ቤተሰብ ስም ሲያወጣላት በምክንያት ነው። ሰላም እንዳየሁ በማለት የሰላምን አስፈላጊነት ገልጦባታል። በዚህም ለቤቱ ተስፋና ሰላም ሆና ዓመታትን ከእነርሱ ጋር ዘልቃለች። ነገር ግን ሰላሟን የማይሰጥ አንድ ነገር ገጠማት። ያለዕድሜዋ መዳር። ከትምህርቷ አስተጓጉለው ቤተሰቦቿ ሊድሯት መሆኑን ከሰማችበት ጊዜ ጀምሮ አእምሮዋ ታውኳል። ይህም ቤተሰቦቿ የፈጠሩት ነው። ምንም ሳያጎሉባት በቤት ውስጥ ቢያቆዩዋትም መማርን ግን ሊፈቅዱላት አልቻሉም። አግብተሽ ወልደሽና ከብደሽ ከእኛ ጋር ነው የምትሆኚው የሚል አቋም ነበራቸው። እርሷ ደግሞ ይህንን መቀበል አቃታት። በተደጋጋሚ ልታሳምናቸውም ሞከረች። እነርሱ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ አሉ።
አሁን ነገሮች ሁሉ ተወሳስበዋል። የሚሰማትም አንድም ዘመድ አላገኘችም። ገና በልጅነቷ ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንድትሆን ለአንዱ ልትዳር ነው። ስለዚህም ምን ማድረግ እንዳለባት ካወጣችና ካወረደች በኋላ በቀጥታ አንድ ድምዳሜ ላይ ደረሰች። ይህም ከቤተሰቧ ጠፍታ እግሯ ወዳመራት ቦታ መሄድ ነው። ልክ እንደ እርሷ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ሊጠፉ የተዘጋጁ ጓደኞች ነበሯትና ተነጋግረው በአንድ ምሽት ከቤት አመለጡ። መድረሻቸውንም አዲስ አበባ አደረጉ።
እነ ሰላም አዲስ አበባ ሲደርሱ ማንም የሚቀበላቸው አልነበረም፤ የሚያውቁት ዘመድም የለም። አዲስ አበባን እንደሰሟት አይነት ገነትም አይደለችም። በወከባ የተሞላች ነች። ሲመችም የሚያታልለው ብዙ ነው። እናም እነሰላም ይህንን ሲያዩ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ተጋቡ።
ማንን ማናገርና ማንን አምኖ መከተል እንዳለባቸው ግራ ገባቸው። በዚህም ጎዳና አዳሪነትን ለአንድ ቀን አዩት። በእርግጥ አውቶብስ ተራ ሌሊቱም ቀን ስለሆነ ብዙም አልተቸገሩም። ሆኖም ከአንድ ቀን በላይ ግን በዚያ አልቆዩም። በአንድ ቀን አዳር ቅጽበት ብዙ ተምረዋል። ስለዚህም አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ይህም ወደ ደላላ ቤት ሄዶ ሰው ቤት ተቀጥሮ ሕይወትን መግፋት። ደላላው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ገንዘቡ ነውና ታስተምርሻለች በሚል ሰላምን ለአንዷ የመሸታ ቤት ባለቤት አስረከባት። ጓደኞቿንም እንዲሁ ለመጣው ሰጥቷቸው ተበታተኑ። በወቅቱ ስልክ አልነበራቸውም። ሁሉም መማር ነውና አላማቸው እንደቀያቸው ሰው ሰው ሁሉ ቃሉን አክባሪ ነው በሚል ደላላው ወደ መራቸው ቤት ነጎዱ።
እንደአጋጣሚ ሆኖ የሰላም አሰሪ መጥፎ የሚባል ባህሪ ያላት ናት። ሰው ጤፉ የሚሏት አይነት ናት። በረባ ባልረባው መነታረክና ባስ ሲልም መደባደብ የምታዘወትር ሴት ናት። ከዚሁ ባህሪዋ የተነሳ አስተምርሻለሁ ያለቻትን ሁሉ ትታ መሸታ ቤቷን እንድታሟሙቅ ፈረደችባት። በእርግጥ ለወር ያህል ስትሰራ ምንም አልመሰላትም። ሥራ እንደሆነ ብቻ ነው የተሰማት። በዚህም የታዘዘችውን ማድረጓን ቀጠለች። ሁኔታው እያደር ነው ያማረራት። ጉንተላውና ያም ለኔ ያም ለኔ ማለቱ አሰቃያት፤ አሳቀቃትም።
ለሰላም ከዚያም የባሰባት ግን የባለቤቷ ድብደባ ነበር። እርሷን ያስገባቻት ለአሻሻጭነት በመሆኑ የምትፈልገውን ልትከውንላት አልቻለችምና በአገኘችው እቃ ሁሉ አናቷን ለማለት ትጋበዛለች። ከወንዶች ጋር እንድታድር ትገፋፋታለች። አንድ ቀንም እንደምትገላት ታስባለች። ስለሆነም በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማትችል ስታውቅ ከዚያ መውጣቱ አማራጭ እንደሆነ ታያት። ማቄን ጨርቄን ሳትልም ደሞዝዋን እንኳን ሳትቀበል ነበር ከቤቱ ትታ የጠፋችው። ግን የት እንደምትሄድ እንኳን አታውቅም። ማረፊያና ጊዜ ማሳለፊያ የሚሆናት ሰውም የላትም። አብራቸው ከሀገሯ የተሰደዱት ጓደኞቿ እንኳን ዛሬ ከአጠገቧ የሉም። እናም ብቻዋን ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ የተጋባችበት ጊዜ ነበር።
እግሯ ያደረሳት ቦታ ድረስ ስትጓዝ ያደረችው ሰላም ሊነጋጋ ሲል ጨርቆስ አካባቢ ወደአለ አንድ ድለላ ቤት ገባች። ለመኖር መስራት ግድ እንደሆነ ታውቃለችና መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎቿን አስቀድማ ሰው እንዲያገናኛት ጠየቀችው። በዚህ ውስጥ ግን ከሀገር ቤት የተሰደደችበት የትምህርት ጉዳይ የመጀመሪያው መሰረታዊ ነገሯ ሆኖ ቀርቧል። ምክንያቷ ደግሞ አንድ ነገር ነው፤ ይህንን እድል የሚሰጥ ሰው አዋቂና መልካም ሰው ነው የሚል እምነት አላት። እናም ያለፈው አይነት ስቃይና መከራ እንዳያጋጥማት ወደ ፈጣሪዋ በመጸለይ ጭምር ለደላላውም አደራ አለችው። ደላላውም በሀሳቧ ተስማማና አንዲት ሴት ስትመጣ አስተዋወቃት።
ስትታይ መልካም ትመስል ነበርና ሰላም እንዳለፈው እንዳይገጥማት እየጸለየች ነበር ወደ ሁለተኛዋ አሰሪ ቤት የሄደችው። ግን ደላላውም ሆነ ሴትየዋ እንደዋሿት ገና የሴትዮዋ ቤት እንደደረሱ ነበር ያረጋገጠችው። በፈጣን ምላሳቸው እንዳታለሏትም ተገነዘበች። ግን ደግሞ ከዚህ ብትወጣ የት ልትደርስ ትችላለች። ስለዚህም ልሞክረው በሚል ሁለተኛውን የስቃይ ቤቷን ጀመረች።
‹‹እኔ የማሰራሽ ሥራ በአንድ ጊዜ የሚለውጥሽን ስራ ነው›› ስትላት ምን ለማለት እንደፈለገች አልገባትም ነበር። ሴተኛ አዳሪዎች ከሞሉበት ቤት ከስር ከስር እያለች ስራዋን ቀጠለች። ወጣ ያሉ ተግባራትን ስታይ ጭምር ትሳቀቃለች። በተለይም ቤቱን የሞሉት ሴቶች አለባበስና አኳኳል እጅጉን ያስገርማል። ሆኖም በእነርሱ አካል ምን አገባኝ እያለች ሥራዋ ላይ ታተኩራለች።
አንድ ቀን ግን ይህ ክፉ አጋጣሚ ወደ እርሷም መጣ። አሰሪዋ ዛሬ ለየት ያለ ሰው ስለምታገኚ መዋብ አለብሽ አለቻት። ለምን የሚል ጥያቄዋን እንኳን አልመለሰችላትም። እየጎተተች ወደ መኝታ ቤቷ አስገብታ አይታቸው በማታውቀው መዋቢያዎች አሽቀረቀረቻት። አጭር ቀሚስ እንድትለብስም ታዘዘች። አጭር ቀሚስ በሌሎቹ ላይ ስታየው እንኳን ያስጠላታል፤ ያሸማቅቃታልም። ግን ምርጫ አልነበራትምና ብዙ ታግላ ተሸነፈች።
ቀጣሪዋ ከፍተኛ ገቢ እንደምታመጣላት ታውቃለችና ገና ከገባች ጀምሮ ነበር ስትንከባከባት የቆየችው። ‹‹ ድንግል›› የሚፈልግና ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰጣትን ሰውም ስታማርጥ ወራትን አሳልፋለች። በስተመጨረሻ ዋጋው ተተመነና ልጅቷ ቀረበች። ሰላም አብሯት ከሚያድረው ሰው ጋር ስትገናኝ ነበር ጉዷን የተረዳችው። ሰውዬው በአለባበሱ በጣም የሚያምር ነበር። ምንም የማይጎድለው አይነት ሰው ነው። ለሰላም ግን ምንም አልተመቻትም። እየደባበሰ ሲያሰቅቃትና ውስጧ አልታዘዝ ሲላት ትታው ለመውጣት ተገደደች። ሆኖም ብዙ ርቃ መሄድ አልቻለችም። ምክንያቱም መሽቷል። ሰካራም በበዛበት አካባቢ ላይ የብዙዎች መጫወቻ መሆኗ አይቀርም። ስለዚህም ይህ ከመሆኑ በፊት መመለስና ከአንዱ ጋር ማደር እንደሚሻላት አመነች፤ አደረገችውም።
ሴትዬዋ ከተስማማችው ሰው ጋርም አደረች። አዳሯ ግን ስቃይ የበዛበት ነበር። ሆኖም ብዙውን ገንዘብ የወሰደችው ቀጣሪዋ በመሆኗም ተንከባክባት ነበርና ነገሮችን እያደር አስረሳት። እርሷም ብትሆን ያገኘችው ገንዘብ ብዙ ነበርና ብዙም አልተከፋችበትም። ዓመታትንም በዚህ አይነት ሁኔታ ቀጠለች። ነገር ግን የሚጠራቀም ቀርቶ በልቶ ለማደር የሚበቃ ገንዘብ አላገኘችም። ምክንያቱም ተፈላጊነቷ ትናንት አበቃ። ዛሬ ዋና ተግባሯ እንደሌሎቹ ሴተኛ አዳሪዎች መንገድ ላይ ቆሞ ወንድ መፈለግ ነው።
ሰላም አሁን ከቀጣሪዋ ውጭ ብትሆንም የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት መሯታል። በተለይም አሁን እየሰራችበት ያለው መንደር ብዙ ገበያ የለውም። እናም ቦታ ለመቀየር ወሰነች። ከሳሪስ ሰፈር ወጥታም በሀዲድ ሰፈር መኖሪያዋን አደረገች። ኑሮው በዚህ አይነት ሥራ መቼም የሚገፋ እንዳልሆነ ስትረዳም ሌላ ሥራ ለመጨመር አሰበች። ይህም እንደልማዷ መሸታ ቤት መቀጠር ነው። ከመሸታ ቤት ሺያጭነቷ በተጨማሪም ሴተኛ አዳሪነቱን ትተዳደርበት ጀመር።
ሀዲድ ሰፈር ለሰላም ተጨማሪ ፈተናን ያመጣባት ነው። ራሷን ማኖር ባልቻለችበት ሁኔታ ላይ ሳለች ሌላ ተጨማሪ ነፍስ መጣባት። የመጀመሪያ ልጇን አረገዘች። ነገሩ የተከሰተው በአጋጣሚ ነበር። አውቃው ቢሆን ኖሮ ልጁን አትወልደውም፤ እንዳረገዘች የተረዳችው ወራት ተቆጥረው የተለየ ሕመም ተሰምቷት ለህክምና በሄደችበት ወቅት ነው። በዚህ ኑሮ ላይ ልጅ ተጨምሮ ሕይወት የበለጠ አስከፊ እንደሚሆን ከወዲሁ ገባት። ሌላው በህክምና ክትትል ወቅት የተረዳችው መርዶ ደግሞ በደሟ ውስጥ የኤች አይ ቪ ቫይረስ የመኖሩ ጉዳይ ነው።
በጊዜው የኤች አይ ቪ ምርመራ ቀድሞ ማድረግ አይታወቅም። ወይንም ደግሞ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ጽንስ እንዴት መገላገል እንደሚቻል በቂ ግንዛቤ አልነበረም። ስለዚህም ከቫይረሱ እንዴት ነጻ አድርጋ እንደምትገላገለው ያሳስባት ገባ። የሕክምና ባለሙያዎች በተቻላቸው መጠን ደግፈዋት ነበር። ሆኖም አልተሳካም፤ እርሷም ልጇም በቫይረሱ ተይዘዋል። ስለዚህም ለሁለቱም ብዙ ነገር ያስፈልጋቸዋል። ማንም በሌለበት ይህንን ማድረግ ደግሞ መቼም አይታሰብም።
ከብቸኝነት ጋር ድህነትና በሽታ ሲታከልበት ሕይወት መራር ይሆናል። አርግዞ በሰላም መገላገልና መታረስ ለሰላም የቅንጦት ያህል ነው። በዚህም መታረስ እንኳን ሳያምራት ቀጥታ ወደ ሥራ ገባች። ሆኖም ህጻን ይዞ ባልጠነከረ ሰውነት ሴተኛ አዳሪ ሆኖ መቀጠል አዳጋች መሆኑንም ስለገባት ሰላም ሌላ ስራ መፈለግ ጀመረች። መነሻዋን የቀን ሥራም አደረገች። በየሰው ቤት እየዞረች አሻሮ ትቆላለች፤ ልብስ ታጥባለች በአጠቃላይ የተገኘውን ስራ ሳታማርጥ ትሰራለች።
