፡ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚታየው የማቴሪያል ዋጋ በተለይ የሲሚንቶ ዋጋ መጠነኛ የዋጋ መቀነስ አሳይቶና ገበያው ተረጋግቶ የቆየው ለትንሽ ጊዜ ብቻ ነው። አሁን ግን የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል እስከ 1950 ብር እየተሸጠ ይገኛል። የአህል ዋጋን ለማረጋጋት በመንግሰት ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ወደሚፈለገው ደረጃ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም መንግስት ገበያን ለማረጋገት እየሰራ ነው።
በሸማቾች አማካይነት ገበያን ለማረጋጋት መንግስት የወሰደው እርምጃ በተለይ ጤፍ ባለበት ዋጋ ላይ እንዲቆም አድርጎታል። የኢኮኖሚ ገቢው አነስተኛ የሆነው ኅብረተሰብ በነጋዴዎች ከመበዝበዝ ይልቅ ከሸማቾች ማኅበራት እህል በመገብየት የዕለት ኑሮውን እንዲደጉም አስችሎታል ። ሆኖም ይሄ በቂ አልሆነም።
ከንግድ ሥርዓቱ አለመስተካከል በተጨማሪ የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ምክንያቶች ሌላኛዎቹ የንግዱ ማህበረሰብ” ነገ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል” በሚል የሚያደርገው መደበቅ፣ በሌላም በኩል ደግሞ ሸማቹ ማኅበረሰብ ምርት ከገበያ ላይ ሊጠፋ ይችላል ብሎ በመስጋት በብዛት ገዝቶ ለማከማቸት የሚያደርገው መስገብገብ ጭምር ነው። ለኑሮው መወደድ ሌሎች ዓለምአቀፋዊና አገራዊ ምክንያቶች ቢኖሩም እንኳን ያንን ምክንያት የሚያባብሰው ነጋዴውና ሸማቹ ጭምር ነው።
የንግዱ ማኅበረሰብ ህገወጥ ወይም ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ሲያደርግ ሸማቹ ማህበረሰብ “በህገ አምላክ” ብሎ ከሚመለከተቻው አካለት ጋር በመሆን ሕገወጦች ስርዓት እንዲይዙ ማገዝና በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ማድረግ አለበት። በእኛ አገር ግን መብቱን የሚጠይቅ ሸማች አለ ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም። ለገዛው ማንኛውም ምርት ደረሰኝ መጠየቅና መቀበል መብቱ ቢሆንም ይሄንን ሲተገብር አይታይም። የሸማቾች ማኅበራት ለሸማቹ የሸቀጣ ሸቀጥና የእህል አቅርቦት ከመሆን በተጨማሪ የሸማቹ መብት የሚከበርባቸው አውዶች እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል።
ስለሆነም ሸማቹ ማኅበረሰብ በግብይት ወቅት የሚፈጸሙ የንግድ ጥሰቶችን መከላከል እንዲችልና ለመብቱ እንዲታገል ግንዛቤውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዙሪያ መስራት የሚገባቸው የሸማቹ መብት ተከራካሪና ተቆርቋሪ አካላትና ማህበራት ሊኖሩና ሊጠናከሩ ይገባል።
“በደረሰኝ ግብይት ይፈጽሙ መብትዎን ያስከብሩ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰሞኑን የሸማቾች መብት ቀን ታስቦ ውሏል። በግብይት ወቅት የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን በሕግ አግባብ ብቻ መፍታት ስለማይቻል ሸማቹ መብቱን እንዲያስከብር ግንዛቤ ለመፍጠር የተካሄደ ነበር።
በተቋማት በኩል የንግድ ሥራ ጥሰቶች ሲፈጸሙ በሕግ አግባብ ማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፣ የግብይት ሂደቶችንና የዋጋ ጭማሪዎችን ለመከላከል ለመብቱ የሚታገልና ጠያቂ ሸማች ማኅበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው ፡፡
ሸማቹ መብቱን አውቆ ሲገዛ የማማረጥ፤ ካልሆነውም የመተው መብቱ በተጨማሪ በግብይቱ ጉዳቶች ሲደርስበት ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳለው ሊያውቅ ይገባል።
በግብይት ሂደት ውስጥ ሸማቹ ጥራቱን የጠበቀና፣ ጊዜው ያላለፈበት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የመግዛትና ከመረጠው የንግድ ተቋም የሚፈልገውን ምርት የመሸመት መብትም አለው።
ሸማቹ ለግብይት ሲወጣ መብቱን የማይጠቀም ከሆነ ደግሞ ነጋዴው እንደፈለገው የዋጋ ጭማሪ ሊያደርግ ስለሚችል ይህንን መታገል ያስፈልጋል። ሸማቹ ማኅበረሰብ መብቱን ጠንቅቆ ባለማወቁ የተነሳ የሕግ መብት ጥሰት ሲከሰት ይስተዋላል። ስለሆነም ሸማቹ ማኅበረሰብ የተቀመጠለትን መብት እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሸማቹ ማኅበረሰብ መብቱን እንዲያውቅና በግብይት ወቅት ክፍተት ሲፈጠር ቅሬታውን ለማቅረብ ወዴት መሄድ እንዳለበት እንዲያውቅና በተሰጠው መብት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት ሊደረግ ይገባል። በግብይት ወቅት የሚፈጸሙ የሕግ ጥሰቶችን ለመከላከል ሸማቾች በደረሰኝ ግብይት ተጠቅመው መገበያየት ይኖርባቸዋል ።
ይሄ ልምድ ባለመዳበሩ ግን በአሁኑ ወቅት ደረሰኝ መጠየቅ እንደቁም ነገር አለመቁጠርና የንግዱ ማኀበረሰብም ደረሰኝ ሲጠየቅ የሚያጉረመርምበት ሁኔታ ነው ያለው። ነጋዴውም ለሰጠው ማንኛውም ግብይት ጥያቄ ሳይቀርብለት ደረሰኝ መስጠት ግዴታው መሆኑን ፤ ተጠቃሚውም ትክክለኛው ደረሰኝ ማግኘት መብቱ እንደሆነ መታወቅ አለበት። ይሄ ሲ ሆን ነው አገር የም ታድገውና ህገወጥነት እየቀነሰ ህ ጋዊነት እያበበ የሚሄደው።
ለዚህ ደግሞ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚከበር የሸማቾች ቀን መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኅብረተሰቡን በማስተማር የህግ ስርዓቱን የሚያደነቃቅፉትን ደግሞ በመቅጣትና በማስተማር እንዲሁም ለሌሎች እንዲማሩበት በማድረግ የሸማቹን መብትና ጥቅም እንዲከበር ማድረግ ይገባል። ሸማቹ ማኅበረሰብም መብቱን ለማስከበር ጠንክሮ መስራት አለበት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም