ተወልዶ ያደገው የስንዴ ምርት በስፋት በሚመረትበት ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን አሳሳ ከተማ ነው። ቤተሰቡን ጨምሮ አብዛኛው የአካባቢው ማህበረሰብ ግብርና የኑሮ መሰረታቸው ሲሆን፣ እሱም ይህን እየተመለከተ አድጓል። ግብርናውን ጨምሮ በንግድ ሥራም የተዋጣለት ለመሆን መብቃቱን ይናገራል። ወላጅ አባቱን ተከትሎ አሽከርካሪነትን፣ የእህል ንግድን፣ የትራንስፖርት አገልግሎትንና የኮምባይነር ሥራን በመሥራት ውጤታማ መሆን ችሏል። ይህ ሰው የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ ፍቅሩ ጋረደው ይባላል።
ከትምህርት ይልቅ ለንግድ ሥራ በማድላት ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ብቻ የተማረው አቶ ፍቅሩ የ“ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ” መስራችና ባለቤት ነው። እሱ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ወላጅ አባቱ መሰረቱ መሆናቸውን ይገልጻል። ከግብርና ሥራ የተነሱት ወላጅ አባቱ የእህል ወፍጮ ቤት አቋቁመው፣ እህል ነግደው የጭነት መኪና ገዝተዋል። በጭነት መኪናውም የወፍጮ ቤትና የእህል ንግድ ሥራቸውን ይበልጥ አጠናክረዋል።
የሥራ ባህልን ከቤተሰቡና ከአካባቢው ማህበረሰብ የተማረው የዛሬው ታታሪ ባለሀብት አባቱን ለሰባት አመት በአሽከርካሪነት አገልግሏል። ይህን ሁሉ የተረዱት አባትም ‹‹ሰርተህ ትከፍላለህ›› በሚል ለፍቅሩ የሥራ መኪና ገዙለት። እሱም ሌት ተቀን ስርቶ መኪናው የተገዛበትን ገንዘብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መለሰ።
ይህ ስኬቱ በሁለተኛው ዓመት ኮምባይነር መግዛት አስቻለው። ወዲያውም የአርሶ አደሩን አዝመራ መሰብሰብ ውስጥ ገባ። በኮምባይነር ስራውም ከአንድ ኮምባይነር ወደ ሁለት እያለ ውጤታማ ሆነ። የኮምባይነር ሥራ ጊዜያዊ መሆኑ ያሳሰበው አቶ ፍቅሩ፣ የትራንስፖርት ፈቃድ አውጥቶ የአፈር ማዳበሪያና እርዳታ የመሳሰሉትን በማጓጓዙ ስራ ደግሞ ተሰማራ። ይህ ውሳኔው ጊዜያዊ ችግርን ወደ እድል መቀየር የሚችል እሳቤ እንዲያዳብር አድርገው።
የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ለተለያዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ስንዴ ያከፋፍል ነበር። አዲስ አበባን ጨምሮ ሀዋሳና አዳማ ላይ ለሚገኙ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የስንዴ ምርትን ሲያከፋፍል በመሰል ስራ ላይ ቢሰማራ ውጤታማ እንደሚሆን ተገነዘበ። ስንዴን በግብአትነት የሚጠቀም ፋብሪካ ማቋቋም እንዳለበትም ወሰነ።
ፋብሪካ የመገንባት ውስጣዊ ፍላጎቱን አንግቦ ወደ አዳማ ያቀናው አቶ ፍቅሩ፤ በ2003 ዓ.ም አራት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በአዳማ አካባቢ ጋራ ዱኮ ቀበሌ ላይ ፋብሪካውን በመገንባት ወደ ሥራ ገባ። ግንባታውን እንዳጠናቀቀም በአነስተኛ አቅም የስንዴ ዱቄት ማምረት ጀመረ። በወቅቱ በቀን 420 ኩንታል ዱቄት ብቻ ያመርት እንደነበር ያስታውሳል። በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው አቅሙን በማሳደግ በቀን 1920 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ያመርታል። ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ማምረት እንዳይችል አልፎ አልፎ የመብራት መቆራረጥ ቢያጋጥመውም ችግሮችን ተቋቁሞ በማለፍ የፋብሪካውን አቅም እያሳደገ መጥቷል።
በአነስተኛ አቅም ዱቄት ብቻ በማምረት ወደ ሥራ የገባው ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ዱቄት የማምረት አቅሙን ከማሳደግ በተጨማሪ የተለያዩ ብስኩቶች ማምረት የሚያስችሉትን ሁለት አይነት ዘመናዊ የብስኩት ማሽኖችን በመትከል የተለያዩ አይነት ጣዕምና ይዘት ያላቸውን ብስኩቶች እያመረተ ይገኛል። ፋብሪካው ከዱቄትና ከተለያዩ የብስኩት ምርቶቹ በተጨማሪም ወደ ችፕስ ምርት መግባት መቻሉን የጠቀሰው አቶ ፍቅሩ፤ ምርቶቹን ማስፋት የቻለውም ፋብሪካውን በማስፋትና የተለያዩ ማሽኖችን በመትከል እንደሆነ ይናገራል።
ስምንት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል በመያዝ የፋብሪካ ሥራን ዱቄት በማምረት የተቀላቀለው አቶ ፍቅሩ፤ በመጀመሪያ አራት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ፋብሪካውን እንዳቋቋመ አጫውቶናል። ሥራውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ በመሄድም የፋብሪካ ምርቶቹን ለማሳደግ ፋብሪካውን አስፋፍቷል። የፋብሪካ ይዞታውንም ወደ 14 ሺ 600 ካሬ ሜትር ስፋት በማሳደግ ምርቶቹን በከፍተኛ ጥራት እያመረተ ይገኛል።
ፋብሪካው ከሚገኝበት 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የድንች ምርት በስፋት እንደሚመረት ያጫወተን አቶ ፍቅሩ፤ በዚሁ መነሻ ነው ወደ ቺፕስ ማምረት የገባው። ዩኒክ በሚለው የንግድ ስሙ በአሁኑ ወቅት ድንች ላይ እሴት ጨምሮ ዩኒክ ችፕስን አምርቶና አሽጎ ለገበያ ያቀርባል።
ፋብሪካው በአካባቢው የሚመረተውን ድንች ፋብሪካው በቀጥታ መጠቀም እንዲያመቸው ድንች አምራች ከሆኑ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሯል። በተፈጠረው የገበያ ትስስርም አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለፋብሪካው እያስረከበ ይገኛል። ይህም ፋብሪካውን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የገበያ ዕድል በመፍጠር ምርቱን በቀላሉ መሸጥ እንዲችል አግዞታል።
ከቺፕስ ማምረት ባሻገር በስንዴ ዱቄት የተለያዩ ምርቶችን ማምረት እንደሚችል የተረዳው አቶ ፍቅሩ፤ የሁሉም ነገር መነሻው በሆነው ዱቄት ላይ ከ2004 እስከ 2011 ዓ.ም ትኩረት አድርጎ ሠርቷል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮም ጥናት በማድረግና በዕቅድ በመንቀሳቀስ ወደ ብስኩት ምርቶች መሸጋገር እንደቻለ ነው የገለጸው።
አቅሙን እያሳደገ በጥናትና በዕቅድ ወደ ብስኩት ማምረት የገባው ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፤ አንደኛውና መደበኛው ብስኩት በሚያመርተው ማሽን በሰዓት 1450 ኪሎ ግራም ብስኩት የማምረት አቅም አለው። ሁለተኛውና ዋፈር የተባለውን ለህጻናት ምግብ መሆን የሚችለውና ጣፋጭ ብስኩቶችን የሚያመርተው ዘመናዊ ማሽን ደግሞ 250 ኪሎ ግራም ዋፈር ብስኩት የማምረት አቅም አለው። ቺፕስን በተመለከተም በቀን 200 ኪሎ ግራም ቺፕስ እያመረተ ይገኛል።
በአብዛኛው ህጻናት የሚጠቀሙት ዋፈር የተባለው የብስኩት አይነት የተለያየ ጣዕም ያለውና ወተት፣ ቅቤና ሌሎች ግብዓቶችንም የሚፈልግ እንደሆነ የገለጸው አቶ ፍቅሩ፤ ከስንዴ በስተቀር ተጨማሪ የሆኑ አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ አገር የሚመጡ በመሆናቸው በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሚያጋጥመው ጠቁሟል። ይሁንና አሁን አሁን እንደ ቅቤ ያሉ ግብዓቶች በአገር ውስጥ እየተመረቱ መሆኑ አበረታች ነው ይላል። ነገር ግን የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ምርቶች የሚያመርት አምራች ኩባንያ በአገሪቱ ባለመኖሩ ግብዓቶቹን ከውጭ ማምጣት የግድ ነውና አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ ናቸው ይላል።
ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ምርቶቹን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ናቸው። ወኪል ከሆኑ ነጋዴዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የክልል ከተሞች ተደራሽ መሆን እንደቻለ ይናገራል።
በፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዘይት ምርት ለመሰማራት የፋብሪካ ግንባታውን አስጀምሯል። በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የዘይት ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ምግብ አምራች ፋብሪካ እንደመሆኑ ዘርፉን የተቀላቀለው አቶ ፍቅሩ፤ በአዳማ ከተማ አካባቢ ቦኩ ሸነን ቀበሌ ከከተማ አስተዳደሩ በተረከበው 30 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የዘይት ፋብሪካውን እየገነባ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ግንባታውን አጠናቅቆ ወደ ምርት ለመግባት የማሽን ጥናት እያደረገ ይገኛል።
የዘይት ፋብሪካው ሲጠናቀቅም 1100 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ዱቄት፣ ብስኩትና ችፕስ በማምረት የሚታወቀው ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ አጠቃላይ 800 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከእነዚህ መካከልም 580 የሚደርሱት በቋሚነት ሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ፋብሪካው የተለያዩ አበርክቶዎችን ለማህበረሰቡና ለመንግሥት እያደረገ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ፍቅሩ፤ በተለይም አገራዊ ለሆኑ ማንኛቸውም ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ቀዳሚ መሆኑን ይናገራል። ለአብነትም በ2014 ዓ.ም ብቻ ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ለተደረገለት ጥሪ ከሶስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል። በክፍለ ከተማ ደረጃም እንዲሁ ትምህርት ቤትና የስብሰባ አዳራሽ ገንብቶ አስረክቧል። አዳማ ከተማን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ፋብሪካው ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በተለይም ዱቄት በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንዲችሉ በአካባቢው የችርቻሮ መሸጫ ሱቅ ከፍቶ ምርቱ ነጋዴ ጋ ሳይደርስ የአካባቢውን ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ያደርጋል። ፋብሪካውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት እንዲችል የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ፋብሪካ ከሚጠቀመው የውሃ መጠን ባለፈ በአካባቢው የውሃ እጥረት በሚገጥምበት ወቅት ማህበረሰቡ የጉድጓድ ውሃውን በፈለገ ጊዜ እንዲጠቀም እያደረገ ይገኛል። ለፋብሪካው ሠራተኞች ቁርስ በነጻ እንዲሁም ምሳም 50 በመቶ ወጪ በመጋራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሠራተኞችን እያገዘ እንደሆነም አቶ ፍቅሩ አጫውቶናል።
በአሁኑ ወቅት የስንዴ ምርት በአገሪቱ ባልተለመደ መልኩ በስፋት እየተመረተ መሆኑ በተለይም እንደ ፍቅር የምግብ ማቀነባበሪያ ላሉ ፋብሪካዎች የሚኖረው አበርክቶ የጎላ መሆኑን የሚናገረው አቶ ፍቅሩ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ገበያው በተወሰነ መንገድ መረበሽ ታይቶበታል ይላል። ይህም ለጉዳዩ አዲስ ከመሆን ጋር ተያይዞ የመጣ ቢሆንም በሥራው ላይ ግን ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ መቆየቱንና እንደነበር ጠቅሷል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በነበረው የግብይት አሰራር የስንዴ ምርቱ አዳማ ድረስ በስፋት ይቀርብ እንደነበር አስታውሶ፣ የፋብሪካውን የጥራት ደረጃ አሟልቶ ሲገኝ ፋብሪካው ወስዶ ያራግፍ እንደነበር ይገልጸል። አሁን ላይ ግን ከተለመደው የግዢ ስርዓት ውጭ ምርቱ ካለበት ቦታ ሄዶ መግዛት እንደሚያስፈልግ ይናገራል። የገበያ ስርዓቱ አዲስ እና ያልተለመደ በመሆኑ ለቁጥጥርም አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ጠቁሟል። አሁን ችግሩን ለማቃለል መንግሥት ኮታ መድቦ ፋብሪካዎች የስንዴ ምርት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም አስረድቷል።
በቀጣይ የፋብሪካውን ምርቶች በከፍተኛ ጥራትና በሙሉ አቅሙ ለማምረት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ፍቅሩ፤ በተለይም ግንባታው የተጀመረውን የዘይት ፋብሪካ አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ሥራ ማስገባትና እንደ አገር ያለውን የዘይት ምርት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረትን በማቅለል አማራጭ የመሆን እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑ ይጠቁማል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015