የአካባቢው አስተዳደርም በሴፍትኔት ተደራጅታ እንድትሰራ ዐውድን አመቻቸላት። በዚህ ስራ ለአምስት አመታት ቀጠለች። ጥሩ ገንዘብም ቋጠረች። ከአምስት አመታት በኋላም በቋጠረችው ብር ለንግድ የሚሆን ቤት ተከራይታ የሻይና ቡና ሥራን ጀመረች። አሁንም በዋናነት መተዳደሪያዋ ይህ ሥራ ነው። ሆኖም አንድ አስከፊ አጋጣሚ ተከሰተ። ለችግር የፈጠራት ይህቺ ሴት አንዲት ልጇን በሞት አጣች።
ሰላም ልጇን በሞት ካጣች በኋላ መረጋጋት አልቻለችም። በዚህም አዕምሮዋን ለማሳረፍ በሚል ራሷን በሥራ ትወጥር ነበር። በሞት ያጣቻትን አንዲት ልጇን እያሰበች በሃሳብ ትብሰለሰል ገባች። ይህ ደግሞ ከኤች አይቪ ኤድሱ በተጨማሪ ለሌሎች በሽታዎችም ተጋላጭ እንድትሆን አደረጋት።
ለሰላም ፈተና የሆነው ጉዳይ በሽታዋ ብቻ አይደለም፤ የቤት ጉዳይም ነው። በሀዲድ አካባቢ የአልጋ ኪራይ ጉዳይ የተለመደ ነው። በዚህም እርሷ የአከራይ ተከራይ ሆና ነው የምትኖረው። ከአከራይዋ በኮምፖልሳቶ የተከፈለች አነስተኛ ክፍል ተከራይታ እሷ መልሳ በማከራየት ነው ሕይወቷን የምትገፋው።
የአከራይ ተከራይ ሕይወት በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው። ሰላምም በብዙ የተፈተነችበት ቤት ነው። ቤቷን ዘግታ ማደር አትችልም። በየቀኑ የሚያድሩትን ሰዎች ገንዘቡን ሰብስባ ማስረከብ ግዴታዋ ነው። የሚከራዩት ሰዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሰካራምና በአሽሽ የደነዘዙ በመሆናቸው በጊዜ አይገቡም። እስከ ሰባት ሰዓት እነርሱን ትጠብቃለች። በዚህም መድኃኒቷን ወስዳ በጊዜ መተኛት አትችልም። ከፍዬሻለሁ ብሎ የማይሰጣትም ብዙ ነው። ይህንን ደግሞ የመክፈሉ ግዴታ የእርሷ ይሆናል። ይባስ ብሎ ሰክሮ የመጣ ሰው ይደበድባታል። ግን ቀን እስኪያልፍ ያለፋልና ይህንን ታግሳ እየኖረች ትገኛለች።
የቤቱ ባለቤትም ቢሆን ሌላኛው ፈተናዋ ነው። ሰካራም ነው፤ ስድቡና የዘወትር ውጪልኝ ጥያቄው ያሰጋታል። ምክንያቱም ሰፈሩ ሴተኛ አዳሪ የሞላበት አካባቢ በመሆኑ በቀን ኪራይ 200 ብር ያገኝበታል። ስለዚህም ቤቱን ልቀቂ በሚል ያንገበግባታል። ከሁሉም የሚብሰው ደግሞ ለፍታ ያመጣችውን ገንዘብ ሙሉ ባይከራይም የሙሉ አልጋ ዋጋ ይቀበላታል። ግን ቦታውን ብዙዎች የለመዱት በመሆኑ ከዚያ ለመራቅ አልፈለገችም። በሻይ ቡናው የምታገኘውን ገንዘብ ማጣትም አትሻም።
በአጠቃላይ ከገጠር የጀመረው የሰላም የሕይወት ውጣ ውረድ ቂርቆስ ድልድይ አካባቢም ቀጥሏል። ሆኖም እጅ ላለመስጠት ዛሬም እየታገለች ትገኛለች። ለዚህ ሁሉ እፎይታ የሚሆናት አንድ ነገር እንደሆነ ታስባለች። ይህም መንግስት ቤት ቢሰጣት ነው። ስለዚህ ‹‹ለእንቅልፌና ለህመሜ›› መከታ ሁኑኝ ስትል ትጠይቃለች። አዎ እነዚህ አይነት ሰዎች አጋዥን ይፈልጋሉ፤ ብዙ እጅ ዘርጊዎች ደግሞ አይጠፉምና ድረሱላቸው በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015